በተለያየ ዘርፎች ማህበራዊ ኃላፊነቶችን ለመወጣት መትጋት በጎነትና ልበ ቀናነት የሚፈጥረው የአዕምሮ እሳቤ ውጤት ነው:: ከሀሳብም ዘልሎ በተግባር የሚገለጽ በጎነት ደግሞ በወጣትነት ሲሆን ያስደስታል:: ምክንያቱም ወጣትነት ለመልካም ሲውል አካባቢን ቀርቶ አገርን ብሎም ዓለምን የመለወጥ አቅም አለውና ነው:: ይህ ደግሞ ከወጣትም በላይ በሴት ወጣቶች ትምህርት ተፈጥሮለት ሲተገበር ውጤቱን የሚያጎላው መሆኑ እሙን ነው:: ይህን ያነሳነው ያለምክንያት አይደለም፤ ይልቁንም ዓለም አቀፍ ገጽታ ያለው የወጣት ሴቶች ክርስቲያናዊ ማህበር በኢትዮጵያ በአገራችን እያከናወነ ያለው ተግባር በተለይም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከልና በመቋቋም ሂደት እያበረከተ ያለው መልካም ሥራ መነሻ ሆኖን እንጂ::
ይህ ማህበር በዓለም አቀፍ ደረጃ በ1962 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን፤ የወጣቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ዓላማው አድርጎ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል:: በኢትዮጵያም መሠረቱን ካደረገ 20 ዓመታት አስቆጥሯል:: ወጣቶችን ማዕከሉ በማድረግ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን መፍታት ላይ አተኩሮ ሲሰራ ቆይቷል:: በቅርቡ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በማድረግም ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል:: በዚህም ከግንዛቤ ማስጨበጥ እስከ ምግብና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉንም ቀጥሏል:: እኛም ከሰሞኑ ለ150 ቤተሰቦች ያደረገውን የምግብ ነክና ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍን መመልከት የቻልን ሲሆን፤ ይሄንኑም ለእናንተው ልናደርስ ወደድን::
ወይዘሮ ንጋቷ ካብቲመር፣ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ቀበሌ 11 ነዋሪ ናቸው:: የሚደግፋቸው ዘመድም ሆነ ልጅ ስለሌላቸው በደከመ አቅማቸው ልብስ በማጠብ ነበር ራሳቸውን የሚያኖሩት:: ሆኖም የዕድሜ መግፋት ከጤና ችግር ጋር ተዳምሮ ለመሥራት ፈተና ሆኖባቸው እያለ፤ በግማሽ ጎናቸው የመደንዘዝ ስሜት ስለተሰማቸው አንድ እጃቸው መሥራትን እንቢ አለ:: ይህ አልበቃ ብሎ በመውደቃቸው ምክንያት በደረሰባቸው ተደጋጋሚ ጉዳት የልብስ አጠባ ሥራቸውን እርግፍ አድርገው ተውት:: መቼም ያለ ደጋፊ ዘመድና ያለ ጧሪ ልጅ በብቸኝነት ያውም በሕመምና ዕድሜ መግፋት ምክንያት ባዶ ቤት ውስጥ መኖር የሚኖረውን ፈተና ያየ ያውራው ነውና ላላየ ቢያወሩትም ቢሰሙትም ከጆሮ አልፎ ጠብ ባይልም፤ በሕመም ጎናቸው ያለሥራ ቤት ውስጥ መዋል ሥነ ልቡናቸውንም፣ አካልና ጤናቸውንም እጅጉን እንደጎዳው ነው የነገሩን::
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉም፣ በዚህ ችግር ውስጥ ሆነው ያውም የሰው እጅ እየጠበቁ ኑሮን መግፋቱ አልበቃ ብሎ፤ አሁን ላይ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የከፋ ችግር ይዞ የመከራ ጥላውን አጠላባቸው:: ሆኖም ላይጠግን አይሰብር ነውና፣ ቀድሞም የአካባቢው ነዋሪ ሲጎበኛቸው እንደነበር ሁሉ፤ አሁንም ወረርሽኙን ተከትሎ የተጀመረው የማዕድ ማጋራት ተግባር ጾም እንዳያድሩ አድርጓቸዋል:: ከግለሰብ እስከ ተቋም በሚደረግ ድጋፍ ውስጥ እርሳቸውም ተሳታፊ እንዲሆኑና እንዲደገፉ የተደረገ ሲሆን፤ እኛም አግኝተን ያነጋገርናቸው ከሰሞኑ ወጣት ሴቶች ክርስቲያናዊ ማህበር ባዘጋቸው የምግብ ነክ ድጋፍ መርሃ ግብር ላይ ነበር:: እርሳቸውም በወቅቱ እንደነገሩን ድጋፉ ለእርሳቸው ብቻ ሳይሆን በተለይ በዚህ ችግር ወቅት በርካታ ጠያቂ ላጡ ወገኖች እፎይታን የሰጠ እንደመሆኑ መንግሥትም ሆነ ድጋፉን ላደረጉ አካላት ምስጋን ይገባቸዋል:: ሆኖም በርካታ በመሰል ችግር ውስጥ ያሉ እንደመሆኑ ሌሎች ወገኖችም ተመሳሳይ ድጋፋቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል::
በዚህ መርሃ ግብር ላይ ልጇን አዝላ ያገኘናት ሌላዋ ተረጂ ወይዘሮ ብርሃኔ ቱንካ የዚሁ ወረዳ ነዋሪ ናት:: ይህች ወጣት ወይዘሮ እንደምትናገረው፤ ቀደም ሲል ራሷንና ልጇን ለማኖር በየሰው ቤት ልብስ ታጥብ ነበር:: የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ ግን ይሄን ሥራ ማከናወን ባለመቻሏ ሥራዋን ትተዋለች:: ሆኖም ሆድ ሳይበላ ማደር አይችልምና ለእርሷም ሆነ ለልጇ ጉርስ የጎረቤትና አካባቢን እጅ ለማየት ተገደደች:: በዚህም ጎረቤትና አካባቢው እንጀራ ሲጋግሩ ከሚረዷት ባለፈ ሌላ የገቢ ምንጭ አጣች:: እናም ዛሬ ላይ በጎረቤቶቿ ድጋፍ ጾም ባታድርም፤ የተከራየቻትን አነስተኛ ማዕድ ቤት ኪራይ መክፈል ባለመቻሏ ኪራይ ሳትከፍል ሁለት ወራትን አስቆጥራለች:: በዚህ መሰል ችግር ውስጥ ሆና ወራት ቢቆጠሩም በርካታ ሰዎች ድጋፍ ሲደረግላቸው ከመስማት ባለፈ ተሳታፊ ሆና አታውቅም ነበር::
ሆኖም ቀኑ ደርሶ ወጣት ሴቶች ክርስቲያናዊ ማህበር ያዘጋጀው የምግብ ነክ ድጋፍ ተሳታፊ መሆን ችላለች:: ይህ ድጋፍ ደግሞ ልጅ ይዛ አንድ ዳቦ መግዣ አጥታ ስትቸገር ለከረመችው ለእርሷም ሆነ እንደርሷ ላሉ ወገኖች ሁሉ አስደሳችና ተስፋ ሰጪ ሲሆን፤ ድጋፉም በየቤቱ ተቸግረው ላሉና ከቤትም መውጣት ላልቻሉ ብዙ ወገኖችን ደጋፊና አስታዋሽ እንዳላቸው ያመላከተ ሆኗል:: ሆኖም አሁንም ድረስ በርካታ ተቸግረው ያሉና ተመልካች ያጡ መሰል ወገኖች በመኖራቸው ሰዎች ጎረቤታቸውን በማየት ከቻሉ በራሳቸው ሊረዱ ካልቻሉ ግን ሊደግፍ ለሚችል አካል አሳውቆ እንዲደገፉ በማድረግ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል:: ወጣት አሸናፊ ፀጋዬ፣ ሌላው በድጋፍ መርሃ ግብሩ ላይ ድጋፍ ሲደረግለት ያገኘነው በክፍለ ከተማው የወረዳ ሁለት ነዋሪ ነው::
ወጣት አሸናፊ፣ ቀደም ሲል እንደ ጓደኞቹ ወጥቶ ሠርቶ የሚገባ ብርቱ ወጣት ነበር:: ሆኖም አንድ የቀን ጎዶሎ ለሥራ የሚታትርበትን አፍላ ወጣትነቱን በመኪና አደጋ ነጠቀው:: እናም እግሩንና ሌሎች የሰውነት ክፍሎቹን ስለተጎዳ ሠርቶ መኖር እየናፈቀ ከቤት ውስጥ መዋል የግድ ሆነበት:: ለሰው የሚተርፍ የነበረው ወጣት ለራሱ መሆን አቅቶት ላለፉት ሁለት ዓመታት በብቸኝነት ኑሮ ውስጥ ሆኖ የሰው እጅ ለመመልከት በቃ::
አሁን ላይ የተደረገለት ድጋፍ እጅጉን ያስደሰተው ሲሆን፤ እንዲህ አይነት ድጋፍ የተደረገለት የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ነበር:: ከሁለት ዓመት በኋላ ያውም በወረርሽኙ ምክንያት ችግሩ በፀናበት ወቅት እንዲህ መደገፉ በቀጣይ ተስፋን ያጫረለትም ሆኗል:: ሆኖም እንደርሱ ሁሉ ብዙዎች በየቤታቸው በችግር ውስጥ ሆነው አስታዋሽ ይሻሉ:: ይህ መሰል ተግባር ደግሞ ለተረጂዎቹ ደስታና ተስፋን፤ ለረጂዎቹም እርካታና ጽድቅን የሚያሰጥ ሰናይ ምግባር ነው:: በመሆኑም በየአካባቢው በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን በተለይም ከቤት ውጭ በየጎዳናው ያሉ በርካታ ወገኖችን በዚህ መልኩ የማሰብ ተግባሩ በሁሉም መልኩ ሊጠናከር ይገባዋል::
የወጣት ሴቶች ክርስቲያናዊ ማህበር በኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ደሀብ ሙስጠፋ በበኩሏ እንደምትናገው፤ ማህበሩ ቀደምት ከሚባሉ የሲቪል ማህበራት መካከል አንዱ እንደመሆኑ ላለፉት 20 ዓመታት ወጣቶችን በተለይም ወጣት ሴቶችን በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እንዲሁም ከሥርዓተ ጾታ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን መርሃ ግብሮች ቀርጾ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ሲያደርግ ቆይቷል:: አሁንም ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ በተለያየ መልኩ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ሲሆን፤ ይህ ደግሞ ቫይረሱ እንደ ዓለምም እንደ አገርም በመጣው የማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ምክንያት በችግር ውስጥ የወደቁ ወገኖችን በመደገፍ ሂደት አንድም በመንግሥት የቀረበውን ጥሪ በመቀበል ሁለተኛም አገራዊ ድርሻን ለመወጣት እየተከናወነ ያለ አስተዋጽዖ ነው::
ይህ ተግባር ማህበረሰብ ውስጥ እንደሚሠራ አንድ ድርጅት የሚጠበቅ የበጎ ፈቃደኞች እንቅስቃሴ ሲሆን፤ ችግሩን በመከላከል ሂደትም የማህበሩን በጎ ፈቃደኞችን በመጠቀም የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል:: ከዚህ ባለፈም የቤት ለቤት ግንዛቤ ማስጨበጫዎችንና የቁሳቁስ ድጋፎችንም ማድረግ የቻለ ሲሆን፤ በተለይም ማህበሩ ከፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት ምቹና አካታች ከተሞች በሚል ፕሮጀክት ነድፈው እየሠሩ ይገኛል::
በዚህ ፕሮጀክት እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉት የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት፣ ወረዳ አራት እና ወረዳ አምስት ውስጥ ያሉ በጎ ፈቃደኞችን በማንቀሳቀስም ነው የቤት ለቤት የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እና የንጽህና ቁሳቁሶችን ድጋፍ እያደረገ የሚገኘው:: ይህ ተግባር በአዲስ አበባ ብቻ የተገደበ ሳይሆን ከአዲስ አበባ ውጭ በመሄድም በአዳማ ከተማ መሰል እንቅስቃሴዎችን ሲያደረግ የቆየ ማህበር ነው::
አሁንም ለ150 ቤተሰብ ዱቄትና ዘይትን ጨምሮ የተለያዩ የምግብ ነክ እንዲሁም እንደ ሳሙና ያሉ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፤ ማህበሩ ከዚህ ቀደምም በመንግሥት የቀረበውን ጥሪ በመቀበል ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ2ሺህ በላይ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያዎችን አበርክቷል:: በዕለቱ የምግብ ነክ ድጋፍ መርሃ ግብርም በአብዛኛው ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረገ ነው:: ምክንያቱም ወረርሽኙ ምንም እንኳን መላውን ህብረተሰብ የሚያጠቃ ቢሆንም ሴቶች ግን እጅጉን ተጠቂዎች ናቸው::
እነዚህን የሚደገፉ ወገኖች በተለይም ሴቶች ተጠቃሚ በማድረግ ሂደት ከባለድርሻዎች ጋር እየሠራ ይገኛል:: በተለይ ደግሞ ምቹና አካታች ከተሞች በሚለው መርሃ ግብር ይህ ትብብር ጎልቶ የሚታይ ሲሆን፤ የሚደገፉ ወገኖችን በመምረጥና ለይቶ በማቅረብ ሂደቱም የተለያዩ መስፈርቶችን በማውጣት ድጋፉ ሊደርሰው ይገባል ተብሎ ለሚታመንበት ተገቢው ሰው እንዲደርስ ነው እየተደረገ ያለው:: በመሆኑም ማህበሩ ድጋፍ የሚያደርገው ከሚቀርቡ ቤተሰቦች ውስጥ የበለጠ ድጋፉ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ባዘጋጀው መስፈርት መሠረት የመረጣቸውን ሲሆን፤ አሁን ላይ ችግሩ በእጅጉ የበረታባቸው በዚህ መልኩ ይረዱ እንጂ አሁንም ሊረዱ የሚገባቸውና በርካቶች በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖች መኖራቸውን ይገነዘባል::
ማህበሩም በቀጣይ አቅሙ በፈቀደ ልክ እነዚህንና ሌሎችም በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን ለማገዝ የሚችልውን ሁሉ የሚያደርግ ሲሆን፤ በዚህም እስከዛሬ ሲያከናውኗቸው ከነበረው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ጀምሮ የንጽህና መጠበቂያዎችን፣ የምግብ ነክና ሌሎች ቁሳቁሶችን ድጋፍ የሚያደርግ ይሆናል:: ይሄን ድጋፉን ግን ብቻውን ሆኖ የሚወጣው ሳይሆን እንደከዚህ ቀደሙ ከደጋፊ አካላት ጋር በመተባበር ነው:: በመሆኑም እንደ ፕላን ኢንተርናሽናል ሁሉ ሌሎችም ዜጎችን መደገፍ የሚፈልጉ አካላትና ወገኖች በአጠቃላይ ባለድርሻ አካላት ከማህበሩ ጋር ሆነው ማገዝ ቢችሉ፤ ህዝቦችም እንደ ዜጋ ሃላፊነታቸውን ቢወጡ የተሻለ መሥራትና ወገኖችን ከሚደርስባቸው የከፋ ችግር መታደግ ይቻላል::
የአራዳ ክፍለ ከተማ ሴቶችና ህፃናት ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ወይዘሮ ዓይናለም ፍቅረ እንደሚሉት ደግሞ፤ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት አንዱ ዓላማም መንግሥት ሊደርስ ባልቻለባቸው ቦታዎች በመድረስ የመንግሥትን ደካማ ጎኖች ማገዝ እንደመሆኑ፤ ከወሴክማ ጋር በመሆንም በቤተሰቦች በተለይም በእናቶች ላይ በርካታ ሥራ እየተሠራ ነው:: በዚህም ከጽህፈት ቤቱ ጋር በመሆን መንግሥት ሊደርስባቸው ያልቻላቸው ቤተሰቦችን የማገዝ ሥራን እያከናወነ ይገኛል:: ዛሬ ላይ ለ150 ቤተሰቦች የምግብ ነክ ድጋፍ ማድረግ መቻሉም የዚህ ሥራው አንድ ማሳያ ነው::
ይሁን እንጂ ማህበሩ ከኮሮና በፊትም ሆነ በኋላ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየና እያከናወነም ያለ ነው:: ከእነዚህ ተግባራቱ መካከልም፤ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ እንዲሁም ሳኒታይዘር ድጋፍ ማድረግ የቻሉበትን መጥቀስ ይቻላል:: በዚህ እርምጃም እንደ ክፍለ ከተማ በርካታ ሴቶችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል:: በዕለቱ የተደገፉ 150 ቤተሰቦችም ብቻቸውን ሳይሆን በሥራቸው በርካታ ሰዎችን ይዘው ያሉ እንደመሆኑ ድጋፍ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው::
እንደ ጽህፈት ቤት የተያዘው አቅጣጫም በዚህ ወረርሽኝ በብዛት ተጎጂና ተጋላጭ የሚሆኑት ሴቶችና ህፃናት ናቸው የሚል እሳቤ ተይዞ እየተሠራ ሲሆን፤ በዚህም ከግንዛቤ ማስጨበጥ የማስተማር ሥራ ጀምሮ ግብዓትና ሌሎች ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ ቤት በሚቀመጡበት ጊዜ የሚጎድላቸውን ብዙ ነገር ለማሟላት ጥረት እየተደረገ ነው:: ለዚህ ሥራ ደግሞ በየቀበሌ ያሉ ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች በጥንቃቄ እንዲለዩ የተደረገ ሲሆን፤ ባለው ሁኔታም 26ሺህ በጣም ችግረኛ ሴቶች መኖራቸው ተለይቷል::
ከዚህ አንፃር እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ ነው ማለት ስለማይቻል፤ እነዚህን ወገኖች ከችግራቸው ለመታደግ የሚያስችሉ ሰፋፊ ሥራዎችን ማከናወን ይጠይቃል:: በተለይ ከቤት ውጭ በሸራ እና በተለያዩ መጠለያዎች ያሉ ዜጎች ችግሩ ስለሚከፋባቸው እነዚህን ታሳቢ ያደረገ ሥራ አስቦ መሥራት የግድ ይላል:: ይሄን ያማከለ ሥራም ከክፍለ ከተማው ጀምሮ በወረዳዎች ጭምር ድጋፍ እየተደረገ ቢሆንም፤ ሥራው በአንድ ወገን ብቻ ከዳር የሚደርስ ባለመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ የሚጠበቅበትን ሁሉ ማበርከት ይኖርበታል::
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2012
ወንድወሰን ሽመልስ