ማስታወሻ የራቀን ዘመን አቅርቦ በትዝታ የማስቃኘት ታላቅ ኃይል ስላለው ብዙዎች አጥብቀው መያዝን ይመርጣሉ።ማስታወሻው በተለይ ደግሞ በሕይወት የሌለ ወዳጃችንን የምናስብበት ከሆነ ቀሪ ሀብታችን ነውና ለማንም አለማጋራትን ምርጫችን እናደርጋለን።ስለማስታወሻ ያነሳሁላችሁ ያለምክንያት አይደለም።ይልቁንም አንዲት እናት ከ40 ዓመታት በፊት ከልጅነት ውሃ አጣጫቸው ጋር ያቀኑት መኖሪያ ቤታቸው ያረፈበትን ስፍራ የክፍለ ከተማው መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ለአጎራባቻቸው ተደራቢ ካርታ በመስጠቱ ቅሬታ አሳድሮባቸው ፍትሕ በማጣታቸው ፍረዱኝ ሲሉ አቤቱታቸውን ለተቋማችን በማቅረባቸው እንጂ።እኛም የካርታ መደራረቡ እንዴት ተፈጠረ? ችግሩንስ እንዴት መፍታት አልተቻለም? ስንል የቅሬታ አቅራቢዎቹን አቤቱታ፣ የአጎራባቾቹን ሐሳብ እንዲሁም የሚመለከተውን አካል ምላሽና የሰነድ ማስረጃዎችን ፈትሸን እንዲህ ይዘንላችሁ ቀረብን።
ከአንደበታቸው
ዕድሜያቸው 75 ዓመት እንደሞላ የሚናገሩት ወይዘሮ ፈለቀች ገብረየስ ነዋሪነታቸው በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ነው።በዚሁ ወረዳ የሚገኘው የቤት ቁጥሩ 596 የሆነውን ቤታቸውን ከልዕልት ወለተ እስራኤል ሥዩም ቤተ ርስት ጽሕፈት ቤት እንዳገኙት ያስታውሳሉ።ባለቤታቸው ዘመቻ ሄደው ቢቀሩም ከልጆቻቸው ቀጥሎ አንድ ያላቸው ማስታወሻቸው እንደሆነ ከዓይኖቻቸው የሚወርዱትን የእንባ ዘለላዎች ትከሻቸው ላይ ጣል ባደረጉት ነጠላ አበስ እያደረጉ በሐዘን የደረሰባቸውን በደል ይገልፃሉ፡፡
ፈረንሳይ አካባቢ ልዩ ሥሙ ልዕልት ወለተእስራኤል ሠፈር ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ፈለቀች፤ ከ40 ዓመታት በፊት በልዕልቲቷ ምሪት ያገኙት መኖሪያ ቤታቸው ከውሃ አጣጫቸው ጋር ያቆሟት የልጅነት ሀብታቸው እንደሆነች የኋሊት በትዝታ ተጉዘው ያስታውሳሉ።ለዓመታት ለብቻቸው ያሳደጓቸው ልጆች ደርሰውላቸው ያረጀውን ቤታቸውን ለማደስ የነበረውን አፍርሰው ከሚመለከተው አካልም የግንባታ ፈቃድ አውጥተው ሥራ ሊጀምሩ ሲነሱ ግን ከአጎራባቻቸው በይዞታው ላይ የይገባናል ጥያቄ ይነሳባቸዋል፡፡
አንድ መኖሪያና አንድ ማዕድ ቤታቸውን ፕላን አስነስተው፣ ግንባታ ፈቃድ አውጥተው ነባሩን ቤት አፍርሰው ሌላ ሊገነቡ ከሠራተኛ ጋር ተነጋግረው ሲጨርሱ አጎራባቻቸው ‹‹የእኛ ቦታ ነው›› የሚል ጥያቄ እንዳነሱባቸው የሚያስታውሱት ወይዘሮ ፈለቀች፤ ቤታቸው ፈርሶ ኩሽናና አጥር ካጡ አራት ዓመታትን ቢያስቆጥሩም አስተዳደሩ ሕግን ሊያስከብርላቸው አለመቻሉን ይጠቁማሉ።በዚህም ቤታቸው በቀበና ወንዝ መውረጃ አፋፍ ላይ የሚገኝና ከጀርባው ጫካ በመኖሩ ዘወትር ልጆቻቸው መሸት ካለ ሲወጡ በሰቀቀን እንደሚጠባበቋቸው በሐዘን ፊታቸውን ቅጭም አድርገው የችግራቸውን ተደራራቢነት ይናገራሉ።‹‹ፍትሕን ነው የምፈልገው›› የሚሉት ወይዘሮ ፈለቀች ምላሽ የሚሰጥ የአስተዳደር አካል በማጣታቸው ተስፋ ቆርጠው እንደተቀመጡ በምሬት ይገልፃሉ።
ወይዘሮ እታፈራሁ በርሔ፤ ወላጆቻቸው ይዘውት የኖሩት ከ40 ዓመት በላይ ያስቆጠረ መኖሪያ ቤታቸውን አፍርሰው ለግንባታ ሲነሱ ከጎረቤቶቻቸው ክርክር እንደገጠማቸው ሁኔታውን ያስታውሳሉ።ችግሩ እንደተፈጠረ ለክፍለ ከተማው ቢያሳውቁም ይዞታውን አስመልክቶ ምንም ምላሽ ሳይሰጣቸው እንዳመላለሳቸው ይገልፃሉ።
ሕብረተሰቡን ለማስተዳደር ሥልጣን የተሰጠው አካል ከለላ ሆኗቸው አጥራቸውን ማጠር ካልቻሉ እንዴት ይዞታቸውን ሊስከብሩ እንደሚችሉ የዘወትር ጥያቄያቸው ሆኗል።ፍትሕን ተርቤያለሁ የሚሉት ወይዘሮ እታፈራሁ በሕግ ኃላፊነት የተሰጠው ክፍለ ከተማው ውሳኔ መስጠት እንዳለበትና ይናገራሉ።ችግራቸው አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጠው የከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ ቢሰጣቸውም መፍትሔ አለማግኘታቸውን በመግለጽ፤ ለጥያቄያቸው ትክክለኛነት ደጋፊ ይሆኑኛል ያሏቸውን ማስረጃዎች አሳይተውናል፡፡
ሰነዶች
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ከያዟቸው ማስረጃዎች መካከል የቤቱን የቆየ ታሪክ የሚያሳየውን የልዕልት ወለተ እስራኤል ሥዩም ቤተ ርስት ጽሕፈት ቤት የፃፈውን የመሬት ኪራይ ውል ሰነድ በቀዳሚነት ተመለከትን።በወቅቱ የቦታው አዋሳኝ ተብለው በውሉ ላይ የተቀመጡትም፤ በምሥራቅ የአቦ ወንዝ፣ በምዕራብ ከልዕልት ወለተ እስራኤል ቦታ፣ በሰሜን ከልዑል ራስ መንገሻ፣ በደቡብ ከቄስ ሠፈር ሲሆኑ፤ ስፋቱ 200 ሜትር ካሬ የሆነው ይዞታ ጥር 30 ቀን 1966 ዓ.ም ለአለቃ በርሔ አስፋው እንደተከራየ ያሳያል።
የማህደር ቁጥር 17=23 በቀን 26/11/91 ዓ.ም በአቶ በርሄ አስፋው ሥም ወጪ የተደረገው የቦታ ኪራይና የቤት ግብር ሂሳብ ማስታወቂያ ሰነድ ይዞታው የመኖሪያ እንደሆነና የተሰጠበት ዘመንም 1966 ዓ.ም እንደሆነ ያመላክታል።የቦታው ስፋት 249 እንደሆነ ያሰፈረው ሰነዱ፤ የግብሩን መጠን አስቀምጧል፡፡
በየካ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት በቀን 12/7/2008 ዓ.ም በመዝገብ ቁጥር የካ/መ/ባ/ማ/ጽ/ቤት/1274/08 ወጪ በተደረገው ደብዳቤ የሊዝ ክፍያ ማጠናቀቅን አስመልክቶ ለእነ ፈለቀች ገብረየስ መግለጹን ያሳያል።አዋጅ ቁጥር 721/2004 ለማስፈፀም በወጣ ደንብ ቁጥር 49/2004 የከተማ መሬት ሊዝ አፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 11/2004 መሠረት በይካተትልኝ ይዞታ ያገኙትን የቦታ ስፋቱ 113 ሜትር ካሬ የሊዝ ክፍያ በ40 ዓመት ለማጠናቀቅ ውል ግዴታ ቢገቡም አጠቃለው ለመክፈል መጠየቃቸውን ደብዳቤው ያትታል።በደረሰኝ ቁጥር 958898 ክፍያ በመፈፀማቸው የክፍያ የምስክር ወረቀት ከምስጋና ጋር እንደተሰጣቸው የክፍለ ከተማው መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት በደብዳቤ አስፍሯል፡፡
በዚህ መነሻ ደግሞ በጽሕፈት ቤቱ መሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት አግባብነት ባለው አካል ሳይፈቀድ የተስፋፉ ቦታዎችን ለማስተካከልና ለመከላከል በወጣው የአፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 18/2006 መሠረት በቀን 14/08/2008 ዓ.ም የሊዝ ውል ሥምምነት ተፈርሟል።በይካተትልኝ ጥያቄ ቀርቦበት የተስተናገደው ቦታና ቤታቸው ተለክቶ የተጠየቀው 113 ሜትር ካሬ ይዞታ በሊዝ ስሪት ተጨምሮ ካርታ እንደተዘጋጀላቸው ደግሞ በቀን 24/10/2008 ዓ.ም በቁጥር የካ/ይዞ/አስ/27050/08 ወጪ የተደረገው ደብዳቤ ያሳያል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በቀን 24/10/2008 ዓ.ም በሴሪ ቁጥር 0630986 ለእነ ፈለቀች ገብረየስ የተሰጠው የነባር ይዞታ የባለይዞታነትና የቤት ባለቤትነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሌላው የተመለከትነው ሰነድ ነው።ማረጋገጫው ወይንም ካርታው ላይ ሰፍሮ እንደሚገኘው፤ የካርታ ቁጥሩ የካ/01/194706/08 በሆነ መለያ ተመዘገበው ይዞታ ስፋቱ 312 ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን የካ ወረዳ ሁለት ለእነ ፈለቀች በቀን 16/05/2009 ዓ.ም የግንባታ ፈቃድ የምስክር ወረቀት መስጠቱን የሚያሳይ ሰነድ ሌላው የተመለከትነው ማስረጃ ነው።ከወር ቆይታ በኋላም በቀን 30/06/2009 ዓ.ም ለክፍለ ከተማው የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት እነ ፈለቀች ቅሬታ ማቅረባቸውን የሚያሳይ የአቤቱታ መቀበያ ቅጽ ከሰነዶች መካከል ይገኛል።አቤቱታ አቅራቢዎቹ በተለያየ ጊዜ የወሰን ችካል ቢጠይቁም በአግባቡ ሊስተናገዱ አለመቻላቸውን በመግለጽ፤ የካርታ ግልባጫቸውን ማቅረባቸውንና ጽሕፈት ቤቱ እንዲያስተናግዳቸው መጠየቃቸው በቅጹ ሰፍሯል፡፡
የጽሕፈት ቤቱ ባለሙያ ቅሬታውን በማጣራት የደረሰበትን ድምዳሜና ውሳኔ በቅጹ ያስቀመጠ ሲሆን፤ በዚህም በካርታ 312 ሜትር ካሬ በልኬት ደግሞ 310 ሜትር ካሬ እንደሆነ ያብራራል።ጂአይኤስ አጥር ያካተቱ በመኖሩ የ1997 ላይን ማፕ (መስመር ካርታ) አጥር ታይቶ በካርታ ግልባጭ (ኮፒ) ሊስተናገዱ የሚችሉት 271 ሜትር ካሬ ይሆናል።ቀሪው ግን ከጂአይኤስ እንዲሁም 1997 የአየር ካርታ ውጪ በመሆኑ ሊካተት አልቻለም በሚል ቅሬታ አቅራቢዎቹ አገልግሎት ሊያገኙ የሚችሉበትን ሁኔታ ማብራሪያ ተሰጥቷል።ይህንን መነሻ በማድረግም የቡድን አስተባባሪው የልኬት ሥራ በተከናወነውና በአካል በያዙት መሠረት ካለው መረጃ ጋር ተገናዝቦ ሊሰጣው የሚችል የካሬ ስፋት መጠን ባለሞያ ባስቀመጠው መሠረት ይስተናገዱ በሚል መርተውበታል፡፡
የክፍለ ከተማው መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት የአሠራር ጥናት ኦዲት አቤቱታና ቅሬታ አፈታት ዴስክ ለይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በቀን 21/07/2009 ዓ.ም በቁጥር የአ/ጥ/ኦ/16452/2009 ወጪ ያደረገው ደብዳቤ የእነ ፈለቀች አቤቱታን አስመልክቶ አገልግሎቱ እንዲሰጣቸው መጠየቁን ያሳያል።የተካተተው ይዞታ ልኬት ተወስዶ እንደሚሆን በመጥቀስ፤ ለወሰን ችካል የተለካው ልኬት ደግሞ ቀደም ሲል የተሠራውን ካርታ የሚቆርጥ የተካተተውንም ቦታ ወደ ውጪ የሚተው መሆኑንም ደብዳቤው ይጠቁማል።በመሆኑም አገልግሎቱ በአንድ ተቋም እየተሰጠ ያለ ስለሆነ በይካተትልኝ የተሠራው ካርታ የሚቆርጠው ልኬት በድጋሚ በባለሞያ ተረጋግጦ ቅሬታ አቅራቢዎቹ የጠየቁት አገልግሎት እንዲሰጣቸው ይላል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎች ለክፍለ ከተማው ዳግም አቤቱታ ማቅረባቸውን በቀን 01/13/2010 ዓ.ም የተሞላው ቅጽ ያመለክታል።በዚህም ካርታና ፕላን ባለው የግል ይዞታቸው ላይ ያረፉ ቤቶችን አፍርሰው ለመገንባት ፈቃድ ቢያገኙም ቤቱን ዳግም እንዳይሠሩ እንደተከለከሉና ከሁለት ዓመት በላይ አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻሉ ሰፍሯል።ይህንንም የሚያግዙና ሕጋዊነታቸውን የሚያረጋግጡ ሰነዶች እንዳላቸው አቤቱታ አቅራቢዎቹ ገልፀዋል፡፡
አቤቱታውን መነሻ በማድረግ ጉዳዩን ያጣራው ባለሙያም ለአቶ መንገሻ ኤደኤ ወይንም የቅሬታ አቅራቢዎቹ ጎረቤት በአካል ያልያዙት ይዞታ 2004 ዓ.ም በአየር ካርታ በጂአይኤስ ብቻ ስለታተመ በተገቢው አካል ማስተካከያ ይደረግበት የሚል ውሳኔ አሳርፏል።በዚህ መልኩ ሲስተካከል በእነ ፈለቀች ሥም ተመዝግቦ የሚገኘው ካርታ መቀጠል ቢችል በሚል የውሳኔ ሐሳብ መቅረቡን ቅጹ ያሳያል።በተያያዘ በ2004 ዓ.ም ለእነ አቶ መንገሻ ታትሞ የተሰጠው ካርታ የተሠራበት አግባብ ትክክል ባለመሆኑ እንደታገደና የተካተተው የእነፈለቀች ይዞታ እንዲቀጥል በቡድን አስተባባሪው ተመሳሳይ ውሳኔ አልፏል፡፡
ባለሙያውና የቡድን አስተባባሪው ከሰጡት የውሳኔ ሐሳብ በተጨማሪ የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ በ2004 ዓ.ም የተሠሩ ካርታዎች ቤዝማፕ ያልተደራጁ በመሆኑ የአቶ መንገሻ ካርታ በአካል በያዙት ልክ እንዲስተካከል ከዚሁ ጎን ለጎን ቅሬታ አቅራቢዎቹ በተካተተላቸው መሠረት አገልግሎት እንዲገኙ መወሰናቸውን ቅጹ ያስረዳል።አያይዘውም ኃላፊው እነ አቶ መንገሻ በ2004 ዓ.ም ጂአይኤስ መነሻ ተደርጎ ካርታ እንደተሰጣቸውና እነ ፈለቀች ግን በ09/06/1999 ዓ.ም ካርታ እንደተሰጣቸው በውሳኔያቸው ላይ አክለው ገልፀዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ለክፍለ ከተማው መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ለይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በቀን 20/02/2010 ዓ.ም በቁጥር ይአስ/410/2010 ወጪ አድርጎ የላከው ደብዳቤ ከቅሬታ አቅራቢዎቹ ካገኘናቸው መረጃዎች መካከል የመጨረሻው ነው።ደብዳቤው የእነ ፈለቀች ከሁለት ዓመት በላይ ይዞታቸውን በተመለከተ ወደ ክፍለ ከተማው ቢመላለሱም ምንም ዓይነት ምላሽ ሳያገኙ እንደተጉላሉና ቅሬታ እንዳቀረቡ ያብራራል።ካርታና ፕላን ያለው ይዞታቸው ላይ የነበረን ቤት ለማደስ አፍርሰው ፈቃድ አውጥተው የነበረ ቢሆንም ቤታቸውን መልሰው እንዳይሰሩ እንደተከለከሉ በመግለጽ ቅሬታ ማቅረባቸውን ያወሳል፡፡
ክፍለ ከተማው የቅሬታ አቅራቢዎቹን አቤቱታ በመቀበል ችግሩ የተከሰተው ለአጎራባቻቸው አቶ መንገሻ ኤድኤ ካርታ ሲዘጋጅ በአካል ያልያዙት የ1988 አየር ካርታ መሠረት አድርጎ እንደተሰጣቸውና ይህም የተሰጠበት አግባብ ትክክል ባለ መሆኑ ካርታው መታገዱን በቅሬታ ማቅረቢያ ቅጹ ላይ እንዳሰፈረ ደብዳቤው ያሳያል።
በሌላ በኩል ቅሬታ አቅራቢዎች በተካተተላቸው መሠረት ማንኛውንም አገልግሎት መውሰድ እንደሚችሉ በዚሁ ቅጽ ላይ መስፈሩን ያስረዳል።ይሁን እንጂ በተዘጋጀላቸው ካርታ መሠረት ግንባታ ፈቃድ አውጥተው ነባር ቤቶቻቸውን አፍርሰው ለመገንባት ሥራ ሲጀምሩ ከአጎራባች በተነሳባቸው ክርክር እየተጉላሉ መሆኑንና ክፍለ ከተማውም ተገቢ ምላሽ ሊሰጣው ባለመቻሉ ወደ ከተማ አስተዳደሩ ለማቅናት መገደዳቸውን ደብዳቤው አስቀምጧል፡፡
ደብዳቤው እንደሚያመላክተው፤ ማዕ ከሉ ችግሩን ሲያጣራ ሁለቱ ይዞታዎች መደራረብን የሚያሳዩ መሆናቸውን ማረጋገጥ ችሏል።ሁለቱም ይዞታዎች በ1988 የአየር ካርታ መሠረትና በ1997 የመስመር ካርታ መሠረት በአካል አጥረው የያዙትን መሠረት በማድረግ የካርታ ኮፒ አገልግሎት ተሰጥቷቸው ካርታቸውን በማስተካከል በካርታቸው መሰረት የወሰን ችካል በማስቀመጥ አፋጣኝ ችግራቸው እንዲፈታ የከተማ አስተዳደሩ አሳስቧል።
ሌላኛው ወገን
ክርክር በተነሳበት ይዞታ የቅሬታ አቅራቢዎቹ አጎራባቻቸው የሆኑት የእነ አቶ መንገሻ ቤተሰብ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ምላሽ ለመቀበል ወደቤታቸው አመራን።ሆኖም በቤቱ ውስጥ ያገኘናቸው እናት አቶ መንገሻ በሕይወት እንደሌሉና እርሳቸውም አቅማቸው ስለደከመ ለልጆቻቸው ውክልና መስጠታቸውን ገለፁልን።እኛም ተወካይ ወይዘሮ ትዕግስት አለማየሁን ያነጋገርናቸው ሲሆን፤ አንድ ቦታ ለሁለት ሰው ተሰጥቷል ይላሉ።ይህም ለቅሬታ አቅራቢዎቹ በ1997 ዓ.ም እና ለእነ አቶ መንገሻ ደግሞ በ1988 ዓ.ም እንደሆነ በመግለጽ፤ ቦታው ቀደም ብሎ የእነርሱ እንደሆነና አቤቱታው ትክክል እንዳልሆነ ያብራራሉ፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንዴትና በምን ዓይነት ሁኔታ ካርታ አሻሽለው እንዳወጡ እንደማያውቁ የሚናገሩት ወይዘሮ ትዕግስት፤ ባለሞያዎች ቦታው ላይ በመሄድ ሲያጣሩ የካርታ መደራረብ እንደተፈጠረ እንዳሳወቋቸው ያስታውሳሉ።አስተዳደሩን የችግሩ ምንጭ የቱ ጋ ይሆን? በሚል ጥያቄ ሲያቀርቡለትም የእነፈለቀች በ1997 ዓ.ም ማለትም እነ አቶ መንገሻ ካርታ ከተሰጣቸው 11 ዓመት በኋላ ሲሠራ የተፈጠረ ክፍተት እንደሆነ ምላሽ እንደሰጣቸው ነው የሚያስረዱት።ችግሩ የተወሳሰበ በመሆኑም ያለው አማራጭ ወደሚመለከተው የፍትሕ አካል ማምራት ቢሆንም እነ ፈለቀች ግን ይህንን አማራጭ መጠቀም አይፈልጉም ባይ ናቸው።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ጉዳያቸው ትክ ክል ቢሆንና ጥያቄያቸው ተገቢ እንደሆነ ቢያውቁ ወደሚመለከተው የሕግ አካል በመሄድ የደረሰባቸውን በደል አስረድተው ተከራክረው መርታት ይችሉ ነበር በማለት፤ ይህንን የማያደርጉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ ጥያቄያቸው ትክክል አለመሆኑን ስለሚያውቁት ነው ጉዳዩን ማንሳት የማይመርጡት ሲሉ ሐሳባቸውን ሰጥተውናል፡፡
ክፍለ ከተማው
ጽሕፈት ቤቱ ቅሬታውን ሊፈታ ምን አዳገተው? የ1988 ዓ.ም የአየር ካርታ እንዲሁም የ1997 የመስመር ካርታ ቀጥሎም በከተማው በ2003 ዓ.ም የተደረገው መረጃ የማቀናጀት ሥራ በይዞታዎቹ ላይ ምን ያመለክታሉ? የካርታ መደራረቡ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? ችግሩ ከተፈጠረ በኋላስ ስለምን ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት አልተቻለም? የሚሉ ጥያቄዎችን ይዘን በየካ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አቀናን፡፡
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ መረጃውን ሊሰጡን ከተስማሙ በኋላ ሐሳባቸውን ለውጠው ተቋማችን መረጃውን በደብዳቤ መጠየቅ እንደሚገባው አሳው ቀውናል። እኛም የኃላፊውን ምላሽ ተቀብለን ደብዳቤ ብንወስድም ጽሕፈት ቤቱ ግን ጉዳዩን አስመልክቶ ጋዜጣው ለህትመት እስከተላከበት ጊዜ ድረስ መረጃ ሊሰጠን አልቻለም።
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2012
ፍዮሪ ተወልደ