የሕይወት ውጣ ውረድ እንደ ገብስ ቆሎ ፈትጋዋለች፤ በእርግጥ ዛሬም ብዙ የቤት ሥራዎች ከፊቱ እንደሚጠብቁት ያምናል። ከ100 ብር ወርሃዊ ደመወዝ ተነስቶ የራሱን የባህላዊ ውዝዋዜ ማሰልጠኛ እስከ መክፈት፤ በ16 ዓመት ዕድሜ በምሽት የባህል ቤቶች በተወዛዋዥነት እስከ ውጭ አገር ጉዞ ፍጋት አይቷል። እርሱ ለጥበብ፤ ጥበብም ለእርሱ ትርጉማቸው የጠለቀ ነው። ትናንትን በፈተና አልፏል፤ ዛሬም ካሰባቸው የተወሰኑትን አሳክቷል፤ ስለነገ ደግሞ ብዙ ያስባል የዛሬ ‹‹ሕይወት እንዲህ ናት›› ዓምድ እንግዳ -ኤፍሬም መኮንን (ኤፊ ማክ)።
የአዳማ ፍሬ
ኤፍሬም መኮንን (ኤፊ ማክ) ይባላል። ምድርን ከተቀላቀለ 27 ዓመት አስቆጥሬያለሁ ይላል። ውልደትና እድገቱ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ በመሸገችው አዳማ በቀድሞ አጠራሯ ናዝሬት ሲሆን ለቤተሰቤ የመጀመሪ ልጅ ነው። እናቴ ልጅነቷን ሳትጨርስ ገና በአሥራ ስድስት ዓመቷ ወለደችው። እርሱም ከእናቱና ከእናቱ ጓኞች ጋር ነው ያደገው። የመጀመሪያ ልጅ እንደመሆኑ መጠን በብዙ ፍቅር ተከብቦ ነው ያደገው፤ ትላንት ከቤተሰቡ ያገኘው ፍቅር ለዛሬ መሰረት እንደጣለለት ያምናል።
አስተዳደጉ አሁንም ድረስ በዓይነ ህሊና ትዝ እያለው መወደዱን ሊረሳው ልቻለም። ‹‹የሰፈራችን እናቶች ለሁሉም ልጅ እናት ናቸው በአካባቢው ያሉ አባቶችም እንደዛው የጎረቤት ልጅ እንደ ልጆቻቸው ይመክራሉ አልፎም ጥፋት ስናጠፋ ይገርፉናል። ደስ የሚል የልጅነት ጊዜ ነበረኝ።›› ሲል የትላንቱን ያስታውሳል።
የቤተሰቡ ብዛት ስድስት ነው። ከሁለት ወንድሞች እና አራት እህቶች ጋር ሲጫወት ያደገው ኤፍሬም መኮንን (ኤፊ ማክ) ከቤተሰቡ ወደ ጥበብ ዘርፍ ከእርሱ ውጪ የመጣ የለም። ለቤተሰብም አንድ የኪነጥበብ ባለሙያ ካለ ለዓይን ማሳረፊያና የጥበብ ጥም ቆራጭም ይሆናል፤ በቂም ነው ይላል። በመሆኑም ሌሎቹ ወንድምና እህቶቹ ደግሞ ያልተዳሰሱት የሕይወት መስመሮች ላይ የሚያተኩሩ ይመስለኛል ባይ ነው።
‹‹በየኔታ እግር ስር››
‹‹ትምህርት ከቄስ ትምህርት ቤት ነው የጀመርኩት አስተማሪያችን የእውነትም ቄስ ነበሩ በዚያ ላይ ጎበዝ የባህል ቀማሚ ናቸው። ድንገት ሆዳችንን ከታመምን ወደ ቤት አንላክም እዛው ቀምመው ፈዋሽ መድኃኒት ይሰጡናል ከዛማ ጤነኛ ነን። እንዲያውም ለብዙ ጊዜ አያመንም።›› ሲል ከየኔታ እግር ስር ሆኖ ሀ! ሁ! ሲል ያሳለፋትም ጊዜ ሲታመም የፈወሱትን ከእውቀት ማዕድ ያካፈሉትን ያስታውሰዋል። በዕድሜው ከፍ ሲል አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አዳማ ቦሰት ገባ። ሁለተኛ ደረጃ በተለምዶ አጠራር ‹‹ገደል ግቡ›› ሁለተኛ ደረጃ ትምርቱን አጠናቀቀ። በወቅቱ ‹‹ትምህርት መጨርሼ ወደ ውዝዋዜ የሚያስገባ ስለመሰለኝ ሙሉ ትኩረቴን ወደ ባህል ውዝዋዜ አድርጌ ቀረሁ።›› ሲል ከትምህርት ዓለም ጋር ትውውቁን ያላላበትን ወቅት ያስታውሳል። የሆነው ሆኖ ግን ከትምህርት ተራርቆ አይሆንምና በቀጣይ ዓመት አንድ ነገር እማራለሁ ብዬ እቅድ ላይ ነኝ ይላል- ኤፍሬም መኮንን።
ወደ ውዝዋዜ
‹‹ከአሥር ዓመት በፊት ነው ከትምህርት ቤት ተሰብስበን ቀበሌ ውስጥ ዝግጅት አለ ተብለን ለመመልከት ሄድን። እኔ ደግሞ ልጅ እያለሁ ዘፋኝ ወይ ደግሞ ተወዛዋዥ የመሆን ፍላጎት ነበረኝ። የቀበሌው መድረክ ላይ ያየኋቸው ልጆች እኔም እንደነሱ እንድሆን ስሜት ፈጠሩብኝና ተመዘገብኩ። የተመዘገብኩት ግን ዘፋኝነት ላይ ነው። ሆኖም ግን ተሰጥዖዬ ዘፈን አልነበረምና ብለው! ብለው! ከየት ይምጣ። ወደ ዳንስ ገባሁ ዳንስ ላይ ጎበዝ ሆንኩ። ወዲህ ደግሞ ሌላ ጣጣ መጣ። በዘመናዊው ዳንስ እንዳልገፋ ደግሞ አሰልጣኜ ተደባዳቢ ቢጤ ስለነበር፤ ቡጢውን አልቻልኩትም። የመጨረሻ ምርጫዬ የባህል ውዝዋዜ አደረኩና መማር ጀመርኩኝ›› ሲል የኋሊት በሃሳብ ፈረስ ጋልቦ የሆነውን ያስታውሳል። ‹‹እራሴን ነው ያስተማርኩት ከልምምድ ሰዓት ቀድሜ እገባና በቴሌቪዥን ላይ ያየሁትን እስክስታ አጠናለሁ። ቶሎ ለውጥ አመጣሁ በስተመጨረሻም እንዳሰብኩት ስኬታማ ሆንኩኝ።››
የ100 ብር ደመወዝተኛ
‹‹በመጀመሪያ አራት ሆንና በመቶ ብር የወር ደመወዝ ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩ። ከዛም ከፍ እያለ የተለያዩ ምሽት ቤቶች መስራት ቀጠልኩ። የወር ደመወዜ 800 ብር ሲገባልኝ በዚያን ወቅት ሀብታም የሆንኩ ያህል ተሰማኝ በደንብ ጠንክሬ መስራት ጀመርኩ። የኢትዮጵያን አይዶል በ2004 ዓ.ም ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ተወዳድረን ተሸላሚ ነበርን። እሱ ስላላረካን ኮካ ኮላ ሱፐር እስታር አይዶል ላይ 2005 ዓ.ም በባህል ውዝዋዜ ተወዳድረን አንደኛ በመውጣት የመቶ ሃያ ሺህ ብር ተሸላሚ በመሆን ሌላኛውን ምዕራፍ ጀመርኩ። የልጅነት ነገር ስለሆነ ብሩን ምን ላይ እንዳዋልኩት ብዙም አያስታውሰውም። የሆነው ሆኖ ግን ማሸነፋችን ግን ጠቅሞኛል። በመቀጠል ደግሞ ብሔራዊ ቴአትር የመስራት ዕድሉን አገኘሁ። በዛም ለአንድ ዓመት አገልግያለሁ። ብዙ ትምህርትም አግንቼበታለሁ።
በ16 ዓመቴ የምሽት ክለቦች ውስጥ መስራት ከባድ ነበር። በዚያን ሌሊት ሙሉ ሥራ አድሬ ጠዋት ትምህርት ቤት ነኝ። ሁኔታው በጣም ይከብድ ነበር። ነገር ግን እነ ደስታ ገብሬ ፣ እንዬ ታከለ ፣ አብዮት ካሳነሽ ፣ ልጅ ተመስገን መለሰን የመሳሰሉ ተወዛዋዦችን በቴሌቪዥን እመለከት ስለነበርና እንደነሱ ለመሆን ህልም ስለነበረኝ ተስፋ አያስቆርጠኝም ነበር ይላል። በአንድ ወቅት አርቲስት አብዮትን (ካሳነሽ) አገኘሁት ሥራዬን አይቶ አበረታታኝ። ያኔ እንደምችል ተሰማኝ ከዛ በኋላ በብዙ ክሊፖች ምናልባትም ከ100 ያላነሱ ዘፈን በውዝዋዜና በኬሮግራፈርነት ተሳትፊያለሁ። ኢትዮጵያን በሚባል ደረጃ በዚህ ሥራ ዞሬያለሁ። በዚህም የተነሳ ሀገሬን በሙሉ የማውቃት ይመስለኛል። ሀገሬን አብዝቼ እወዳታለሁ።››ሲል አጫውቶናል።
ዛሬ …
‹‹በትምህርት አቀባበል ላይ ጥሩ ነበርኩ። ውጤቶቼም ጥሩ የሚባሉ ነበሩ። በነገርህ ላይ መሸነፍ የማይወድ አይነት ነኝ። ግን ሽንፈቴ ተገቢ ከሆነ እቀበላለሁ። ከአቅም ችግር ከሆነ ያሳምነኛል።ለዛም በትምህርትም ስበለጥ የሚቆጨኝና ጠንክሬ እንድሰራ የሚረዳኝ ጭምር ነው። የውሳኔ ሰው ሆንኩኝ መሰለኝ ወስኜ ወደ ውዝዋዜው ገባሁ›› ሲል የመጣበትን ሂደት ያስታውሳል።
በአሁኑ ወቅት ከውዝዋዜ ውጪ ገጣሚ ነው። ቪዲዮ ግራፊ ተምሯል ፤ምንም እንኳን በጊዜ ማጣት ባይሰራበትም። ነገር ግን ከሙያው ጋር ተያያዥነት ስላለው እየተጠቀመበት ነው። በተለይም ‹‹ኬሮግራፊ ሳወጣ በምን ዓይነት የካሜራ አንግል መወሰድ እንዳለበት እንዳስብ ይረዳኛል። ሙሉ ቀኔን የሚወስድብኝ ውዝዋዜ ነው በቀን ውስጥ ለአምስት ሰዓት በሥራ ላይ ነኝ።›› ጠዋት ለሁለት ሰዓት ከሰዓት ደሞ ለሦስት ሰዓት- በውዝዋዜ ራሱን ይፈትናል ፤ ራሱን ያበቃል።
ኤፍሬም መኮንን (ኤፊ ማክ) በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ አየር ኃይል ኦርኬስትራ ባንድ ውስጥ የባህል ውዝዋዜ ኃላፊና ተወዛዋዥ ሆኖ እየሰራ ነው። ‹‹ኢትዮጵ የባህል ውዝዋዜ ማሰልጠኛ›› የሚል ትምህርት ቤት በግሉ ከፍቷል። በዚህ ማሰልጠኛ ብዙ ተወዛዋዦችን በማፍራት ላይ ነው። በግል ደሞ በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችና የግጥም ምሽት መድረኮች ላይ አዲስ ፈጠራ የሆነው የግጥም በውዝዋዜ ልዩ በሆነ አቀራረብ ከገጣሚና ተዋናይ ተስፋሁን ከበደ (ፍራሽ አዳሽ) ጋር እየሰራ ነው። ‹‹ይህ አቀራረብ ለየት ያለና የመጀመሪያውም ሲሆን ባህል እና ስነፅሁፍን በማዋሀድ የሚቀርብ ነው። በዚህም ጥሩ ተቀባይነትን አግኝተንበታል። ግጥም በውዝዋዜ በተለያዩ ከተሞች ተዘዋውረን ሰርተናል። አንድ አዲስ ነገር ፈጥረናል የሚል ሀሳብ አለኝ›› ይላል።ኤፍሬም መኮንን በሥራው ወጪ ሀገራትን የመጎብኘት ዕድል ቢኖረውም የሀገር ውስጥ ሥራዎች ግን የበለጠ ይማርኩታል።‹‹ በውዝዋዜ ሥራ አንድ ጊዜ ወደ ዱባይ ሄጄ በምሽት ክለብ ውስጥ ሠርቻለሁ። ከዛ በኋላ ግን እዚህ ጥሩ ተቀባይነቱን እያገኘው ስመጣ ወደ ውጭ የመሄዱን ጉዳይ ገታ አድርጌ የበሰሉ ሥራዎችን የመስራት እቅድ ያዝኩኝ። አሁን ላይም ጥሩ ተሳክቶልኛል፤ ቀጣይ ደሞ የማስባቸው አዳዲስ አቀራረቦች ይኖሩኛል። ለዛም ጊዜ ሰጥቼ እየሰራሁ ነው›› ይላል ኤፍሬም።
ባህል ማለት የአንድ ማህበረሰብ ማንነት ጭምር ነው። በባህል ውዝዋዜ ውስጥ አመጋገብ አለባበስ አኗኗር የሥራ ሂደታቸውን እንዲሁም አካባቢያቸውን ጭምር የያዘ ምስጢራዊና ጥበባዊ እንቅስቃሴ ነው። ለአብነት አንድ የምንጃርን ውዝዋዜ ብንመለከት ከብቶቹን ከማባበል ይጀምራል፣ ያርሳል፣ ይዘራል፣ ይታጨዳል፣ ይወቃል፣ ይሰበስባል፣ ሴቶቹ ሲያበጥሩ ይታያል። ይሄ የአካባቢውን አኗኗር ይገልፃል የሌላውም እንደዛው። ለዚህ ሙያና ሙያተኛው የሚሰጠው ግምት ግን ዝቅተኛ መሆኑ ኤፍሬምን ያስቆጨዋል።
ትኩረት ለጥበበኞች
‹‹ሙያው ትኩረት ባለማግኘቱ በመንግሥት ደረጃ ትምህርት ቤት የለም፣ እውቅና የሚሰጥ አካል የለም። ሆኖም ግን የህዝቡ ነውና ህዝቡ ታዋቂ ያደርግሃል። ይህ ግን ጥበቡ እንዳያድግ ማነቆ ሆኖበታል። ሁሉም ተነስቶ ኬሮግራፈር፤ ሁሉም ተወዛዋዥ ነኝ የሚልበት ሙያ ነው። ደረጃ የሚሰጥ አካል የለም። እጅግ ለሙያው የተሰጡ ወጣቶች እና አንጋፋ ባለሙያዎች አሉ፤ እንደዛውም ደግሞ ቦታው የማይገባቸው ባለሙያዎች የተጠራቀሙበት ነው።
መመዘኛ ኖሮት ደረጃ ቢሰጠው ሁሉም ለማደግ ይለፋል። በደረሰበት ደረጃ ልክ አሻራውን ያሳርፋል። ይህ ሙያ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሊሰጥ የሚገባና ሰው ተምሮ በእውቀት የሚሰራበትና የልፋቱን ውጤት ሊከፈለው የሚገባበት ዘርፍ ነው። አማራጭ ሲጠፋ የምትገባበት ዓይነት ሙያ መሆን የለበትም። ኪነጥበብ ለሀገር እድገት ያለው ሚና ከፍተኛ ስለሆነ ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል። ››ሲል ሙያው በትምህርት መታገዝ እንደሚገባው ያሳስባል።
ደራሲው
ኤፍሬም መኮንን (ኤፊ ማክ) የጥበብ ጥሪው በተወዛዋዥነት ብቻ ልትገታው አልፈለገችም። ብዕር ጨብጦ ደማቅ ቀለም ያሳርፋል። ሁለት የግጥም መጽሐፎች አሉት። ለባለቅኔው ቅኔ አጣሁለት በ2008 ዓ. ም የታተመ ሲሆን ሁለተኛው የወፍ ጎጆ ምህላ የተሰኘው መጽሐፉን በ2011 ዓ.ም ለህትመት አብቅቷል። ከሌሎች ሰዎች ጋር ‹‹ሰሚ ያጡ ብዕሮች›› እና ‹‹የግጥም ከተራ›› የተሰኙ መጽሐፍትን አሳትሟል።
‹‹የመጀመሪያ መጽሐፌ 80 ግጥሞችን የያዘና በ83 ገፅ የተከተበ ሲሆን ዋጋውም በ35 ብር ተሸጧል። ሁለተኛው የወፍ ጎጆ ምህላ የግጥም መጽሐፌ 61 ግጥሞችን የያዘና በ94 ገፆች የተቀመጠ ሲሆን ዋጋውም አርባ ዘጠኝ ብር ከሰባ ተሸጧል። ሁለቱም መጽሐፍ ተሸጠው አልቀዋል። የመጀመሪያው መጽሐፌ በዲዛይነር ማፊታ (ምዕራፍ ፍሰሀ) ሰርፕራይዝ የተደረኩት ሲሆን ሁለተኛው ግን በራሴው ገንዘብ የታተመና ብዙ ባለሙያዎች ከጎኔ ሆነው ለንባብ የበቃ መጽሐፍ ነው። በቀጣይነት ፈጣሪ ፈቃዱ ከሆነ የወግ መጽሐፍ ይኖረኛል›› የሚል እምነት አለው።
ኮረና እና ጥበብ
‹‹በውዝዋዜው ብዙ የማስባቸው ወደ ተግባርም ለመቀየር ትግል ላይ ያሉ ሥራዎች አሉኝ። ከተለመደው አቀራረብ ወጣ ባለ መልኩ አዲስ መንገድ ይዤ እመጣለሁ። ልክ እንደ ግጥም በውዝዋዜው። በግጥም በውዝዋዜውም ከነበረው እረቀቅ ባለ መልኩ አዲስ ሥራዎችን ለህዝቡ ለማቅረብ እየሰራን ነው። በግጥሙ ዘርፍ ከዚህ በኋላ ብዙ የበሰሉና ለንባብ የበቁ መጽሐፎችን ለአንባቢያን አደርሳለሁ የሚል እቅድ አለው።
በዚህ ከባድ ወቅት ኮሮና ከቤት ስለማያስወጣን በማንበብና አዳዲስ የሥራ ሀሳቦችን በማፍለቅ እያሳለፍን ስለሆነ ይህ ጊዜ ሲያልፍ በአዲስ ሃሳብና በአዲስ ጉልበት ጥሩ ነገር ይዤ ብቅ የምል ይመስለኛል።
ኮሮና በሁሉም የሥራ ዘርፍ ተፅዕኖ ፈጥሯል። እንደማንኛውም በእኛ ሙያ ላይም ይህ ተፈጥሯል። የኛ ሥራ ህዝብ የሚሰበስብና ለታዳሚያን የሚቀርብ በመሆኑ የአዋጁ ሰለባ ሆኗል። ሁሉም ሙያተኛ እቤቱ ነው ያለው። ፈጣሪ ይህን ጊዜ ያሳልፍልን የዓለም ህዝብ ሁሉ ችግር ነው። ያለን አማራጭ ፀሎት ማድረግ ነው። በጎ ጎኑ ደሞ ጥሩ የጥሞና ጊዜ ሰጥቶናል።
ታዲያ ችግሩን መሸሽ ብቻ ሳይሆንም በተቻለኝ አቅም ባለኝ ሙያ ማህበረሰቡን ለማስተማር ጥረት አድርጊያለሁ። በቅርቡም ከተወዛዋዥ ጓደኛዬ አበባው ኃይለ ሚካኤል ጋር ተው! ተው! የተሰኘ የፉከራ ዓይነት ይዘት ያለው ስለኮሮና ማስተማሪያ ቪዲዮ ሰርተን ለቀናል። በቀጣይም በብዙ የደግነት ሥራዎች ላይ እሳተፋለሁ። ይህን ጊዜ ያለንን በማካፈል እንጂ በመከፋፈል መሻገር አንችልም። በመተዛዘብ ሳይሆን በመተሳሰብ በጋራ እናልፈዋለን። በእኛ መዘናጋት የብዙ ሕይወትን መዝጋት እንዳይፈጠር እራሳችንን እንጠብቅ።›› የሚለው የጥበበኛው መልዕክት ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር