አቶ ግርማ ቲመርጋ ይባላሉ፤ የሚደግፋቸው ወገን ዘመድ የሌላቸው ከመሆኑም በላይ በህመም ምክንያት ራሳቸውን ደጉመው መኖር እንዳይችሉ አደረጋቸው። ደጋፊ ማጣት ከህመም ጋር ተዳምሮም ኑሮን በጎዳና እንዲያደርጉ አስገደዳቸው። ዛሬ ላይ ኑሮአቸውን በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ካደረጉ በርካታ ወገኖች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ግርማ፤ የጎዳና ህይወት እንኳን ከህመም ጋር እየታገሉ ይቅርና፤ ጤናን ከአቅም ጋር አዳምረው ለያዙ እንኳን የማይቋቋሙት ፈተና ሆኖባቸዋል። እናም ይህ የጎዳና ኑሮ እጅጉን ከብዷቸው ሕይወት ፈትኗቸው ክፉኛ አጎሳቆላቸው።
በዚህም ለብሶ ሳይሆን ጎርሶ ማደር አቃታቸው። እናም ችግር ሲበረታባቸው “ከመሞት መሰንበት” እንዲሉ ቀምሰው የሚያድሩት ነገር ሲፈልጉ አንድ ቦታ ላይ የጎዳና ሰዎችን አንስቶ የሚያጥብ፣ የሚያለብስና የሚመግብ ማህበር መኖሩን ይሰማሉ። ይሄን የሰሙት አቶ ግርማም ጊዜ ሳያባክኑ ወደስፍራው ያመራሉ። ድካማቸውም ከንቱ አልቀረምና በሄዱ እለት ገላቸውን ታጥበው፤ የተጎሳቆለ ምንነታቸውን አጉልቶ የሚያሳየውን ልብሳቸውንም ቀይረው፤ ለእለቱም ምግብ በልተው ወደ ማደሪያቸው ይመለሳሉ።
ከዛን ጊዜ ጀምሮ በዚህ ቦታ እየመጡ ሲቆሽሹ እየታጠቡ፣ ሲታረዙ እየለበሱ እና ሲርባቸውም እየጎረሱ ህይወትን እየገፉ ይገኛሉ። በዚህ መልኩ ከመታጠብና ከመልበስ ባለፈ አሁን ላይ አስቸጋሪና ጎዳና ላይ ላለ ሰው ቀርቶ በቤት ውስጥ ለሚኖረውም ቢሆን ከባድ በሆነበት በዚህ ወቅት በየቀኑ ምገባ እየተካሄደ መሆኑ ያለ ችግር የሚመገቡትን እንዲያገኙ እንዳደረጋቸው በመግለጽም፤ ይሄን የሚያደርጉ ወገኖችን በማመስገን መሰል ችግር ላይ ያሉ በርካታ ወገኖች በመኖራቸው ይሄን መሰል ተግባር በየቦታው ሊተገበርና ሁሉም አለሁ ተብለው ወገን እንዳላቸው እንዲያስቡ ሊደረግ እንደሚገባ ይጠይቃሉ።
ለአቶ ግርማና ሌሎች እርሳቸውን መሰል በርካታ ወገኖች ይሄን አይነት ተግባር የሚያከናውነው የጎዳናው ሻወር የበጎ አድራጎት ማህበር የተባለ የወጣቶች ስብስብ ሲሆን፤ ቀደም ሲል በየ15 ቀኑ፣ አሁን ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝን ተከትሎ በየቀኑ በመርካቶ አንዋር መስጂድ አካባቢ በአስፓልት መንገድ ላይ የተለመደ ተግባሩን ሲያከናውን መመልከት አዲስ አይደለም። ማህበሩ አሁን ላይ ከ250 በላይ መሰል ወገኖችን ከማጠብና ማልበስ ጀምሮ የመመገብና በየቤቱም እየዞሩ የመጎብኘት ተግባር እያከናወነ ይገኛል። ይሄንንም የማህበሩ አባላትና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እንዲህ ይገልጹታል።
ወጣት ኤርሚያስ ዝና፣ ከቡራዩ ከታ አካባቢ እየተመላለሰ የሚያገለግል በጎ ፈቃደኛ ነው። ያለውን ሂደትም እንዲህ ሲል ያስረዳል። የጎዳናው ሻወር የበጎ አድራጎት ማህበር ረዥም ጊዜ የቆየ ቢሆንም እኛ የምናውቀው ግን ሶስት ዓመት ያህል ነው። ላለፉት ሶስት ዓመታትም አብረን እየሰራን ነው ያለነው። በየ15 ቀኑ እየመጣን ገላ በማጠብ፣ ፀጉራቸውን በማሽን የመላጨት እና በምላጭ የሚላጨውንም በምላጭ የመላጨት፤ በማልበስ እንዲሁም በማብላት ከጎዳናው ሻወር ጋር አብረን እየሰራን ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ቀን በቀን ከ250 ያላነሱ ሰዎች ቁርሳቸውን፣ ምሳቸውንና እራታቸውን እየተመገቡ ነው ያሉት። ለዚህም እኛ ከከታ እየመጣን ነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን እየሰጠን ነው ያለነው።
በእስካሁን ጉዟችን ጥቂት ቢሆኑም የተለያዩ አካላት ድጋፍ አድርገውልናል። ለምሳሌ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝን ተከትሎ በየቀኑ ምገባ በምናካሂድበት ወቅት ደርባን ሲሚንቶ ለ250 ሰዎች ቁስር፣ ምሳና እራት መርሃ ግብር ለአንድ ወር አዘጋጅቶ እርሱን እያበላን እንገኛለን። ሌሎች ግለሰቦችም አልፎ አልፎ ያግዙናል። በተለይ በምገባ መርሃ ግብሩ ከ150 ሰው በላይ በካርድ የምናስተናግዳቸው ናቸው። እነዚህ በየ15 ቀኑ እየመጡ ይታጠባሉ፣ በተባይ የተበላ ልብሳቸውን ይቀይራሉ፣ ምግብም ይመገባሉ። ከዚህ ባለፈ ቤት ለቤት ሽሮ፣ በርበሬ፣ ዘይት፣ ከሰልና ሳሙና የመሳሰሉ ቁሳቁሶችን በመያዝ መረዳት የሚገባቸውን አቅመ ደካሞችና ጠያቂ የሌላቸውን ወገኖች እንጎበኛለን። እነዚህንም በየቀኑ በቋሚነት የምንጎበኛቸው ሲሆን፤ እንደ አቅማችን ከዘይት በርበሬና ተያያዥ ነገሮች ባለፈ ለአስቤዛ ወይም ለእንጀራ የሚሆን መጠነኛ ሳንቲም እንሰጣቸዋለን።
በመሆኑም ሁሉም አካላት አይቶ ማለፍ ብቻ ሳይሆን፤ ስራው እንዴት ነው እየተሰራ ያለው? በምን አይነት ቦታ ላይ ነው እየተሰራ ያለው? ምንስ ያስፈልጋል? የሚሉ ጉዳዮችን ከከተማ አስተዳደሩ እስከ ወረዳ ጽህፈት ቤት ድረስ ያሉ አካላት መጥቶ የጠየቀ ሰው የለም። ሆኖም ስራውን አላዩትም ማለት ስለማይቻል፤ ያሉን ሰዎች ብዛት ያላቸው ከመሆናቸው አንጻር ቢያንስ የቦታ ችግር የሚፈታበትን እድል ቢፈጥሩልን መልካም ነው። በዚህ መልኩ ቦታ ቢያመቻችልን፤ እናንተ ቦታ አግኙ እንጂ እኛ ግንባታ እንገነባላችኋለን ብለው ቃል የገቡልን ሰዎች አሉ። በመሆኑም መንግስት ይሄን ተገንዝቦ ለጊዜያዊም ሆነ ቋሚ ቦታ ቢያመቻችልን ብዬ መልዕክት አስተላልፋለሁ።
ምክንያቱም ሁል ጊዜም የምንለውና የምናስበው ይህ ስራ በዚህ በጎዳና ላይ ብቻ ተወስኖ እንዲቀርና እንዲቆም አይደለም። በየአካባቢው ላይ ያሉ ወጣቶች በየሰፈራቸው ያሉ ወጣቶች ቢያንስ በዚህ መልኩ ልብስ በማሰባሰብ ጎዳና ላይ የወደቁ ወገኖችን አንስተው አጥበው ቢያለብሱ የሚሰማቸው ደስታ በምንም የማይገመት ነው። ይልቁንም በፈጣሪም ቢሆን ለድሃ የሰጠ ለአምላኩ እንዳበደረ እንደሚቆጠር ነው በየሃይማኖቱም የሚነገረው። ስለዚህ በየአካባቢው ያሉ ወጣቶች ርቆ ከመሄድ ይልቅ ይሄን መሰል ስራ ከጎረቤትና አካባቢ በመጀመር የድርሻቸውን ሊወጡና ሊያበረክቱ ይገባል።
እኔ በግሌ ይሄን ስራ በመስራቴ የሚሰማኝን ደስታ ለመግለጽ ይከብደኛል። እዚህ ሰርቼ ውዬ ቤቴ ገብቼ ሳርፍ ውስጤ በጣም ደስተኛ ስለሚሆን ደስ የሚል እንቅልፍ እተኛለሁ። ይሄን መልካም ተግባር ያየሁት በዚህ አካባቢ ድንገት ሳልፍ ነው። ከዛ በኋላ በዚህ ስፍራ ለመስራት ወስኜ ነው ከጓደኞቼ ጋር ወደዚህ የመጣነውና አገልግሎት መስጠት የጀመርነው። ይህን ስራ ለመስራት የምንመጣው በርካታ ጓደኛሞች ስንሆን፤ ቀደም ሲልም ከቡራዩ እስከ መገናኛ ድረስ የሚሰራ እኛ ለእኛ የሚል የበጎ ፈቃደኞች ወጣቶች ማህበር ውስጥ የተሰባሰብን ከ45 በላይ የሆንን ጓደኛሞች ወጣቶች ነን። ሁላችንም ይሄን በማድረጋችን ተመሳሳይ የደስታ ስሜት ነው የሚሰማን።
ሌላዋ የማህበሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣት ቅድስት ቸርነት በበኩሏ ከአስኮ አካባቢ በመመላለስ ነው አገልግሎቱን የምትሰጠው። እርሷም ስለሁኔታው ስታስረዳ እንዲህ ብላለች። ይሄን መሰል በጎ ተግባር የማከናወን ህልሙና ምኞቱ ቀድሞውንም ነበረኝ። ስለዚህ ማህበር የሰማሁትና ወደዚህ የመጣሁት በሰው ነው። እዚህ በመምጣቴም ሆነ እዚህ መጥቼ መልካም ይሄን መሰል አገልግሎት ሰጥቼ ውዬ ስገባ የሚሰማኝ ስሜት ከፍተኛ ነው። ምክንያቱም ስራውን የምሰራው ማንም አስገድዶኝ ሳይሆን በራሴው ፍላጎት እንደመሆኑ የማከናውናቸው ተግባራት ሁሉ ደስታ እየሰጡኝ የማከናውናቸው በመሆናቸው ነው። በዚህ ቦታ አጠባ፣ ማልበስና ምግብ ማብላት አለ። ሁሉም ነገር ደግሞ በጣም ደስ የሚል ተግባር ነው።
በዚህ መልኩ በጎዳና ላይ ከሚያከናውኗቸው ባለፈ ደጋፊ የሌላቸውን ሰዎች ቤት ለቤት እየሄዱ ይጎበኛሉ። እነዚህ ሰዎች ደግሞ አንድም በእርጅና፣ ካልሆነም በህመምና አቅም በማጣት ምክንያት በቤት የዋሉ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህን ሰዎች ደግሞ በአዘቦት ብቻም ሳይሆን በበዓልም እንጠይቃቸዋለን። እናም የሚጎድላቸው ብዙ ቢሆንም መሟላት ያለባቸው ቁሳቁሶችና አስቤዛ ካላቸው እንገዛላቸዋለን፤ የቤት ኪራይ መክፈል ላቃታቸውም ቢያንስ ግማሽ ክፍያም ቢሆን በመክፈል እናግዛቸዋለን። ይህን የምናደርገው ደግሞ የተለየ ገቢ ወይም ድጋፍ ስላለን ሳይሆን በሚሰበሰብ ገንዘብ ነው። አልፎ አልፎም አሁን ላይ ደርባን እንዳደረገልን አይነት ድጋፍ ስንደገፍ ሲሆን፤ እኛም በቋሚነትም ሆነ በደራሽነት የምንደግፋቸው በርካታ ወገኖች ናቸው። እኛም በቋሚነት አውቀው የሚመጡትንም ሆነ አዲስ የሚመጡትን ባለን ልክ እንደ አመጣጣቸው እናስተናግዳለን። አሁን ላይ ደግሞ በየቀኑ ምግብ የሚመገቡ እንደመሆኑ በርካታ ወገኖች መጥተው ይገላገላሉ።
ሆኖም ይሄን መሰል ተግባር ለማከናወን የተለየ ነገር አያስፈልግም። ሰው የሚረዳው ደግሞ ባለው ነው። ይሁን እንጂ እንደ ሰው ሲታሰብ ብዙ ጊዜ እንዲህ አይነት ሰዎችን ቀርቦ ከመርዳት ይልቅ መራቅን ነው የምንመርጠው። ሆኖም ከእኛ ይልቅ እነርሱ ጋ ጤነኝነት አለ። ከእኛ ይልቅ ንጹህና ቀና አስተሳሰብ እነርሱ ጋ አለ። ይሄን መረዳት የሚቻለው ደግሞ ቀርቦ በማየት ነው። በመሆኑም የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል እነዚህን ወገኖች በመራቅ ሳይሆን ቀርቦ በመደገፍ ነው መረዳት ያለበት።
እነዚህን ወገኖች ችግራቸውን ደግሞ ልንገነዘብም ሆነ ከችግራቸው እንዲወጡ ልናግዛቸው የምንችለው ስንቀርባቸው ብቻ ነው። ህዝብ መንግስትም እንደ መንግስት እነዚህን ሰዎች ቀርበው ሊረዷቸውና ሊያግዟቸው ይገባል። በመንግስት በኩልም እንዲህ አይነት ተግባራትን ለመደገፍ ከሌሎች በተሻለ አቅም አለው። እናም መንግስት በብዙ ነገር ሊያግዝና ቢያንስ የማህበሩን መሰረታዊ ችግር ተረድቶ ሊደግፍ ያስፈልጋል።
በማህበሩ ውስጥ ህጻናትን መንከባከብና የተለያየ ቦታ እንዳይውሉ ማስተማር ላይ የሚሰራው የማህበሩ አባል ወጣት ያሬድ ፋንታሁን እንደሚለው ደግሞ፤ ከዛሬ 16 ዓመት በፊት አስመሮም ተፈራ በሚባል ግለሰብ አንድ ብሎ ስራውን የጀመረው ይህ ማህበር ከሶስት ዓመት በፊት ነው በማህበርነት ተደራጅቶ መንቀሳቀስ የጀመረው። አሁን ላይ ማህበሩ ወደ አምስትና ስድስት ስራዎችን ያከናውናል። የመጀመሪያ ስራው ከየቦታው የአዕምሮ ህመምተኞችን ከየቦታው እየሰበሰበ በማምጣት ጸጉራቸውን በመላጨት፣ ጥፍራቸውን በመቁረጥና አጥቦ ልብስ የማልበስ፣ እንዲሁም ቅባት ቀብቶ የመመገብ ተግባር ነው። ይሄን በየ15 ቀኑ ነበር የሚያከናውነው። ሆኖም 15 ቀን ጠብቆ ብቻ ሳይሆን በየቀኑም ይሄንኑ ተግባር ያከናውን ነበር። ምክንያቱም የማህበሩ አባላት በማንኛውም ቀን ልብሱ የቆሸሸና በተባይ የተበላ፣ ጸጉሩ ያደገ፣ የተጎሳቆለና ሲመለከቱት የአእምሮ ህመምተኛ መስሎ የሚታይን ሰው በመያዝ ተመሳሳይ ተግባር ያከናውናሉ።
ሌላኛው ተግባሩ ህጻናትን ሰብስቦ ማስተማር ሲሆን፤ በዚህም በችግር ምክንያት መማር እየፈለጉ መማር ያልቻሉ ህጻናት የትምህርት ቁሳቁስ እንዲሟላላቸው በማድረግ ነው እንዲማሩ የሚደረገው። ይህን ለማከናወን የተነሳሳነው ደግሞ እዚህ ቦታ የሚደገፉ እናቶች ይዘዋቸው የሚመጡ ህጻናትን ትምህርት ስለመማር አለመማራቸው ስንጠይቅ የማይማሩ መሆናቸውን በመረዳት ሲሆን፤ እንደውም አንዳንዶቹ ህጻናት ለእናቶቻቸውና ታናናሾቻቸው ምግብ ፈልጎ የማምጣት ሃላፊነት ያለባቸው ሁሉ ነበሩ። በመሆኑም ከመመገብ ባለፈ እነዚህን ህጻናት እንዲማሩ ማድረግ ቢቻል የዜግነት ግዴታን እንደመወጣት መሆኑን በመገንዘብ ነው ልጆቹን የትምህርት ቁሳቁስ እንዲሟላላቸውና እንዲማሩ ማድረግ የጀመርነው።
አሁን ላይ በኮሮና ምክንያት ትምህርት የተቋረጠ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም እነዚህ ልጆች ወደተለያየ ቦታ እንዳይሄዱና የተለያየ ቦታ እንዳይውሉ በሚል ማህበሩ ስፍራ አዘጋጅቶላቸው እያስተማራቸው ይገኛል። ለዚህም የማነቃቂያ ትምህርትን ጨምሮ መደበኛ የቀለም ትምህርቱን እንዲማሩ የሚደረግ ሲሆን፤ ይሄንንም ወቅቱን ባማከለ መልኩ በመከፋፈል ቁጥራቸውን በማሳነስ በአዳራሽ ውስጥ በማከናወን ላይ ይገኛሉ። ከትምህርት ባለፈም ለተማሪዎቹ በየቀኑ ቁርስ፣ ምሳ እና እራት እየመገብን ሲሆን፤ ማደሪያም ተመቻችቶላቸዋል።
በሶስተኛነት የሚያከናውነው የቤት ለቤት እገዛ ሲሆን፤ በዚህም ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አቅመ ደካሞች እና የአእምሮ ህመምተኞች በመኖራቸው እነርሱን እንከባከባለን። ምክንያቱም ለምኖ የሚበላ ለምኖ ሊበላ ይችላል። ነገር ግን ለምኖ መብላት የማይችል በየቤቱ አለ። የወገኖቹን እርዳታ የሚፈልግ ነገር ግን የሚያየው በማጣቱ ውሃ ጠጥቶ ተመስገን ብሎ የሚተኛ በርካታ ዜጋ አለ። በመሆኑም እነዚህን በየቤቱ እየገባን ሽሮና በርበሬ፣ ሽንኩርት፣ ከሰል፣ ጨውና የመሳሰሉትን ከእንጀራ ብር ጋር ይዘን እንጎበኛለን።
ከዚህ በተጨማሪ በየጎዳናው የወደቁ ብዙ ሰዎች አሉ። እነዚህ ወደቤተሰቦቻቸው መመለስ ቢፈልጉ እንኳን የሚመለሱበት አቅም የሌላቸው፤ የተለያየ ሙያ ባለቤት የሆኑ ነገር ግን በሙያቸው መስራት ቢፈልጉም የሚሰሩበት እድል ያጡ፤ አንዳንዶቹም በስራቸው ትልልቅ ቦታ ላይ የነበሩ አሁን ግን በጎዳና ላይ የወደቁ ናቸው። በመሆኑም እነርሱን ስራ እንዲያገኙ የስራ እድል እናመቻችላቸዋልን፤ ከዚህ ባለፈም ከእኛ ጋር አብረው እንዲሰሩ እናደርጋለን፤ ወደቤተሰቦቻቸው እንዲሄዱ ለሚፈልጉም ሙሉ ወጪያቸውን ችለን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ እናደርጋለን።
በዚህ ስራ ውስጥ አልፎ አልፎ አንዳንድ በውጪም ሆነ በአገር ውስጥ ካሉ በጎ ኢትዮጵያውያን ከሚያደርጉልን እገዛ በስተቀር ይሄ ነው ብለን የምንጠቅሰው ግለሰብ ወይም ተቋም የለም። ለምሳሌ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝን ተከትሎ ደርባን ሲሚንቶ ኃ/የተ/የግ/ኩባንያ ከአንድ ወር በላይ የሚሆን ቁርስ፣ ምሳና እራት በየቀኑ ለ250 ሰው እያበላልን ይገኛል። ከዛ ውጪ ለአንድ ቀን ምግብ ወይም ልብስ ወይም ሁለቱንም ችለው የሚመግቡልንና የሚያለብሱልን በጎ ሰዎች ከውጭም ከአገር ውስጥም አሉ። ከዛ ውጪ ገቢያችን በየአስፓልቱ ላይ ሳጥን (ባንኮኒ) ይዘን በመለመን በምናገኘው ገቢ ነው ማህበሩን የምናንቀሳቅሰው።
ይህ ገቢ ደግሞ በጎዳና ላይ ለምንሰጠው አገልግሎትም፤ እቤት ለቤት ጥየቃም፣ ለህጻናት የትምህርት ቁሳቁስም፣ ለአልባሳትም እንዲሁም ከጎዳና አንስተን በማህበሩ ውስጥ እንዲያግዙን በመጠነኛ ክፍያ ስራ ለፈጠርንላቸው ክፍያም የሚውል ነው። ለምሳሌ፣ በየሳምንቱ የምናለብሰውን ልባሽ ጨርቅ እየገዛን ነው፤ ሌሎች የሚያስፈልጉ የምግብ አስቤዛዎችን እና የእንጀራ ወጪም በዚሁ በሳጥን ከሚሰበሰብ የሚሸፈን ወጪ ነው። በተመሳሳይ ማህበሩ ግማሽ በበጎ ፈቃደኞች፣ ግማሽ ደግሞ እኛጋ ሲረዱ የነበሩ ነገር ግን አሁን ተሽሏቸው የስራ እድል በተፈጠረላቸው ወገኖች የሚከናወን ነው። በመሆኑም ለምገባ፣ ለማልበስ ብሎም ለጥየቃ የምንጠቀመው ከዚሁ ነው።
እኛ ህልማችን በቃል ተናግሮ መቅረት አይደለም። ያሰብንበት ለመድረስ ግን ብዙ ፈተናና ችግር ስላለብን እነዚህ ችግሮቻችን በተለያዩ አካላት ድጋፍ እንዲፈቱልን እንሻለን። ምክንያቱም ስንተባበርና ስንተጋገዝ ሁሉንም ማለፍ እንችላለንና ነው። ለዚህ ደግሞ ያጣነው ነገር የለም። የመተሳሰብ ችግር፣ ለእኔ ለእኔ የሚል መስገብገብ ካልሆነ በስተቀርም አብረን መቋደስና መተጋገዝ ከቻልን ኢትዮጵያ ሁሉ ያላትና ለሁላችንም የሚበቃ ነገር ያላት ናት። በመሆኑም መስራት እየፈለጉ ያልቻሉ፤ ሁኔታዎች በጎዳና ያዋሏቸው፣ ቤት ውስጥም ያለጠያቂ ያስቀሯቸው በርካታ ወገኖችን በመተጋገዝ መደገፍ ይገባል።
ስራውን ከጎሮቤት ጠዋት ማታ ሰላምታ ከሚለዋወጡት መጀመር ይገባል። ይህን ደግሞ ከቀደሙት አባቶቻችን መማር ይገባል። ምክንያቱም ቀድሞ ጎረቤት በሩን ዘግቶ ካመሸ እንትና ምን ሆኖ/ሆና በሩን/ሯን ዘጋ/ች ይሉ ነበር። አሁን ግን ይህ ታሪክ እየሆነ ነው። ጎረቤት የቸገረው እያለ አልፎ ሩቅ ለመርዳት ይሄዳል። ሊሆን የሚገባው ግን ይህ ሳይሆን፤ መጀመሪያ ጎረቤት ያለን ችግረኛ መደገፍ፤ አቅም ከፈቀደ ደግሞ በአካባቢ ያሉትን መጎብኘት ነው። ይህ ሲሆን ሁሉም አካባቢው ያለውን ችግረኛ ስለሚያውቅ መረዳዳቱ ይሰፋል፤ ሌሎችን ለመደገፍ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግም ለተቸገሩ ወገኖች መድረስ ያስችላል።
እኛም ትልቅ ተስፋ ይዘን እየሰራን ቢሆንም፤ በግለሰብ ብሎም በተቋም ደረጃ ከተጠቀሱት ውጪ ያን ያክል ድጋፍ የለንም። ከመንግስት በኩልም ያገዘን አካል የለም። ሆኖም ይህ የኮሮና ጊዜ አልፎ ማህበሩም የተሻለ መስራት የሚችልበት፤ በግለሰብና በተቋማት ተደግፎ እንዲሁም መንግስት ተመልክቶት የተሻለ የስራ ቦታ ኖሮት የበርካቶችን ችግር ለመካፈል እድል ያገኛል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2012
ወንድወሰን ሽመልስ