ኢትዮጵያ ቱባ ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች ባለቤት ናት ሲባል፤ እነዚህ የባህል እሴቶቿ ትናንት ላይ ብቻ ተንጠልጥለው ያሉ ሳይሆን ዛሬም ድረስ ዘልቀው የህዝቦች የአብሮነትና መተሳሰብ መሰረት ሆነው መኖራቸውን የሚያሳይ ነው።በዚህ መልኩ የኢትዮጵያውያን የአኗኗር ማህበረሰባዊ ትስስር ከሚገለጹባቸው መንገዶች እንደ እድርና ዕቁብ ያሉ ባህላዊ እሴቶችን መጥቀስ ይቻላል።ለምሳሌ እቁብን ብናይ ኢትዮጵያውያን ያኔ እንዳሁኑ ዘመን ሰልጥኖ ከቴክኖሎጂም ተዋውቆ ገንዘቡን ማኖሪያ ብቻ ሳይሆን ሲቸግረው ተበድሮ መስሪያ የሚያቀብሉ ባንኮች ባልተቋቋሙበት ዘመን ህዝቦች ለችግሮቻቸው መሻገሪያ አድርገው የመሰረቱት ነው።እናም እቁብ በዛን ዘመን አንድ ጉዳይ ሲገጥማቸው ብቻ ሳይሆን አንድ ተግባር ማከናወን ሲያስቡ ያንን ስራ ለማከናወን የሚያስችላቸውን ጠርቀም ያለ ገንዘብ ለማግኘት የሚችሉበትና መደጋገፋቸውን የሚገልጹበት የአርቆ አሳቢነታቸው መገለጫም የሆነ የፋይናንስ ስርዓት ነው፡፡
እቁብ ደግሞ በባህሪው የስራ ባልደረቦች፣ የአንድ አከባቢ ነዋሪዎች፣ ጓደኛሞች ወይም አብሮ አደጎች፣ ወዘተ በጋራ በመሰባሰብና በተወሰነ የጊዜ ልዩነት ውስጥ በጋራ ያዋጡትን ገንዘብ በየተራ ለባለእድል እየሰጡ የሚከወን ነው።ይህ ደግሞ ሰዎች ለችግራቸው የሚያውሉት ገንዘብ አሁን ላይ ባላቸው ብቻ ሳይሆን ወደፊት ሊኖራቸው በሚችልበት ሁኔታ ላይ ተመስርቶ የነገ ህልማቸውን እንዲያሳኩ የሚያስችል አሰራር ነው።ምክንያቱም ዛሬ ላይ ትንሽ ገንዘብ ያለው ሰው ነገር ግን ትልቅ ህልም ኖሮት ያንን ማድረግ የማይችልበት አቅም ቢፈጠር እቁብ ለዚህ ፍቱን መድሃኒቱ ነው።ምክንያቱም የእርሱ ገንዘብ ከሌሎች እቁብተኞች ገንዘብ ጋር ተደምሮ ወደ ህልሙ እንዲጓዝ ያደርገዋልና፡፡
በዚህ መልኩ ከሚንቀሳቀሱ የእቁብ ማህበራት መካከል ደግሞ በዘበኛ ሰፈር ዘወትር እሁድ ከ4-6 ሰዓት የሚሰበሰበው ሳምንታዊ እቁብ ማህበር አንዱ ነው።ይህ የእቁብ ማህበር እንደ ባህላዊ የገንዘብ ቁጠባ ተቋምነቱ በርካቶች የእቁብ አባላቱን ኢኮኖሚ እንዲቀየርና ኑሮም እንዲደጎም ያደረገ ሲሆን፤ ሌሎች በችግር ላይ የወደቁ የህብረተብ ክፍሎችን ሲደግፍ መቆየቱን የማህበሩ አባላትና አመራሮች ይናገራሉ።ከዚህ ባለፈም በዚህ ወቅት በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝን ምክንያት የቀረበውን አገራዊ ጥሪ ተከትሎም የዘመናዊ ፋይናንስ ተቋማት የሆኑት ባንኮች እንዳደረጉት ሁሉ ይሄው ባህላዊ የገንዘብ ቁጠባ ተቋም እቁብ አባላትም ካላቸው ላይ በመቀነስ 50 ሺህ ብር ሰሞኑን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አበርክተዋል፡፡
አቶ ኃይለማርያም መላክ፣ ባለትዳርና በጤና ጣቢያ ውስጥ ጠቅላላ አገልግሎት ዘርፍ ላይ የሚሰራ ሲሆን፤ በዘበኛ ሰፈር መብራቱጋ የሚከፈለው ሳምንታዊ እቁብ ፀሐፊ ነው።እርሱ እንደሚለው፤ እቁቡ ለሰባት ዓመታት ያክል የዘለቀ ሲሆን፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ በርካቶች ተጠቃሚም ሆነውበታል።በሚፈለገው መልኩ የውጪውን ተመልክተን የደገፍን ባይሆንም፤ በውስጥ ያሉ በርካታ የእቁብ አባላት በተለያየ መልኩ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።በዚህም ሰው ሲታመም፣ አደጋ ሲደርስበትና በተለያየ መልኩ መረዳት ሲያስፈልገው በእቁቡ ስር ላሉት ድጋፍ ስናደርግ ቆይተናል።ምክንያቱም ሰው ሲጎዳና ሲቸገር ብሎም መስራት እየቻለ ሲያቅተው ድጋፍ እናደርግለታለን።ድጋፉም ሰርቶ መለወጥና በራስ አቅም ራስን መቻል እንደሚቻል ማስተማር ስለሆነም በልግስና መልክ የሚከናወን ሳይሆን ባገኙት ገንዘብ ሰርተው እንዲከፍሉ የሚደረግበት ነው፡፡
ይህ ግን በወለድ መልኩ የሚሰጥ አይደለም።ወለድ አልባ ብድር አይነት ሲሆን፤ ሰው በነጻነት ሰርቶ የወሰደውን በመመለስ በሚያስችለው መልኩ ነው።እንደሚታወቀው እቁብ ባህላዊ ተቋም ነው።ይህ ደግሞ ሰዎች በተለያየ ምክንያት ያላቸውን ማህበራዊ ጉዳይ ለመከወን የሚያግዛቸው ነው።ይሄን መሰረት በማድረግም ነው አባላቱን ሲደጉም ያሳለፈው።አሁን በዚህ መልኩ ወደ ውጪ ተመልክቶ የአቅምን መደገፍ መጀምሩም የገንዘቡን መብዛት ወይም ማነስ መሰረት ያደረገ ሳይሆን፤ ተግባሩ ለሌሎች መነሳሳትን ይፈጥራል፤ እንደ እቁብ ማህበርተኛም ትንሽም ቢሆን ድጋፍ ለማድረግ ያስችላል በሚል ነው።ለዚህ ደግሞ የአባላቱ ቁጥር እንደየወቅቱ የሚለያይ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ወደ 240 የሚሆኑ አባላት መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ ኃይለማርያም፤ ይህ ባህላዊ ተቋም የቁጠባ ባህልን የሚያሳድግ እንደመሆኑም ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ሰዎች እንዳያቋርጡ ለማድረግ ጊዜውን ባማከለ መልኩ ሰው ተሳትፎውን እንዲቀጥል ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውንም ነው አቶ ኃይለማርያም የገለጹት።
እንደ አቶ ኃይለማርያም ማብራሪያ፤ በዚህ እቁብ ውስጥ በርካቶች ኑሯቸውን ለውጠዋል።በርካቶች መኪና ገዝተው ወደ ትራንስፖርቱ ዘርፍ ገብተዋል።የቤት ቦታ የገዙ እንዲሁም ቤት ሰርተው የቤት ባለቤት የሆኑም አሉ።ይህ ደግሞ እንደየሰዉ ችግር እና ገንዘቡን የመፈለግ ደረጃ ቅድሚያ እንዲያገኝ በማድረግ የሚከወን ሲሆን፤ የወሰዱትን ገንዘብም የሚያባክኑት ሳይሆን በብሩ እየሰሩ እዳቸውን መክፈል በሚችሉበት አግባብ ላይ እንዲያውሉት ስለሚደረግ ነው።ይህ ደግሞ የወሰደውን ለእዳ ክፍያ የሚያውለው ሳይሆን በገዛው ነገር እየሰራ እዳውን በመክፈል በመጨረሻ የገዛው ንብረት የራሱ ሆኖ የሚቀርለት በመሆኑ ያ ሰው በኑሮው ተለወጠ ማለት ነው።በዚህ መልኩ እየተቀየሩ ያሉትም ብዙ ናቸው፡፡
ለሰዎች መድረስ ማለት በትልቅ ስጦታ ማንበሽበሽ ወይም ትልቅ ነገር ይዞ መቅረብ አይደለም።ከትንሽ ጀምሮ የራስን አስተዋጽዖ በማድረግ ለሌሎች ምሳሌ መሆንንም የሚጠይቅ ነው።በመሆኑም ከትንሽ አንስቶ ሁሉም ባለው አቅሙ ለወገኖቹ ሊደርስ ያስፈልጋል።እኛም እንደፈጣሪ ፈቃድ ባለን አቅም ሁሉ ከእነዚሁ ወገኖች ጎን ነን።ሆኖም ወረርሽኙ ከእለት እለት እየከፋ ቁጥሩም እየጨመረ እየሄደ ነው ያለው።ይህ እጅግ ያሳዝናል።እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ቀድሞ የምንባለውን ነገር እንሰማ ነበር።አሁን ላይ ግን እየሰማን አይደለም።በጤና ባለሙያዎች የሚነገረንን እና ከመንግስትም የሚባለውን ተግባራዊ ብናደርግ፤ በሽታውን እንቆጣጠረዋልን፤ ችግሩንም አሸንፈን እናልፈዋለን።በዚህ ላይ በሁሉም የኃይማኖት ተቋማት እያለቀሱ የሚለምኑ እንደመሆኑ የአባቶች ጸሎት አለ።ባለው ሁኔታ ግን ከዓለማቀፍ ሁኔታው አንጻር በኢትዮጵያ ያለው የተሻለ እንደመሆኑ የተባልነውን ተግባራዊ እያደረግን፤ በጸሎትም እየተጋን፤ በቫይረሱ ምክንያት ለተቸገሩ ወገኖችም እየደረስን ወረርሽኙን ማሸነፍ እንችላለን፤ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ከድሮም ጀምሮ ያደግነው በእቁብ ነው፤ ላለሁበት ደረጃ የበቃሁትም በእቁብ ነው፤ የሚለው ደግሞ በመካኒክነት ስራ ላይ የተሰማራውና የዘበኛ ሰፈር ነዋሪ የሆነው የእቁቡ አባል አቶ ብርሃኑ ባህሩ ነው። አቶ ብርሃኑ ስለ እቁቡና ተግባሩ በራሱ አንደበት እንዲህ ሲል ያስረዳል።“እኔም ራሴን ከቻልኩ ጀምሮ አንድ ትልቅ ሰው ስለነበሩ እሳቸው ጋር እቁብ በመጣል ነው የጀመርኩት።በዚህ መልኩ እድገት ሲመጣ ደግሞ ለምን ራሳችንን ችለን እቁብ በመጣል ሌሎች እንዲያድጉ ማድረግ አንችልም በሚል ሀሳብ ተሰባስበን እቁብን ጀመርን።ይሄንንም መጀመሪያ ስንጀምር በ60 ሺህ ብር ነው የመሰረትነው።በሁለተኛው ዙር ሰው እየጨመረ ሲሄድ ወደ 120 ሺህ ብር አሳደግነው።በዚህ መልኩ እያደገ መሄዱ ሰውን ለመርዳት ካለው ጉጉት አንጻር እየተበራከተ መጥቶ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል”፡፡
አሁን ባለው አገራዊ ሁኔታ ከኮቪድ 19 ወረርሺኝ ጋር ተያይዞ እንደ አገር ባለው የስራ መቀዛቀዝ ውስጥ የእቁብ አባላቱም የስራ መቀዛቀዝ ውስጥ ገብተዋል።ይህ ደግሞ እቁባችን ላይም የተወሰነ ተጽዕኖ ፈጥሮብናል።ይህ ደግሞ በውስጥ ካለው ችግር በመነሳት የውጪውን እንድንመለከት ምክንያት ሆኖናል።በእድር አባላቱ ስም የተለገሰውን 50 ሺህ ብር ለከተማ አስተዳደሩ ስናስረክብም ባለን አቅም ለተቸገሩ ወገኖች መድረስ መቻላችንን በማሰብ ደስተኛ ሆነን ነው።ተግባሩም የአገራዊ ጥሪን መሰረት ያደረገ ከመሆኑም በላይ ነግ በእኔ ስለሆነ ቀጣይነት ይኖረዋል፡፡
አሁን አገራዊ ጥሪውን ተቀብለን ለተቸገሩ እንድንደርስ ያደረገን ቀደም ሲልም በእቁብ አባላቱ መካከል ያለው የመረዳዳትና የመደጋገፍ ልምዳችን ነው።ለምሳሌ፣ አንድ የእቁብ አባል ተቸግሮ ከሆነና ችግሩንም ካማከረን እቁቡ በሚችለው አቅም ያንን ሰው ለመርዳት ወደኋላ አይልም።በቀጣይ በዚህ መልኩ ብቻ ሳይሆን በየአከባቢው ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ።እኛ በምንኖርበት ቀጨኔ አካባቢ ደግሞ ምንም ገቢ የሌላቸው እና ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አረጋውያን ጭምር አሉ።በመሆኑም በቀጣይ እነዚህን ወገኖች የተለያዩ ቁሳቁሶችን ገዝቶ በመስጠት የመደገፍ ሀሳብም፤ እቅድም አለን።ይህ ደግሞ የኮሮና ቫይረስ እስካለ ብቻ ሳይሆን ወረርሽኙ ካለፈና ከሄደ በኋላም ካለባቸው ችግር አኳያ ድጋፉ ቀጣይነት እንዲኖረው ነው የምንሰራው፡፡
ሆኖም ይሄን ችግር በአሸናፊነት ከመሻገር አንጻር እንደ ህዝብ የጤና ባለሙያዎችን ምክር እንዲሁም የመንግስትን መመሪያዎች ተገንዝቦ በአግባቡ መተግበር ይገባል፤ ያስፈልጋልም።ለዚህ ደግሞ ስራው ከራስ የሚጀምር እንደመሆኑ እኛ እንደ እቁብ አባላት የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እያከናወንን እንገኛለን።እሁድ እሁድም የእቁብ አባላት ክፍያ ለመፈጸም ሲመጡ በተቻለ መጠን ርቀት የመጠበቅ ብቻ ሳይሆን የሰው መሰባሰብ እንዳኖር እየሰራን ነው።ከዚህ ባለፈም ውሃ፣ ሳኒታይዘርና አልኮል በማዘጋጀት እንዲጠቀሙ እያደረግን ነው።ይህ የጥንቃቄ ስራ እንደተጠበቀ ሆኖ ወረርሽኙ ከአገራችን እንዲወገድ ሁሉም በየእምነቱ በጸሎት ሊተጋ ያስፈልጋል።
አቶ መብራቱ ጣሰው፣ የዚሁ ሰፈር ነዋሪ እና የእቁቡ ዋና ሰብሳቢ ናቸው።እርሳቸውም ስለ እቁቡና አጠቃላይ እንቅስቃሴው ብሎም ስለ ወቅታዊው የኮሮና ወረርሺኝ እንዲህ በአንደበታቸው ያስረዳሉ።እቁብን እኛ ጀመርነው የምንለው ነገር አይደለም።ምክንያቱም ይህ አካባቢ ከጥንት ጀምሮ እስካሁን እቁብን እንደ ባህል ይዞ ያለ ነው።ለዚህ አካባቢ ህብረተሰብም እቁብ ባህል ነው።ይህ እቁብ ደግሞ በራስ ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣ ሲሆን፤ የራስን ብቻ ሳይሆን የቤተሰብን ህይወትና ኑሮ የሚለውጥ፣ ኢኮኖሚያችንን የምናሳድግበትና ጥሪትም የምንይዝበት ነባር ባህላዊ ተቋም ነው።እናም ይህ እቁብ በእኛ የተመሰረተ ሳይሆን እንደ ውርስ የተቀበልነው ሀብታችን ነው፡፡
ለምሳሌ፣ እኔ ድሮ አባቴ እቁብ ሊከፍል ሲሄድ እጄን ይዞኝ አብሬው እሄድ ነበር።በሂደትም እኔኑ ክፈል እያለ ይልከኝ ነበር።ይህ ደግሞ እቁብ ከልጅነቴ በውስጥ ተቀርጾ እንዲቀር አደረገው።እናም እኛ ለአቅመ አዳም ስንደርስና ስራም መስራት ስንጀምር እቁብ መግባት ጀመርን።በዚህ ውስጥ እያደግንና አቅም እየፈጠርን ስንሄድና የራሳችን ተቋምና ድርጅት ሲኖረን ደግሞ ሌላጋ ከመጣል ለምን የራሳችንን አንጀምርም የሚል ፉክክር አዘል ስሜት አደረብን።አቅም፣ ሞራልና ኃላፊነትን የመውሰድ ብቃቱ ካለህ ደግሞ እንዲህ አይነት ተግባር ማከናወን የሚከብድ ስለማይሆን በራሳቸው ወደመንቀሳቀስ ገባን።በዚህ ሂደት ነው እቁብ ከመጣል ወደ መሰብሰቡ የገባሁት።በዚህ መልኩ የተጀመረው እቁብም ዛሬ ላይ እኔም እየተጠቀምኩበት ህብረተሰቡም እየተጠቀመበት በርካቶችን ለውጤት ማብቃት የቻለ ሆኗል።ይሄው ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
የእቁብ አባላት ኮሚቴ በዚህ መልኩ ኃላፊነት ወስደን እቁቡን ስንመራና ስንሰበስብ የተለያዩ ተግባራትን እናከናውናለን።ከእነዚህ መካከል አንዱ እቁቡ በሕግና ደንብ እንዲመራ ማስቻል ሲሆን፤ የእቁብ ማህበሩን ስርዓትና ደንብ በተላለፉ አባላት ላይ በተስማሙበትና በተወሰነው መሰረት እንዲቀጡ ይሆናል።ይሄን መሰል የቅጣት ገንዘብ ደግሞ ማህበሩ ማህበራዊ ተግባራትን ለማከናወን የሚጠቀምበት ነው።ለምሳሌ፣ በአካባቢው የተጎዱ ሰዎች፣ ችግር ላይ የወደቁ ሰዎችና ሌሎችም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ያለባቸው ወገኖችን ለመደገፍ የሚውል ሲሆን፤ አሁን እንደ አገር የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ አይነት ችግር በሚፈጠርበት ወቅት አገራዊ ጥሪ ሲቀርብ ከዚህ ገንዘብም ከኪስ በማዋጣትም የሚጠበቅብንን ለመወጣት የሚውል ነው።በጥቅሉ ይህ ገንዘብ ለመረዳጃ የሚውል ነው፡፡
ምክንያቱም ይህ እቁብ በዋናነት የእቁብ አባላቱን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማሳደግና ኑሮን ለመደጎም የሚያስችል ሲሆን፤ ከዚህ ባለፈ አንድም በማህበሩ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ለማገዝ፣ ሁለተኛም ከማህበሩ አባላት ውጪ ያሉ እና በችግር ውስጥ ወድቀው ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ለመደገፍ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል።ከሰሞኑም አገራዊ ጥሪውን ተከትሎ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያስረከብነው የ50 ሺህ ብር ድጋፍም የዚሁ አካል ሲሆን፤ ይሄን መሰል ጥሪ ሲቀርብ ደግሞ ከአባላት በተለይም ከኮሚቴዎች ኪስ ጭምር እየተዋጣ እንዲሸፈን የሚደረግ ነው።ምክንያቱም፣ እቁብ ማለት ቁጠባ ማለት ነው።የሚቆጠበው ደግሞ ብር ነው።ይህ ማለት ቀድሞ ሰዎች ብራቸውን ለመቆጠብ የሚጠቀሙበት ባህላዊ ተቋም ማለት ሲሆን፤ አሁን ላይ ባንኮች ይሄን ተግባር ወስደው እየሰሩት ይገኛል።ይሁን እንጂ ባንኮች ሙሉ በሙሉ የእቁብን ተግባር ወስደዋል ማለት አይቻልም።ምክንያቱም ባንኮችም ቁጠባን ተክተው የማይሰሩበት በርካታ ነገሮች በመኖራቸው ነው፡፡
እቁብ ገንዘብ መቆጠቢያ ብቻ ሳይሆን፤ መረዳጃም መደጋገፊያም ነው።ባንክ ደግሞ ገንዘብን ከማስቀመጥ፣ በዚህም ወለድ ከማሰብና በወለድ ከማበደር ባለፈ ማህበራዊ ጉዳዮችን በእቁብም ልክ ትኩረት የሚሰጥ አይደለም።እኛም ይሄን እቁብ ስንጀምር ያቀፍናቸውን ህብረተሰቦች የምንደግፍበት፤ ወንድማችንን የምናቋቁምበት መሆኑን ተገንዝበን ነው።ለምሳሌ፣ አንድ ሰው ብር ኖሮት መኪና ላይገዛ ይችላል።ወደ እኛ እቁብ ሲገባ ግን ትንሽ ብር ካለው እቁቡ አግዞት መኪና መግዛት እና በመኪናው እየሰራ እዳውን መክፈል ይችላል።በዚህ መልኩ በርካታ የቀጨኔ አካባቢ ሰዎች የታክሲ ባለቤት የሆኑ ሲሆን፤ አብዛኛው አዲስ አበባ ታክሲዎችም ከዚሁ አካባቢ የወጡ ናቸው።ይህ ደግሞ ባለታክሲዎች ከቤተሰብ በተሰጣቸው ብር ወይም በባንክ ካላቸው ገንዘብ አውጥተው ሳይሆን በእቁብ ብር የገዙት ነው፡፡
ይህ ደግሞ የአካባቢው ሰው አስርም ሆነ ሃያ ሺህ ብር እጁ ላይ ካለ እቁብ በመግባት በሚያገኘው ድጋፍ የሚገዙ ሲሆን፤ ያ ሰው ገንዘብ በእጁ ይዞ እሱን እየከፈለ ከሚጨርስ ይልቅ ታክሲ በመግዛት በታክሲው እየሰራ እንዲከፍል እና እዳውን ሲጨርስ የመኪናው ባለቤት እንዲሆን ስለሚደረግ ነው።ምክንያቱም የገዛው ታክሲ ስራም፣ ገቢ ማግኛም፣ እዳ መክፈያም ሆኖ የሚያገለግል ነው።በዚህም አንድ ሰው እስከ 100 ሳምንት ባለ ጊዜ ውስጥ የመኪና ባለቤት ይሆናል ማለት ነው።ይህ በመኪና ብቻ ሳይሆን በሌሎች የንግድ መስኮች ሊሆን ይችላል።በዚህ አይነት መልኩ ደግሞ የባንክ ሰዎች ሳይቀር እየተሳተፉ ሲሆን፤ በእንደዚህ አይነት መልኩ ደግሞ ያልተለወጠና ያልተሻሻለ የአካባቢያችን ሰው የለም።ይህ ትናንት የነበረ የባህል ተቋም ዛሬ ደረሷል፤ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡
አሁን የአገር ስጋት ከሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ጋር በተያያዘም ወገኖቻችንና የአገራችን ህዝቦች በዚህ ጉዳይ ቸልተኝነት እየታየባቸው ይገኛል፡፡ይህ ወረርሺኝ ደግሞ ትልቅ ስጋት የሆነ በላያችን ላይ ያጠላ ግዙፍ ደመና ነው።በመሆኑም ይህ ያንዣበበው የኮቪድ 19 ደመና በላያችን ላይ እንዳይዘንብ ሁሉም በጋራ ሊሰራ፤ የሚተላለፉ የባለሙያና የመንግስት መልዕክቶችን መተግበር፤ እርስ በእርስ መተሳሰብና መተጋገዝ የግድ ነው።በዚህ መልኩ እያንዳንዳችን ኃላፊነታችንን ወስደን መስራት ካልቻልን ይህ ደመና ወርዶ የሚፈጀን መሆኑንም መገንዘብ ይገባል።በመሆኑም በመጠንቀቅ ችግሩን መከላከል፤ በቫይረሱ ምክንያት በቤታቸው ተቆልፎባቸው ችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን ማሰብና ማገዝ ይገባል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2012
ወንድወሰን ሽመልስ