አቡዳቢ አንደኛዋ በአረብ ኢምሬቶች ውስጥ የምትገኝ ከተማ ስትሆን፣ ቀደም ብሎ ትሩሲዓል ኦማን ተብላ ትታወቅ ነበር። በወቅቱ ለነበረው ፌዴሬሽንም ዋና ከተማ ሆና አገልግላም ነበር። ከተማዋ በተመሳሳይ ስም የሚጠሩ አነስተኛ ደሴቶች የያዘች ሲሆን፣ ደሴቶቹም በባህረ ሰላጤ አካባቢ የሚገኙና እርስ በርሳቸው በአነስተኛ ድልድዮች የተያየዙም ናቸው።
አቡዳቢ ቀደም ብሎ በእድገት ወደ ኋላ የቀረችና የአገር ውስጥ እንቅስቃሴ ብቻ የሚከናወንባት ከተማ ነበረች። ነገር ግን በአረብ ኢምሬቶች የሚገኘው የነዳጅ ሀብት ባመጣው እድገት ምክንያት ወደ ዘመናዊ ከተማነት ከመሻገር ባለፈ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ የላቀች ከተማ ልትሆን ችላለች።
ከእኤአ 1761 በፊት ስለአቡዳቢ ከተማ የሚናገር ታሪክ ማግኘት ባይቻልም፤ የአብሉፋላህ ነገድ የባዩናስ ጎሳ አባላት በቦታው እስካሁን ድረስ እየኖሩ እንደሚገኙ ይነገራል። እነዚህ የጎሳ አባላት እኤአ 1795 አካባቢ ከሊዋ ከሚባል ደሴት ተነስተው አቡዳቢ አካካቢ መስፈራቸውን የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ። በ19ኛውና 20ኛው ክፍከዘመን ከተማዋ የትሩስያል ጠረፍ ዋና እና ተመራጭ ቦታ እየሆነች ትገኛለች። ከተማዋ ለንግድና ለኢኮኖሚ መነሃሪያነት ከዱባይና ከአል ሻሪካ ከተሞች በበለጠ ሁኔታ እንቅስቃሴ እየተደረገባት ይገኛል።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ የአቡዳቢ ከተማ ነዋሪዎች ብዛት ስድስት ሺህ አካባቢ የሚገመት ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ የባንክ ባለቤቶችና የአገር ውስጥ ንግድ ያላቸው ነበሩ። በብዛት የኢራንና የህንድ ዜግነት ያላቸው ሀብታሞች ይገኙባታል። እኤአ 1929 በኋላ በአቡዳቢ የጃፓኖች የባህልና የኢንዱስትሪ አብዮት በመቀዛቀዙ የኢኮኖሚ መዋዠቀ አጋጥሞ ነበር።
በአቡዳቢ እኤአ 1958 ማንነቷን ያገኘችበት እንዲሁም እኤአ 1962 ደግሞ የንግድ እንቅስቃሴ የተጧጧፈበት እና የነዳጅ ሀብት የከተማዋን ኢኮኖሚና ፖለቲካ እንቅስቃሴ የለወጠበት ጊዜ ተደርገው ይወሰዳሉ። እንግሊዝ እኤአ 1961 ላይ በአቡዳቢ የከተማዋ ጠባቂ እራሷን አድርጋ በመሾም በከተማው የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በመጀመር ዱባይን ጨምሮ መቆጣጠር ችላ እንደነበርም ይገለጻል።
የነዳጅ ምርት ዋነኛ መገኛ የሆነችው አቡዳቢ፣ ከፍተኛ የሆነ የከተማ እድገትም የሚታይባት ነች። ከተማዋ ቀስ በቀስ እያደገች የመጣችው በወግ አጥባቂው መሪ ሼክ ሻኩቡት ኢብን ሱልጣን አል ናህያን በሚከተሉት ፖሊሲ ምክንያት ነበር። በጊዜ ሂደት ግን በስልጣኑ የተተካው ታናሽ ወንድማቸው ዛይድ ኢብን ሱልጣን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የከተማዋ ገዥ የነበሩ ሲሆን፣ አጠቃላይ የነዳጅ ሀብቱን በመጠቀም ለውጥ ማምጣት ችለዋል።
ሼክ ዛይድ የመንገድ ግንባታዎችን በፈጣን ሁኔታ እንዲገነባ በማድረግ አጠቃላይ የከተማው ክፍል እርስ በርሱ እንዲገናኝ አድርገዋል። በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በርካታ የመንገድ ስራዎችን ለማጠናቀቅ እቅድ በመያዝ ዘመናዊ የሆነ ከተማ መፍጠር ተችሏል። ኤሌክትሪክ መስመር፣ የንፁህ መጠጥ ውሃና የፍሳሽ አገልግሎት በዘመናዊ መንገድ እንዲገነቡ ተደርገዋል። በተጨማሪም ዘመናዊ የመንግስት ቢሮዎች፣ ሆቴል፣ የቤት ግንባታዎች እንዲሁም አዳዲስ ወደቦች ተገንብተዋል።
በእኤአ 1976 በኡሚ አል ናር ደሴት አካባቢ የነዳጅ ማጣሪያ ተገንብቶ ስራ ጀምሯል። የአቡዳቢ አለም አቀፍ አየር መንገድ በደሴቱ ደቡባዊ ክፍል ላይ ይገኛል። ቀላል ኢንዱስትሪዎች ደግሞ በሙሰፋህ አቅራቢያ ይገኛሉ። የሞተር መንቀሳቀሻ መንገድ ከዱባይ በሰሜን ምስራቅ ከአል አይን በምስራቅ እንዲሁም ከኳታር በስተደቡብ በኩል ይዋሰናል።
እንግሊዝ በመጨረሻ የገልፍ አገራትን ለቃ ስትወጣ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች እኤአ 1971 ነጻነታቸውን ያገኙ ሲሆን፣ ከዚህም በኋላ አቡዳቢ ዋና ከተማ ሆና እንድታገለግል ተመረጠች። እኤአ 1990 አካባቢ አቡዳቢ በቋሚነት የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ዋና ከተማ ሆና እንድታገለግል ተመረጠች። ከዚህ በኋላ በርካታ የልማት ስራዎች በመሰራታቸው ከተማዋ የንግድና የቱሪዝም መነሃሪያ እንድትሆን አድርጓታል። የከተማዋ የልማት እቅድ ሲነደፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ አለም አቀፍ አየር መንገድ እንዲሁም ለመኖሪያነት የሚመቹ ቤቶች እንዲካተቱ ተደርጓል።
በአቡዳቢ ከተማ በርካታ ዘመናዊ ህንጻዎች የሚገኙ በመሆናቸው ለከተማዋ ድርብ ውበት ሰጥተዋታል። በከተማው ከሚገኙ ዘመናዊ ህንፃዎች መካከል የጀመሪያው ኢትሀድ ታውር ሲሆን፣ ታወሩ የተገነባው በሼኪ ሱሮር ፕሮጀክትና በአለም አቀፍ የአርክቴክቶች ውድድር ተካሂዶ ነው። በዚህ ሁኔታ ካለፈ በኋላ እኤአ 2011 ላይ የታወሩ ዲዛይን ተነደፈ።
ይህ የተለየ ዲዛይን ያለው ግንባታ ከኢምሬት ፓላስ ሆቴል በተቃራኒ በኩል ይገኛል። ህፃዎቹ በሁሉም በኩል ተመሳሳይነት ያላቸው ሲሆን፣ ሶስቱ ታወሮች ለመኖሪያ ግልጋሎት፣ አንደኛው ታወር ለቢሮ እንዲሁም የተቀረው አንደኛው ታወር በከተማው ምርጥ ባር የያዘ ሆቴል ነው። የታወሩ ሆቴል በውስጡ 14 ሬስቶራንት፣ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ስኩዌር ቦታ የያዘ አለም አቀፍ መገበያያ እና ከአንድ ሺህ እስከ አንድ ሺህ አራት መቶ እንግዳ መያዝ የሚችል አንድ ሺህ ስምንት መቶ ስኩዌር የሆነ የመኝታ አገልግሎት ይሰጣል።
ሁለተኛው ደግሞ የአልዳር ዋና መስሪያ ቤት ህንፃ ሲሆን፣ በተገነባበት ወቅት የመጀመሪያው ‹‹ክብ ቅርፅ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ነበር። የህንፃው አሰራር በሰያፍ የቆመ ሳንቲም አይነት በመሆኑ በወቅቱ ከፍተኛ ትኩረትን ስቦ እንደነበርም ይታወሳል። ህንፃው 12 የሰዎች መወጣጫ የያዘ ሲሆን፣ የአሳንስሩ አሰራር ከተለመደው ወጣ ያለ ሆኖ አጠቃላይ አቡዳቢን ከላይ ሆኖ ለማየት ያስችላል።
ሶስተኛው የካፒታል ጌት ሆቴል ነው። ግንባታው በአቡዳቢ ታሪክ ከተሰሩ ህንፃዎች በተለየ መንገድ ዲዛይን ተደርጎ የተገነባ ነው፤ ህንፃውን የሰራው አርክቴክቱ ዲዛይኑን ጣሊያን ከሚገኘው ፒሳ ታወር መነሻ በማድረግ የሰራው ሲሆን፣ ዲዛይኑ የጊነስ ወርልድ ሪከርድ መስበር ችሏል። ህንፃው 160 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፣ 35 ወለሎች ይዟል። በከተማው ከሚገኙ ህንፃዎች በረጅምነቱ ይጠቀሳል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2012
መርድ ክፍሉ