የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 5ኛ ልዩ ስብሰባው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጥያቄ ፦ ኮሮና ቫይረስ በአለም ብሎም በሃገራችን ስርጭቱ በከፍተኛ ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፤ በተለይም በድንበር አካባቢ የሚገኙ ዜጎች ለከፍተኛ ስጋት እየተዳረጉ ይገኛሉ፤ ስለሆነም በአካባቢ ያለውን የቫይረስ ስርጭት ለመከላከል እንዲሁም ቫይረሱ የምጣኔ ሀብቱን በተለይም የግብርናውን ዘርፍ እንዳይጎዳው በመንግስት በኩል ምን እየተሰራ ነው ?
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፦ ቫይረሱ ሁለቱን የከተማ አስተዳደሮች ጨምሮ በመላ ሃገሪቷ በከፍተኛ መጠን ተሰራጭቷል። በዚህም ኮሮና በመላው ዓለም ከ 113 በላይ አገራትን ያጠቃ ትልቁን ትንሹን ያነጋገረ ከአንድ መቶ ዓመት በኋላ አስከፊ ክስተት ሆኖ የ 21ኛው ክፍለ ዘመን ቴክኖሎጂ፣ ሀብትና እውቀት ሊመክተው ያልቻለ አደገኛ ክስተት ነው፤ ይህ ሁኔታ እስከ ዛሬ ባለው መረጃ በዓለም ላይ 7 ሚሊየን ህዝብ አጥቅቷል። ከነዚህም መካከል 4 መቶ ሺ ገደማዎቹ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ይህም ቢሆን በንጽጽር ቁጥሩ ያነሰ የሚመስል ነገር ግን በፍጥነት እያደገ ያለውን የአፍሪካ ሁኔታ ስንመለከት እስከ አሁን 185 ሺ ገደማ ሰዎች በዚህ በሽታ መያዛቸውን ሪፖርቶች ያመለክታሉ። ከተያዙ ሰዎች ውስጥም 5 ሺዎቹ ህይወታቸው አልፏል።
ይህም የሚያሳየው በሽታው በአህጉራችንም ከመያዝ አልፎ በመግደልም በኩል ቁጥሩ እየጨመረ መምጣቱን ነው። አሁንም በንጽጽር ከአፍሪካ በምስራቅ አፍሪካ አነስተኛ ቁጥር ያለው ቢመስልም 18 ሺ ሰዎች በዚህ በሽታ የተጠቁ ሲሆን 581 ሰዎች ሞተዋል። ከላይ ጀምሮ ስንመለከት እኛ ጋ እስከሚደርስ ቁጥሩ ትንሽ ቢመስልም በሁሉም አቅጣጫ በስፋት የመሰራጨትና ህይወትን የመቅጠፍ አቅሙን እያሳየ ይገኛል።
እስከ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ 2020 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ 27 ወገኖቻችን ህይወታቸውን አጥተዋል። ዓለም ላይ ካለው ስርጭትና የመግደል አደጋ አንጻር እስከ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የህዝብ ቁጥር አንጻርም የተያዘውና የሞተው ሰው መጠን አነስተኛ ነው። ይህ በመሆኑ የመዘናጋትና ኮሮናን የመናቅ ዝንባሌ በስፋት ይታያል።ኢትዮጵያ ውስጥ 2020 ሰዎች መያዛቸው ብቻ ሳይሆን በሁሉም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በሽታው ተገኝቶባቸዋል፤ እያንዳንዱን ስንመለከት ከፍተኛ ቁጥር ያለው አዲስ አበባ ላይ ነው 1ሺ 444 ሰዎች በንክኪ ብቻ በበሽታው ተይዘዋል። ኦሮሚያ ላይ 125 ዎች፣ አማራ 119 ሰዎች፣ ሶማሌ ክልል 112፣ ትግራይ 64፣ አፋር 34፣ ሀረሪ 14፣ ደቡብ 11፣ ድሬደዋ 10፣ ቤሻንጉል 4 እና ጋምቤላ 1 ሰው በበሽታው ተይዟል። ይህ የሚያሳየው ቁጥሩ በዓለም ላይ እያደገ የመጣ ብቻ ሳይሆን በአህጉራችን ብሎም በምስራቅ አፍሪካ ወደ ኢትዮጵያ ከዛም አዲስ አበባ እሱንም አልፎ በሁሉም ክልሎች እየታየና እየተስፋፋ ያለ መሆኑን ነው።
በሽታው ብዙሀኑን የሀዘን ማቅ አልብሷል፤ የአለምን የኑሮ ዘዬ በመፈተን የማደግና የመለወጥ ተስፋችንን አቀጭጯል። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ያለው የጤና ስርዓት በተለይም ያደጉት አገራት የጤና ስርዓት ዜጎቻቸውን ከሞት መታደግ እንዳይችል ያደረገም ነው።
ኮሮና ዛሬ 4 መቶ ሺ ሰው ገደለ ብለን ሪፖርት ስናቀርብ ሁለተኛ ዙር እንደማይመጣ ከልምዳችን ተምረን ማስቆም ካልቻልን በብዙ ሚሊየን ሊባዛ ይችላል። በሽታው በእድሜ፣ በቀለም፣ በዘር፣ በአየር ጸባይ ልናቆመው የማንችለው ከመሆኑ አንጻር ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል።
እንደ ሃገር ቫይረሱን መከላከል ሳይሆን ያለበትንና የሌለበትን ሰው መለየት የሚያስችል ብቃት አልዳበረም፤ ባለፉት ሶስት ወራት በተሰራው ውጤታማ ስራ በአሁኑ ጊዜ በቀን 8 ሺህ ሰው መመርመር የሚያስችሉ 31 ላብራቶሪዎች ተፈጥረዋል።
ከደቡብ አፍሪካ፣ ጋናና ሞሮኮ በመቀጠል ኢትዮጵያ 143 ሺህ ሰው የመረመረች ሲሆን፣ ሃገሪቷ የመመርመር አቅሟን አጠናክራ ትቀጥላለች። በመጭው ሐምሌ ወር ላይ የላብራቶሪ ቁጥሮቹን ወደ 38 በማሳደግ በቀን እስከ 14 ሺህ ሰው ለመመርምር እየተሰራ ነው።
ቫይረሱን ከመከላከል ጎን ለጎን የጤና ስርዓቱን ለማዘመን 5 ቢሊዮን ብር ተመድቦ እየተሠራ ሲሆን፤ 54 የሕክምና መስጫዎች ማዕከላት፣ 30 ሺህ የቫይረሱ ምልክት ያለባቸውን ሰዎች እንዲሁም 17 ሺህ 500 በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎችን ማስተናገድ የሚያስችሉ ቦታዎች ተዘጋጅተዋል።
ጥያቄ ፦ የኮቪድ 19 በሽታ ወረርሽኝ በአገራችን አጠቃላይ ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመከላከል በመንግስት በኩል ከአጭርና ረጅም ጊዜ አኳያ እየተወሰዱ ያሉ የመፍትሔ እርምጃዎች እንዲሁም እየተከተለ ያለ የፖሊሲ አቅጣጫ ካለ ማብራሪያ ቢሰጥበት?
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፦ ኮሮና በጤናው ዘርፍ ካስከተለው ዘርፈ ብዙ ችግር ባሻገር በኢኮኖሚው ላይ የአለምን ጠቅላላ ሁኔታ በማናጋት የአቅርቦትና ፍላጎት ችግር እንዲከሰት በዚህ ምክንያት ደግሞ ገበያው ላይ የሚፈለጉ እቃዎች እንዳይኖሩ አንዳንድ ምርቶችም ፈላጊ እንዲያጡ አድርጓል። በመሆኑ እነዚህን ነገሮች አስተካክሎ መምራት በጣም ያስቸግራል። ከጤናው ጋር ተያይዞ የመጣው ችግር ኢኮኖሚውን በከፍተኛ ሁኔታ ሊፈትነው ችሏል። ኢኮኖሚው በራሱ ሁኔታ ሲፈተንና አንዳች ኃይል ከውጭ መጥቶ ሲፈትነው የሚመጣው ውጤት አንድ አይደለም፤ በዚህ ጊዜ በተለመደው በኢኮኖሚ ቀመር ብቻ መፍትሔ ማስቀመጥ ስለማይቻል ችግሩ በመጣበት አግባብ መፍትሔውንም ማፈላለግ ይጠይቃል።
አሁን ላይ ከ 170 በላይ አገራት ዓመቱን ሲጀምሩ ከነበራቸው የኢኮኖሚ እድገት በእጅጉ ሊያሽቆለቁሉ እንደሚችሉ የአለም ባንክ ሪፖርት ገልጿል። ይህ ደግሞ ወደዜጎች ሲከፋፈል ብዙዎችን የሚያደኸይ ነው። እኛም በዝቅተኛ ደረጃ ከሚጎዱትና ለማገገም ደግሞ ረዘም ያለ ጊዜ ከሚወስድባቸው አገሮች ተርታ የምንመደብ በመሆናችን ሙሉ እሳቤያችንና ስትራቴጂያችን ምቱን መቀነስ ጊዜውን ማሳጠር ላይ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ የዓለም የሸቀጦች ንግድ በ 27 በመቶ እንደሚቀንስ ይታሰባል፤ ይህ በጣም በብዙ ደረጃ ኢኮኖሚውን የሚያናጋ ሲሆን በዚህም ከ 350 ሚሊየን ገደማ ሰዎች ከስራቸው ተፈናቅለዋል። ይህ ማለት ደግሞ በስራቸው ያሉ ቤተሰቦችና ህጻናት አደጋ ላይ ወድቀዋል። ከነዚህ ውስጥ ምናልባትም 2 መቶ ሺ ኢትዮጵያውያን በውጭ አገር የሚሰሩና ስራ አጥ የሆኑ ካሉ ከእነሱ የምናገኘውንም ገቢ እንድናጣ ያደርጋል። በሌላ በኩልም የዓለም ምግብ ድርጅት በኮሮና ምክንያት 265 ሚሊየን ህዝብ ለረሀብ ይጋለጣል ብሏል። ይህ ደግሞ ቀደም ሲል ከነበረው በእጥፍ ማለት ነው። ይህ ሁኔታ በልካችን ይደርሳል ማለት ነው።
በአለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት (International monetary fund) ትንበያ መሰረትም በኮሮና ምክንያት ከ 170 ሃገራት በላይ እድገታቸው ኔጌቲቭ ይሆናል። በዚህ ዓመት የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት 9 በመቶ ለማሳደግ የታቀደ ቢሆንም በኮሮና ምክንያት 6 በመቶ እድገት ብቻ ሊመዘገብ ይችላል።
አሁን ባለው ሁኔታ የንግድ ስርዓታችን ከአለም ንግድ ጋር ከ30 በመቶ በታች የተሳሰረ መሆኑ፣ የፋይናንሻል ሴክተሩ በከፍተኛ እድገት ላይ መገኘቱ በተለይም የተበላሸው ብድር መቀነሱንና በዚህ ዓመት የኤክስፖርት አቅማችን 13 በመቶ በማደጉ እድገቱ ሊመዘገብ እንደሚችል ምክንያት ነው።
ባለፉት 10 ወራት በሁሉም ዘርፍ አበረታች እድገት ሲመዘገብ ቢቆይም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት ባለፉት ሶስት ወራት እድገቱ መቀዛቀዝ አሳይቷል። ይህም ቢሆን የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ በዚህ ሂደት አልተጎዳም።
በመሆኑም በዚህ ወቅት 138 ቢሊየን ብር ብድር ተመልሷል፤ በአንጻሩ ደግሞ 221 ቢሊየን ብር ብድር በባንኮች አማካይነት ተሰጥቷል። በተጨማሪም 87 ቢሊየን ብር በባንኮች ተቆጥቧል፤ ይህ የሚያሳየው ደግሞ በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛ እድገት መታየቱን ነው።
ከተበላሸ ብድር ጋር በተያያዘም አሁን ላይ የግል ባንኮች የተበላሸ ብድር 3 ነጥብ 4 በመቶ እንዲሁም የንግድ ባንክ ወደ 2 በመቶ ቀንሷል፤ መንግሥት ከግል ባንኮች ቦንድ ማስቀረቱ፣ ብሄራዊ ባንክ ከኮሮና ቫይረስ መከሰት በኋላ ለባንኮች 48 ቢሊየን ብር ፈሰስ ማድረጉ፣ አነስኛና ጥቃቅን ኢንዱስትሪዎች እንዳይጎዱና ብድር እንዳይስተጓጎል መደረጉ፣ ከፍተኛ ዕዳ ለነበረባቸው ግብር ከፋዮች ከ78 ቢሊየን ብር ያላነሰ እዳ መሰረዙ የሃገሪቱን ምጣኔ ሀብት ታድጓል።
ባለፉት 10 ወራት ወደ ውጭ የሚላክ ምርት በ13 በመቶ አድጓል፤ ቡና 667 ሚሊየን ዶላር፣ አበባ 440 ሚሊየን ዶላር እንዲሁም ስጋ 45 ሚሊየን ዶላር ገቢ አስገኝተዋል።
ለዚህ ደግሞ ኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ዓለም ላይ ባስከተለው ተፅዕኖ ሳቢያ የፍላጎት መጨመርና የተፈጠረው የአቅርቦት እጥረት አስተዋጽኦ አድርጓል።
ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት 10 ወራት የ27 ሚሊየን ዶላር ዋጋ ያለው 800 ኪሎ ግራም ወርቅ ብሄራዊ ባንክ ገቢ ተደርጓል።
ከኮሮና ቫይረስ ዓለም ላይ መከሰት በኋላ ወደ ሃገር ውስጥ የሚገባው ነዳጅ መቀነሱን እና ይህም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪንም ቀንሷል።
እንደ መድሃኒት እና ማዳበሪያ ያሉ አቅርቦቶች ግን ወደ ሃገር ውስጥ እየገቡ ነው፤ አሁን ላይ በኮቪድ-19 ምክንያት የቱሪዝም ዘርፉ በተለይም አገልግሎት ዘርፉ ተጎድቷል። ይሁን እንጂ አሁን ላይ በቱሪዝም ዘርፍ በተለይም የቱሪስት መስህብ የሆኑና በኪነ ጥበብ የተዋቡ የከተማ ፓርኮች ልማት እየተከናወነ መሆኑ ከኮሮና ማግስት ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ይሆናል።
ጥያቄ፦ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተ በኋላ ከፍተኛ ሰብዓዊ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እያስከተለ ይገኛል፤በአገራችንም ይህንን ተከትሎ የኑሮ ውድነትና የስራ አጥነት መንሰራፋት የምግብ ዋስትናና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ለመከላከል ግብዓቶችን በአስተማማኝ ለማቅረብ በተለይም ግብርናውን ምርታማነት ለማሳደግ የአፈር ማዳበሪያና ሌሎች ከውጭ አገር የሚገቡ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶች አቅርቦት በወረርሽኙ ምክንያት በተፈጠረ የሎጂስቲክስና የትራንስፖርት ማነቆዎች እንዴት እየተፈቱ ነው?
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፦ በግብርናው ዘርፍም ሰፊ የማዳበሪያ እና የማሳ ዝግጅት ተደርጓል፤ የተጀመረውን ኩታ ገጠም እርሻ ማሳደግ፣ በአነስተኛ ማሳ ላይ በስፋት ማምረት፣ በቆላማ አካባቢዎች የተጀመረውን ሰፋፊ እርሻ ማስቀጠል ያስፈልጋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የማዳበሪያ የምርጥ ዘር እና የአረም ተባይና ኬሚካል ዝግጅትም ተደርጓል።
ዜጎቻችን በጎርፍ እንዳይወሰዱ ጎርፍ እንከላከላለን ብለን በእሳት ማስበላት ወይም ዜጎቻችን በጥይት ክላሽ መሞት የለባቸውም ብለን በሚሳኤል እንዲበሉ መፍቀድ የለብንም፤ ማድረግ ያለብን ከሞት መከላከል ነው። ከሞት ለመከላከል ደግሞ ኮሮናን መከላከል ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚው ላይ በጥንቃቄ መስራት ያስፈልጋል። ይህንን ማድረግ ካልቻልን እራሱ ድህነትና ረሃብ ግድያ ያመጣሉ። አንደኛው የበልግና የመኸር ምርታችን ነው። እንደሚታየው ዓመቱን ሙሉ አይተን በማናውቀው ልክ ከፍተኛ የሆነ ዝናብ እያገኘን ነው። ግንቦት የሚታወቀው ሀሩር ጸሐይ ያለበት ሆኖ ነው። ዘንድሮ ግን ግንቦት የክረምት ያህል ነው የዘነበው። ይህ ሁልጊዜ የሚገኝ እድል ባለመሆኑ መጠቀም ያስፈልጋል።
መንግስት አንድም መሬት ጦም ማደር የለበትም ሲል መሬት ይዘን ዝናብ እየዘነበ እኛ ሳናርስ ቀርተን የምግብ እጥረት ቢያጋጥመን ገንዘብ ኖሮን እንኳን እንግዛ ብንል ሌሎች አምራቾችን የሚመለከት በመሆኑ ልንቸገር እንችላለን። ሆኖም በቂ ምርት አምርተን ከበላን በኋላ ቢተርፈንና ገዢ እንኳን ብናጣ ለጅቡቲ ለሱዳን ለሶማሌ እንሰጠዋለን በዚያውም ወንድሞቻችን እንዳይራቡ ማድረግ እንችላለን።
እዚህ ላይ መሬት ጦም ማደር የለበትም ሲባል ምናልባት መሬቱን ባለሀብት መንግስት ባንክ የያዘው ሊሆን ይችላል ግን በባለቤትነት ጥያቄ ምክንያት ሳይታረስ የሚቀር መሬት መኖር የለበትም።
ሌላው ከኮሮና በኋላ በውጭ ንግዱም በሌላው ዓለም ላይ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችል ስራ በመስራት ደንበኞቻችንን ይዘን መቆየትና ማርካት በቱሪዝምም እንደዛው መስራት እድገታችንን ሊያረጋግጥ በሚችል ዘርፍ ሀሉ ጠንካራ ስራን መስራት ይጠበቅብናል።
የተከበረው ምክር ቤትም እንዲገነዘበው የምፈልገው ነገር እንደ ኮሮና ያለ ክስተት ሲያጋጥም መንግስትም ይሁን ማንኛውም የስራ ኃላፊ ግብታዊ ከሆነ ውሳኔ ራሱን መጠበቅ እንዳለበት ነው።
ጥያቄ፦ አረንጓዴ አሻራን በማስፋት ኮቪድን መከላከል ከሚለው ስራ ጎን ለጎን የተለያዩ ሀይቆች በእንቦጭ እየተወረሩ በመሆኑ መላ ቢዘየድ፤
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፦ በጣና ሐይቅ ላይ እየተስፋፋ ካለው የእምቦጭ አረም ጋር በተያያዘ መንግስት ከአውሮፓ የተሻለ ማሽን በ3 መቶ ሚሊየን ብር ለመግዛት ድርድር ላይ ነው። ከዚህ ስራ ጎን ለጎን ግን የጣና ሐይቅን መታደግ ካልተቻለ ሌሎች ፕሮጀክቶችም አደጋ ይገጥማቸዋል።
እምቦጭን በጊዜያዊነት በሰው ኃይልና በማሽን ማስወገድ ቢቻልም ፥ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ዘላቂ መፍትሄ መሆኑ ግን አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል። ከዚህ ጋር በተያያዘም የበርካታ ወንዞች መፍለቂያ የሆነው የጉና ተራራ አካባቢን ማልማት በርብ እና ጉማራ ወንዞች ከፎገራ አካባቢ ካለው እርሻ ወደ ሐይቁ የሚገባውን የእምቦጭ አረም ምግብ ማስቀረት ያስፈልጋል። ጣና ሐይቅ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ውኃ ምንጭ በመሆኑም ጣና ሐይቅን መታደግ ተገቢ ነው።
እንቦጭን ለማጥፋት ከአጭር ጊዜ መፍትሄ ይልቅ በረጅም ጊዜ እና በዘላቂ መፍትሄ ላይ ማተኮር ይገባል። የፌዴራል መንግስት እንቦጭን ለመከላከል የሚረዳ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ የተሻለ ማሽን ከአውሮፓ ለመግዛት በመደራደር ላይ ሲሆን በማሽን እና በሰው ኃይል የሚደረግ እንቦጭን የመከላከል ሂደት ጊዜያዊ መፍትሄ ብቻ የሚያመጣ በመሆኑ በዘላቂነት የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ በማተኮር መፍትሄ ማምጣት ይቻላል።
የእንቦጭ አረምን ሁለት አይነት የመከላከያ መንገድ አለው፤ የረጅም ጊዜ እና የአጭር ጊዜ ናቸው። ዘንድሮ የሚተከሉት 5 ቢሊዮን ችግኞች እንቦጭን በዘላቂነት ለማጥፋት ዋነኛ መፍትሄም ናቸው። የአጭር ጊዜ የመከላከያ መንገዱ በሰው ኃይል እና በማሽን በመታገዝ ለማስውገድ መሞከር ነው፤ ነገር ግን ይህኛው መንገድ ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም። የረጅም ጊዜ የመከላከያ መንገዱ ደግሞ የአካባቢ ጥበቃ ስራ መስራት ነው።
የጉና ተራራ ጣናን እና ተከዜን የሚመግቡ ወንዞች መነሻ ነው፤ በተራራው ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች፣ ተራራው የነበረውን ደን እያጣ በመምጣቱ ምክንያት በተለይ በፎገራ አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች በጎርፍ ይጠቃሉ፣ ለም መሬታቸው እና የተጠቀሙት ማዳበሪያ ታጥቦ ተወስዶ ለጣና ሀይቅ እንቦጭ ምግብ ይሆናል።
የክልሉ መንግስት ችግሩን አስመልክቶ በማሽኖች እና በሰው ኃይል እንቦጭን ለመከላከል ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር በጉዳዩ ላይ እየመከረም ይገኛል።
ጥያቄ ፦ መንግስትና መሪ ድርጅቱ ብልጽግና በአገር አቀፍ ደረጃ በወሰዳቸው የፖለቲካ መጫወቻ የማስፋት ሚና እውነተኛ የዴሞክራሲ ግንባታ እንዲዳብር መንገድ ጠራጊ መሆኑ ይታወቃል፤ ነገር ግን አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን ብቻ ማዕከል በማድረግ ህዝቡ በእነሱ መዳፍ ስር የሆነ በማስመሰል የማደናገርሪያ ሀሳቦችን በማቅረብ መንግስት ደካማ እንደሆነና መምራት እንዳልቻለ እየፈረጁ ምርጫ እናካሂዳለን የሽግግር መንግስት መመስረት አለበት እያሉ ነው፤
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፦ ምርጫውን በተመለከተ ኮቪድ 19 በገባበት ሰሞን ብልጽግና ፓርቲ ምርጫው እንዲካሄድ ፍላጎት ነበረው ፥ በዚህ ሳቢያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ከወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ጋር ጫን ባለ መልኩ ነው የተነጋገርነው። ይሁን እንጂ ዋና ሰብሳቢዋ በሰው ጫና ሳይሆን ስራቸውን ባመኑበት መንገድ በመከወን በመወሰናቸው ውሳኔው ትክክለኛ እንደነበር ተገንዝበናል።
ምርጫው እንዲደረግ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት የነበረው ከመሆኑም በላይ ሰፊ እንቅስቃሴዎችንም ሲያደርግ ነው የቆየው፤ ሆኖም ለምርጫ ተብሎ በህዝብ ህይወት ላይ ከፍ ያለ ዋጋ የሚያስከፍል አካሄድ መከተል ደግሞ አይገባም።
ምርጫው የማይካሄደው በመንግስት ዝግጁነትና ፍላጎት ያለመኖር ሳይሆን ምርጫውን የሚያስፈፅሙ አካላት ለዝግጅት በቂ ጊዜ ያስፈልገናል በማለታቸው መሆኑን መገንዘብ ይግባል። ምርጫና ችግኝ ተከላን በማነፃፀር የሚነሱ መከራከሪያዎች ምርጫው የማይካሄደው ምርጫውን የሚያስፈፅሙ በርካቶችን ማሰልጠንና ቁሳቁሶችን ለማሰራጨት የሚያስችል ዝግጅት ለማድረግ ስለማይቻል መሆኑን መገንዘብ ይገባል።
ብልፅግና ለምርጫው ሰፊ ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበር መላ የአገሪቷ ህዝብና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያውቃሉ፤ ከሁሉም በላይ ግን አብዛኛው የምክር ቤት አባል የብልፅግና ፓርቲ አባል ስለሆነ የመንግስትን አቋም ዝግጁነትና ፍላጎት ያውቃል። ኮሮና የገባ ሰሞን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎችን በጠራበት ስብሰባ ላይ ብልፅግና ምርጫው መደረግ አለበት ኮሮና ምርጫን የሚያስቆምበት በቂ ማስረጃ አሁን የለንም የሚል አቋም ነበረው። ብልፅግና የተሻለ ዝግጅት፣ ተቀባይነትና ብቃት ያለው ምርጫ የሚያስፈራው ፓርቲ እንዳልሆነ ለሁሉም ግልፅ ነው፤ ቦርዱ ምርጫውን ማካሄድ አልችልም ብሎ ለምክር ቤቱ በላከበት ወቅት ከሰብሳቢዋ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ጋር ጠንከር ያለ ንግግር አድርገናል።ሆኖም ምርጫ ቦርድ ከእኛ በተቃራኒ መቆሙ ተቋም እየገነባን መሆኑን እንድንገነዘብ አድርጎናልም።
ምርጫ ለማስፈፀም በህግ ስልጣን ያለው ምርጫ ቦርድ አልችልም በማለቱ በጉዳዩ ላይ በመወያየት የህግ ባለሙያዎች የፖለቲካ ውሳኔው የህግ ውሳኔውን ሳይጫን ከሁሉም ወገን የተውጣጡ ሶስት ቡድኖች ተዋቅረው አራት አማራጮችን ይዘው እንዲቀርቡ ከመደረጉም በላይ ከሶስቱ ቡድኖች 90 በመቶው ህገ መንግስት ይተርጎም፤ ጥቂቶች ደግሞ ይሻሻል የሚለውን እንደ አማራጭ አቅርበዋል።
የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም ምርጫ ቦርድ ያለውንና በህግ ባለሙያዎች በቀረበው ላይ በመወያየት የህገ መንግስት ትርጉም የሚለውን አማራጭ ምክር ቤቱ ወደ ፌዴሬሽንና አጣሪ ጉባኤ መላኩንና እነዚህ አካላት በጉዳዩ ላይ ተወያይተው ውሳኔ በሚሰጡበት ጊዜ መንግስት ይህን ያስፈጽማል።
በምርጫው ዙሪያ ውይይት፣ ምክክር፣ ሽግግር የሚሉ ሃሳቦች ይነሳሉ እነዚህ ሃሳቦች እንደ እውቀት ማግኛና የግለሰቦች አስተያየት የሚጠሉ አይደሉም፤ ለውጡ የሚፈልገውም ይሄንን ነው ሃሳቦቹ ግን ኢ-ህገመንግስታዊ በመሆናቸው አይፈፀሙም። ምርጫ እንዳይራዘም የሚፈልገው ከማንም በላይ ብልፅግና ፓርቲ ነው፤ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትዕግስት በማድረግ በሚሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ምርጫ ቦርድ ተዘጋጅቶ ሁሉም ተዋንያን የሚያምኑበት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማድረግ በምክር ቤት ውስጥ ሁሉም ድምፆች የሚሰሙበት ምክክሮች ይበልጥ በኃላፊነት ስሜት የሚደረጉበት፤ አገሪቷ ዴሞክራሲ ለመገንባት መሰረት ያላት አገር መሆኗን የሚያረጋግጥ ምርጫ ማካሄድ ለሁሉም ጠቃሚ ነው።
ጉዳዩን በህግ አግባብ ብናየው ለሁሉም የአገሪቷ ህዝብ የሚጠቅም፣ ለፓርቲዎች የሚጠቅም፣ ኢትዮጵያም ያላትን ብሄራዊ ጥቅም ለማሳካት የሚያግዝ ነው።
አምስት ቢሊዮን ችግኝ መትከል ከቻልን ምርጫ ለምን ማካሄድ አንችልም የሚሉ መከራከሪያዎች ይነሳሉ ሆኖም 5 ቢሊዮን ችግኝ መትከል በጣም ብዙ የኢትዮጵያን መከራ የሚቀርፍና እድገትን ለማረጋገጥ መሰረት የሆነ ከምርጫ ጋር ትስስር የሌለው ነው።
ምርጫ እንዳይደረግ ያደረገው እያንዳንዱ ግለሰብ ሄዶ ድምፅ ለመስጠት ስለሚቸገር ሳይሆን ምርጫ የሚያስፈፅሙ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ማዘጋጀትና ማሰልጠን ስለማይቻል ነው። ችግኝ ለመትከል ግን አስፈፃሚ የለውም በተመቸን ሠዓት የሚደረግ እንጂ እንደ ምርጫ በአንድ ጀንበር የሚፈፀም አይደለም።
በአንድ ቀን ውስጥ ግለሰቦች ርቀታቸውን ጠብቀው ድምፅ መስጠት ይችሉ ይሆናል፤ አስፈፃሚዎች ካልሰለጠኑ ቁሳቁሶች ካልተደራጁ ሰው በመሰለፉና ለመምረጥ በመፈለጉ ትክክለኛ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም። ምርጫው እንዳይካሄድ ያደረገው ምርጫውን በህግ እንዲያስፈፅም ኃላፊነት የተሰጠው አካል ለዝግጅት ጊዜ ያስፈልገኛል በዚህ ሁኔታ የተሳካ ምርጫ ማካሄድ ይቸግረኛል በማለቱ ነው።
ችግኝ የምንተክለው የግብርናና የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴሮች ላለፉት ወራት ከአምስት ቢሊዮን በላይ ችግኝ ሲያፈሉ በቂ ዝግጅት ሲያደርጉ ስለቆዩ ሰዎች በፈለጉት ቀን ጉድጓድ ቆፍረው፣ በፈለጉት ጊዜ ችግኝ ተክለው ከማንም ሳይነካኩ ከኮሮና ራሳቸውን ጠብቀው ለመፈፀም የሚያስችል ከሰኔ ጀምሮ የወራት ጊዜ ስላላቸውም ነው።
ማንኛውም የልማት እሳቤ ሲነሳ በሌላ ነገር ከምናጣፋ የምንችለውን እየሰራን ከአቅም በላይ የሆነውን ደግሞ እየተመካከርን ብንሄድ ለአገሪቱ የሚበጅ መሆኑንም መገንዘበ ይገባል።
ጥያቄ ፦ የሕዳሴው ግድብ መደራደሪያ ሆኗል፤ ተሸጧል እየተባለ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት እንዳይሳካ ከሚሰሩ የውጭ ኃይሎች ጋር ተሰልፈው በየጊዜው የተለያዩ ሀሳቦችን በማንሳት ለአንድነት የቆሙ አስመስለው የኢትዮጵያን ህዝብ የሚያምታቱ አካላትን መንግስት እስከ መቼ ሊሸከማቸው ይችላል?
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፦ ሃሳቡ ከተሳሳተ አመለካከት የመጣና አሁን ላይ የግድቡ ግንባታ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ካለመረዳት የመነጨ ነው። የግድቡ ግንባታ መዘግየት ሃገሪቱን በርካታ ጥቅሞች አሳጥቷታል። ግድቡ የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት በእኩልነት የሚጠይቅ በመሆኑም ለሁላችንም ዕድገት ወሳኝነት ያለው በበጎ ዕይታ መመልከት ይገባል።
የህዳሴ ግድብ ከተጀመረ አንስቶ የዲፕሎማሲው ስራ ጠንካራ ፈተና ገጥሞት አያውቅም፤ ሆኖም ስራው ሲጠነክር የዲፕሎማሲው ፈተና ከብዷል።
የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ በጥሩ ሁኔታ በመከወኑም በዘንድሮው ክረምት 4 ነጥብ 9 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ ይይዛል ፥ ከድርድሩ ጋር በተያያዘ እየሰሩ ያሉ ኢትዮጵያውያን ምስጋና ይገባቸዋልም።
ከሱዳን ጋር በተያያዘም ሱዳናውያን የኢትዮጵያውያን ወንድምና ወዳጅ በመሆናቸው የሰሞኑ ከድንበር ጋር በተያያዘ የነበረው ክስተት ሙሉ በሙሉ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ብቻ ይፈታል።
ከለውጡ በፊት በተለያዩ ችግሮች ተተብትቦ የነበረውን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የለውጡ አመራር በብዙ መልኩ ለውጦት ግንባታው በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል፤ ግድቡ በተያዘው ወር መጨረሻ 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ መያዝ ይጀምራል።
ግድቡ ኢትዮጵያን ከድህነት የሚያወጣ ፕሮጀክት ሲሆን፤ ኢትዮጵያም አብሮ የመልማት እንጂ የሌሎች አገራትን ጥቅም የመንካት ፍላጎት የሌላት መሆኑን ያሳያል። የግድቡን ግንባታ በተመለከተ መሰረተ ቢስ ወሬ እንደሚናፈስና ግንባታው ከሚናፈሰው ወሬ በተቃራኒ በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛል። በሌላ በኩል ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር የተፈጠረው ክስተት የኢትዮጵያ መንግስት ከሱዳን መንግስት ጋር ሰፊ ውይይት እያደረገ ሲሆን፤ መሰል ውይይቶች በቀጣይም ይካሄዳሉ፤ የሚነሱ ጉዳዮችን በሠላማዊ መንገድ በውይይት ለመፍታት ጥረት እየተደረገም ይገኛል።በሱዳን በኩል ሚሊሻ ወደ አገራችን እየገባ ነው፣ ጉዳዩ በገላጋይ ዳኛ ይታይ የሚሉ ሃሳቦች እየተነሱ ነው፤ ጥያቄዎቹም ተገቢ ስለሆኑ ጉዳዩ ጥይት ለመተኮስ የሚያደርስ ባለመሆኑ በድርድር ለመፍታት ጥረት ይደረጋል።
ጥያቄ፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ሊደርስ የነበረውን ጫና ለመቀነስ የወሰዳቸው እርምጃዎች ምን ምን ነበሩ?
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረገ የሚያሰጉ አገራትን እየለየ ደረጃ በደረጃ በሽታው ወደ ኢትዮጵያ የማይገባበትን ስራ እንዲሰራ ሆኖም ጠቅሎ ስራውን እንዳያቆም ውሳኔ ተወስኖ ነበር።ምክንያቱም ከቻይና በረራ ያቁም የሚል ክስ ስለነበረ ማለት ነው። ሆኖም ኤምሬት ከቻይና ይበራል እኛ እዛ ባንሄድ ዱባይ ከሄድን በሽታውን እናመጣዋለን። በመሆኑም በወቅቱ ሙሉ በመሉ ዘግተን ካልተቀመጥን በስተቀር ቻይናን ዘግተን ሌላ አገር ብንሄድ በሽታው ይመጣል።
በዚህ የደረሰብን ጉዳት አምስት የአየር መንገዱ ሰራተኞች በበሽታው ታመውብን ነበር በአሁኑ ሰዓት ሁሉም ሙሉ በሙሉ አገግመዋል። ሆኖም አየር መንገዱ ስራውን ቢያቆም ኖሮ ልናጣ የነበረው ኢኮኖሚያዊ ችግር ከአገሪቱ አቅም በላይ ነው። ባለፉት ሶሰት ወራት ብቻ አየር መንገዱ ለደመወዝ፣ ለአየር ኪራይ እና ለአንዳንድ ወጪዎች 15 ቢሊየን ብር አውጥቷል። አስቁመነው ቢሆን ኖሮ ደግሞ 15 ቢሊየን ብር ከምታውቁት ሀብት ላይ ይወጣ ነበር። በወሰዷቸው እርምጃዎች አየር መንገዱ በርካታ አመርቂ ውጤቶችን አስመዝግቧል። አየር መንገዱ በችግር ጊዜ በረራ ባለማቆሙ ቻይና አሁን ላይ ከአየር መንገዱ ጋር ለመስራት እንድትወስን አድርጓታል። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ ግብታዊ የሆነ ውሳኔ ያሳለፉ በርካታ የአለም በተለይም የአፍሪካ አገሮች በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድተዋል፤ አገራዊ ነባራዊ ሁኔታን ሳያመሳክሩ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ለማቋረጥ መወሰን ተገቢም አልነበረም።
በዓለም ላይ አሉ የተባሉ ትልልቅ አየር መንገዶች ሰራተኛ ቀንሰዋል ደመወዝ ቀንሰዋል ኪሳራ አውጀዋል፤ የእኛ አየር መንገድ እስከ ዛሬ ድረስ አንድ ብር አልጠየቀንም። ይህ የሆነበት አንዱ መንገድ አሁን ባለው ሁኔታ የህዝብ ትራንስፖርት ቢቆምም አብዛኛውን አውሮፕላኖቻችንን ወንበር ነቅለው ካርጎ በማድረግ በዓለም ላይ ስመ ገናና ለመሆን መብቃታችን ነው።
ለዚህም ማኔጅመንቱና ሰራተኞቹ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል እንደ ኩባንያ ትልቅ መሆኑንና ትልቅ ነን ብለው ከሚሉት የሚሻል መሆኑን በተግባር አስመስክሯል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2012
እፀገነት አክሊሉ