
አዲስ አበባ፡- በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን በመተማ በኩል የሚገቡ ሰዎች በመጨመራቸው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እየተስፋፋ እንደሚገኝ ተገለጸ። የፌዴራል መንግስት ከወትሮ የተለየ የህክምና ቁሳቁስና የሰው ሃይል ድጋፍ ማድረግ እንዳለበትም ተመልክቷል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዋለ በላይነህ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በክልሉ በምዕራብ ጎንደር ዞን የቫይረሱ ስርጭት እየሰፋ ይገኛል። አብዛኛዎቹ ሰዎች የሚመጡት ከሱዳን በመተማ በኩል ነው። በመተማ በኩል ከሚገቡት ሰዎች አብዛኛዎቹ ወደሌሎች ክልሎች የሚሄዱ ሲሆኑ ፣ በአካባቢው ብዛት ያላቸው ሰዎች በማቆያ ውስጥ ይገኛሉ። ለዚህም የፌዴራል መንግስት ከወትሮ በተለየ ድጋፍ ማድረግ አለበት።
በመተማ በኩል እስከ 30 የሚደርሱ መግቢያ በሮች እንዳሉ አቶ ዋለ ጠቅሰው፣ በእነዚህ በሮች የሚገቡትን ሰዎች በለይቶ ማቆያ እንዲገቡ እንደሚደረግ ተናግረዋል። ይህ ስራ በክልሉ መንግስት ብቻ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተው፣ የለይቶ ማቆያዎች ጥበትና የህክምና ቁሳቁስ እጥረት እንዳይፈጠር የፌዴራል መንግስት ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።
እንደ አቶ ዋለ አባባል፤ በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተለያዩ ኮሚቴዎች ተቋቁመው አስቸኳይ ምላሽ እየሰጡ ይገኛሉ። ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በሰፊው እየተሰጡ ናቸው። ቫይረሱ ህብረተሰቡ ውስጥ ስርጭቱን እንዳያሰፋ የቅኝት ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን፣ በአየር መንገድ በኩል የሚገቡ ሰዎች የሙቀት ልኬት መስራት፣ በመኪና የሚገቡ ሰዎች ሙቀታቸውን በየቦታው እንዲለኩ የማድረግ እና የቤት ለቤት አሰሳና ቅኝት ስራ እየተሰራ ነው። በቅኝት ስራው ወቅት ከሙቀት ልኬት በተጨማሪ የተጠረጠሩ ሰዎችን ናሙና የመውሰድ ስራ ይሰራል።
በለይቶ ማቆያ፣ ለይቶ ማከሚያ እና የኮሮና ማገገሚያ ማዕከላት የማቋቋም ስራ መሰራቱን በመጥቀስ፤ አስራ አምስቱም ዞኖች የየራሳቸውን ማዕከላት እንዲያቋቁሙ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል። ለይቶ ማከሚያው በርካታ ወጪ እንደሚጠይቅ ገልጸው፣ የተፈለገውን ያክል እየተሰራ አለመሆኑን አስረድተዋል።
እንደ አቶ ዋለ ገለፃ፤ ከውጭ የሚመጡ ሰዎችን በለይቶ ማቆያ በማስገባት የምርመራ ስራ እንዲከናወን ይደረጋል። በዚህም ውጤቶች መጥተዋል። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የመመርመሪያ ኪቶች፣ ማስኮች፣ ሳኒታይዘር እና ሌሎች እቃዎችን እየደገፈ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2012
መርድ ክፍሉ