ሰኔ በአንድ ወሳኝ ጉዳይ ላይ ጎልቶ ከመታየት ባለፈ በብዙዎቹ ብዙም የለበትም። በፖለቲካውም ከጀርባ ሆኖ ከመዘወር ያለፈ እዚህ ግባ የሚባል ነገር የለውም። በሃይማኖትም ከመደበኛዎቹ ወርሃዊ በአላት ውጪ ሊጠቀስለት የሚችል ጥምቀትንም ሆነ ፋሲካን መሰል ክብረ በአላት የሉትም።
ሰኔ ጎልቶ የሚታይበት ጉልህ ዘርፍ ግብርናው ሲሆን በእሱ በኩል ያለ ተወዳዳሪና ተቀናቃኝ እየመራ ይገኛል። “ለሞኝ ሰኔ በጋው / መስከረም ክረምቱ” እንዲሉ በግብርናው ዘርፍ እሱን የሚተካከል የለም፤ ካመለጠ መዘዙ ብዙ ነውና።
እኛ ጋር ብቻ አይደለም፤ ነጮቹም ከወራት ሁሉ አንዱን ነጥለው ሲክቡ አሊያም ሲያጣጥሉ ይታያሉ። ለምሳሌ ግንቦት ከወራቶች ሁሉ በተለየ መልኩ ችግር የበዛበት መሆኑን ለመግለፅ “May is the most boring month» ሲሉ መስማት አዲስ ነገር አይደለም (ዛሬ ዛሬ በሁሉም ወራት መከራ በሽበሽ ስለሆነ አንድን ወር ለይቶ ማብጠልጠል ተገቢ አይደለም የሚሉ ቢበዙም)።
ክፉ ገድን፣ መጥፎ እጣ ፋንታን፣ አጓጉል ገጠመኝን በተመለከተ ግን ሰኔን በሚያክል ደረጃ የተጠቀሰ ወይም የሚጠቀስ ያለ አይመስልም – “ሰኔና ሰኞ” (አበቅቴ)።
የይታገሱ ዘውዱ ፅሁፍ “’ሰኔና ሰኞ’ መነሻው አንድ ሰኞ ቀን በዋለ ሰኔ አንድ ተግባር ላይ በዋለ አዋጅ ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል” ይለናል። “ይገመታል” ነውና እስኪጣራ በዚሁ እንለፈው።
ልክ እንደዚህ ወር፤ በአገራችን ሰኔ ፩ ሰኞ ቀን ከዋለ መጥፎ ነው (ዘመኑ የረሃብና ቸነፈር፣ የሰቆቃ፣ የበሽታ፣ የጦርነት…) ይሆናል የሚል እድሜ ጠገብ አባባል አለ። ይህንን “ሰኔና ሰኞ” አባባል እንደ ተራ ነገር በመቁጠር፣ ጉዳዩን ከመሰረቱ ባለመረዳትና “ለምን?” ብሎ ካለመጠየቅ የተነሳ ሳይንሳዊ መሰረት የሌለው (እንዲኖረው ማድረግ እየተገባ)ና ጉንጭ ከማልፋት ያላለፈ አነጋገር አድርገው የሚቆጥሩት ብዙ ናቸው፤ የፃፉም አሉ። ግን እንደሱ አይደለም።
ሰዎች ስለሌላው ብቻ ሳይሆን ሰኔና ሰኞን በራሳቸው ላይ የደረሰን ክስተትም “ዘንድሮ ምነው ሰኔ እና ሰኞ ገጠመብኝ?” በማለት የደረሰባቸውን ከባድ፣ ተደራራቢና ያልተለመደ ችግር ሲገልፁ መስማት አዲስ አይደለም።
“ሰኔ” እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወር ወር ነው፤ በቃ። ነገር ግን አንድ ማህበረሰብ አንድን ጉዳይ ለመግለፅ ሲፈልግ ከአንድ ጉዳይ ጋር አያይዞ፤ በአንድ ጉዳይ አስደግፎ፤ አንድን ጉዳይ አንተርሶ ነውና ማለት፤ መግለፅ ለፈለገው ጉዳይ አንድን ክስተት፣ ቦታ፣ ጊዜ፣ ገጠመኝ ቢመዝ አያስገርምም። በመሆኑም ለአንድ ክፉ ክስተትና ገጠመኝ መግለጫ ከወራት ሁሉ ሰኔን ወስዶ ቢጠቀም ምን የሚገርም ነገር አለ? ይህን ስንል ትከሻችን የነገረንን እንጂ የባህረ ሃሳብን እውቀት እና ቀመርን ተክነን ያገኘነው እውቀት አይደለም። “ሰኔና ሰኞ”ን በ”አንድ አበቅቴ”ነቱ መጠቀሱ ኣሳምኖናልና በዛው እንቀጥላለን።
ለምሳሌ ተፅፎ እንዳነበብነው በ1863 የገጠመውን ሰኔና ሰኞ ተከትሎ የርስ በርስ ጦርነት የገባችው፤ በጦርነቱም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎቿን ያጣችው አሜሪካ ዘንድሮም በኮሮና ቫይረስ እና ዘረኝነቷ በጫረው እሳት ምክንያት “ሰኔና ሰኞ ሆኖባታል” ብንል ማለት የተፈለገው ሟርት ሳይሆን የደረሰባትን ተደራራቢና ክፉ አጋጣሚ ለመግለፅ ነው። መልእክቱም አሻሚ አይደለም። አሻሚ ባልሆነበት ሁኔታ የግድ ሰኔን በሳይንሳዊ መንገድ ለመተንተን መሞከር (ከተቻለ እሰየው) ትርፉ ድካምና ፈጠራን መገደብ ነው። ሰኔ ፩ ሁሌ ሰኞ እለት በመዋል የተለመደ እንደማይሆነው ሁሉ አንዳንድ ክስተቶችም እንዲሁ ሁሌ አይከሰቱም። በመሆኑም ከስንት አንዴ የሚከሰቱ በመሆናቸው ልዩ ትኩረትን ይስባሉ። ሰኔና ሰኞም ያው ነው። ከዚህ በተረፈ “ሰኔን ከሌሎቹ ምን ልዩ አደረገውና ነው…?” ብለው የሚያጣጥሉ የቀዳሚውን ትውልድ የመፍጠርና ማገናዘብ አቅም እያጣጣሉ ነውና ተሳስተዋል።
ሰሞኑን “አንድሮሜዳ”ን በመጥቀስ በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገፆች ላይ ሃሳባቸውን ያሰፈሩ ሰዎች “ሰኔ እና ሰኞ በ5፤ አንዳንዴም በ6 አመታት ልዩነት ይመጣና ቀጥሎ በ5 እና 6 በመደመር በየ11 አመት ይመጣል፤ ይህም አንድ አበቅቴ ይሆናል።” ያሉን ሲሆን “ሰኔ እና ሰኞ በፈረንጅ ካላንደር ከገጠመ፤ በሳምንቱም በኢትዮጵያ ካላንደርም ሰኔ እና ሰኞ መልሶ” እንደሚገጥምም ነግረውናል።
ለበርካታ አለም አገራት የሳምንቱ ሁለተኛ፤ ለአውሮፓ አገሮች ደግሞ የመጀመሪያ ቀን የሆነው፤ በእሁድና ማክሰኞ እቅፍ ውስጥ የሚገኘውን፤ በአንዳንዶችም ዘንድ እንደ መጥፎ የሚቆጠረውን ቀን “ሰኞ (ሰኑይ) ሰነየ፣ አማረ፤ በጀ፤ ተስተካከለ፤ ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ቃል ሲሆን በሥነ ፍጥረት 2ኛዋ ቀን ናት። ሰኞ ለፍጥረት የመጀመሪያዋ እለት ለሆነችው እሑድ ተከታይ፣ ሳኒታ፣ ማግስት ትባላለች።” የሚለን አንድ ሰንበት ያለ ፅሁፍ ላይ ያገኘነው ሃሳብ ነው። መጽሀፍ ቅዱስን በመጥቀስም (ዘፍ 1÷6፤ ማር 11፥14፤ ማቴ. 22፥13) ሁለቱን (ሰኔን እና ሰኞን) ያብራራል። 1997 ዓ/ም “ሰኔና ሰኞ በኢትዮጵያ ገጥመው እለቱ ጥቁር ቀን ሆኖ በኢትዮጵያውያን ላይ የማይረሳ ግድያ፣ ጭፍጨፋ፣ እስራትና ግርፋት የተፈፀመበትና በታሪካችን ከተመዘገቡት ጥቁር ቀናት አንዱ” መሆኑንም ይሄው ጽሑፍ ያስታውሳል።
ሌላው የሰኔና ሰኞን መግጠምና ልዩ ክስተት የማይቀር መሆኑን የሚነግሩን ከሰሞኑ ብቅ ብቅ እያሉና “በ2012 የፀሀይ ግርዶሽ ይታያል፤ ግርዶሹንም በቅርበት ለማየት ተመራጭ የሆነችውም ሀገር ኢትዮጵያ ስትሆን በሰኔ 14 ወይም በፈረንጆቹ ጁን 21/2020 (በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር በአማካይ ከጠዋቱ 12:50 – 3:15) ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ የሚታይበትም ቀን ይሆናል።” በማለት እየነገሩን ስለሆኑ ክስተቱ ወደፊት ነውና የምናየው ይሆናል።
አንድ አበቅቴ በየ11 አመቱ (2020፣ 2026፣ 2037፣ 2043፣ 2048፣ 2054፣ 2065፣ 2071፣ 2076፣ 2082፣ 2093፣ 2099 –) አንዴ ይመጣል ተብሎ የሚነገርለት ቀመር በያዝነው ሚሌኒየምም በቅንፍ በተገለፁት አመታት ሰኔና ሰኞ እውን ይሆናልም እየተባለ ነው። (ሁለት ጊዜ በጎዶሎ፤ ሁለት ጊዜ በሙሉ ቁጥር እየተከታተለ መከሰቱን ልብ ይሏል።)
ይህንኑ አንድ አበቅቴ (11 አመት) ይዘን ምን ምን አሳዛኝ ሁነቶች ተፈጥረው ነበር ስንል የህዳር በሽታ፣ ሁለተኛው የኢትዮጵያና ጣሊያን ጦርነት፣ የአጼ ቴዎድሮስ ሞት ወዘተ የሚሉትን እናገኛለን። ወደ ፈረንጆቹም ስንሄድ ያው ሲሆን በአውሮጳ እና በአሜሪካ እንደመጥፎ ዘመን የሚቆጠረው 1931 ሰኔና ሰኞ የገጠመበት መጥፎ ዘመን ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን ለዚህም Great Depression በመባል የሚታወቀው የሁሉ ነገር ድቀት መከሰት ምክንያት ነው፤ የ1942 – የሁለተኛው አለም ጦርነት ሁሉ የሰኔ እና ሰኞ አበቅቴዎች መሆናቸውን ነው ሰነዶችን ስንፈትሽ የምናገኘው።
በአጠቃላይ የ”ሰኔና ሰኞ” ጉዳይ ከላይ እንዳልነው ሆኖ፤ ሪከርድ የያዘውና በ1783 በአይስላንድ የሚገኘው ላኪ የተባለው ተራራ በእሳተ ገሞራ (Laki eruption) ፈንድቶ 9ሺህ ህዝብ በአሰቃቂ ሁንታ ከማለቁ በፊትና እስካሁኗም ሰአት ድረስ የሆነውና እየሆነ ያለው ብዙ ነውና ጉዳያችንን በዚሁ እንቋጨው። ከዛ በፊት ግን “ሰኔና ሰኞ” እንዳይሆንብን ፈጣሪን እንለምን።
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2012
ግርማ መንግሥቴ