በአመት አንድ ቢሊየን ዶላር የውጪ ምንዛሬ እንደሚስገኝ እና ለ60 ሺ ዜጎችም የስራ እድል እንደሚፈጠር ይጠበቃል።ሞዴል ፓርክ በመባልም ይታወቃል።በአገሪቱ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሲገነቡ የእዚህ ፓርክ ተሞክሮ ጭምር እየተወሰደ ነው፤ የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ።በፓርኩ ለ35 ሺህ ሰራተኞች የስራ እድል ተፈጥሯል።ፓርኩ ወደ ስራ ከገባ አንስቶ በተለይም ከ2009 እስከ 2011 ባሉት አመታት ወደ ውጪ የሚልከው ምርት እያደገ መጥቷል፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ እስከ ተቀሰቀሰበት ጊዜ ድረስ በወር 10 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ ሲሆን፣ የኮሮና ወረርሽኝን በበርካታ ተቋማት ላይ ጠንካራ ክንዱን እያሳረፈ ባለበት በአሁኑ ወቅት ደግሞ ወረርሽኙን በመከላከል አተኩሮ እየሰራ ይገኛል።
አንዳንድ ኩባንያዎች ትእዛዝ ቢሰረዝባቸውም፤ አሁን ደግሞ እየተነቃቁ እንደሚገኙና እረፍት የወጡ ሰራተኞችም እየተጠሩ መሆኑን በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የፓርኩ ስራ አስኪያጅ አቶ በላይ ሀይለሚካኤል ይገልጻሉ።በርካታ ተቋማት ለመዘጋትና ለኪሳራ እየተዳረጉ ባለበት በዚህ አስከፊ ወቅት ፓርኩ ምርቶቹን ወደ ውጪ እየላከ ነው ይላሉ።ባለፈው ግንቦት ወር ብቻ 5ሚሊየን ዶላር ምርት መላኩን ይገልጻሉ።ከስራ አስኪያጁ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል፤መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሀገሪቱ በሞዴልነት የሚጠቀስ ነውና ስለ ፓርኩ ጠቅለል ያለ መረጃ ቢሰጡን?
አቶ በላይ ፡- የኢንዱስትሪ ፓርኩ በተሟላ ደረጃ የተገነባ ነው፤ ሞዴል ነው።ፓርኩን የምናየው እንደእናት /ማዘር/ ፓርክ ነው።ሁሉን ነገር እዚህ እንሞክራለን፤ እዚህ ላይ ያሉትን ህጸጾች ካረምን በሌሎች አዳዲስ የሚከፈቱ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ እንጠቀምበታለን።ሁሉንም ነገር ልክ የምንሞክረው እዚህ ነው።እንደ ላቦራቶሪ የሚታይ ነው፡፡
እንደ ፓርክ የአንድ ማእከል አገልግሎት መሟላት አለበት። የአንድ ማእከል አገልግሎት ማለት ደንበኞች ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ቦታ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።እኛ ኦ ኤስ ኤስ እንለዋለን።በአገሪቱ በአፍሪክም ጭምር / የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ፓርኮች አመታዊ ስብሰባን ላለፉት ሁለትና ሶስት አመታት ተካፍያለሁ፡፡/አንድ ማእከል ውስጥ የተሟላ አገልግሎት የሚገኘው በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ ነው፡፡
የባንክ ስራ ለመስራት ማንኛውንም የወጪ እና ገቢ /የኢምፓርት እና ኤክስፓርት/ ሂደቶችን ጨምሮ ኤልሲ ለመክፈት፣ ኤክስፓርት ፈቃድ ለማግኘት ንግድ ባንክ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ብሄራዊ ባንክ ሳይቀር ተከቶም ጭምር እየተሰራ ነው።ኢምግሬሽን፣ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች እና ኢንሹራንስ አለ።ቴሌኮም እና የፓወር ስራም እንዲሁ በፓርኩ ይገኛል።በአንድ ማእከል ውስጥ ወደ አስራ ሁለት ተቋማት አሉ።ይህንን ሁሉ አገልግሎት በተሟላ መልኩ እየሰጠ ያለው ሀዋሳ ብቻ ነው።ሞዴል የሚያሰኘው ይሄ ነው።ከእኛ በኋላ የተከፈቱ ፓርኮች በሙሉ የተከፈቱት በእኛ ሞዴል ነው ።
ስልጠና እንሰጣለን።ኮምቦልቻዎች እና መቀሌዎች ሁሉም ፓርካቸው ከመከፈቱ በፊት ከእኛ ጋር መጥተው የ15 ቀናት ስልጠና ወስደዋል።አንደ ማዕከል የተደራጀ ነው፤ የአስተዳደር ስርዓቱ በጣም ዘመናዊ ነው።ለአንድ አመት ማኔጅመንቱን ይዘውት የቆዩት ቻይናዎች ናቸው።ከዚያም በኛው ልጆች እየተሰራ ነው፡፡
ወደ 52 ሼዶች አሉ።ኮምቦልቻ እና መቀሌ ቢደመሩ የሀዋሳን አያህሉም።የሃዋሳ ፓርክ በመጠንም በኦፕሬሽንም መሪ ነው። በዘመናዊ ማጣሪያው በቀን ወደ 11 ሚሊየን ሊትር ውሃ ያጣራል።ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር መልካም ግንኙነት ያለው ሲሆን፤ ከፓርኩ ምንም አይነት ውሃ አይወጣም።95 በመቶው ውሃ በማጣራት ድጋሚ ጥቅም ላይ ይውላል።ለመጠጥ ጥቅም ላይ ባይውልም ለተቀረው ስራ ያገለግላል።ለፋብሪካው ለመጸዳጃ ቤት እና ለአረንጓዴ ልማት እንገለገልበታለን፡፡
በፓርኩ ውስጥ የሚገኘው ጉሙሩክ ወደ 50 ሰራተኞች አሉት። ባንኩም 40 ሰራተኞችን ይዟል።በጣም ትልቅ ሥራ ይካሄድበታል።በወጪ ንግድም በ2010 እና በ2011 በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኤክስፖርት ከተደረገው ግማሹ የተላከው ከሀዋሳ ፓርክ ነው።በሁሉም ፓርኮች በ2011 ዓ.ም 105 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ንግድ ተፈፅሟል።ከዚህ ውስጥ ከ50 ሚሊየን በላይ የሚሆነው ወደ ውጭ የተላከው ከሀዋሳ ነው።በሰው ሀይል በኩልም ግዙፉ ነው።በአጠቃላይ በአገሪቱ ኢንዱስትሪ ፓርኮች 75 ሺህ ሰራተኞች ይገኛሉ።ከዚህ ውስጥ 35 ሺው የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኞች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- እንደሞዴልነቱ ሌሎች ፓርኮችም በዚህ መሰረት እየተገነቡና እየተንቀሳቀሱ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ በላይ፡- አዎ! ከሀዋሳ በኋላ በተገነቡት ማለትም የመቀሌ ኢንደስትሪ ፓርክ ላይ በሀዋሳ ላይ በመመስረት የግንባታ ማስተካከያ ተደርጓል።ሥራውን በማንቀሳቀስም ሀዋሳ ጀማሪ ነበር።በዚህም ብዙ ፈተናዎች ገጥመውታል።ሌሎች ግን እኛ ባለፍንበት መንገድ በፈተና ውስጥ ማለፍ የለባቸውም።ችግሮችን እንዴት እንደፈታን ስራ ከመጀመራቸው በፊት ስልጠና እንሰጣቸዋለን።
አዲስ ዘመን፡- ፓርኩ በሀገሮች መሪዎች፣ አምባሳደሮች እና ተዋቂ ሰዎች እየተጎበኘ ነው። የጎብኚዎቹ ግብረመልስ ምን ይመስላል?
አቶ በላይ፡- ይህንን የምለው የፓርኩ ሃላፊ ስለሆንኩ አይደለም። ከውጪ በጣም የምርምር ሰዎች፣ አምባሳደሮች፣ የሐገር ጎብኚዎች ይመጣሉ።ሁሉም ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ እንደዚህ አይነት ነገር አለ?›› ሲሉ ይጠይቃሉ።የማምረቻ ቴክኖሎጂው የመጨረሻው ነው።ፓርኩ ውስጥ የማይመረት ነገር የለም።በአለም ላይ ‹‹አሉ›› የሚባሉ ብራንዶች (ታዋቂ መለያዎች) ይመረቱበታል።ጂንሶች ቢጠቀሱ እነራንግለር፣ ሊቫይስ፣ሊ ራንግለር በፓርኩ ይመረታሉ።በአለም ላይ ምርጥ የሚባሉት ሸሚዞችን ያመረታል።ይህ የሆነው ኩባንያዎቹ ሲመረጡ በጥንቃቄ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ነው።ምርጫው የተደረገው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እና ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ሃላፊዎች ኩባንያዎቹ ያሉበት ሀገር ድረስ በመሄድ ነው።እነዚህን በአለም ላይ ‹‹አሉ›› የሚባሉ ታላላቅ ባየሮችንና ብራንዶችን፤ ከፍተኛ ሃላፊዎቹ አገራቸው ድረስ ሄደው ጎትጉተው (ሎቢ አድርገው) አምጥተዋል።ያመጧቸው ግንባታው እየተካሄደ ባለበት ወቅት አሳምነው ሲሆን፤ ግንባታው እንዳለቀ የመጡ እንዲሁም ግንባታ እየተካሄደ ቸኩለው የመጡ ኩባንያዎችም አሉ።ገንብተን የምንጠራው አይደለም። ጥሪው የሚካሄው ጎን ለጎን ነው፡፡
አዲስ ዘመን ፡- በአሁኑ ወቅት በፓርኩ ውስጥ ምን ያህል የውጭ ኩባንያዎች አሉ? የአገር ውስጥ ባለሀብቶችስ አሉበት? ኢትዮጵያውያን ኩባንያዎች ለውጪዎቹ የሚያቀርቧቸው ጥሬ እቃዎች ይኖሩ ይሆን? አምርተው የሚልኩስ አሉ?
አቶ በላይ፡- የውጪዎቹ ወደ 22 ናቸው።ሶስት የአገር ውስጥ ባለሀብቶችም ፓርኩ ውስጥ ገብተው እያመረቱ ናቸው። ከሶስቱ የአገራችን ባለሀብቶች መካከል ግብዓት የሚያቀርበው አንዱ ብቻ ነው።ሁለቱ አምራች ናቸው። አምራቾቹ በቀጥታ የሚልኩ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ከፓርኩ ይጠበቃልና በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? በትስስር መስራትስ ምን ይመስላል?
አቶ በላይ፡- በፓርኩ ውስጥ በማቅረብ ላይ የሚሰሩ አሉ። በአብዛኛው ጨርቁንም ፋብሪክሱንም የሚያገኙት በፓርኩ ውስጥ ነው።የሸሚዝ ጄፒ አለ።ትስስር አለ። የፓኬጂንግ፣ የህትመት፣ የፓሊባግ እና የሌብሊንግ ስራ የሚሰሩ አሉ፤ ትስስሩ አለ።ውስጥ የሚያቀርቡ አሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በፓርኩ ያለው አጠቃላይ እንቅስቃሴ የአገሪቱን የኢንዱስትሪ ልማት ራዕይ ላይ ያሳረፈው አሻራ አለ ተብሎ ሊወሰድ ይችላል?
አቶ በላይ ፡- ለአገሪቱ አማራጩ ኢንዱስትሪ ነው። በኢንዱስትሪው ላይ ካልተሰራ ኢኮኖሚውም ሊሻሻል አይችልም።ኢኮኖሚ ሲባል የስራ እድል ፈጠራና ገቢ አለ።ፓርኮች የተለየ የሚያደርጋቸው ወዲያው ሥራ ላይ ይሆናሉ።ኩባንያዎች እንደመጡ በሁለትና ሶስት ወራት ውስጥ ሰው ቀጥረው በመስራት ኤክስፓርት ውስጥ ይገባሉ።በዚህ ምክንያት ጊዜ ስለማይጠብቁ ከሌላው የኢኮኖሚ ዘርፍ ጋር ሲወዳደሩ ብዙ ገንዘብ ያስገኛሉ።ብዙ የስራ እድል ይፈጥራሉ፡፡
መንግስት ፓርክ ላይ ያተኮረው ለእዚም ነው።ዱሮ ኢንቨስተሮች ሲመጡ መሬት ማግኘት ነበረባቸው፤ የግንባታ ጉዳይ አለ፤ እነዚህን ለማስፈጸም ደግሞ ሶስትና አራት አመታትን ሊወሰድ ይችላል።አሁን ግን ወደ ፓርክ ውስጥ በገቡ በሶስትና አራት ወራት ውስጥ ወደ ምርት ወደ ውጭ መላክ ይጀምራሉ።ይህ ማለት ኢኮኖሚውን ቶሎ መደገፍ ይጀምራሉ ማለት ነው፡፡
የስራ እድል ፈጠራም ሆነ የወጪ ንግድ ለአገሪቱ ወሳኝ ናቸው። የአገሪቱ የወጪ ንግድ እና የሚገባው ምርት አልተመጣጠነም። ወጪ ንግድ ሶስት ቢሊየን እንኳ አልገባም። ወደ ሀገር ውስጥ የምናስገባው ከ15 እስከ 16 ቢሊየን ዶላር በላይ ነው።ወጪ ንግድ ግን እየተዳከመ ነው።
ፓርኮች ለኤክስፖርቱ ህይወት ናቸው።ፈጥነው ወደ ኤክስፖርት ይገባሉ። የመንግስትም አቅጣጫ ይሄንኑ ታሳቢ ያደረገ ነው።ሀገሪቱን ኢንደስትሪያላይዝድ ለማድረግ እና የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ቁንጮ ለማድረግ እየተካሄደ ባለው ጥረት ፓርኮች ቁልፍ ሚና አላቸው።ቶሎ ወደ ሥራ ገብተው የስራ እድል ይፈጥራሉ።ገንዘብ ያስገኛሉ። ኢኮኖሚው ቶሎ እንዲያንሰራራ ስለሚያደርጉ ተፈላጊ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው ምርት ምን ያህል የውጭ ምንዛሬ እየተገኘ ነው? ገቢው የሚጠበቀውን ያህል ነው? መቼ እንደሚሆን ባላውቅም ፓርኩ በአመት አንድ ቢሊየን ዶላር ያስገኛል ተብሏልና የፓርኩ ጉዞ ምን ያመልክታል?
አቶ በላይ ፡- ፓርኩ ወደ ስራ የገባው በ2009 ነው።ከ2009 አንስቶ ምርቶቹ እየተላኩ ናቸው።ገቢውም በየአመቱ እድገት እያሳየ ነው።አሁን በወር 10ሚሊየን ዶላር ከፓርኩ ኤክስፓርት ይደረጋል።ኮቪድ 19 ሳይቀሳቀስ በፊት የሚላከው መጠን በወር እስከ 10 ሚሊዮን ደርሷል።ይህ ግን ከመስከረም አንስቶ እየቀነሰ መጥቷል። ባለፈው ችግሩ ቻይና ላይ ሲከሰት ጥሬ እቃ ማግኘት ከባድ ነበር።ይህን እንፈታለን እያሉ ባሉበት ወቅት ገዥዎቻቸው ያሉባቸው አውሮፓና አሜሪካ ተዘጉ።እንደዚያም ሆኖ ግን ባለፈው ወር 3 ሚሊዮን ዶላር በወጪ ንግድ ተገኝቷል።
ኩባንያዎቹ በችግሩ የተነሳ መዘጋት እና ሰራተኞችን ማሰናበት ሲገባቸው፤ ገዥዎቻቸው ሙሉ ለሙሉ ትእዛዝ ሰርዘውባቸው ባለበት ባለፈው ወር ሶስት ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ምርት ተልኳል። በአሁኑ ወር ደግሞ የ5ሚሊዮን ዶላር ምርት ወደ ውጪ ልከዋል።የዘንድሮውን ሳይጨምር ከ2009 እስከ 2011 ድረስ /ባለፉት ሶስት አመታት /ወደ 96 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር አስገኝተዋል።የዘንድሮው ምርት ደግሞ ምናልባትም ይህን ያህል ሊሆን ይችላል፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ሌላው የኢንዱስትሪዎች ትልቅ ስጋት ተደርጎ ይነሳ የነበረው የገበያ እጦት ያጋጥማቸዋል የሚለው ነበር።ፓርኩ ከእዚህ አንጻር ምን ይመስላል? የፓርኩ ምርቶች ተፈላጊነት ምን ይመስላል?
አቶ በላይ ፡- እንደነገርኩህ የፓርኩ ምርቶች በአለም የሚታወቁ ብራንዶች ናቸው።አምራቾቹ በጋርመንት ኢንዱስትሪ ውስጥ ለብዙ አመታት የቆዩ ናቸው።መቶ አመት የሆነው እንደ ፒቪኤች አይነቱ አለ።70፣ 80፣ 50 አመት የሰሩ አሉ።ትንሹ እድሜ 40 አመት የሞላቸው ናቸው።እነዚህ ብራንዶቻቸው የታወቁ እና ሌላ ሀገር ሲሰሩ የነበሩ ናቸው።የገበያ ችግር የለባቸውም።አንድ ቀንም ስለገበያ አስበው አያውቁም፡፡
ሀገር ውስጥና ፓርክ ውስጥ ያለው ነገር ተሟልቶ ሰራተኛ አግኝተው አሰራሩ ምቹ ከሆነላቸው አሁን በወር የሚልኩትን 10ሚሊዮን ዶላር እስከ መቶ ሚሊዮን ማድረስ ይችላሉ። ነገር ግን የሰራተኛ ጉዳይ አለ።እኛ ለኢንዱስትሪው አዲስ ነን።እዚህ የሚሰሩት 90 በመቶው የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው።ከገጠር ከሀዋሳ ዙሪያ የመጡ ናቸው።ኢንዱስትሪውን መልመድ አለባቸው።የመኖሪያና የትራንስፖርት ጉዳይን ስታነሳ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡
ከኛ በኩል እንጂ ከኩባንያዎቹ በኩል ምንም የጎደለ የለም፡፡ ፓርኩ እስከ ተዘጋጀ እና ነገሮች እስከተመቻቹ ድረስ ።እንደሚታወቀው ከዚህ እስከ ሞጆና ጅቡቲ ድረስ የሎጂስቲክ ችግሮች ነበሩብን።እነዚህ ከተስተካከሉ ገበያው በእጃቸው ነው፤ ይታዘዛሉ።የተፈለገውን ያህል ያመርታሉ። ምክንያቱም ምርቶቻቸው በአለም ገበያ ውስጥ ለብዙ አመታት ይታወቃሉ፤ ኩባንያዎቹም በአለም ገበያ ውስጥ ብዙ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡
አሁን የሚያነጋግረው የገበያ ጉዳይ ሳይሆን የሀገራችን ጉዳይ ነው። ለኢንዱስትሪው አዲስ ነን፤ ቢሮክራሲው ፤ ፓርኩ ውስጥ የምንሰራው ራሳችን ለኢንዱስትሪው እንግዳ ነን።እየለምድን እንመጣለን።ያ ችግር ካልሆነባቸው በስተቀር የገበያ ችግር የለባቸውም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ምን ያህል ሰራተኞች በስራ ላይ ይገኛሉ? ሰራተኞች የሚቀጠሩበት አግባብስ ምን ይመስላል? አካባቢው ላይ ያተኮረ ነው ወይስ ኢትዮጵያዊ መልክ አለው?
አቶ በላይ፡- ከኮቬድ በፊት 35 ሺ ነበሩ።አሁን ወደ 30 ሺ አሉ። ከኮቬድ ጋር በተያያዘ በመደናገጣቸው እንዲሁም ኩባንያዎች ትእዛዝ እየተሰነዘረባቸው ከክፍያ ጋር እቤት እንዲቆዩ ረፍት ያስወጧቸው ሰራተኞች አሉ።አሁን ደግሞ ኩባንያዎቹ እንደገና እየተንቀሳቀሱ ሰራተኞቹም በስልክ እየተጠሩ ናቸው።
የስራ እድሉ ለሁሉም ክፍት ነው።በተለይ ሙያተኞቹ ከየትኛውም ክልል ሊቀጠሩ ይችላሉ።የስፌት ስራ የሚሰሩት ግን ክፍያውም ትንሽ ስለሆነ ለአንድ ወር ለሁለት ወር ስልጠና እየተሰጣቸው የተቀጠሩ ናቸው።ለእዚህ ደግሞ የሚመረጡት የአካባቢው ወጣቶች ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን ፡-ፓርኩ ለአካባቢው ጥሩ የስራ እድል ፈጥሯል ማለት ይቻላል?
አቶ በላይ፡- 35ሺ ሰው በሀዋሳ የስራ እድል ማግኘቱ ለከተማዋ ትልቅ እድል ነው።የውጭ ዜጎችን ትራንስፖርት ላይ የሚሰሩትን፣ ምግብ የሚያቀርቡትን ሲጨምር ፓርኩ ይዞ የመጣው የሰው ሀይል ወደ 50 ሺ ይደርሳል።በዚህ ሀይል ሳቢያ የሚፈጠረው የስራ እድል ፤በስሩ ያለው ቤተሰብ ሲታሰብ ፓርኩ ለከተማዋ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡
ለከተማው የሚያስገኘው የገቢ ግብር አለ።እስከ መቶ ሚሊዮን ብር ድረስ ለሰራተኞች ደመወዝ ይከፈላል።ይህ በከተማው ኢኮኖሚ ውስጥ ይገባል።በታክስም ከተማው ወደ አስራ ምናም ሚሊዮን ብር ያገኛል።በፓርኩ ምክንያት የሀዋሳ ከተማ በዚህ ሁለትና ሶስት አመታት ውስጥ እየተለወጠች ናት።
ሀዋሳ እንደሚታወቀው ትላልቅ ሆቴሎች አሏት።ለኑሮ ለቱሪስቶች ትመቻለች። በፓርኩ ምክንያት አውሮፕላን ማረፊያ ተሰርቷል። የፍጥነት መንገዱም እየተሰራ ነው። በመሆኑም ለከተማዋ ለአካባቢው ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡
ትላልቅ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ደግሞ ከፓርኩ ጋር ይሰራሉ።የማህበራዊ ሃላፊነት ሰራዎች በሴቶች በጾታ እና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከፓርኩ ውጪ ከተማ ውስጥ የሚሰሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች አሉ።ብዙ ለጋሽ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አሉ።ከተማዋን ተጠቃሚ ያደርጋሉ።በርካታ ፋይዳዎችን ይዞ የመጣ ፓርክ ነው።ቁጭ ተብሎ ቢሰላ ቢሰላ አያልቅም።እንደ ጥናት ቁጭ ተብሎ የሚሰላም አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኞች በቂ ደመወዝ አይከፈላቸውም።ከክፍያ ማነስ ጋር በተያያዘ ሰራተኛው ተረጋግቶ እየሰራ አይደለም፤ ይለቃል ይባላል፡፡ይህ ችግር ሀዋሳ ላይ አለ?
አቶ በላይ፡- የደመወዝ ችግሮች በመጀመሪያው አመት ላይ ይነሱ ነበር።መጀመሪያ ላይ ደሞዛቸው ትንሽ ነበር።ሁለተኛና ሶስተኛ አመት ላይ ግን ሰራተኞች ከደሞዛቸው ውጪ ጥቅማ ጥቅም እንዲከፈላቸው ተደርጓል።ኩባንያዎቹም ይህን ያበረታታሉ። ደሞዛቸው ሊያንስ ይችላል።መጀመሪያም የረብሻ መነሻው ሰው ዝም ብሎ 750 የሚለው ነው፤ ግን ተጨማሪ አለው።የምግብ፣ የትራንስፖርት እና የሥራ ላይ መገኛ ጥቅማጥቅም አለ።ይህ ሁሉ ሲደመር ከአንድ ሺ ሶስት መቶና አራት መቶ ብር በላይ ይሆናል።ሰው የሚያወራው ግን 750ውን ነው።እነዚህ ሁሉ እያሉ ደግሞ ሌላ ማበረታቻ እየተሰጠ ነው።ይህም ባመረቱት መጠን ተጨማሪ ክፍያ የሚያገኙበት ነው።መጀመሪያ አመት ላይ ምርታማ አይሆኑም፤ ሁለተኛ አመት ላይ ምርታማ መሆን ይጀምራሉ።ምርታማነት እየጨመረ በሄደ ቁጥር ተጨማሪ ክፍያ ያገኛሉ፡፡
ኩባንያዎች ‹‹ይህን ከሰራህ ይህን ታገኛለህ›› እያሉ ተጨማሪ ክፍያ ይሰጣሉ።በዚህ መንገድ ከደሞዛቸው በላይ የሚያገኙም አሉ።ካለፈው አመት ጀምሮ ከደመወዝ ጋር በተያያዘ ቅሬታ የለም።ይህን ያህል ሸሚዝ ካመረትክ ይህን ያህል ታገኛለህ እየተባለ ነው።በዚህም በቀን ከ10 እስከ 50 ብር ተጨማሪ ክፍያ የሚያገኙበት ሁኔታ ውስጥ ገብተውም ነበር።ይህም ሰራተኛው ተረጋግቶ እንዲሰራ አድርጎትም ነበር፡፡
ካለፈው አመት አጋማሽ አንስቶ ነገሮች እየተስተካከሉ ባለበት ወቅት መጀመሪያ ሀዋሳ ከዚያም ኦሮሚያ እንደገና ሀዋሳ ላይ ችግሮች ተፈጠሩ።አሁን ደግሞ ኮቪድ መጣ።ብዙ ፈተናዎች ገጠሙን እንጂ ፓርኩ በዚህ ሰዓት በወር እስከ 15 ሚሊዮን ዶላር ያመርት ነበር።እናም የደመወዝ ጥያቄ ፓርካችን ውስጥ የለም።በደንብ የማይሰሩት በሚገባ ክፍያ ላይገኙ ይችላሉ።ደሞዛቸውን ብቻ ይዘው ይሄዳሉ።የደመወዝ ጉዳይ ጥያቄው አያልቅም።የእኔን ደመወዝ ብትጠይቀኝ ‹‹ይበቃኛል›› አልልህም።ግን የተሻለ ክፍያ እያገኙ ናቸው።
አዲስ ዘመን ፡- በሌሎች ፓርኮች የትራንስፓርትና የመኖሪያ ችግር አለብን የሚሉ ነበሩና በሀዋሳስ ምን ይመስላል?
አቶ በላይ፡- ይህ የሁሉም ፓርኮች ችግር ነው። ከመጀመሪያው አንስቶ የተጋረጠብን ችግር ነው። ለ35 ሺ ሰራተኛ መኖሪያ ቤት መንግስት ለማዘጋጀት ይከብደዋል።ገና መጀመሪያ አመት ላይ የተደረገው በፓርኩ አካባቢ ለሚገኙ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች ገንዘብ በማበደር የሚከራይ ቤት እንዲሰሩ ተደረገ።መንግስት ለእዚህ ስራ ወደ 40 ሚሊዮን ብር በቁጠባና ብድር ተቋማት በኩል አቅርቧል።ያለ ወለድ ብድሩ ተሰጥቶ ቤቶቹ እንዲገነቡ በማድረግ ሰራተኞቹ ፓርኩ ባስቀመጣው ዋጋ እንዲከራዩ ተደረገ።ብድሩን በ15 አመታት እንዲከፍሉ ተደርጎ ወደ 600 እና 700 ቤቶች ተሰሩ።በዚህ ፕሮጀክት ብዙ ባለቤቶች ነበሩ። መጨረሻ ላይ ባለቤት አጣና ብዙም ሳንሄድበት ቀረን።
እንደ ሁለተኛ ፕሮጀክት የያዝነው አለ።የከተማው አስተዳደር ፓርኩ አካባቢ ለባለሀብቶቹ ቦታ እንዲያቀ ርብና ማደሪያዎችን እንዲገነቡና ለሰራተኞቻቸው ቤቶቹን እንዲሰጡ መንግስት የግንባታ እቃዎችን ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገባ ተስማማን።ለእዚህም መሬት እየቀረበ እያለ ይህ ችግር የመጣው።ይህን እንገፋበታለን፡፡
ሶስተኛ ፕሮጀክታችን ደግሞ በአለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ በዝቅተኛ ዋጋ ቤት በመገንባት የሚታወቁ ኩባንያዎች ሪል ስቴት ገንቢዎች አሉ።መንግስት ለእነዚህ ባለሀብቶች ቦታ ሰጥቷቸው ገንብተው እንዲያከራዩ ወይም ለኩባንያዎቹ እንዲሰጡ ለማደረግ እየተሞከረ ነው።ኩባንያዎቹ ፓርኩ ድረስ መጥተው አይተዋል።በዚህ አይነት መልኩ ለ35 ሺ ሰራተኞች ቤቶችን ለማቅረብ እየሞከርን ነው።የቤት ጉዳይ ትልቁ ፈተናችን ነው።ለሰራተኛው መልቀቅም ምክንያት እየሆነ ነው፡፡
ትራንስፖርትንም በተመለከተ ትልቅ ፈተና ነው።35 ሺህ ሰራተኛ ማጓጓዝ ይጠበቅብሃል።ኩባንያዎቹ ከግል የአውቶብስ ማህበራት ጋር በመነጋገር እየተከራዩ ሰራተኞ ቻቸውን ያጓጉዛሉ። አብዛኞቹ ትራንስፖርት ያቀርባሉ። አንዱ ኩባንያ እስከ 20 እና 30 አውቶብሶችን በማቅረብ የሰርቪስ አገልግሎት ይሰጣል።ጥቂት ትራንስፖርት የማያቀርቡት ደግሞ የከተማ አውቶብስ ቁጥር እንዲጨምር በማድረግ አገልገሎቱን እየሰጡ ናቸው።በዚህም በተወሰነ ደረጃ ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ ነው።ትራንስፖርት እና መኖሪያ ቤት ትላልቆቹ ችግሮቻችን ናቸው።የሁሉም ፓርኮች ችግሮች ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን ፡-ፓርኩ ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ሲገባ ሊሆን ይችላል።ለ60 ሺ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል ፤ በአመት አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስገኝም ተጠቁሞ ነበር።እነዚህ ላይ መቼ ይደረሳል ይላሉ?
አቶ በላይ ፡- እሱ አይታወቅም።ባለፈው ኦሮሚያ ላይ መንገድ ተዘግቶ ኩባንያዎች መከራ ሲያዩ ነበር።ጥሬ እቃ ሊገባ አልቻለም።ይህን ስንወጣ ደግሞ ሀዋሳ ላይ ከህዝበ ውሳኔ ጋር በተያያዘ አንድ ሙሉ አመት ስንናጥ ቆየን።ያም መስከረም አካባቢ መልስ አገኘ።ከመስከረም ጀምሮ ደግሞ ያለውን ታውቀዋለህ።ኮረና በቻይና ጥቅምት ይሁን ህዳር ላይ ጀመረ።ይሄ የምንለው ነገር መቼ እንደሚሆን አናውቀውም፡፡ብዙ ጣልቃ የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡
የኮቪድ ጉዳይ በአለም ገበያ ላይ ያለው ተጽእኖ መቼ እንደሚያበቃም አይታወቅም፡፡እኔ የምለው በ2011 አንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር አካባቢ አቅደን የሰራነው 50 ሚሊዮኑን ነው።2012 ደግሞ 184 ዶላር አቅደናል አሁን ግማሽ ላይ ደርሰናል፡፡
ብዙ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች አሉ።አገሪቱ ውስጥ ኢንዱስትሪው እንደ ውጪው አይደለም። ኢንዱስትሪዎቹ ብዙ የለመዱ ናቸው።እናም እንደተ ፈለገው መሄድ አይቻልም። የአንድ ቢሊየኑ ጉዳይ ሊሳካ የሚችለው ሁሉ ነገር በተሟላበት ነው።አሁን ባለው አቅም በ2012 ነገሮች ቢስተካከሉ 200ሚሊየን ድረስ እንልካለን፡፡
ሰራተኞች 60 ሺ ገብተው፣ ፈረቃ ተጨምሮ የሎጂስቲክስ ጉዳዮች ምላሽ ቢያገኙ በአመት እስከ 300 እና 400 ሚሊየን ዶላር መላክ ይቻላል።የአንድ ቢሊየኑ ግን ፓርኩ ከመገንባቱ በፊት የታቀደ እንደመሆኑ ስለእሱ ብዙ የምናገረው የለም፡፡
አዲስ ዘመን፡-ፓርኩ ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ እንዳለው ተገልጾ ነበርና ምን ደረሰ?
አቶ በላይ ፡-አለው! መንግስት ሌሎች ፓርኮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንጂ ሁለተኛ ምዕራፍ አለው።ቦታው ተዘጋጅቷል፤ ባለሀብቶችም ተጋብዘው ውል ተፈራርመው ተቀምጠዋል።ነገሮች ከተረጋጉና ከተስተካከሉ ግንባታው ይቀጥላል፡፡
አዲስ ዘመን፡-ፓርኩ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ማዕከል እንደሚሆን ይጠበቃልና ከዚህ አንጻር ምን እየተከናወነ ይገኛል?
አቶ በላይ ፡- የኛ ልጆች እየተረከቡ ናቸው። የውጪ ዜጎች /ኤክስፖርተሮች/ እየወጡ ናቸው። ኤስክፖርቶች የግድ ካልሆነ በስተቀር ከሶስት አመት በላይ አይቆዩም።አሁን የኛ ልጆች የአስተዳደር ሥራውንም /ማኔጅመንቱንም/ እየተረከቡ ናቸው።በአብዛኛው አዳዲስ ምሩቃን ናቸው።የእውቀት ሽግግሩ በአግባቡ እየተፈጸመ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሀገራችን ኢንዱስትሪዎች ትልቁ ተግዳሮት የሀይል አቅርቦት ማነስ ነው።ፓርኩ ይህ ችግር ተግዳሮት ሆነበት ያውቅ ይሆን?
አቶ በላይ ፡-እሱ ላይ ምንም ችግር የለም፤ የኤሌክትሪክም የስልክም ችግር የለበትም።መብራት ለደቂቃ አይቋረጥም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የወቅታችን ችግር የሆነውን የኮሮና ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ፓርኩ ምን እየሰራ ነው?
አቶ በላይ፡-እኛ የመከላከሉን ስራ የጀመርነው ችግሩ ገና ቻይና ላይ እንደተከሰተ ነው፡፡ያኔ ጉዳዩ ከዜና ያለፈ አልነበረም። ከባድ ችግር ተደርጎም አይታወቅም ነበር።ሁለት የቻይና ኩባንያዎች ስላሉን የመከላከልና መቆጣጠር ስራውን የገባንበት አስቀድመን ነው ፡፡
ኮሮና የመከላከል ስራው በሶስት ደረጃ ይሰራል። በኩባንያ ፣ በፓርክ እና በከተማ ደረጃም ቁጥጥር ይደረጋል።አንድ ቫይረሱ ያለበት ሰው ፓርኩ ውስጥ ገባ ማለት ይህ ትልቅ ፓርክ ሊዘጋ ይችል ነበር።የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተዘጋ ማለት ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል።እንደ ሀገርም እናት ፓርክ እንደመሆኑ በሌሎች ፓርኮችም ላይ ተጽዕኖ ሊያሳርፍ እንዳይችል ምንም አይነተ ኬዝ እንዳይኖር በጥንቃቄ እየሰራን ነው፡፡
አንድ የውጪ ዜጋ ሾልኮ ከገባ ችግር ስለሚፈጥር ፓርክ ውስጥ የትኛውም ዜጋ 14 ቀናት ሳይቆይ እንዳይገባ አድርገናል። አየር መንገድ የሚያስገባው ትኩሳት እየለካ ነው። እኛ ጤነኛ ይሁኑ አይሁኑ አናውቅም።ስለዚህ ራሳቸውን ለ14 ቀናት ካላገለሉ ወደ ስራ እንዳይገቡ እናደርጋለን።ፓርክ ውስጥ መኖሪያ ቤት ያላቸው ቻይናዎች ራሳቸውን በራሳቸው መኖሪያ ቤት ቢያገሉ ችግር እንደሚፈጠር በማመን ራሳቸውን ማግለል ያለባቸው ከፓርኩ ውጪ እንዲሆን አድርገናል።ሁሉም ኩባንያዎች ከውጪ የሚመጡ ዜጎቻቸውን ለ14 ቀናት በዚህ አይነት መንገድ እንዲያገሉ ተደረገ።በዚህ አይነት መልኩ አንድም የውጪ ዜጋ ፓርኩ ውስጥ እንዳይገባ አደረግን፡፡
ሁለት መታወቂያዎችን አዘጋጅተናል።አንዱ የኩባን ያው መታወቂያ ነው።ውጪ አለመሄዳቸው ስራ ላይ መቆየታቸውን የውጪ ጉዞ ታሪክ የሌላቸው መሆኑን የሚያመለክት ሌላ መታወቂያ አዘጋጅተናል።በር ላይ ሁለቱንም ካላሳዩ አይገቡም።የኩባንያዎች ሰራተኞቹ 14 ቀን ካልገቡ ስራ ስለሚበደልባቸው አሾልከው ለማስገባት ይሞክራሉ።የያዝናቸውም አሉ፡፡ይህን ችግር በዚህ አይነት መንገድ ፈትተናል።
በየኩባንያዎቹ የሚደረጉ የጥንቃቄ እርምጃዎች በየቀኑ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል።በ52ቱም ሼዶች ላይ ይህ ይሰራል።ሁሉም ሰራተኛ ማስክ እንዲጠቀም፣ ተራርቆ እንዲገባና እንዲመገብ እያደረግን ነው።ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና ከጤና ሚኒስቴር የሚወጡ መመሪያዎችን እንዲተገበሩ እንሰራለን።ፈጣሪ ረድቶን 35 ሺ ሰራተኛ ባለበት ግቢ ውስጥ ምንም በቫይረሱ የተያዘ አልተገኘም፡፡
ፓርኩ ከመዘጋት ድኗል።በግንቦት ወር ወደ 5 ሚሊየን ዶላር ልከናል። በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ በወር ይላክ ከነበረው 10 ሚሊየን ዶላር ግማሹን መላክ ችለናል።ብዙም ሰራተኞች ከስራ ባለቀሩበት ሁኔታ ይህን ያህል መስራት ትልቅ ነገር ነው።በፓርኩ በኩል ያለው ነገር መሻሻል እያሳየ መጥቷል።የተሻለ ነገር ይመጣል ብለን እንጠብቃለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለትብብርዎ በአዲስ ዘመን ስም አመሰግናለሁ፡፡
አቶ በላይ ፡-እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2012
ኃይሉ ሣህለድንግል