በትግራይ ክልል የኦፍላ ወረዳ ጓራ ቀበሌ (አዲስ አለም) ነዋሪ የሆኑት ገብረመስቀል ተስፋዬ እና አቶ ረዳ አዲሱ በአካባቢያቸው ማለፍ የሚገባው መንገድ አቅጣጫው ተቀይሮ በሌላ መንገድ ማለፉን በመቃወም ቅሬታቸውን አቅርበዋል።እነዚህ ቅሬታ አቅራቢዎች የአካባቢያቸው ህብረተሰብ እንደወከላቸው በመግለጽ በየደረጃው ለሚገኙ የመንግስት አካላት ያቀረቡት ቅሬታ ሊፈታላቸው ባለመቻሉ ሕዝብ ይፍረድ ሲሉ አቤት ይላሉ።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ወደዝግጅት ክፍላችን ቀርበው መንገዱ አቅጣጫውን መቀየሩ አሳድሮብናል ያሉትን ተጽዕኖ እንዲህ አስረድተውናል። የኮረም ሰቆጣ መንገድ በ1951 እና 1952 ዓ.ም የተሰራ ጥርጊያ መንገድ ነበር። በ1987 ዓ.ም በአካባቢያቸው ለማለፍ ሰባት ኪሎ ሜትር ሲቀረው በውል በማይታወቅ ሁኔታ መንገዱ የእነሱን ቀበሌ ትቶ በሌላ አቅጣጫ ማለትም ዛታ ቀበሌ በሚባል በኩል እንዲያልፍ ተደርጓል።
በወቅቱም ይህ ለምን ይሆናል? በሚል ጥያቄ ተነስቶ እንደነበረ የሚያነሱት ቅሬታ አቅራቢዎች፤ ስራው ስልጣንን እና ባለሃብቶችን መከታ አድርጎ ስለነበረ ምላሽ ሊያገኝ አልቻለም ባይ ናቸው።በወቅቱም በማን አለብኝነት የተፈጸመ መሆኑንም ያነሳሉ። አንድ ልማት ሲሰራ የነበረውን አፍርሶ ሌላ መፍጠር ሳይሆን የመጀመሪያውን አጠናክሮ ሌላ ማልማት ነው የሚል አቋምም አላቸው። ይህ ሳይሆን የቀደመው መንገድ ተዘግቶ የዛታ መንገድ እንዲገነባ ተደርጓል ሲሉም ይቃወማሉ።
በ1986 ዓ.ም ከኮረም ተነስቶ- አዲስ አለም- ጽራሬ ወይም ጓልመርቆሬስ ቀበሌን አቋርጦ እስከ ሐሙሲት ድረስ ሕዝብ ለሕዝብ ለማገናኘት የተገነባ ድልድይ እንደነበር ያስታውሳሉ። ድልድዩም በአካባቢው በጀት መገንባቱን ይጠቁማሉ። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የመንገዱ ግንባታ በዛታ በኩል እንዲያልፍ መደረጉን በምሬት ያነሳሉ። ይህ የተደረገው ሆን ተብሎ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማቋረጥ፣ የአካባቢው ህብረተሰብ እንዳይጠቀም ለማድረግ ነው ይላሉ።
በ2005 ዓ.ም በፌዴራል መንግስት አማካኝነት ከኮረም-ሰቆጣ-አብይአዲ የአስፋልት መንገድ ሲጠና በዛታ ቀበሌ እንዲያልፍ ተደርጎ የተሰራ ጥናት መቅረቡን ያነሳሉ።
የኮረም ሰቆጣ የመንገድ ፕሮጀክት ፕላን (ካርታ) ከኮረም ተነስቶ-ፋላ-ላት- አዲስአለም (ጓራ)- ጓልመርቆሬዎስ-ሰዎሪያ-ሐሙሲት-ወለህ-ሰቆጣ-ሊገነባ የታቀደ መንገድ እንደነበር ይናገራሉ። ሆኖም በቂ ምክንያት ባልቀረበበት ሁኔታ ግንባታው ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲቀየር ውሳኔ መተላለፉን ነው የሚያብራሩት። ነባሩ መንገድ በካርታ እያለ በሌላ መስመር እንዲገነባ መደረጉ ተገቢ አይደለም ሲሉም የህብረተሰብ ተወካዮች ያብራራሉ።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት አዲስ ይገነባል ተብሎ የታሰበው የኮረም ሰቆጣ የመንገድ ፕሮጀክት የሚያልፈው በኮረም- ፋላ- ዛታ- ወለህ- ሰቆጣ ነው ይህ ደግሞ ጥናት ያልተደረገበት ነውⵆ
ቅሬታ አቅራቢዎቹ የረር ኢንጂነሪንግ በተባለ አማካሪ መሃንዲስ የቀረበው የጥናት ሰነድም ከዕውነት የራቀ ባለሙያ በስፍራው ተመድቦ ያላጠናው በመሆኑ ተቀባይነት ሊያገኝ የማይገባውና መስተካከል ያለበት መሆኑን ይናገራሉ። በዚህ ደረጃም ለየረር ተቋራጭ አቤቱታ ማቅረባቸውን በመጠቆም ተቋራጩ ‹‹ወረዳው በፈለገው መሰረት ነው የሰራሁት›› የሚል ምላሽ እንደሰጣቸውም ይጠቅሳሉ።
እንደ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገለጻ፤ ነባሩ የመንገድ ፕሮጀክት አዲስ ይገነባል ተብሎ ከሚታሰበው ይበልጣል። ምክንያቱም በኦፍላ ወረዳ ጓራ ቀበሌ አካባቢ ከ80 እስከ 90 ሺ የሚገመት ሕዝብ ይኖራል። ይህ ሁሉ ሕዝብ ብዛት እያለ አዋጭ አይደለም የሚል ሪፖርት መቅረቡ ተገቢ አይደለም። የቦታ አቀማመጡም ቢሆን አሁን ከተመረጠው የሚሻል መሆኑን በገለልተኛ ባለሙያ ሊጣራ የሚችል ሃቅ ነው። በአካባቢው የተለያዩ አትክልቶች የሚመረቱ በመሆኑ ወደ ገበያ ለማቅረብ መኪና ገብቶ መጫን አለበት አሁን ግን አስቸጋሪ በመሆኑ ልማቱን ገድቧል ። ሂደቱ ህጋዊ አግባብን ያልተከተለ፣ ስልጣንን መከታ ያደረገ በመሆኑ መታረም አለበት ሲሉም ይከራከራሉ።
መንገዱ ለምን አቅጣጫ እንደቀየረ አሳማኝ ምክንያት አቅርቦ የሚያስረዳቸው መሪ አለማግኘታቸውም እንዳስከፋቸው ያመለክታሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የአካባቢው ሕዝብ ተጎድቷል፣ መንገዱ እንዲገነባ የሚታሰብበት ቦታ አመቺ ካለመሆኑም በላይ የመንግስት ሃብት አላግባብ እንዲወጣ እና እንዲመዘበር የሚያደርግ በመሆኑ ግንባታው ባለበት ተቋርጦ በገለልተኛ አካል እንዲታይም ይጠይቃሉ።
‹‹የወረዳው እና የክልሉ መሃንዲሶች በመወያየት የሰሩት ስራ መሆኑን፣ ህዝቡም የመንገድ እና የቤት ካሳ ሳይቀበል እንዲሰራ መወሰኑ ይገለጻል እንጂ የረር ኢንጂነሪንግ ‹‹ክልል እና ወረዳ ተገኝቼ አላጠናሁም›› የሚል ምላሽ ማቅረቡን ነው የሚናገሩት።
በአንጻሩ አሁን እንዲገነባ የታሰበው የመንገድ ፕሮጀክት የልማት ተጠቃሚ ህብረተሰብ ብዛት ከ15 ሺህ እስከ 20 ሺህ የማይበልጥ ነው። የቦታ አቀማመጡም ቢሆን ከባድ ተሽከርካሪዎችን ለማስተላለፍ አዳጋች የሆነ ገደላማ መሆኑንና ተሽከርካሪዎች ምናልባት መንገድ ላይ ቢበላሹ እንኳን ስፍራው በረሃማ በመሆኑ በቀላሉ ጥገና ለማግኘት የማያስችልና ለአደጋ የሚያጋልጥ መሆኑን ይናገራሉ።
መንገዱ እስከ 90 ሺ የሚገመት ሕዝብ ያለበትን አካባቢ ተጠቃሚ ማድረግ ሲገባው ጥቂቶችን ለመጥቀም ስልጣንን መከታ ያደረግ አካሄድ ሊታረም ይገባዋል። በ1986 ዓ.ም የተሰራው የጥራሬ ድልድይም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ከነበረበት ቦታ ፈርሶ አቅጣጫውን ቀይሮ እንዲሰራ መደረጉም ትክክል አይደለም ሲሉ በቅሬታ ያነሳሉ።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ሂደቱ እንዲታረም ከትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን ኦፍላ ወረዳ ጀምሮ ለዞን፣ ለትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት፣ ለክልሉ መንገዶች ባለስልጣንና ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አቤቱታ ቢያቀርቡም ተገቢ ምላሽ ሊያገኙ እንዳልቻሉም ይናገራሉ።
የአካባቢው ሕብረተሰብ ምላሽ ማጣቱን ተከትሎም የክልሉ ብዙሃን መገናኛ ሁኔታውን እንዲዘግብ ቢጠየቅም ሽፋን ሊሰጠው አልተፈለገም። ጥያቄውን በሰላማዊ ሰልፍ ለመግለጽ ቢሞከርም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰበብ፣ በልዩ ሃይል እና በፖሊስ አሳግደው መንገዱን እያስገነቡት ይገኛሉ።በመሆኑም የመንገዱ ግንባታ ለጊዜው ባለበት እንዲቆምና ተገቢ ጥናት ተደርጎ ምላሽ እንዲሰጣቸውም ይጠይቃሉ። ወደባሰ ሁኔታ ሳይገባ የሚመለከተው አካል ጣልቃ ሊገባ ይገባልም ይላሉ።
አሁንም ቅሬታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እና ለትራንስፖርት ሚኒስቴር አስገብተው ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙም ያክላሉ።
ጓራ ቀበሌ
የጓራ ቀበሌ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባዲ አማረ በመንገዱ ግንባታ የአካባቢው ህብረተሰብ ቅሬታ እንዳለው ይታወቃል። ‹‹ወደ ክልሉ ስንቀርብ ፌዴራል ነው ያደረገው፤ ፌዴራል መንገዶች ስንጠይቅ ደግሞ ክልሉ በሰጠው መሰረት ነው እየተሰራ ያለው›› የሚል ምላሽ በመስጠት የህብረተሰቡ ቅሬታ ሳይፈታ ግንባታውን በጉልበት እየሰሩት መሆኑን ያመለክታሉ።
እንደእርሳቸው ማብራሪያ ስህተቱ የተፈጸመው በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አብርሃም ተከስተ (ዶክተር) ነው። በተደጋጋሚ ቀርበን ብናነጋግራቸውም ያላለቀውን እንደተጠናቀቀ፣ በወረዳው ምክር ቤት ያልታየን እንደታየ፣ ሕዝብ ያልተወያየበትን እንደተወያየ አድርጎ መጻፍ ስህተት ነው ሲሉ ይጠቅሱና፤ ወደክልሉ ርእሰ መስተዳድር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል (ዶክተር) ዘንድ ይዘው መቅረባቸውን ይናገራሉ። ይህ ተገቢ ያልሆነ ነገር ለምን ተፈጸመ? ብለው መጠየቃቸውን እና ‹‹ሂደቱ ተሳስቷል ይስተካከላል›› መባላቸውንም ያነሳሉ። ሆኖም መስተካከል አልቻለም።
ለረጅም አመታት ሲያገለግል የነበረ መንገድ በቂ ምክንያት ሳይኖር መቀየር የነበረበትን መንገድ ዘግቶ አዲስ መንገድ እንዲወጣ ማድረግ መታረም ይገባዋል ይላሉ።
ሂደቱን በመቃወምም ግንቦት13 እና 14 ቀን 2012 ዓ.ም ሰላማዊ ሰልፍ ሲወጡ ህግ አይፈቅድም፣ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል በሚል በመከልከላቸው ቅሬታቸውን ይዘው ለመቀመጥ መገደዳቸውን ክልሉ፣ ወረዳውና ዞኑ በተገቢው ሁኔታ እንደሚያውቁት ይናገራሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት የቅሬታ አቅራቢዎቹ ጥያቄ ትክክለኛ በመሆኑ የመንገዱ ግንባታ ድሮ ተጠንቶ በነበረው የመልክአ ምድር አቀማመጥ በቀላልና ምቹ ሁኔታ ተጠንቶ መመለስ ይኖርበታል።
በመንገዱ ግንባታ ሂደት ቅሬታ ያላቸው 11 ቀበሌዎች ይገኛሉ፣ መንገዱ በእነርሱ በኩል ቢያልፍ አራት ወረዳዎችን ያገናኛል ፣አካባቢው ወይናደጋ እንደመሆኑም ሁሉም ነገር ይመረታል፤ በተለይ በሚጥሚጣ ቃሪያ ምርት ታዋቂ ነው፣ ሽንኩርት፣ ምስር፣ ጤፍ በቀላሉ ወደገበያ ይወጣሉ።
የአካባቢው ህብረተሰብ በጠቅላላ ሲሰላ 84 ሺ ይደርሳል በአንጻሩ አሁን አዲስ በተቀየሰው መንገድ ግን ሶስት ቀበሌዎችን ብቻ የሚያቋርጥ፣ በኦፍላ ወረዳ ባለስልጣን መከታ ተደርጎ የተሰራ በመሆኑ በአግባቡ ተጣርቶ በህግ መጠየቅም አለባቸው ይላሉ።
የኦፍላ ወረዳ አስተዳደር
አቶ ረዳኢ ዱበሎ ስለመንገዱ ታሪካዊ አመጣጥ ብዙም ዕውቀት እንደሌላቸው ግን የኮረም ሰቆጣ መንገድ ፕላን ከ1989 ዓ.ም አካባቢ አንስቶ አሁን እየተገነባ ባለው መንገድ የሚያመለክት መሆኑን ነው የሚናገሩት። በ 2005 ዓ.ም ገደማ የመንገዱ ፕላን እንዲከለስ በተደጋጋሚ ጥያቄ መነሳቱንና በኮረምና በኦፍላ ጥያቄ ቀርቦ ከጠጠር መንገድ ተቀይሮ በአስፋልት ደረጃ እንዲገነባ የሕዝቡ ጥያቄ እንደነበረ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ታይቶ ይሰራ በሚል ወደ ኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን መቅረቡን ያመለክታሉ።
ጥናት የሚያደርግ ቡድን እንዳጠናው ቀበሌዎቹ በእዚህ መንገድ ይሁንልን የሚል ጥያቄ በማቅረባቸው ‹‹ጥያቄው ከአቅማችን በላይ በመሆኑ ሌሎች ባለሙያዎች እንዲያጠኑት አድርገናል። በመሆኑም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በሰጠው አማካሪ መሃንዲስ ተጠንቶ በዛታ ቀበሌ እንዲያልፍ ተወስኗል። ይህንንም አክብረናል›› ብለዋል። ከዚህ ውጪ ወረዳው ድርሻ እንዳልነበረው፣ ተቃውሞም እንዳልቀረበ፣ ማስተካከያም እንዳልተጠየቀ በመግለጽ በጥናቱ መሰረት ቶሎ ወደስራ እንዲገባ ተደርጓል ብለዋል።
የወረዳው፣ የክልልና የዞን ውሳኔ ተመሳሳይ ነው። መንገዱ የሁለት ክልል እና የፌዴራል መንግስት ፕሮጀክት በመሆኑ በወረዳ፣ በቀበሌ ፍላጎት ሊቀየር አይችልም። የቀረበውን ጥናት ተቀብለናል። አማካሪ መሀንዲሱ በስፍራው ተገኝቶ ጥናት አላደረገም በማለት የቀረበውን ቅሬታም ምላሹን የሚሰጠው ያጠናው አማካሪ መሃንዲስ እንጂ እርሳቸው እንዳልሆኑ ተናግረዋል።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ በዛታ እንዲሆን የተወሰነው ኢኮኖሚያዊ አዋጭነቱ በጥናት ተረጋግጦ ነው። በርግጥ በጓራ ቀበሌ ከሚያልፍ ይልቅ በዛታ ቀበሌ ቢያልፍ የሚነካቸው ቀበሌዎችና አጎራባች ቀበሌዎች ቁጥራቸው ይልቃል። በሕዝብ ብዛትም ቢሆን የዛታ ነዋሪዎች ይበልጣሉ። የከተማው ማዘጋጃ ቤትም የሚገኘው እዛው ነው። የመንግስት መሰረተ ልማቶች እንደጤና ጣቢያ߹ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገንብቷል።ወረዳው ሂደቱን የተቃወመ ቢሆን እንኳን ውሳኔው የየረር ኢንጂነሪንግ ነው።
በመንገዱ ግንባታ የአካባቢው ነዋሪዎች ቅር መሰኘታቸውን እንደሚገነዘቡ የሚናገሩት አቶ ረዳኢ፤ የጓራ ቀበሌ ነዋሪዎች ባገኙት አጋጣሚ ስብሰባ ሲደረግ እንደሚያነሱትና ‹‹መከታ ማድረግና አለማድረግ የሚቻለው ስልጣን ሲኖርህ ተጠቅመህ የምትጠቅመው ወይም የምትጎዳው ሲኖር ነው›› ባይ ናቸው። ይህ መንገድ ሙሉ ስልጣኑ የፌዴራል ነው። ወረዳው አቅሙም፣ ችሎታውም የለውም። አንዱን ጠቅሞ ሌላውን የሚጎዳበት አካሄድም የለም፣ የተወሰደው ሙያዊ ጥናቱ ነው ።
ድልድዩ ድሮ ከነበረበት ተነስቶ ወደሌላ አቅጣጫ እንዲቀየር መደረጉን ግን እርሳቸውም ተገቢ እንዳልነበረ ያነሳሉ። መጀመሪያም መነሳት እንዳልነበረበትና መንገድ ሲገነባ ያለው በነበረበት እንዲቀጥል ማድረግ ይገባል እንጂ የነበረውን አውድሞ ሌላ መገንባት ጥሩ አይደለም ይላሉ።
ድልድዩ የጥራሬ ወንዝን በማቋረጥ ወደ ሐሙሲት የሚያገናኝ ነበር ፤ ለመነሳት ምክንያቱ ምን እንደነበረ ባላውቅም መነሳቱ ግን ትክክል አይደለም። ድልድዩ ተገጣጣሚ ብረት በመሆኑ ቢቻል ተነቅሎ ወደነበረበት ቢመለስ ለማህበረሰቡ ያገለግላል የሚል እምነት እንዳላቸውም ያነሳሉ።
አጠቃላይ ሂደቱን ማህበረሰቡ ተገቢ ባልሆነ መንገድ እየተረዳው ተቸግረናል። እስካሁን በምንነጋገረው እንኳን መተማመን አልቻልንም። ጥናቱን የሰራው የረር ኢንጂነሪንግ አማካሪ መሀንዲስ ሆኖ ሳለ፤ ወረዳው ለአንዱ ጠበቃ ሆኖ ሌላውን እንዳገለለ ተደርጎ የሚነገረውና የሚታመነው ትክክል አይደለም። ብዙ ጊዜ ለመተማመን ሞክረንም አልቻልንም። በጊዜው ጥናቱ አሳታፊ ቢሆን ኖሮ እውነታውን በማረጋገጥ እያስተካከልን ለመቀጠል ያስችለን ነበር። ለወደፊቱ መንግስት ለሚሰራቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የማህበረሰቡ ተሳትፎ ቢኖር የተሻለ ነው ሲሉም ይመክራሉ።
አሁን እየተገነባ የሚገኘው መንገድ ለሁሉም ቀበሌዎች ያገለግላል። ቢቻል ድልድዩ ቦታው እንዲመለስ ቢደረግ መልካም ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን
እንዲህ አይነት ተመሳሳይ ጉዳዮች በጣም በርካታ ናቸው፤‹‹ተመሳሳይ ቅሬታ የሚነሳባቸው 50 ምሳሌዎች መጥቀስ እችላለሁ›› የሚሉት ደግሞ በባለስልጣኑ የዲዛይን ማኔጅመንት ዳይሬክተር አበበልኝ መኩሪያ ናቸው።
መንግስት ባለበት አገር፣ ህዝብ እየተከራከረ፣ ብዙሃን መገናኛ እየጠየቁ ሕዝብን ለመጉዳት ተብሎ መስመር አይቀየርም፤ በአሁኑ ሰዓት ኢኮኖሚው ከሚፈቅደው አንጻር ሲመዘን የተሻለ ነው የሚባለውን መንገድ መንግስት መርጦ አጽድቋል ብዬ አምናለሁ ይላሉ።
በጥናቱ ባይሳተፉም በጉዳይ ላይ ያሉ ሰነዶችን በመመልከትና ባለሙያዎችን በማማከር እኛ ብንሆን እንዴት እናየው ነበር ብዬ ለማየት ሞክሬያለሁ የሚሉት አቶ አበበልኝ ሁለቱን መስመሮች በማወዳደር ከተመለከትን ቅሬታ አቅራቢዎቹ እየጠየቁ ያሉት የሚመረጥ መስመር አይደለም። ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ የትግበራ ጥናቱ የቴክኒክና የፖለቲካ ፍላጎትን የሚያሟላው አሁን የተመረጠው መስመር ነው ብለዋል።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ መንገዱ በተፈለገው ሁኔታ ቢመረጥም እኛን ምን ታደርጉናላችሁ? የሚል ጥያቄ ቢሆን ጥሩ ነበር። ለመንግስትም ፈታኝ የሚሆነው እንዲህ አይነት አቀራረብ ተላብሶ ቢቀርብ ነበረ። ግን ውድድር ከሆነ ቀላል ነው። የእኛ ይበልጣል የሚለው መበለጥ ይኖረዋል። የእኔ ይበልጣል ለማለት ከ100 በመቶ በላይ እርግጠኛ መሆን ይኖርብሃል። በሙያ ሲመዘን የቅሬታ አቅራቢዎቹ ነጥብ አራት ሆኖ የእነዛ አምስት ከሆነ ተሸነፉ ማለት ነው። ኢኮኖሚ እስከፈቀደ ድረስ የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል መንገድ ያስፈልገዋል። እውነት ለመናገር ይሄ ሁሉ የመንግስት አካል ተሰብስቦ በእነርሱ ላይ ግፍ አይሰራም። ሰሜን አካባቢ ሰዎች መንገድ ያስፈልጋቸዋል። ይሄንን እኛም እናምናለን። መልክአ ምድሩ ተራራው… ለግንባታ ፈታኝ ነው። ኢኮኖሚ ነው የያዘን እንጂ ለሁሉም አዳርሰን ሕዝቡ ቢያመሰግነን፣ ቢመርቀን ደስ ይለናል።
ባለስልጣንን ተገን አድርጓል ወይም ሌላ ተጽእኖ አለ ተብሎ የሚነሳው ቅሬታ ልክ አይደለም ለአብነት የሚጠቅሱት ኦሮሚያ ክልል መቱ የተሰራውን መንገድ ነው። እራሳቸው በአካል ተገኝተው የቀየሩት መስመር አለ። እኔ ነኝ የቀየርኩት እያልኩኝ አልተቀበሉትም። ‹‹የቀየርከው አስፈራርተውህ ነው›› ይሉኛል። ባለሙያዎች ካሉ ህብረተሰቡ ይወክላቸውና ልከራከር እስከማለት ደርሻለሁ። ግን ሰው ሁሌ የጠየቀው ካልተሟላለት ተበድያለሁ ብሎ ነው የሚያምነው። ይሄ ትክክለኛ አካሄድ አይደለም።
ወደብልጽግና፣ ወደስልጣኔ እና ዕድገት አያመጣም። እንዲህ አይነት አስተሳሰብ መቀየር አለበት። ሁሌ ካልተስማማቸው ጥናቱ ልክ አይደለም ተብሎ ይቀርባል። ከነስህተቱም ቢሆን ምህንድስናው መታመን አለበት። ይሄን ያህል ደግሞ የሚጮህበት ነገር ሙያዊ ጥንቃቄ ይደረግበታል። እኔ እነርሱን ሳይሆን ባለሙያውን ነው የማምነው እንጂ አንድም ሰው እኔ ዘንድ ስልክ ደውሎ እንኳን ያናገረኝ የለም።
ተመሳሳይ ቅሬታ የሚሰማባቸው ብዙ ተሞክሮዎች አሉ ከእነዛ መካከል ሻምቡ አገምሳ የሚባል መንገድ ይጠቀሳል። አንዱ መስመር 16 ቀበሌ በሌላው ደግሞ 06 ቀበሌ አለ ተብሎ መቅረቡን በማስታወስ ከእራሳቸው ባለሙያ ልከው የቀረበላቸው ሪፖርት ግን የተለየ መሆኑንና አንደኛው መስመር 08 ሌላው ደግሞ 06 ቀበሌ መኖሩን ማረጋገጣቸውን ነው የሚጠቁሙት። ከተራራው በኋላ፣ ማዶ ያለ ሰፈር የሚቀርብ አለ የሚል ነገር ያቀርባሉ። ሌላውም እንዲህ ከሆነማ እኔም ያልቆጠርኩት አለ ብሎ ይነሳል አካባቢዬ የማለማው ብዙ አለኝ ቢሉም፤ ምርትን አስመልክቶ ሪፖርት የምንጠይቀው የወረዳውን ወይም ቅርብ የሚገኘውን የግብርና ቢሮ ነው። ይህ ስህተት የሚሆን ከሆነ ጥያቄ የሚቀርብበት መረጃውን የሰጠው አካል ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
አማካሪ መሀንዲሱ የተሰጠውን መረጃ መሰረት አድርጎ እንጂ በስፍራው ተገኝቶ የሰራው ጥናት አይደለም በሚል ከጓራ ቀበሌ ነዋሪዎች የሚነሳውን ቅሬታም አቶ አበበልኝ አይቀበሉትም። ሰዎቹ ቅሬታውን እንዳቀረቡ ለፍትህ በማሰብ ሌላ ሶስተኛ አካል በድብቅ በመላክ ማስጠናታቸውን ይጠቁማሉ።
ለመለየት የምትጠቀሙባቸው መስፈርቶች ምንድን ናቸው? በሚል ከዝግጅት ክፍሉ ላቀረብንላቸው ጥያቄ በተፈጥሮ ብዙ ቆረጣ፣ ብዙ መሻገሪያ ድልድይ የማይፈልግ፣ ናዳ የሌለበት፣ በተነጻጻሪ የተሻለ ማህበረሰብን የሚያገናኝ ከሆነ ውጤቱ የሚያዘው በእነዚህ መለኪያዎች መሰረት ነው ሲሉ ይናገራሉ። ይህ ማለት በአንድ ድልድይ መበላለጥ ከመጣ ተጽዕኖ ይኖረዋል። በሆነች ሜትር ኪዩብ የአፈር ቁፋሮ መበላለጥ ሊኖር ይችላል። ከእዚህ ባሻገርም ወደልዩ ልዩ ትርጉሞች የምንሄድባቸው አሉ።
መሻገሪያ ድልድይ ተነስቶ ወደሌላ አቅጣጫ መሻገሩን መረጃ እንዳላቸው የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ የቆየ መሆኑን እና ባለስልጣኑ እንደማያውቀው ይናገራሉ። የክልሉ መንገዶች ባለስልጣን ሲሰራ ድልድዩን መቀየሩን ያነሳሉ። አካባቢ የሚለማው መንገድን ተከትሎ እንደመሆኑ በአዲሱ መንገድ ልማት መምጣቱንም ያነሳሉ። አዲሱ የጥናት ቡድን የሚመለከተውም አሁን ያለውን ልማት ነው። ለእኔ የሚቀርበው ሪፖርትም አዲስ ያለውን ሁኔታ መሰረት ባደረገ መልኩ ነው።
መንገዱ ከ15 ዓመታት በፊት ወደሌላ አቅጣጫ በመቀየሩ ነው አካባቢው የለማው የሚል መከራከሪያ ሊያነሱ ይችላሉ። ይሄንን ያህል ዓመታት ወደ ኋላ ተመልሰን ማስተካክል ይከብደናል። ይሄ የፖለቲካም ውሳኔ ይሆናል። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ሊመልሰው አይችልም።
የቅርብ ታሪክ ማንሳት ይቻላል ከዳንግላ ጃዊ የሚሰራ የመንገድ ግንባታ በቅርብ ጊዜ የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ከነበረበት መንገዱን ቀይሮ እየሰራው ይገኛል። እኛ ስንሄድ ተፈጥሮን አጥፍቷል፣ የመንገዱን መሰረት አዘጋጅቷል። በነበረው መንገድ ብንሄድ ኖሮ የተሻለ ይሆን ነበረ። የአማራ መንገዶች ያንን መንገድ ወደ ጠጠር ደረጃ ስላሳደገው ተመራጭ ሆነ። ከእዚህ በኋላ ፖለቲካ ነው የሚሆነው። ይሄ ተመራጭ አይሆንም ልንል አንችልም። መጀመሪያ መንገዱን የቀየረው አካል ነው ኃላፊነት የሚወስደው።
በእነዚህ አካባቢ ያሉ መሰረተ ልማቶች፣ የማይታዩ ሃብቶች አሉ ለምሳሌ መስመር የሚቀየረው ሊለማ የሚችል ሃብት አለ ተብሎ ሲታሰብ ነው።
የመንገድ ልማት ጥያቄያቸው ምን ይሁን ?
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንም ይሁን በክልሉ መንግስት አማካይነት የእዚህ አካባቢ ሰዎች መንገድ እንዲሰራላቸው መጠየቅ መብታቸው ነው። በዕቅድም ይያዛል፣ ከማንም ጋር ሳይነጻጸር ለብቻው የሚጠናበት ዕድልም ይኖራል። አሁን ባያመለክቱም ጥያቄ እያቀረቡ ስለሆነ ማየት ይኖርብናል። እንዳመለከቱም እንቆጥራለን። እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ለዘላለምም መነፈግ የለባቸውም። ዕቅድ ውስጥ እንዲገባም መታገል አለባቸው።
ከዳንግላ ጃዊ የሚሰራው የመንገድ ግንባታ ክልሉ ሃላፊነት ወስዶ የተቀየረውን መንገድ እነሱ ወደተሻለ እንዲያሳድጉ እኛም በአስፋልት ደረጃ ለመገንባት ወስነናል። እንዲህ አይነት ነገሮች በእነርሱም አካባቢ መኖር አለባቸው። ፕሮግራሞቹ መመጋገብ አለባቸው።
አሁን ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረገ የ10 ዓመታት የመንገድ ማስተር ፕላን እያዘጋጀን ነው። ሰፊ የመንገድ መሰረተ ልማት ዕቅድ አለን። የእነርሱ ጥያቄ ምናልባት በእዚህ እቅድ ተመልሶ ሊሆን ይችላል። ያስቀመጥናቸው ራዕዮች አሉን። የትኛውም የወረዳ ከተማ አስፋልት መንገድ ማግኘት አለበት የሚለው አንዱ ነው። ወረዳ ካላቸው የአስፋልት ፕሮግራም አላቸው ማለት ነው። ካልሆነም ይህ ፕሮግራም በቅርቡ ይፋ ሲደረግ ከመጽደቁ በፊት እንዲካተት ማድረግ ይቻላል። እስከ 2013 ዓ.ም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የተዘጋ ነው። የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን ነው የምንጨርሰው። ከ2014 ጀምሮ እስከ 2024 ዓ.ም የሚተገበር ሰፊ የመንገድ ማስተር ፕላን እየተዘጋጀ ነው። ክልሎችን ከክልሎች የሚያገናኝ እና የቀለበት መንገድ አለው።
ማስተር ፕላኑ ለመድረስ ረጅም ጉዞ የሚፈጀውን ማሳጠር የሚያስችል ነው። አስፋልት መንገድ ለመድረስም አንድ ሰው ከ15 ኪሎ ሜትር በላይ በጠጠር መንገድ እንዳይጓዝ ማድረግ ያስችላል። የተለጠጠ ዕቅድ ነው። ክረምት ከበጋ ሊያስኬድ የሚያስችል መንገድ ዕቅድም በክልል ደረጃ ሊኖር ይችላል። የአስፋልት መንገድ በብቸኝነት የሚገነባው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ነው። ክልሎች አቅማቸው በእዛ ደረጃ ሊያድግ ይገባል። በክልል ደረጃም የሚገነባ ቢሆን ለማዳረስ ያስችላል የአቶ አበበልኝ መልእክት ነው።
በጉዳዩ ዙሪያ የትግራይ ክልልና የየረር ኢንጂነሪንግን ምላሽ ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ምላሽ የሚሰጡን ከሆነ በእዚሁ ገጽ እንደደረሰን የምናስተናግድ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2012
ዘላለም ግዛው