እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
ስለ ሦስተኛ ወገኖች በወፍ በረር
በውል ውስጥ በተዋዋይነት ተሳታፊ ያልሆኑ ነገር ግን በውሉ ውጤት ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚሳተፉ አካላት ሶስተኛ ወገኖች ነው የሚባሉት።
በመሰረተ ሀሳብ ደረጃ እነዚህ ወገኖች እነሱ ተሳታፊ ያልሆኑበት ውል ከሚያስገኘው ፍሬ የመቋደስ መብት የላቸውም። የውሉን ግዴታ ለመሸከምም ትከሻውን ዝቅ ማድረግ አይኖርባቸውም።
ምክንያቱም ውል ከመነሻው በተዋዋይ ወገኖች መልካም ፈቃድ የሚመሰረትና የመብቶቹ ተቋዳሽም ሆነ የግዴታዎቹ ፈጻሚ ራሳቸው ተዋዋዮቹ ወገኖች በመሆናቸው። ውል በተዋዋይ ወገኖች መካከል ሕግ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው።
በመርህ ደረጃ ውሎች የሚጠቅሙትም ሆነ የሚጎዱት ተዋዋዮቹን ነው ቢባልም ቅሉ በውሎች ውስጥ ተለይቶ ከተቀመጠ ወይም ውሎቹ ከተዋዋዮቹ ውጭ ባሉ አካላት ላይ ውጤት የሚያመጡ ከሆነ ሶስተኛ ወገኖች ያልናቸው ሰዎች የውሉ ፍሬ ተጠቃሚና የግዴታዎቹም ፈጻሚ ሊሆኑ ይችላሉ።
የፍትሐብሔር ሕጋችን እነዚህ ሶስተኛ ወገኖች በውል የሚያገኟቸውን መብቶችና የሚሸከሟቸውን ግዴታዎች አስመልክቶ “ከውሉ ጋራ ግንኙነት ስላላቸው ሶስተኛ ወገኖች” በሚል ርዕስ ሰፊ ድንጋጌዎችን አካቷል።
በሕጉ መሰረት ከውል ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል እውቅና የተሰጣቸው ሶስተኛ ወገኖች የሚባሉት በተዋዋዮች የውሉ ተጠቃሚ እንዲሆን ወይም ባለዕዳ እንዲሆን የተስፋ ቃል የተገባለት/የተገባበት ሰው፤ በውል የተገኘ የገንዘብ መብት የተላለፈለት ሰው፤ የተዳረገ ሰው፤ የውል ግዴታ ፈጻሚነት ምትክ ውክልና የወሰደ ሰው፤ መብት ከነግዴታው የተላለፈለት ሰው እንዲሁም የተዋዋዮች ወራሾችና ከተዋዋዮች ገንዘብ የሚጠይቁ ሰዎች ናቸው።
በዛሬው ጽሁፋችን ታዲያ ከእነዚህ ሶስተኛ ወገኖች ውስጥ ስለዳረጎት ዝርዝር ጉዳዮችን እንዳስሳለን።
ዳረጎት ምንድን ነው?
የውል ግዴታ የሚፈጸመው በባለዕዳው ነው። ውሉ የብድር ከሆነ ብድሩን ለባለገንዘቡ የሚመልሰው ራሱ ተበዳሪው ነው። በቤት ወይም በመኪና ሽያጭ ውል ውስጥ ገንዘቡን የከፈለው ተዋዋይ ቤቱን ወይም መኪናውን የሚረከበው ከሻጩ እጅ ነው።
ይሁንና ከውሉ ባህርይ በመነሳት ባለዕዳው ራሱ እንዲፈጽመው ከማይገደድበት ግዴታ ውጭ (ለምሳሌ ባለዕዳው ዘፋኝ ወይም ሰዓሊ ካልሆነ) ዕዳው በባለዕዳው ወኪል፣ ዋስ ወይም ወራሽ ለባለገንዘቡ ሊከፈል ይችላል።
በዚሁ መሰረት የውሉ ዕዳ በእነዚህ ሶስተኛ ወገኖች ለባለገንዘቡ ከተከፈለ የውሉ ግዴታ ቀሪ ይሆናል ማለት ነው። እናም በባለገንዘቡና በባለዕዳው መካከል በውሉ ተመስርቶ የነበረው የግንኙነት ድር ይቆረጣል።
ይህ ማለት ግን የባለገንዘቡ ገንዘብ ስለተከፈለው ብቻ ውሉ ሞቷል ወይም ከእንግዲህ ሕይወት የለውም ማለት እንዳልሆነ ልብ ይሏል።
ይልቁንም ባለገንዘቡ ከውሉ ውስጥ ቢወጣም በውሉ ውስጥ የእሱ የነበሩት መብቶችና ግዴታዎች ሁሉ በባለዕዳው ቦታ ሆኖ ዕዳውን ወደተወጣው ዋስ፣ ወራሽ ወይም ወኪል ይሸጋገራሉ። የውሉ ግዴታ ቀሪ ስላልሆነ የባለዕዳው ኃላፊነት ገና አልወረደም።
በዚህም መነሻ ይህ ሶስተኛ ወገን በቀድሞው ባለገንዘብ ተተክቶ ከባለዕዳው ላይ እሱ ለባለገንዘቡ የከፈለለትን ግዴታ የሚጠይቅ አዲሱ ባለገንዘብ ሆኖ ብቅ ይላል ማለት ነው። ይህ ነው እንግዲህ በሕጉ አነጋገር “ዳረጎት” (Subrogation) የሚባለው።
ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ የኢትዮጵያ የውል ሕግ መሰረተ ሀሳቦች በሚል ባሰናዱት መጽሀፍ ውስጥ ዳረጎት የሚለውን የሕጉን አነጋገር “በባለገንዘቡና በባለዕዳው መሀል ባለ የግዴታ ግንኙነት ውስጥ ከሁለቱ ውጭ የሆነ ሶስተኛ ሰው የባለዕዳውን ግዴታ በመወጣት የባለገንዘቡን የመብት ጥያቄ የሚመልስበትና በምትኩ እርሱ ራሱ በዚያው ግንኙነት የባለገንዘብነት መብት የሚያገኝበት አሰራር ማለት ነው” ሲሉ አንድምታ ሰጥተውታል።
ከዚህ ትርጓሜ እንደምንረዳው ታዲያ የሥር ባለገንዘብ (ዳራጊ)፣ ተተኪው አዲስ ባለገንዘብ (ተዳራጊ) እና ባለዕዳ የተባሉ ሶስት አካላት እንዳሉ ነው።
ዮናታን ኢዲ የተባሉ ጸሀፊ በበኩላቸው በጆርናል ኦቭ ኢትዮጵያን ሎው 9ኛው ቮልዩም ላይ “Payment with Subrogation under the Ethiopian Civil Code” በሚል ባሰፈሩት አርቲክል “ዳረጎት ከሌሎች የውል አፈጻጸም መንገዶች የሚለየው ዋናው ምክንያት በቀድሞው ባለገንዘብና በባለዕዳው መካከል ተቋቁሞ የነበረው የሥር ግዴታ አለመቋረጡ ነው” ሲሉ የፕሮፌሰር ጥላሁንን ሃሳብ በሚያጠናክር መልኩ ገልጸውታል።
እዚህ ላይ አንድ ቁልፍ ጉዳይ ጨብጦ ማለፍ ያስፈልጋል። በዳረጎት የውል አፈጻጸም ወቅት ተዳራጊው በባለገንዘቡ ምትክ ሆኖ ድርጎ ይገባል ሲባል ባለገንዘቡ በሥር ውሉ ውስጥ እያለ ስለ ዕዳው አፈጻጸም ይሰራበት የነበረውን መብት ሁሉ ይጎናጸፋል ማለት ነው።
ይህም ማለት በባለዕዳው እግር ገብቶ ለባለገንዘቡ የከፈለው ገንዘብ እንዲመለስለት ባለገንዘቡን የመጠየቅ መብት ብቻ ሳይሆን ባለገንዘቡ ለዕዳው አፈጻጸም አግኝቷቸው የነበሩ እንደ ዋስትናና መያዣ የመሳሰሉ የዕዳ ማረጋገጫና የቅድሚያ መብቶችም ጭምር ናቸው ወደ ተዳራጊው የሚሸጋገሩት።
በዚሁ መነሻ ዳረጎት ለተዳራጊው፣ ለዳራጊውና ለባለዕዳውም ሳይቀር ጠቀሜታ ስላለው ነው ሕጉ በልዩ ሁኔታ የደነገገው። በተለይም ለውሎች አፈጻጸም ጠቀሜታው የጎላ ነው።
ባለገንዘቡ ከባለዕዳው የሚጠይቀውን ዕዳ ያለብዙ ድካም እንዲያገኝ ያደርጋል። ባለዕዳው በበኩሉ ዕዳውን ለባለገንዘቡ በሚከፍልበት ወቅት አቅም ላይኖረው ስለሚችል ከተዳራጊው በሚያገኘው ገንዘብ ዕዳውን ከፍሎ ለአፍታም ቢሆን የእፎይታ ጊዜ እንዲገዛ ያደርገዋል።
ተደራጊውም ቢሆን በባለገንዘቡ ምትክ ድርጎ በመግባት ባለገንዘቡ ይሰራባቸው የነበሩ የዋስትናና የንብረት መያዣን የመሳሰሉ የዕዳ ማረጋገጫ መብቶችንም ጠቅልሎ ስለሚረከብ እንደተራ ባለገንዘብ ሳይሆን የተሻለ መብት እንዳለው ተዳራጊ ባለገንዘብ ነው ሕጉ የሚቆጥረው።
ከሕግ የሚመነጭ ዳረጎት
በሕጋችን የዳረጎት መብት በሁለት መልኩ ነው የሚመነጨው። በአንድ በኩል ሕጉ ራሱ በአንዳንድ አጋጣሚዎች የባለዕዳውን ግዴታ የተወጣውን ሰው በባለገንዘቡ ሥፍራ ገብቶ ተዳራጊ ያደርገዋል።
እንዲህ ዓይነት ሰዎች ቀድሞውኑም ቢሆን በባለዕዳው እግር ተተክተው የእሱን ግዴታ የፈጸሙት በሕግ ግዴታ ስለተጣለባቸው ነው።
በፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 1971 እንደተገለጸውም የሌላውን ሰው ዕዳ ለመክፈል የሚገደዱ (“…those who are bound to pay for others”) ወይም ከሌላው ሰው ጋር በመሆን ዕዳ ለመክፈል የሚገደዱ (“…those who are bound to pay with others”) ናቸው።
እናም እነርሱ አስቀድመው ለማይጠየቁበት የባለዕዳው ዕዳ ከፋይ ሆነው በመገኘታቸው በምላሹም ሕጉ የማካካሻ መብትን አጎናጽፏቸዋል – መዳረግን።
በዚሁ መነሻ የባለዕዳውን ዕዳ የከፈሉት እነዚህ ሶስተኛ ወገኖች ዕዳውን ከከፈሉባት ቅጽበት ጀምሮ ያለምንም ሌላ ውል ቀጥተኛ የተደራጊነት መብት ያገኛሉ ማለት ነው።
ሕግ ተዳራጊ የሚያደርጋቸው እንዲህ ዓይነት ሰዎች ዋሶች፣ የአንድነትና የነጠላ ባለዕዳዎች፣ የጋራ ወራሾች፣ መድን ሰጭዎች እንዲሁም ንብረታቸውን በመያዣነት የሰጡ ሰዎች ናቸው።
በዋስትና ሕጉ “ዋሱ በከፈለው ገንዘብ ልክ በባለገንዘቡ መብት ተዳራጊ ሆኖ ይገባል” በሚል የተገለጸው አነጋገር እንደሚያሳየው ዋሶች እዳ ለመክፈል የሚገደዱ በመሆናቸው ተዳራጊ የሚሆኑትም በከፈሉት ገንዘብ ልክ መሆኑን ነው።
አንድ ሰው በአንድ ውል ውስጥ ለባለዕዳው ግዴታ አፈጻጸም ሲል ለባለገንዘቡ ማረጋገጫ ይሆን ዘንድ ንብረቱን በመያዣነት ሊያስይዝ ይችላል።
ይህ የንብረት መያዣ ሰጭ ሰው ደግሞ በባለዕዳው ግዴታውን ባለመወጣት መዘዝ የመያዣው ንብረት በባለገንዘቡ እንዳይወሰድበት ወይም እንዳይሸጥበት ዕዳውን ከፍሎ ንብረቱን ያድናል። ይህን ጊዜ ታዲያ በባለገንዘቡ ስፍራ ድርጎ ገብቶ ከባለዕዳው ላይ ገንዘቡን የመጠየቅ መብት ሕጉ ሰጥቶታል ማለት ነው።
ከዚህ በመነሳት ዋሶችና የንብረት መያዣ ሰጭዎች የሌላ ሰውን ዕዳ ለመክፈል የሚገደዱ ሲሆኑ፤ የመዳረግ መብታቸውም ለባለገንዘቡ በከፈሉት ገንዘብ ልክ መሆኑን መረዳት ይገባል።
በሌላ በኩል ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች በማይከፋፈል ኃላፊነት የተጣመሩ ባለዕዳዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ ማለት አንዱ ባለዕዳ ስለሁሉም ባለዕዳዎች ዕዳ አላፊ የሚሆንበት አሰራር ነው።
እንዲህ ባለ ግንኙነት ውስጥ አንዱ ባለዕዳ የሁሉንም ግዴታ እንዲከፍል ተገዶ ሊከፍል ይችላል። በዚህ ሁኔታ የሁሉንም ዕዳ የከፈለው ባለዕዳ ከድርሻው በላይ ለከፈለው ገንዘብ በሌሎቹ ባለዕዳዎች ላይ የባለገንዘብነት መብት ያገኛል – ተዳራጊ ይሆናል።
የጋራ ወራሾች ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። ዕዳ ትቶ የሞተ ሰው ወራሽ የሆኑ ሰዎች ባለገንዘብ ዕዳውን እንዲከፍሉ በጠየቃቸው ጊዜ የውርሱን ዕዳ የከፈለ ልዩ የኑዛዜ ተጠቃሚ የሆነ ወራሽ ስለከፈለው ዕዳ በባለገንዘቡ ተተክቶ ሌሎቹን ወራሾች እንዲከፍሉት የማስገደድ መብትም በውርስ ሕጉ ተሰጥቶታል።
በዚህ መነሻ የአንድነትና የነጠላ ባለዕዳዎችና የጋራ ወራሾች በከፈሉት ዕዳ ልክ ሳይሆን እነሱም በድርሻቸው ልክ ባለዕዳ ነበሩና የመዳረግ መብታቸው ከድርሻው በላይ በከፈሉት ገንዘብ ልክ ነው።
ከውል የሚመነጭ ድርጎ
ሕጉ ከላይ ለጠቀስናቸው አንዳንድ ሶስተኛ ወገኖች በራሱ የተደራጊነት መብት እንደሚሰጠው ሁሉ ከባለዕዳው ወይም ከባለገንዘቡ ጋር በሚደረግ ሥምምነት የተደራጊነት መብትን ማግኘትም ይቻላል።
በሕጉ ቁጥር 1968 ላይ በግልጽ ሰፍሮ እንደምናነበው ከባለዕዳው የሚጠይቀውን ክፍያ ከሶስተኛ ወገን የተቀበለ ባለገንዘብ ይህንን ሶስተኛ ወገን በእሱ ምትክ ተዳራጊ አድርጎ ሊሰይመው ይችላል።
በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሚሰጥ ዳረጎት ግልጽና ክፍያውም እንደተፈጸመ ወዲያው በአንድነት መፈጸም እንዳለበት ነው ሕጉ የሚገልጸው። ይህ ማለት አዲስ በሚፈጸመው የባለገንዘቡና የሶስተኛው ወገን ስምምነት ውስጥ ጉዳዩ የዳረጎት ጉዳይ መሆኑ በግልጽ መታወቅ አለበት።
የውሉ ጉዳይ ዳረጎት መሆኑ በግልጽ ካልሰፈረ ግን የባለዕዳውን ገንዘብ የከፈለው ሶስተኛ ወገን እንደተራ ባለገንዘብ እንጂ እንደተዳራጊ አይቆጠርም።
እናም የከፈለውን ገንዘብ ከባለዕዳው በራሱ መንገድ ያስመልሳል እንጂ እንደተዳራጊ ሆኖ ባለገንዘቡ ይሰራባቸው የነበሩ የዋስትና ወይም የንብረት መያዣ መብቶችን አይጠቀምባቸውም ማለት ነው።
ባለገንዘብ ሶስተኛ ወገንን ተዳራጊ የማድረግ መብት እንዳለው ሁሉ ባለዕዳም ተመሳሳይ መብት በሕጉ ተሰጥቶታል። ከባለገንዘብ የነበረበትን ዕዳ ከሶስተኛ ወገን ገንዘብ ተበድሮ የከፈለ ባለዕዳ ይህንን ሶስተኛ ወገን በባለገንዘቡ ምትክ ተደራጊ ሊያደርገው ይችላል።
በእንዲህ ዓይነቱ በባለዕዳ የሚሰጥ ድርጎ ውስጥ ብድሩ ከሶስተኛ ወገን የተወሰደው ለዕዳው መክፈያ መሆኑን በሥምምነቱ ላይ በግልጽ ማሳየት ያስፈልጋል። ሥምምነቱም ዳረጎቱ የተሰጠበትን ቀን በግልጽ ማመልከት አለበት።
የዳረጎት ውጤት
በሕግም ሆነ በውል በተሰጠ ድርጎ ተዳራጊው ሰው ባለገንዘቡ ቀድሞ ይሰራባቸው የነበሩትን የዋስትና፣ የመያዣና ሌሎችንም ተያያዥ ጥቅሞች በእጁ ያደርጋል።
ይህ ብቻም ሳይሆን ተዳራጊነቱ በሁሉም ዕዳ ላይ ከሆነ ሁሉንም የዕዳውን ዋና (ኦሪጂናል) ሰነዶችና ማናቸውንም ማስረጃዎች ባለገንዘቡ ሊያስረክበው ይገባል። በተመሳሳይ በከፊል ዕዳ ላይ ተዳራጊ ከሆነም በሁለት ምስክሮች የተረጋገጠ ቅጂ ባለገንዘቡ እንዲሰጠው ይጠበቃል።
ሌላው መሰረታዊ የዳረጎት ቁልፍ ውጤት ዳረጎት የቀድሞውን ባለገንዘብ መብት የሚጎዳ መሆን እንደማይገባው በሕጉ መገለጹ ነው። ይኸውም ባለገንዘቡ ገንዘቡ የተመለሰለት በከፊል ከሆነ ቀሪውን ዕዳ ከባለዕዳው ለመጠየቅ ከተዳራጊው ይልቅ የቅድሚያ መብት ተሰጥቶታል።
ይህም ማለት የባለዕዳው ሀብት የባለገንዘቡን ቀሪ ዕዳና የተዳራጊውንም ዕዳ በሙሉ ለመክፈል የማይበቃ ከሆነ በቅድሚያ ሊከፈል የሚገባው ያለገንዘቡ ዕዳ ነው ማለት ነው።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2012
በገብረክርስቶስ