ወይዘሮ ታሪኬ ክፍሌ፣ የአምቦ ከተማ ነዋሪና በግል ሥራ የሚተዳደሩ እናት ናቸው። አንድ ሰው የተወለደበትን፣ ያደገበትንና የሚኖርበትን አካባቢ ችግር በወጉ ስለሚገነዘብ ቢያንስ የዛን አካባቢ ችግር ለመፍታት የራሱን ጥረት ሊያደርግ፤ ችግሩን በመፍታት ሂደትም የሚጠበቅበትን ሊያበረክት ይገባዋል የሚል እምነት አላቸው። እርሳቸውም የአምቦ ከተማ ተወላጅም፣ ነዋሪም እንደመሆናቸው ለ17 ዓመታት በመንግሥት ሥራ ላይ በነበሩበት ወቅት በአምቦ ከተማ የሚታይን ችግር በመፍታት ሂደት በምን መልኩ ይሄን ሃላፊነት መወጣት እንደሚችሉ ሲያስቡ ቆይተዋል። እናም በ2006 ዓ.ም የመንግሥት ሥራ እንዳቆሙና ወደ ግል ሥራቸው እንደገቡ አንድ ሀሳብ መጣላቸው።
ይሄም የእርሳቸውን ሀሳብ ሊያግዙ የሚችሉ ሴቶችን በማሰባሰብ አንድ ማህበር ለመመስረትና በውስጣቸው ሲመላለስ የነበረውን ሀሳብና ምኞት እውን ማድረግ ነበር። እናም በ2007 ዓ.ም አምቦ የፍቅር ማዕድ ማህበርን እውን አደረጉ። የማህበሩ መስራችና ሰብሳቢ ወይዘሮ ታሪኬ እንደሚሉት፤ ማህበሩን በ2007 የመመስረታቸው ዋና ዓላማም ለዓመታት ሊያከናውኑት ሲፈልጉ ነገር ግን ማከናወን ሳይችሉ የቆዩትን በተለያዩ ችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን የማገዝ ህልማቸውን እውን ለማድረግ ሲሉ ነው። እናም የሰፈር ጓደኞቻቸውን፣ አብሮ አደጎቻቸውን እንዲሁም በቀድሞው 12ኛ ክፍል ጨርሰው ያለ ሥራ ቤት ውስጥ ቁጭ ያሉና ሌሎችም በሥራ ላይ ላሉ ሴቶች ሀሳባቸውን በማማከር 16 ሴቶችን ይዘው ማህበሩን እውን ማድረግ ቻሉ።
እንስቶቹም የመጀመሪያ የመገናኛ ምክንያት ያደረጉት ቢያንስ እርስ በእርሳቸው በደስታና በመከፋታቸው ሂደት እየተገናኙ ደስታና መከፋታቸውን እንዲካፈሉ ማስቻል ነበር። ደስታና ሐዘንን መነሻ አድርጎ የተጀመረው ይህ ግንኙነትም በሂደት ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮችን በጋራ ከማሳለፍ አልፎ ሌሎች ማህበራዊ ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎችን ተደራሽ ወደማድረግ እንዲሸጋገር ሆነ። በዚህም ከሚታወቁ የእድርና ማህበር ግንኙነቶች በዘለለ ሌሎች ማህበራዊ መስተጋብሮችን በማድረግ የተሻለ የመደጋገፍና የመተባበር ተግባርን ማከናወን እንደሚቻል ተገንዝበውም በጋራ መራመድ ጀመሩ።
የወይዘሮ ታሪኬን ሀሳብ በዚህ መልኩ የጋራ ሀሳብ አድርጎ እና በየወሩ በመሰባሰብ እየመከረ ወደተግባር የገባው ይህ የእንስቶች ማህበር፤ በማህበሩ ስብስብ እንስቶች ቡና በመጠጣት የማህበሩን የውስጥ ማህበራዊ ቁርኝት በማጠናከር ላይ አተኩሮም ነው ወደ ውጭ መመልከት የቻለው። ለዚህ ደግሞ በየወሩ የቡና ላይ ወግና ምክክር ላይ ከሚነበቡ የመጽሐፍ አንቀጾች በመነሳት የተለያዩ ሀሳቦችን እያነሱ የመወያየት፤ የማህበራዊ ጉዳዮቻቸውን በርዕስነት እያቀረቡም ከንባቡ የተረዱትንና ለህይወታቸው ብሎም ለማህበራዊ ግንኙነታቸው ስለሚሰጣቸው ልምድና ተሞክሮ በመነጋገር ሂደቱ ተጠናከረ። በዚህም ሥራ ያልነበራቸው የማህበሩ አባላት ራሳቸውን በኢኮኖሚ የሚደጉሙበት ዕድልን ከመፍጠር ጀምሮ ኢኮኖሚ ኖሯቸው ደግሞ ደካማ ማህበራዊ መስተጋብር የነበራቸው ቢያንስ ሀሳባቸውን የሚጋራቸውና የሚያማክሩት ሰው እንዲያገኙ ማድረግ ችለዋል።
ምክንያቱም የማህበሩ መመስረት አንዱ መነሻ ሀሳብ ሥራ የሌላቸው ሴቶች የሥራ ዕድል የሚያገኙበት ስለነበር ጉዞው ከማህበሩ አባላት ሊጀምር ይገባዋልና ነው። ይህ ሥራ ታዲያ በሚፈለገው ልክ ውጤታማ ባይሆንም በጅምርነት ያለ፤ ለቀጣይ በትኩረት የሚከወን ስለመሆኑም መስራቿ ያምናሉ። ይህ በራስ የጀመረ መረዳዳትን ማዕከሉ ያደረገ የማህበሩ አባላት ጉዞም ሌሎች እናቶችንና ሴቶችን ወደ መመልከትና መጎብኘት የተሸጋገረ ሲሆን፤ ይህም ሴቶች ኢኮኖሚያዊም ሆነ ሌሎች ማህበራዊ ክፍተቶቻቸውን መሠረት ያደረገ ነበር። ምክንያቱም ሰው ገንዘብ ተቸግሮ የሚራብበት እውነት እንዳለ ሁሉ፤ ሰው ገንዘብ ኖሮት ሰው የሚራብበት ሁነት አለ። በመሆኑም አንድም ኢኮኖሚያዊ ችግር ያለባቸውን መሠረት ባደረገ መልኩ ሲከናወን፤ ሁለተኛም ኢኮኖሚው ኖሯቸው በማህበራዊ ችግር ውስጥ ሆነው ሰው የናፈቃቸውን ቀርቦ የማነጋገርና ችግራቸውን የመካፈል ተግባራቸውን ማከናወን ጀመሩ።
ለዚህ ደግሞ ሰው አውቆ የሚጠይቃቸውን ብቻ ሳይሆን ሰው ሳያውቃቸው በማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ችግር ውስጥ ያሉ አዛውንቶችን በተለይም እናቶችና ሴቶችን ትኩረት ያደረጉ ሲሆን፤ እነዚህም አንድም በሰው ጥቆማ፣ ሁለተኛም በማህበሩ አባላት የማፈላለግ ሂደት የሚያገኟቸው ናቸው። ለምሳሌ፣ ድሃና ጠያቂ ዘመድም ሰውም የሌላትን የወለደች እናት ሄዶ የመጠየቅና ገንፎም አገንፍቶ የማብላት ተግባር አከናውነዋል። ልጆቻቸውን ማልበስ ላልቻሉ ድሃ እናቶች ልብስ ማልበስ ችለዋል። ቀድሞ ሰው ቤታቸውን
ደጋግሞ ይጎበኘው የነበሩ ነገር ግን ሦስት ልጆቻቸውን በሞት ተነጥቀው የወላድ መሃን ሆነው ጠያቂ አጥተው ሰው የተራቡ ወደ 80 ዓመት እድሜ የሆናቸውን እናትን የኢኮኖሚ ችግር ባይኖርባቸውም ሰው ተርበው ነበርና ቡና እያፈሉ አጫውተዋል። በተመሳሳይ ችግር ውስጥ የነበሩ አንድ አባትንም ቀርበው ችግራቸውን ተካፍለዋል።
“እንደ ሴትነቴ ሴት ሴትን እንድትጎዳ ሳይሆን የሴትን ችግር ጠልቃ የምታውቀው ራሷ ሴት እንደመሆኗ እንደ እህትም ሆነ እንደ ጓደኛ ችግሯን ለምታዋያት ሴት መፍትሄ እንድትሰጣት እፈልጋለሁ” የሚሉት ወይዘሮ ታሪኬ፤ እንደ ማህበር ሲንቀሳቀሱም ሴት የሴት መፍትሄ እንጂ ሴት የሴት ጠንቅ እንዳትሆን ካላቸው ፍላጎት አንጻር በማህበሩም ሴቶች እርስ በእርሳቸው እንዲረዳዱና እንዲደጋገፉ፤ አንዳቸው ለአንዳቸው የመፍትሄ መንገድም እህትም መሆንን መሠረት አድርገው እንደሚሠሩ ገልፀዋል። ይህን የሚያደርጉት ደግሞ የሴቶች መጎዳትና መገፋት በወንዶች ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ ህይወት ውስጥ ሴትም ለሴት በብዙ መልኩ እንቅፋት ስትሆን የምትታይ መሆኑን በመገንዘብ እንደሆነም ያስረዳሉ።
ይሄን ታሳቢ በማድረግም እንደ ማህበር ብቻ ሳይሆን አባላቱ በግል ጭምር በየአካባቢያቸው ሴቶችን በሃሳብም ሆነ ባላቸው አቅም ሁሉ የሚያግዙበት ዕድል መፈጠሩንም ይናገራሉ።
እኔም ቀደም ሲል የተጣሉ ባለትዳሮችን ከማስታረቅ ጀምሮ የሚጠበቅብኝን ስወጣ ነበር። በዚህና መሰል መልኩ በገንዘብ የማይተመኑ የሴቶችን የማህበራዊ ኑሮ ዝንፈትና መቃወሶችን ማስተካከል ችያለሁ። በመሆኑም በዚህ መልኩ በገንዘብም፣ በሃሳብም፣ ልንረዳዳባቸው የምንችላቸው የበዙ ጉዳዮች አሉ። እናም ከማህበሩ የጋራ ተግባራት ባለፈ በዚህ አግባብ በአባላቱ በየአካባቢያቸው የሚያከናውኑት ሰፊ ማህበራዊ ህይወትን የማቃናት የመልካምነት ተግባራት አሉ። በመሆኑም ማህበሩ በሴት አባላቱ ለሴቶች የኢኮኖሚም ሆነ የማህበራዊ ችግሮች መቃለል፤ ፍቅር የመስጠትና የማስተማር ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል። ይህ ደግሞ ሴቶች ለሴቶች እንቅፋትን ሳይሆን ፍቅርና ደጋፊነትን ይዘው የሚቀርቡ ስለመሆናቸው የሚያሳይ ነው፤ ሲሉም ነው ወይዘሮ ታሪኬ ስለ ማህበሩና አባላቱ ተግባር ያስረዱት።
“የተወለድንበትን፣ ያደግንበትን እና የምንኖርበትን ችግር እንፍታ” የሚል እሳቤን ይዘው የሚንቀሳቀሱት ወይዘሮ ታሪኬ፤ የዚህ ሃሳባቸው መነሻ ደግሞ እርሳቸው የአምቦ ከተማ ተወላጅም ነዋሪም እንደመሆናቸው አምቦ በልማቱም ሆነ በሰላሙ ያለባት ስምና ገጽታ እንዲለወጥ ካላቸው ፅኑ ፍላጎት የመነጨ ነበር። ምክንያቱም አምቦ ከተማ አንድም ልማቷ በሚፈለገው ልክ አልነበረም፤ ሁለተኛም ስሟ ከረብሻና ሰላም መደፍረስ ጋር ተያይዞ የሚወሳ ነበረ። በመሆኑም ይህ ሃሳባቸው አንደኛ የከተማዋ ልማት እንዲፋጠንና የነዋሪዎቿ በተለይም የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት ካላቸው ብርቱ ፍላጎት የመነጨ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የከተማዋ ሰላምና ፀጥታ ሰፍኖ ነዋሪዎቿ ያለስጋት ወጥተው የሚገቡባትና የጠነከረ ማህበራዊ ቁርኝት ፈጥረው ሰዎች ለሰዎች ደራሽ በተለይም ሴቶች ለሴቶች አለኝታ ሆነው የሚቆሙበት ሁነት እንዲፈጠር ከማሰብ ነው።
በመሆኑም እርሳቸው አምቦ ተወልደው ስለሚኖሩ በዚህ ልክ ስለ አምቦ ከተማና ነዋሪዎቿ ከችግር መውጣትና መለወጥ የሚጓጉትን ያክል፤ ሌሎችም በመላው ኢትዮጵያ ያሉ ሰዎች ስለተወለዱበት፣ ስላደጉበትና ስለሚኖሩበት አካባቢ ችግር
ስለሚያውቁ እነዛ ችግሮች የሚፈቱበትንና ህብረተሰቡ በተለይም ሴቶች በኢኮኖሚም በማህበራዊ መስተጋብርም ራሳቸውን የሚያበቁበት ዕድል እንዲፈጠርላቸው ማድረግ ይችላሉ የሚል እምነት አላቸው። ምክንያቱም ሁሉም ሰው አካባቢውን በዚህ መልኩ አውቆ ቢረዳ፣ የዚህ ድምር ውጤት አገርን መርዳት ስለሆነ፤ ሁሉም አካባቢውን በመርዳት አገርን የመርዳት ህልሙን እውን ማድረግ ይችላል።
እርሳቸውም ማህበሩን መስርተው ወደ ሥራ ሲገቡ በዚሁ እሳቤ ቅኝት ውስጥ በማስገባት ሲሆን፤ የከተማዋ ልምድ ደግሞ ለሌሎች አካባቢና ለአገርም ምሳሌ ሆኖ ማስፋትና መለወጥ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ምክንያቱም ቤት ያለውን ባል በአግባቡ ማገዝ ከተቻለ እና ዛሬ ላይ እምብዛም የሥነ ምግባር ትምህርት የማያገኙ ልጆችን በቤት ውስጥ በወጉ በእውቀትም በሥነ ምግባርም ተኮትኩተው እንዲያድጉ ማድረግ ከተቻለ የዚህ ድምሩ ባሎች ለቤታቸውና ለሚስቶቻቸው ደጋፊ፣ ልጆችም ለቤተሰቦቻቸውና ለአገር አለኝታ እንዲሆኑ ያደርጋል። እናም የቤት ውስጥ እና በአካባቢ ላይ የሚከናወን ሥራ ድምሩ ውጤት የአገር መሆኑን አምኖ ከቤት መጀመር ያስፈልጋል።
ማህበሩ በዚህ መልኩ ሰዎችን የመጠየቅ የበጎነት ተግባሩ ዛሬ ላይ እንደ አገር የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የተጀመረውን ማዕድ የማጋራት ተግባር እያከናወነ ሲሆን፤ ይህ ተግባሩ ግን ዛሬ የጀመረ ሳይሆን ቀደም ሲልም በችግር ውስጥ ያሉና የዕለት ጉርስ ያጡ ወገኖችን የመደገፍና የመመገብ ተግባር ያከናውን እንደነበር ነው የማህበሩ ሰብሳቢ ወይዘሮ ታሪኬ የሚናገሩት። ቀደም ሲል ከምግብ ጀምሮ እስከ አልባሳት በመያዝ ማረሚያ ቤት ካሉ ሴቶች እና በእናቶቻቸው ጥፋት ያለጥፋታቸው ከእናቶቻቸው ጋር በማረሚያ ቤት ካሉ ህፃናት ጋር አዲስ ዓመትን አብሮ የማሳለፍ ተግባር ሲያከናውኑ እንደነበር ጭምር ለአብነት የሚያነሱት ወይዘሮ ታሪኬ፤ በየቤታቸው ያሉ ደጋፊ የሌላቸው ወገኖችንም ሲረዱ መቆየታቸውን ያወሳሉ። ሆኖም ቀደም ሲል በተለያየ ምክንያት የምገባ ሥራውን በሚፈለገው ልክ እንዳይሠሩ እጅ አጥሯቸው መቆየቱን በመጠቆም፤ አሁንም ቢሆን በማዕድ ማጋራት ሂደቱ በሚፈልጉትና ባሰቡት ልክ ተሳታፊ እንዳልሆኑ፣ ባደረጉት ተግባርም የልባቸው እንዳልደረሰ ይገልፃሉ።
የሴቶችንም ሆነ የአካባቢን ጠቅላላ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ተረድቶ ከመፍታት ከዚህ የበጎነት ተሳትፎ ተግባር በተጓዳኝ፤ ሴቶች በብዙ መልኩ የትውልድም የአገርም መሠረት ሆነው ሳለ፣ እናትን መሠረት ያደረጉ ስድቦች በተለይም ፀያፍ ስድቦች መኖራቸውን በመገንዘብ እነዚህ ስድቦች መወገድ አለባቸው በሚል ከእናትነት ስሜት በመነጨ መቆርቆር እየሠሩ ይገኛል። ይሄን በተመለከተ ወይዘሮ ታሪኬ እንደሚያስረዱት፤ እናት ልጆቿን ወልዳ ስታሳድግ ከእርግዝና፣ አምጦ ከመውለድና ከማሳደግ ጀምሮ ፈታኝና እልህ አስጨራሽ ሂደትን አልፋ ነው። ሞቶ የመነሳትን ያክል የሚቆጠር ሂደትም ነው።
እናም በዚህ መልኩ ዋጋ የከፈለች እናት፣ ልጆቿ በጥቅሉ ትውልድ ሊከፍላት የሚገባው መልካም ነገር እንጂ ስድብ ሊሆን አይገባም የሚል ሃሳብና እምነት ነበራቸው። እናት ተከፍሎ የማያልቅ ውለታ ይዛ የምትሰደብበት ሂደት እንደ ግልም ያሳምማቸው ነበር። ማህበሩን ሲያቋቁሙም ሰዎችን በኢኮኖሚም፣ በሃሳብና በፍቅር ከመደገፍ ባለፈ ይሄን መሰል የሴቶችን ጥቃት አስተምሮ መከላከልና ማስቀረት ላይ አተኩሮመሥራትን እንደ አንድ የሥራ ትኩረት ማዕከል በመውሰድም ነበር። ለዚህ ነው የሴቶችን ችግር በቅርበት የሚረዱ ሴቶች የተሰባሰቡበት ማህበር እንዲሆንና በሴቶች የተባበረ አቅም የሴቶችን ችግር ለመፍታት የማህበር ጉዞው በቁጭትና በእልህ የተጀመረው። ይሄን ተግባርም በማስተዋልና በታቀደ መልኩ ማከናወን እንዳለባቸው በማሰብም፤ የከተማውን ማዘጋጃ ቤት በማስፈቀድ በሰልፍ መልኩ መልዕክት የተጻፈባቸው ባነሮችን በመያዝና ስለ እናት ውለታ የሚያወሱ (የእነ ሂሩትን እና የአብተው ከበደን) ሙዚቃዎችን በማሰማት በዕንባ ታጅበው ሥራቸውን አንድ ብለው ወደ መናኻሪያ በመሄድ ነበር የጀመሩት።
የ“እናትን መስደብ ይቁም” ተግባር በዚህ መልኩ መጀመርና ወደ መናኻሪያ አካባቢ አቅንቶ በዚያ ትኩረት ሰጥቶ መልዕክት የማስተላለፍ ምክንያታቸው ደግሞ፤ ብዙውን ጊዜ ልጆችን የሚያበላሹ ስድቦች የሚነሱትና የሚሰራጩት ከመነኻሪያ ውስጥና አካባቢ ነው የሚል እሳቤ ስላላቸው ነው። የመጀመሪያ ሥራ ጉዟቸውን ወደዛው አደረጉ። በጉዟቸውም ሆነ በመነኻሪያ አካባቢና ውስጥ የሚያገኟቸውን ልጆች ልመና በታከለበት መልኩ የመምከርና የማስተማር ተግባርን እያከናወኑም ነበር። መነኻሪያን ጨምሮም በተለያዩ የከተማዋ ማዕከላዊ የሆኑ ቦታዎች ላይ እናትን መስደብ ይቁም የሚል መልዕክት ያላቸው ባነሮችን ሰቀሉ።
ልጆቻቸውንም ሥነ ምግባርን በቤት ውስጥ ከማስጨበጥ በመጀመር፣ ትውልድ ይቀረጽባቸዋል በሚባሉ ትምህርት ቤቶች ላይ በመሄድም በሰልፍ ላይ እናትን መስደብ በሞራልም፣ በፈጣሪም ቅቡል አለመሆኑን እና ነውርና የማይገባ ስለመሆኑ ማስተማር ጀመሩ።
ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ ትውልዱ የግብረ ገብ ትምህርት እጦት ያለበት መሆኑን መገንዘባቸው ሲሆን፤ እናትን ለመስደብ ያበቃውን የግብረ ገብነትና የሥነ ምግባር ችግር ማቃለልና ልጆች እናታቸውን ከመስደብ ይልቅ ሊያከብሩና ሊታዘዟቸው እንደሚገባ እያስተማሩ ይገኛል። ከዚህ ባለፈ እንደ ቀደሙት ዘመን ትውልዶች ለእናት ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ክብር ሰጥቶና ታዝዞ መኖርን፤ ሌሎች ሰዎችንና መምህሮቻቸውን ጭምር እንዲያከብሩ ብሎም አገርን እንዲወዱ ማድረግንም የሥራቸው አንድ አካል አድርገው እየሠሩ ይገኛል።
ይሁን እንጂ እነርሱ እነዚህን ሥራዎች ሲሰሩ በማህበሩ አባላት አቅም እና በጥቂት አካላት ድጋፍ መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ ታሪኬ፤ አባላቱ ተገናኝነው የሚወያዩበት ቢሮ እንኳን ስለሌላቸው የእርሳቸው ሱቅ ውስጥ እየተገናኙ ሥራ የሚከፋፈሉና የቀጣይ ተግባራቸውን የሚነድፉ ስለመሆኑ ያስረዳሉ። ለሥራቸው አጋዥ የሚሆናቸው የስልጠናም ሆነ ቢሮ እና የፋይናንስ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን በመጠቆምም፤ በዚህ ረገድ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ለአባላቱ ሁለት ጊዜ ሥልጠና ስለመስጠቱ ብሎም ቢሮ ለመስጠት ቃል ስለመግባቱ ይገልፃሉ። ከዚህ ባለፈም የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳት ከዓመት በፊት አምቦ ሄደው በነበረበት ወቅት ለሥራችን የሚያግዝ የልብስ ማጠቢያ ማሽን ሊሰጡን ቃል የገቡ ቢሆንም፤ ማሽኑ እነርሱጋ እንዳልደረሰም ይገልፃሉ።
እስካሁን ማህበሩ የሚንቀሳቀሰው አባላቱ በሚያዋጡት 50 ብር ወርሐዊ መዋጮ ቢሆንም፤ አሁን ላይ እሱንም መክፈል ያቃታቸው አሉ። በዚህ ውስጥ ሆኖም ግን ማህበሩ በቀጣይ ሰዎች በተለይም ሴቶችና አዛውንቶች ያለባቸውን የኢኮኖሚ ችግር እንዲሁም የኢኮኖሚ ችግር ሳኖርባቸው የገጠማቸውን ማህበራዊ መስተጋብር ክፍተት ለመሙላትና ለማገዝ በስፋት ለመንቀሳቀስ ትልም አለው። ይህ ትልሙ እውን እንዲሆን ደግሞ በብዙ መልኩ ድጋፍ ያስፈልገዋል። በመሆኑም ከግለሰብ እስከ ተቋም ያሉ አካላት የማህበሩን ራዕይ ተረድተው ሊያግዙትና ህልሙን እንዲያሳካና በየአካባቢው ያሉ መሰል ችግሮች እልባት እንዲያገኙ በማስቻል ሂደት ውስጥ የድርሻቸውን ሊያበረክቱ ይገባል።
ለዚህ ደግሞ ቀርበው ሊያናግሩ እና ሴቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ፣ ጠያቄ ያጡና ሰው የናፈቃቸው ወገኖች ካሉበት ችግር እንዲወጡ፣ ዋጋ ከፍለው ትውልድ የሚተኩ እናቶች ከስድብ ይልቅ ተገቢው ክብር እንዲሰጣቸው የማድረግ ሂደቱን ሊደግፉና በአገርም በትውልድም ግንባታ ሂደት ውስጥ ከማህበሩ ጎን ሆነው የበኩላቸውን ሊያበረክቱ ይገባል። መንግሥትም ቢሆን እናት ክብር ሲገባት የሚሰድቧት አካላት አደብና ሥርዓት እንዲይዙ የሚያስችል ሕግና ሥርዓት ዘርግቶ ሊተገብር ያስፈልጋል። በመሆኑም በጉልበትም፣ በገንዘብም፣ በእውቀትም ሁሉም ባለው አቅም ሁሉ ማህበሩን በመደገፍ የዜግነትም የሰብዓዊነትም ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲሉም ነው ወይዘሮ ታሪኬ የአደራ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት። ከዚህ ባለፈም ለእናት ደራሽ እናት እንደመሆኗም በቅርቡ በማህበሩ ደም ለመለገስ መዘጋጀታቸውን በመግለጽም፤ በዚህ ወቅት ሁሉም ለዚህ ተግባር ሊነሳሳ እንደሚገባም አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2012
ወንድወሰን ሽመልስ