በኢንዶኔዢያዋ ‹‹ባሊ›› በምትባል ደሴት የውሃ ጉድጓድ ውስጥ ወድቆ ለስድስት ቀናት የቆየው እንግሊዛዊ በስተመጨረሻ ሕይወቱን ማትረፍ ተችሏል።
የ29 ዓመቱ ጄኮብ ሮበርትስ በፔካቱ መንደር ውሻ ሲያሯሩጠው ለማምለጥ ሲሞክር ነው አራት ሜትር በሚጠልቀው ጉድጓድ ውስጥ የወደቀው። እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከአደጋው በኋላ እግሩ እንደተሰበረ የአካባቢው ባለስልጣናት ገልጸዋል። ምንም እንኳን ጉድጓዱ ውሃ ባይኖርበትም እግሩ በመሰበሩ ምክንያት መውጣት ሳይችል ቆይቷል።
በአካባቢው የነበሩ የአይን እማኞች እንደገለጹት፤ በጉድጓዱ ውስጥ ትንሽ ውሃ በመኖሩ ለስድስቱ ቀናት የሚጠጣውን ማግኘት ችሏል። ጄኮብ ሮበርትስ ለስድስት ቀናት ያለመታከት የድረሱልኝ ጥሪውን ሲያሰማ ነበር። በመጨረሻም አንድ የአካባቢው ነዋሪ ድምጹን በመስማቱ ሕይወቱ ልትተርፍ ችላለች።
እምብዛም ሰዎች በማይኖሩበት አካባቢ በሚገኘው የውሃ ጉድጓድ አቅራቢያ ከብቶቹን ሲጠብቅ የነበረው ግለሰብ ሁኔታውን ከተመለከተ በኋላ ወዲያው የአካባቢው ኃላፊዎችን ጠርቷል።
ጃኮብ በግለሰቡ የተገኘው ባሳለፍነው ቅዳሜ ሲሆን ወዲያውኑ ከጉድጓዱ ወጥቶ ህክምና እንዲያገኝ ተደርጓል።
ደሴቲቱ ውስጥ የምትገኘው የፔካቱ መንደር እንደ ጄኮብ ያሉ በርካታ ጎብኚዎች የሚያዘወትሯት ሲሆን እንዲህ አይነት አደጋ እምብዛም የተለመደ አይደለም ተብሏል።
ከቦምብ ሰሪነት ወደ ሰላም ሰባኪነት
ክላሽን የሰራው ሰው በአንድ ወቅት እንዲህ ተብሎ ተጠየቀ አሉ፡፡ ‹‹በሰራኸው መሳሪያ ሰዎች ሲገዳደሉበት ምን ይሰማሃል?›› የሰውየው መልስ አናዳጅም አስቂኝም ነበር፡፡ ‹‹ጅል ይገዳደልበት እኔ ምን አገባኝ›› ብሎ መለሰ፡፡
እንግዲህ በሰውየው የተበሳጨ ሰው እሱን በልጦ መገኘት ነው፡፡ ክላሽን ንቆ መተው ማለት ነው፡፡ ንቆ መተው ሲባል ግን ሁሉም ንቃተ ህሊናው ከክላሽ በላይ ከሆነ ነው፡፡ አንዱ በጦር እያመነ ሌላው ቢንቀው መገዳደሉ አይቀርም፡፡
ቢቢሲ ሰሞኑን ያስነበበን አሊ ፋውዚ የተባለው ሰውየ ግን ከቦምብ ሰሪነት ወደ ሰላም ሰባኪነት በመለወጥ ለዓለም ምሳሌ ሆኗል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡
አሊ ፋውዚ ከአል ቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው ጀማ ኢስላሚያ ቡድን ቁልፍ አባል ነበር። ይህ ቡድን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2002 ኢንዶኔዥያዋ ባሊ ላይ ከፍተኛ የቦምብ ጥቃት ሰንዝሯል። የ200 ሰዎች ሕይወትም ተቀጥፏል። ‹‹የባሊውን የቦምብ ጥቃት ያደረሱት ወንድሞቼ ናቸው። በቱሪስት መናኸሪያዋ ከተማ የተጣለው ትልቅ ፈንጂ ነበር›› ብሎም ተናግሯል፡፡
ቡድኑ በኢንዶኔዥያ ሌሎችም ጥቃቶች አድርሷል። ሆቴሎች፣ የምዕራባውያን ኤምባሲዎችም ኢላማው ነበሩ። ምሽጋቸው የኢንዶኔዥያዋ ምሥራቅ ጃቫ ውስጥ የምትገኘው ተንጉሉን ነበረች።
‹‹ጎበዝ ቦምብ ሠሪ ነኝ። በአምስት ደቂቃ ውስጥ ቦምብ ሠርቼ እጨርሳለሁ›› የሚለው አሊ፤ ዛሬ ላይ የሕይወት መርሁን ለውጧል።
በደቡብ ምሥራቅ እስያ ይንቀሳቀሱ የነበሩ የቀድሞ ጂሀዲስቶች ሕይወታቸውን እንዲለውጡ ያግዛል። ከነውጥ እንዲወጡ፣ አዳዲስ ታጣቂዎች መመልመል እንዲታቀቡም ይደግፋቸዋል።
‹‹ሰዎች የአሸባሪ ቡድን እንዲቀላቀሉ መመልመል ቀላል ነው። አንድ ጥይት ተኩሰው በርካቶች ይከተሏቸዋል። በተቃራኒው አንድን ሰው ከጽንፈኛ አመለካከቱ ማላቀቅ (ዲራዲካላይዜሽን) ግን ጊዜ ይወስዳል›› ብሏል አሊ።
ሰዎችን ከጽንፈኛ አመለካከት ለማላቀቅ መሞከር ቀላል ነገር አይደለም። አሊ ብዙ ጊዜ የሞት ማስፈራሪያ እንደደረሰው ይናገራል። ‹‹ቢሆንም አልፈራም። የማደርገው ነገር ትክክል እንደሆነ አውቃለሁ። ለዚህ ተግባሬ ለመሞትም ዝግጁ ነኝ›› ሲል አቋሙን ያስረግጣል።
‹‹የቦምብ ጥቃታችን ያስከተለውን አስከፊ ጉዳት ማየቴ ሕይወቴን እንድለውጥ አደረገኝ›› ብሏል፡፡
አሊና ወንድሞቹ በሚኖሩበት መንደር በአፍጋኒስታን፣ ቦስንያና ፍልስጤም ያሉ ጦርነቶችን የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በስልካቸው ይመለከቱ ነበር። ታጣቂ ቡድን ለመቀላቀል የወሰኑትም ለዚህ ነው።
‹‹ንጹሀን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጭካኔ የተሞላው ጥቃት አይተናል። በጂሀድ ሙስሊሞችን ለመታደግ ቆረጥኩ። በወጣት፣ ሙቅ ደሜ ለመታገል ወሰንኩ።››
ወንድሞቹ ለትግል ወደ አፍጋኒስታን ሲሄዱ እሱ በፊሊፒንስ ያሉ ታጣቂዎችን ተቀላቀለ።
‹‹እዛው መሞት እፈልግ ነበር። ሞቴን ብዙ ጊዜ አስቤዋለሁ። ትግል ላይ ሳለሁ ከሞትኩ ቀጥታ መንግሥተ ሰማያት እንደምገባ አምን ነበር። መሪዎቻችን በየቀኑ ይህንን ደጋግመው ይነግሩን ነበር›› ይላል።
ወንድሞቹ ከአፍጋኒስታን ሲመለሱ የተማሩትን ተገበሩ። በዓለም አቀፍ ጎብኚዎች በሚዘወተረው ባሊ ላይ በ2002 ጥቃት አደረሱ።
‹‹ጥቃቱን በቴሌቪዥን ሳይ ደነገጥኩ። ብዙ አስክሬን ነበር። ባለሥልጣኖችም የት እንዳለን አውቀው ነበር›› ሲል ያስታውሳል።
ሁለቱ ወንድሞቹ ተገድለዋል። ሌላው ወንድሙ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል።
አሊ በባሊው የፈንጂ ጥቃት እንዳልተሳተፈ ይናገራል። ከሌላ የሽብር ጥቃት ጋር በተያያዘ ሦስት ዓመት ታስሯል። ሕይወቱ የተለወጠውም በዚህ ወቅት ነው።
‹‹ፖሊሶቹ ለሰው በሚገባ ክብር ነበር የያዙኝ። አሰቃይተውኝ ቢሆን ኖሮ እስከ ሰባት ትውልዴ ድረስ የኢንዶኔዥያን መንግሥት ይታገል ነበር።›› ብሏል አሊ።
ፖሊሶች ‹‹ሰይጣን ናቸው›› ተብለው ይማሩ እንደነበር ይናገራል። እውነታው ግን ከዛ የተለየ ሆኖ አግኝቶታል። በሱ ቡድን አባላት የደረሰ የቦምብ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ሲያገኝ የተሰማውን ሀዘንም እንዲህ ይገልጻል።
‹‹አለቀስኩ። ልቤ ተሰበረ። የቦምብ ጥቃታችን ያስከተለውን አስከፊ ጉዳት ማየቴ ሕይወቴን እንድለውጥ አደረገኝ። ከጦርነት አጋፋሪነት ወደ ሰላም አርበኛነት ለመሸጋገር ወሰንኩ።››
‹‹ሌሎች አሸባሪዎችም እንዲቀየሩ እረዳቸዋለሁ›› የሚለው አሊ፤ ተንጉሉን በተባለችው መንደር በሚገኘው ዋና መስጊድ አቅራቢያ አሊ የመሠረተው ተቋም ይገኛል። ‹‹ሰርክል ኦፍ ፒስ›› ወይም የሰላም ክበብ ይባላል።
አንድ ምሽት ላይ በዋናው መስጊድ የተካሄደው የምሽት ጸሎት የተመራው በሁለት የቦምብ ጥቃት ሰለባዎች ነበር። መንደሩ የሁለቱን ሰዎች ሕይወት ያመሰቃቀሉት ታጣቂዎች ምሽግ ነበር።
አሊ እንደሚለው፤ የቦምብ ጥቃት ሰለባዎችን ወደ ማኅበረሰቡ ይወስዳቸዋል። ‹‹አመለካከቴን የለወጠው እነሱን መተዋወቅ ነው›› ይላል።
በመስጊዱ ውስጥ በኢንዶኔዥያ የደረሰ የቦምብ ጥቃት ያስከተለው ጉዳት በተንቀሳቃሽ ምስል ይታያል። በመስጊዱ በሽብር ጥቃት ታስረው የነበሩ ሰዎች እንዲሁም ያሰሯቸው ፖሊሶችም በጋራ ተሰባስበዋል።
የቦምብ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ሰቆቃቸውን እያለቀሱ ሲናገሩ ያደምጣሉ።
በመስጊዱ ከተገኙት አንዱ የ33 ዓመቱ ዙሊያ ማህንድራ ነው። አባሩ አምሮዚ ሲታሰር ዙሊያ ወጣት ነበር። አባቱ ከባሊው የፈንጂ ጥቃት ጋር በተያያዘ በሞት ተቀጥቷል።
አምሮዚ ቅጣቱን ሲቀበል አንዳችም ጸጸት አላሳየም ነበር። ስለዚህም መገናኛ ብዙሀን ‹‹የሚስቀው ገዳይ›› ይሉት ነበር።
የአምሮዚ ልጅ ዙልያ የመስጊዱ ጸሎት ካለቀ በኋላ፤ የቦምብ ጥቃት የደረሰባቸውን ሁለት ሰዎች አግኝቶ፣ አቅፏቸው ደጋግሞ ይቅርታ ጠይቋቸዋል።
‹‹ይቅርታ የምለው እኔ ስላጠፋሁ አይደለም። በአባቴ ድርጊት የተጎዱ ሰዎችን ይቅርታ የመጠየቅ ኃላፊነት ስላለብኝ ነው›› ይላል ዙልያ።
ዙልያ አባቱ ሲገደል ለበቀል ተነሳስቶ ነበር። ቦምብ መሥራት መማር ፈልጎ እንደነበርም ይናገራል። አጎቱ አሊ ግን ሃሳቡን አስቀይሮታል፡፡
‹‹አጎቴ አሊ ፋውዚ እና አሊ ኢምራን ስህተት ውስጥ ልገባ እንደነበር አሳይተውኛል። የነሱን ፈለግ ተከትዬ ሌሎች አሸባሪዎችም እንዲቀየሩ እረዳቸዋለሁ። ዛሬ የሆንኩትን ሰው ለመሆን ብዙ ርቀት ተጎዣለሁ። ጂሀድ ሰዎችን መግደል ወይም መዋጋት ሳይሆን ለቤተሰብ መትጋት መሆኑን ተረድቻለሁ›› ይላል።
የዙልያ ጓደኞች ከአይ ኤስ ጋር ግንኙነት ያለው የኢንዶኔዥያ ታጣቂ ቡድን መቀላቀላቸውን ይናገራል። አንዳንድ ሰው በድህነት ሌሎች ደግሞ ሥራ በማጣት መሰል ቡድናችንን ይቀላቀላሉ ይላል።
አጎቱ አሊ ከጽንፈኛ ሃሳብ የሚያላቅቃቸውን ሰዎች ከማረሚያ ቤት ይመለምላል።
‹‹የምመክራቸው ከሕይወት ተሞክሮዬ ተነስቼ ነው። ታጋይ፣ አሸባሪ ነበርኩ። ስለዚህ ማረሚያ ቤት የምሄደው እንደ ጓደኛቸው ሆኜ ነው›› ብሏል፡፡
ታራሚዎችን ማሳመን ግን ቀላል አይደለም። አንዳንዶች የፖሊሶች ቅጥረኛ ነው ብለው ያስባሉ።
‹‹ከፖሊሶች በላይ ኢ-አማኒ (ካፊር) ነህ ይሉኛል። በድረ ገጽ ማስፈራሪያም ይደርሰኛል። ግን እችለዋለሁ›› ይላል አሊ።
ያስተምራቸው ከነበሩ 98 ሰዎች መካከል ሁለቱ ከእስር ቤት ከተለቀቁ በኋላ በድጋሚ ታጣቂዎችን ተቀላቅለዋል። በሰዎች አዕምሮ ሰርጾ የገባን ሃሳብ ማስለወጥ ቀላል እንዳልሆነና ሁሌ እንደማይሳካም አሊ ያስረዳል። ‹‹የጥፋት ሕይወትን እተዋለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ›› ብሏል፡፡
ከአሊ ተማሪዎች አንዱ ሱማርኖ ነው። ቀድሞ ከታጣቂዎች ጋር መሣሪያ ይሠሩበት የነበረውን ቦታ ለአሊ አሳይቶታል፡፡
ሱማርኖ ከሦስት ዓመት እስር ሲለቀቅ በአሊ ድጋፍ የጎዞ ወኪል ቢሮ ጀምሯል። ቢሮው አማኞችን ወደ መካ ይወስዳል።
‹‹በዚህ የጉዞ ወኪልነት ሥራ የጥፋት ሕይወትን እተዋለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ›› ይላል ሱማርኖ።
ለደንበኞቹ ስለቀደመ ሕይወቱ ሲነግራቸው ስጋት ይገባዋል። ሆኖም ግን ሥራው አዕምሮውን ነፃ እንደሚያወጣው ያምናል።
‹‹ለደንበኞቼ ባሊ ቦምብ አፈንድተው የተገደሉት አሊ ጉፍሮን እባ አምሮዚ ዘመድ ነኝ እላቸዋለሁ። የአሸባሪ ቡድኑ አባል ነበርኩ አሁን ግን አላህ ምስጋና ይግባውና ከክፉ አስተሳሰቤ ነጽቻለሁ እላቸዋለሁ። ወደ መካ የምወስዳቸው አስጎብኛቸው እንደሆንኩም እነግራቸዋለሁ›› ብሏል፡፡
የአሊ ባለቤት ሉሉ ታዳጊዎችን ቁርዓን ከሚያስተምሩ አንዷ ናት። ከምታስተምራቸው ታዳጊዎች የእያንዳንዶቹ ቤተሰቦች በሽብርተኝነት ተከሰው ቢታሰሩም ‹‹ሁሉም ሰው አንድ አይነት አይደለም›› ስትል ልጆቹን ትመክራለች።
‹‹ማኅበረሰባችን ውስጥ ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች አሉ። ሃይማኖታችንን እስካላደናቀፉ ድረስ ልናከብራቸው ይገባል›› ትላለች ሉሉ። ነገር ግን በሃሳቧ የሚስማማ እንዳለ ሁሉ የሚቃወማትም አለ።
‹‹አሁንም ታጥቀው ያሉ ሰዎች አይወዱንም። ከኛ ይርቃሉ። በአንድ ቡድን ለአንድ አላማ የቆምን ነበርን። የባሊው ፍንዳታ ብዙ ሙስሊሞችን ጨምሮ ንጹሀንን ከቀጠፈ በኋላ እኛ ተለውጠናል። ያልተቀየሩም አሉ።››
ባለፈው ዓመት የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ አጥፍቶ ጠፊዎች ሦስት ቤተ ክርስቲያኖችን በቦምብ አጋይተዋል።
አጥቂዎቹ ከአይ ኤስ ጋር ግንኙነት ያለው ጀማ አንሽሩት ዱላይ ቡድን አባላት ናቸው። በኢንዶኔዥያ የጸጥታ ኃይልና ሙስሊም ባልሆኑ ሰዎች ላይ ጥቃት አድርሰዋል።
አሊ በፈጠረው የሰላም ክበብ ውስጥ ሴቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየተሳተፉ መሆኑ ሉሉን ያስገርማታል።
‹‹ባለቤቴ የቀድሞ አሸባሪዎች ከእስር ሲለቀቁ ወደ ሽብር እንዳይመለሱ ለማድረግ ደፋ ቀና እያለ ነው። የብዙ ሰዎችን ሕይወት ቢለውጥም አሁንም በርካቶች ጽንፈኛ ናቸው። ሙሉ በሙሉ ልናጠፋው አንችልም›› ብላለች።
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2012
ዋለልኝ አየለ