ልጆች ሆነን በትምህርት ቤት ከጓደኞቻችን ጋር ስንጣላ፣ ለጓደኞቻችን ተደርበን ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ስንጋጭ መፎከሪያችን ሰኔ 30 እንገናኝ የሚል እንደነበር አስታውሳለሁ። ሰኔ 30 ጠብቀኝ ! የሚል ዛቻ ታዲያ በእኛ ትምህርት ቤት፣ በእኛ ሰፈር ብቻ የነበረ አይደለም። ሁሉም ቦታ ተመሳሳይ ነው። በወቅቱ በተጣላንበት ጊዜ ብንደባደብ አንደኛ ዝግጅት ስለሌለን ልንጎዳዳ እንችላለን፤ ስለዚህ አቅማችንን አጠንክረን የመቧቀሻ ቁሳችንን አዘጋጅተን ያኔ ይሻላል በሚል ይመስለኛል። ከዚህም ባለፈ ዕድል ቀንቶት ያሸነፈ በሌላ ዙር እንዳይሸነፍ ለሁለት ወራት አካባቢ ትምህርት ቤቶች ዝግ መሆናቸውም ታስቦ ይመስላል።
ግን ደግሞ ይሄ ብቻ አይመስለኝም የፈሪ ቀጠሮም በውስጠ ሚስጥር አለ። ልብ ያለው ተማሪ እኮ ከትምህርት ቤት ከተለቀቅን በኋላ መንገድ ላይ ጠብቆ ይጣላል፤ ይደባደባል። ያኔ ተማሪ ብዙም ህብረት አይፈጠርም። ዳር ሆኖ ወይ ከቦ ይዋጣላቸው! ፣ ይዋጣላቸው!… እያለ የድራማው ተመልካች ይሆናል። አንዳንዱ ጸብ ያለሽ በዳቦ ዙሪያውን እየዞረ በለው፣ አስገባለት፣ በቦክስ ፣በቴስታ …. ብቻ ምን አለፋችሁ ጸቡን ያራግባል። ትርፉ ምን እንደሆነ ባይታወቅም። አንድ መንገደኛ ጣልቃ ገብቶ ካልገላገለ በስተቀር እሽት እንደ ገብስ ወይ አናት አናቱን እንደ አውራ ዶሮ ይሆናል። የደማም ይደማል። የተቦጫጨረውም እንደዚያ ነው። ፊት ነጥቶ አይን ደም ለብሶ፣ ልብስ በአቧራ ተለውሶ ድብድቡ ይቋጫል። የተሸነፈው ያው እንደለመደው ሰኔ 30 እንገናኝ ብሎ ይሸኛል።
አንዳንዱ ደግሞ ለመደባደብ የሚያበቃ ምክንያት ቢኖረውም ምን አልባት ከተማሪ ጋር ብጣላ ከትምህርት ቤት ልባረር እችላለሁ፣ ይህን አደረገ የሚለውን ወላጆቼ ቢሰሙ ይደበድቡኛል። ሌላም ሌላም… ምክንያት አስቦና ደርድሮ ለድብድብ ቀነ ቀጠሮ ይቆርጣል።
ምላስ እንጂ ልብ የሌለውም ጉልበትና ብዛት ያለው ቡድን ለማሰባሰብ ሲል ያችኑ የሰነፍ ተማሪዎች የመደባደቢያ ጊዜን ይጠባበቃል። ምክንያቱም እንዳይደባደብ አቅም የለውማ። ደግሞ ነገረኛነቱ ከተማሪ ጋር አያስማማውምና በትርኪ ምርኪው ይጋጫል፤ ይጣላል። የስነ ምግባር ችግሩም ሰፊ ነውና ይሰዳደባል። እንዳይተወው አመል እንዳይቀጥል ልብና አቅም የለውምና በቃ ሁሌም ሰኔ 30 እንገናኝ ይሆናል።
የሀገራችን ፖለቲከኞችም ይሄው ክፉ አመል ተጣብቷቸዋል መሰል ሰኔ ባይሉ መስከረም 30 እንገናኝ ማለቱን ቀጥለዋል። ልክ እንደ ትምህርት ቤት ጨቅላ አእምሮ እንዳላቸው ልጆች። ተማሪዎች ሰኔ 30 ሰርተፍኬት ከወሰዱ በኋላ ተደባድበው በሁለት ወራት ውስጥ ሁሉን ትተው መስከረም በአንድ የእውቀት ገበታ ላይ ይገናኛሉ። ቂም በቀልን እርግፍ አድርገው። ደግሞ የመብሰላቸው ምልክትም ነው መስከረም የሚጀምሩት አዲሱ ተከታዩ ክፍል እናም የተሻለ ለመሆን ይጥራሉ። ደግሞም ይሆናሉ። ከተማሪዎች ያነሰ ብስለት የተላበሱት አንዳንድ ፖለቲከኞቻችን ታዲያ ይገርሙኛል። ሀገርና ህዝብ ለማመስ ቀነ ቀጠሮ መስከረም 30 ሲሉ። ጥያቄዬ ግን ቀኑ ለእነሱ መጨረሻ ወይስ መጫረሻ? የሚል ይሆናል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2012
አልማዝ አያሌው