በዘርፈ ብዙ መንፈሳዊ ህይወትና እውቀት የተካኑ ናቸው። ሊቃውንት እኚህን ሰው በተለያየ መንገድ ይገልጿቸዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ የቅኔ መምህራቸው መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ ናቸው። እርሳቸው እንዲህ ይላሉ ‹‹በአውደ ምሕረቱ፣ በቅኔው፣ በማኅሌቱ፣ በዝማሬው ቢጠመዱ ሁሉም ጋር እኩል የሚያገለግሉ ናቸው›› ። ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረትም ‹‹እንኳን በዘመንዎ ተገኝተን አየንዎት። እውቀት፤ ዜማ፣ ስብከት፣ ትጋት ምነው አንድ ሰው ላይ ሰፈራችሁ? ሌላ ሰው ይታዘበናልም አትሉም ?›› በማለት የዕውቀት ባለቤት መሆናቸውን በአደባባይ መስክረውላቸዋል።
አድናቂዎቻቸውም ቢሆኑ እንዲሁ በተለየ መንገድ ነው የሚገልጿቸው። በእርግጥ ብፁዕነታቸው ስያሜውን ባይስማሙበትም ለአብነት ያህል ‹‹የዘመኑ ያሬድ›› እያሉ ይጠሯቸዋል። የዛሬው ‹‹የሕይወት እንዲህ ናት አምድ›› እንግዳችን ብፁዕ አቡነ ናትናኤልን።
ከእንግዳችን ጋር ቆይታ ለማድረግ ብዙ ተፈትነናል። ተሟግተናል። ‹‹እንደ እኔ አይነቱ ምን ሰርቶ ያስተምራል፤ ገና እየሰራሁ እኮ ነው። ምን ሰራሁ ብዬ አደባባይ ወጥቼ ልናገር›› ሲሉ ብዙ ተከራክረውናል። ምክንያታቸው ደግሞ ከእርሳቸው የተሻሉ ብዙ ሰዎች እንዳሉም በማሰብ ሕይወታቸውን ለማጋራት አለመፈለግ ነበር። በስተመጨረሻ ለመሸነፍ ተሸንፈው የህይወት መንገዳቸውን አጋርተውናል። ከመጋቢት 27 ጀምሮ ለወር ያህል በታወጀውና በየቴሌቪዥኑ መስኮት ውስጥ በምናየው የምህላና የጸሎት መርሃ ግብር በመሳተፍ የሰውን ቀልብ በእጅጉ ስበዋል። እኛም ‹‹አባይን በጭልፋ›› ቢሆንም በአባታዊ ምክራቸው ያስተምሩን ዘንድ አቀረብናቸው።
ውዳሴ ማርያምን ለበጎች
አባታቸው ካህን፣ አርሶ አደርና ነጋዴም ነበሩ። ስለዚህ እርሳቸውም ከአባታቸው እግር ሥር በመሆን ሥራ ያግዛሉ። ክህነትን ለመቀበልም ከአባታቸው እግር ስር ሳይርቁ ተከትለዋቸዋል። ብዙ ጊዜም ቤተክርስቲያን ለመሄድ ቀስቃሹ እርሳቸው እንደነበሩ ያነሳሉ። አንዳንድ ጊዜም ቀድመው በቤተክርስቲያን ተገኝተው ደውል የሚደውሉትም አባት እና ልጅ እንደነበሩ ያወሳሉ። ይህ ልምዳቸው ደግሞ በዲቁና ከአባታቸው ጋር በሚመላለሱበት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን እንዲቀድሱ አስችሏቸዋል።
በልጅነታቸው ከቤተሰብ የተለዩት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፤ ከሌላው ሥራ ባሻገር ከብት በማገድም እንዳሳለፉ ይገልጻሉ። ብፁዕነታቸው ከአብሮ አደጎቻቸው ለየት የሚያደርጋቸው የውዳሴ ማርያምን እደላ በበጎቹ ላይ መለማመዳቸው ነው። ለሚያግዷቸዉ በጎች ውዳሴ ማርያምን ያድሉ ነበር። በጎቹም ሲያመነዥኩ እየደገሙ ይመስላቸው ነበርና ዘወትር ያንን ያደርጋሉ። ይህ ደግሞ የሚማሩትን በቀላሉ እንዲያጎለብቱ እንዳደረጋቸው አጫውተውናል።
የእንግዳችን የልጅነት ጨዋታቸው በአብዛኛው መንፈሳዊ ነው። ብዙዎቹን የጨዋታ አይነቶችም መንፈሳዊ መልክ እንዲይዙ ያደርጓቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ቤተሰቦቻቸውንም ሆነ ጎረቤቱን በሚያግዙበትም ወቅት ይህንኑ መንፈሳዊ ነገር እያሰቡ ነው። ምርቃት መልካም ሰው ያደርጋል ብለው በማመንም ያደርጉታል።
ለቤተሰቡ አራተኛ ልጅ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፤ በምዕራብ ሸዋ ጀልዱ ወረዳ ቢቾ ሚካኤል ተብሎ በሚጠራ ስፍራ በ1966 ዓ.ም ነው የተወለዱት። በዚህ ሥፍራ እንደማንኛውም ልጅ ተጫውተው አድገዋል። ከመንፈሳዊ ጨዋታ ባሻገር እግር ኳስ፣ ሩጫ፣ የጭቃ ላይ ሸርተቴና መሰል ጨዋታዎችንም ተጫውተዋል።
ከአካባቢው ልጆች በባህሪያቸው ተጫዋች የሚባሉ አይነት የነበሩት አቡነ ናትናኤል፤ በጨዋታ ውስጥ ሆነው ከማንም ጋር ተጋጭተው አያውቁም። በፍቅር ሁሉን ነገር ማድረግ ያስደስታቸዋል። በዚህ ባህሪያቸው ደግሞ ከጓደኞቻቸው አልፈው በታላላቆቻቸው ሳይቀር እንዲወደዱ ሆነዋል። አባታቸውም ቢሆኑ የወደፊታቸውን አይተው ገና በለጋነት ዕድሜያቸው ይህ ልጅ ይመነኩሳል ብለው ተናግረውም ነበር። ከምንኩስና በኋላም ጳጳሱ እያሉ ይጠሯቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ጳጳስ ከመሆናቸው በፊት አባ ገ/ሕይወት እየተባሉ ይጠሩ የነበሩት እንግዳችን፤ በልጅነታቸው ኳስ ሲጫወቱ የሁለት ቁጥርን የተከላካይነት ስፍራ ይይዙ ነበር። ከዚያ ባሻገር በተለያዩ ስፖርታዊ ትርኢቶች ላይም ተሳትፈዋል። በተለይ የወላጆች ቀን ላይ የሚያቀርቡትን በእሳት ውስጥ የማለፍ የሰርከስ ትርኢት በማስታወስ ይናገራሉ።
ጥሩ ጋላቢ ነኝ አልልም ቢሉም ፈረስም በልጅነታቸው ይጋልቡ እንደነበር የሚናገሩት ባለታሪኩ፤ በአንድ ወቅት ከፈረስ ላይ ወድቀው እግራቸው ወልቆ እንደነበር አይረሱትም። ውልቃቱ የልጅነት በመሆኑ ቶሎ ድኖላቸው እንደነበር ነግረውናል። ዛሬም ድረስ ፈረስ ባዩ ጊዜ የልጅነት ትውስታቸው እንደሚመጣ አጫውተውናል።
በዘጠኝ ዓመታቸው ዲቁናን የተቀበሉት እንግዳችን፤ በልጅነታቸው መሆን የሚፈልጉት አባታቸው አዕምሯቸው ላይ ያስቀመጡትን ምንኩስና ሲሆን፤ ይህንንም አድርገውታል። ከዚያም አልፈው የጵጵስና ማዕረግን ተቀብለዋል። ያስተማሯቸው ቤተሰቦቻቸውን ማለትም እናታቸውንና አባታቸውን ኢየሩሳሌም ወስደው በእርሳቸው እጅ ለምንኩስና ክብር እንዲበቁም አድርገዋል።
መነኩሴው ተማሪ
የቃል ትምህርትን የጀመሩት ከአባታቸው ሲሆን፤ በእርሳቸው እግር ስር ቁጭ ብለው ፊደል፣ ንባብና ግብረ ዲቁናን ተምረዋል። ከዚያም ወንጌልና ዳዊት እያሉ እስከ ዲቁና መቀበል የሚያደርሱ ትምህርቶችን ከመሪጌታ መለሰ ገብረጻድቅ ተማሩ። ዲቁናን ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ከተቀበሉ በኋላ በክህነቱ እያገለገሉ ዜማን ከመሪጌታ ለይኩን ብርሃኑ እየቀጸሉ ዘመናዊ ትምህርትን በአቅራቢያቸው ባለው ቢቾ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል።
የአብነት ትምህርትን መማራቸው ለዘመናዊው ትምህርት እንዳገዛቸው ያጫወቱን ባለታሪኩ፤ በቢቾ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ስድስተኛ ክፍል ሲማሩ ደግሞ በትምህርት የሚፎካከራቸው አንድ ልጅ ብቻ እንደነበር ያስታውሳሉ። በሁሉም ትምህርቶች የተሻለ ውጤት እንደነበራቸውም አውግተውናል።
ሰባትና ስምንተኛ ክፍልን የተከታተሉት ደግሞ ከአካባቢያቸው ትንሽ ራቅ ብለው ጀልዱ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። ዘመናዊውንም ሆነ መንፈሳዊውን በእኩል ደረጃ እየተማሩ የቀጠሉት አቡነ ናትናኤል፤ ዘጠነኛ ክፍልን የሚከታተሉበት ትምህርት ቤት በቅርብ ባለመኖሩ ወደ አዲስ አበባ አምርተዋል።
በአዲስ አበባም ጉለሌ በሚገኘው መድኃኔዓለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው ዘጠነኛ ክፍልን መማር ጀመሩ። ሆኖም እስከመጨረሻው ማጠናቀቅ ግን አልቻሉም። ምክንያቱም በውስጣቸው የነበረው መንፈሳዊ ፍላጎት አይሎ ነበርና ዘመናዊውን ትምህርት ትተው መንፈሳዊውን ትምህርት ለመቅሰም፤ ከዚያ በፊት ቅድሚያ የሚሰጡትን የልጅነት ህልማቸው የሆነውን ምንኩስና በደብረሊባኖስ ገዳም ተቀበሉ። አባ ገብረ ሕይወትም ተባሉ።
ከምንኩስና በኋላ ለተጨማሪ መንፈሳዊ ትምህርት ወደ ዝዋይ አመሩ። ቅዳሴን ከአባ ወልደ ጊዮርጊስ፤ አቋቋምን ከመምህር ሐረገ ወይን፤ ቅኔን ደግሞ ከአንደበተ ርቱዕ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁና ከመምህር አውላቸው በሐመረብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ተማሩ። ደቀመዝሙር የመምህሩን ፈለግ እንደሚከተል አቡነ ናትናኤል ማሳያ መሆናቸውን ብዙዎች ይስማማሉ። ለአብነትም የሚያነሱት በንግግራቸው ከመጋቤ ሐዲስ እሸቱ ጋር መመሳሰላቸውን ነው ። ራሳቸው መጋቢ ሐዲስ እሸቱም ቢሆኑ በተጠመዱበት ቦታ ማረስ የሚችሉ ናቸው ሲሉ መስክረውላቸዋል።
ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፤ ደብረ አባይ በመጓዝም ባህረ ሀሳብንና ቅዳሴን ከመምህር ሀይለስላሴ ተምረው በመምህርነት ተመርቀዋል። በተጨማሪም መንፈሳዊ ትምህርታቸውን እየተማሩ አለማዊውንም ለማስኬድ ወደ አዲስ አበባ በመመለስ አዲስ ከተማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመዘገቡ። ያቋረጡትን ትምህርት ለመቀጠልም ዘጠነኛ ክፍል በመግባት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታተሉ።
አባ ገብረ ህይወት መነኩሴ ናቸው። ግን ከክፍል ጓደኞቻቸው ጋርም ሆነ ከመምህራቸው ጋር ዘመኑ የሚፈልገውን እያደረጉ ነበር ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት። በትምህርታቸውም ጎበዝ በመሆናቸው ብዙዎች ያደንቋቸው ነበር። የሃይማኖት ልዩነትን እንኳን ሳያሳዩ ሁሉንም በእኩል ደረጃ የሚያከብሩ ናቸው።
እንግዳችን ዘመናዊ ትምህርታቸውን ሲቀጥሉ መንፈሳዊ ትምህርቱን በሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ አምስት ዓመት የሐዲሳት ትርጓሜን ተምረው በዲፕሎማ ተመርቀዋል። በኋላም ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ በመግባት አምስት ዓመት ነገረ መለኮት ተምረው በዲግሪ ተመርቀዋል።
አቡነ ናትናኤል በቋንቋ ትምህርትም ቢሆን በተቻላቸው ሁሉ ለመማር የሚሞክሩ ናቸው። ለአብነት ያህል ጀርመን በአስተዳዳሪነት ተመድበው በሄዱበት ጊዜ ጀርመንኛን በሚገባ ተምረው በኮሌጅና ደረጃ ሁለት ሰርተፍኬቶችን በማግኘት የጀርመንኛ ቋንቋ ምሩቅ ናቸው።
የአገራቸውንም ቋንቋ ቢሆን በሚገባ ለማወቅ ይጥራሉ። በዚህም በአፍ መፍቻነት ከሚያውቋቸው አማርኛና ኦሮምኛ በተጨማሪ ትግርኛንም ይሰማሉ። ጉራጊኛም ቢሆን ለመልመድ ሲጣጣሩ እንደነበር አጫውተውናል።
እርሳቸው በሚማሩበት ወቅት መነኩሴ ሆኖ ደብተር ተሸክሞ ረጅም መንገድ ያለ ታክሲ በእግር ተጉዞ መማር ጥንካሬን ይጠይቅ ነበር። በመሆኑም ብርቱ በመሆናቸው ይህንን ማድረግ ችለዋል። እንዳውም በወቅቱ ኮምፒዩውተር ቤትም በመግባት ለስድስት ወር ያህል ሥልጠና እንደወሰዱ ነግረውናል። አሁንም ቢሆን ሁኔታው ቢመቻችላቸው የመማር ፍላጎት እንዳላቸው አውግተውናል።
‹‹በተሰማራሁበት መስክ መማር ያለብኝን ሞካክሬያለሁ። ሆኖም ግን ተማርኩ ብዬ አላስብም። መማር ነበረብኝ የምለው ይልቅብኛል›› የሚሉት ባለታሪኩ፤ መማር ለደመወዝ መሆን የለበትም። መማር ለእውቀት ሊሆን ይገባል። በዓለም ላይ ሁሉንም የሚያውቅና ትምህርትን ያጠናቀቀ እንደሌለ ሁሉ ዛሬም ነገም መማር ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን ነው እውቀትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ የሚሄደው የሚል እምነት አላቸው።
መማር ገንዘብን አስቦ ከሆነ እውቀት የሚባል ነገር አይኖርም። ቀጣይነት ያለው ትምህርትም አይገኝም። ከዚያ ይልቅ ተስፋ አስቆራጭ ነገሮችም ይገጥማሉ ይላሉ። ምክንያቱም የተማረው ቁጭ ብሎ ያልተማረው ጥሩ ተከፋይ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ አለ። ስለዚህ ትምህርት ለእውቀት ካልሆነ በስተቀር ብዙ ነገር ያሳጣል።
በማህበራዊ ድረ ገጽ(ፌስቡክ) ላይ በርካታ ወሬዎች አሉ። አጫጭር መረጃዎችም ይገኛሉ። ሆኖም የሚጨበጥ እውቀት ግን እንደ መፅሐፍት አይሆንምና ለመማር ዕድሉን ያላገኘ ሁሉ መጻሕፍትን በማንበብ መማር አለበትም ይላሉ። እርሳቸውም ቢሆኑ ዛሬም ትምህርት ቤት ገብተው መማር ቢፈልጉም ምቹ ሁኔታ ስላልገጠማቸው ትምህርትን በማንበብ አድርገዋል።
አብደላ እና አቡነ ናትናኤል
አቡነ ናትናኤል መነኩሴ ቢሆኑም አንድ የእስልምና እምነት ተከታይ ጓደኛ ነበራቸው። ይህንን ጓደኛቸውን ያገኙት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበሩበት ጊዜ ትምህርት ቤት ነው። ልጁ አብደላ የሚባል ሲሆን፤ ገንዘብ በምን መልኩ እንደሚያገኝ ባያውቁም ስለሚያምናቸው ያስቀምጡለታል። እርሳቸውንም አምኖና አክብሮ ስለሰጣቸው ይወዱታል። ምክራቸውን ከፈለገም ይለግሱታል። ከዚያም ባለፈ በእምነት አይምጣባቸው እንጂ የሚያስፈልገውን ሁሉ ሊያደርጉለት ወደኋላ አይሉም። እርሱም ቢሆን ከሁሉም ተማሪዎች አብልጦ ይወዳቸዋል፤ ያምናቸዋል፣ ያከብራቸዋልም።
‹‹የልጁ ገንዘብ ማስቀመጫ ሳጥኑ ነበርኩ። ለዚህ ያበቃው ደግሞ የእኔ አቅራቦት ነው። መነኩሴ መሆኔም ቢሆን ትልቅ ክብር እንዲሰጠኝ አድርጎታል ብዬ አስባለሁ። ስለዚህም ኢትዮጵያዊነት አንድ መሆን ነውና በሃይማኖት ዶክትሪናችን ብንለያይም መዋደዳችን ግን ከልባችን ነበር›› ይላሉ ከሌሎች ጋር በትምህርት ህይወታቸው ጭምር እንዴት እንዳሳለፉ ሲያነሱ።
ከዲቁና እስከ ጵጵስና
የአቡነ ናትናኤል የሥራ ጅማሮ በዲቁና ነው። ሥራቸውን አሃዱ ያሉት በ15 ብር ደመወዝ በጀልዱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን መሆኑን አጫውተውናል። ቀጣዩ የሥራ ቦታቸው ደግሞ ዝዋይ ገዳም ውስጥ ሲሆን፤ ከትምህርት ባሻገር በቄሰ ገበዝነትም ማገልገላቸውን ያስታውሳሉ። ከዚያም በዝዋይ ደሴቶች ላይ ባሉ አብያተ ክርስቲያናትም እየተዘዋወሩ በአስተዳዳሪነት ሰርተዋል።
በአዲስ አበባም ሰሚት መድኃኔዓለም፤ ደብረ ምጥማቅና ቅዱስ ፊልጶስ፣ ብ/ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ፤ አየር ጤና ኪዳነ ምሕረት፣ አስኮ ቅዱስ ገብርኤልና በመሳሰሉት አድባራት ላይ በአስተዳዳሪነት ያገለገሉት ብፁዕነታቸው በአስተዳዳሪነታቸውም ወቅት በሕዝቡ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ እንደነበሩ ብዙዎች ይመሰክራሉ።
በሥራ ምክንያት ወደ ጀርመን አቅንተው፤ የጀርመን ሙኒክ ደብረ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያንን ለስድስት ዓመታት በአስተዳዳሪነት አገልግለዋል። ብዙዎችንም የአብነት ትምህርት አስተምረው ለዲቁናና ቅስና ማዕረግ አብቅተዋል። ብፁዕነታቸው በጀርመን በሚያስተዳድሩበት ቤተክርስቲያን ዳግመኛ አባታቸውም በእንግድነት ሄደው አብረው በመሆን ቀድሰው ቡራኬ ተቀባብለው የነበሩበትን ሁኔታ መቼም አይረሱትም። በተለይ በወቅቱ የነበሩት ምዕመናን አድናቆታቸውንና ደስታቸውን ሲገልጹ ሲያዩም ይገረሙ እንደነበርም ያስታውሳሉ።
በአውሮፓ ሃገረስብከት የልማት መምሪያ ኃላፊ ሆነውም እንደሰሩ የሚያነሱት አቡነ ናትናኤል፤ ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላም መንፈሳዊ አገልግሎቱን አጠናክረው ቀጥለዋል። በዚህም የቄለም ወለጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ለሁለት ዓመታት ከሰሩ በኋላ አሁን ደግሞ እየሰሩ ወዳሉበት የምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮጉዱሩ ወለጋና የምዕራብ ሸዋ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ ሆነው ተመድበዋል።
ዲቁናን ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የሸዋ ሊቀጳጳስ፣ ምንኩስናን ከብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ ቅስናን ከብፁዕ አቡነ ቶማስ፣ ቁምስናን ደግሞ ከብፁዕ አቡነ ገብርኤል እና ጵጵስናን ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የተቀበሉት እንግዳችን፤ የተዋጣላቸው የሃይማኖት አባት፣ መምህር፣ ቀዳሽና፣ ማህሌታዊም ናቸው።
ሁሉ ምክንያት አለው
‹‹የኮሮና መከሰት እጅ ባለመታጠብ የመጣ አይደለም። እጃቸውን እየታጠቡ የተከሰተ ነው። ሀጢአታችንን መቀበል ሲያቅተንና እግዚአብሔር የለም ማለት ስንጀምር መኖሩን ሊያሳየን በምክንያት በተለያዩ በሽታዎች ይቆነጥጠናል። ከስህተታችንም እንታረም ዘንድ የት ድረስ መጓዝ እንደምንችል አሳየን›› የሚሉት እንግዳችን፤ አባት ልጁ ሲያጠፋ እንደሚያደርገው ሁሉ እግዚአብሔርም ከሀጢያታችን እንመለስ ዘንድ በምክንያት ይህንን አድርጓል። ጠራርጎ ሊያጠፋን አለመሆኑን ለማሳየትም መከላከያውን አሳይቶናል። ስለዚህ እኛም ምክንያታዊ ሆነን መለስ ልንል ይገባል ይላሉ።
ዓለም ላይ በሰውም ሆነ በሰይጣን የፈጠራ ጥበብ ብዙ ክፉ ተግባራት ተከናውነዋል። በሀገራችንም ቢሆን ብዙ ዘግናኝ ነገሮች ተከስተዋል። ብዙ አንደበቶች ሕዝብን ከሕዝብ ለያይተዋል፤ ብዙ እጆች የሰው ደም አፍስሰዋል፤ በዚያው ልክ በብዕራቸው ጽፈው በቋንቋና በዘር መከፋፈሉም ሰፍቶ ነበር። ግን በምክንያት ይህ መለያየታችን ይገታ ዘንድ ወሬያችን ሁሉ ኮሮና እንዲሆን እግዚአብሔር አደረገ። እናም በኮሮና ጉዳይ አንድ እንደሆንን ቀጣዩ ሕይወታችንንም በዚሁ አንድነት ልንቋጨው ይገባል ምክራቸው ነው።
እምነት ፣ አንድነትና ብሔር
የራሱን የማይፈልግ ማንም አይኖርም። በዚህም ሁሉም የሚመስለውንና የራሴ የሚለውን ፈልጎ ቢያገባ ስህተት አይሆንም። ስህተቱ የሚመነጨው የሌሎችን መጥላትና ማጥላላት ሲጀመር ነው፤ ብሔር የሚለው አተያይ መስተካከል ይኖርበታል። ኢትዮጵያዊነት መገለጥ አለበት። እስካሁን አንድ አድርጎ ያኖረን ኢትዮጵያዊነታችን ነው። ታሪክና ገድላት የሚነግሩንም በአንድነት እንዴት እንዳሸነፍን ነው። እናም ለነገ አገር ተረካቢው መንገር የተዛባውን ሳይሆን አንድ የሚያደርገውን መሆን አለበት።
የሃይማኖተኛ ሰው ተግባሩ መልካምና አገር ወዳድ ዜጋን መፍጠር ነው። ሃይማኖተኛ ሰው ሀገሩንም ከራሱ አስበልጦ ይወዳል። ለዚህም የኢትዮጵያዊው አቡነ ጵጥሮስን ሰማዕትነትና ተምሳሌትነት ማስታወስ በቂ ነው። ከብሔር ጠባብነት ወጥተን ሃይማኖተኛነታችንን በአንድነትና ለሌሎች አርኣያ በመሆን ማሳየት አለብን ሲሉም ይመክራሉ።
ሰዎች ራዕይ ያላቸው መሆንም ይጠበቅባቸዋል። አይቻልም የሚል ነገር ማሰብ አያስፈልግም። ለጊዜው ገንዘብ በማጣት ድሃ ቢሆንም ሞራል የሌለው መሆን ግን የለበትም። ይልቁንም የአዕምሮ ባለጸጋ መሆኑን በሥራና በመልካም ምግባር ማሳየት ይኖርበታል። ለውጦችም በሰላም መምጣት እንደሚችሉ አስተማሪም መሆን ይገባል። ለዚህ ደግሞ አንድነት ወሳኝ ነገር ነውና የሀይማኖት አባቶችም ሆኑ ትምህርት ቤቶችና የሚመለከታቸው ሁሉ ይህንን ሊያስተምሩ ይገባል ይላሉ።
የምንደርስበትን ደረጃና የምንሆነውን ነገር የሚያውቀው እግዚአብሔር ነው። እኛ ግን የድርሻችንን ማድረግ ግዴታችን ነው። ሰው መስራት በሚቻለው ሁሉ መልካምን ማድረግ ይገባዋል። ይህ ከዚህ ይበልጣል፤ ይህ ከዚህ ያንሳል ማለትም አይገባም። ሁሉም የስላሴ ፍጥረት በእኩል ደረጃ ክብር ሊሰጠው ይገባል። በተለይ እንደ ኢትዮጵያውያን አማኞች ይህ ግዴታችን መሆኑን ማወቅም ያስፈልጋል በማለትም ተግሳፃቸውን ያስቀምጣሉ።
‹‹በማንኛውም ነገር መልካም መሆንን ተመኝ፤ የልብህን መሻት የሚያውቀው አምላክ ምላሹን ይሰጥሃል›› የሚሉት አቡነ ናትናኤል፤ በሀገር ሆኖ አንድ አለመሆንና የራስን ስራ መፍጠር አለመቻሉ በጣም እንደሚያስገርማቸው ይናገራሉ። በሰው ሀገር የምንደክመውን ያህል በአገራችን መከወን አለመቻላችንም ይቆጨኛል ባይ ናቸው።
የሰው ሀገር ሲኮን አገራችን ከአየሩ ጀምሮ ይናፍቃል። በአገራችን ስንሆን ግን በረባው ባልረባው እንጋጫለን። ስለዚህም ልብ ልንል የሚገባንና በቅጡ መተግበር ያለብን አማኞች፣ አንድነት ፈላጊዎችና አገር ወዳዶች መሆናችንን ማጎልበት ላይ ነው ሲሉ ይመክራሉ።
ገጠመኝ
በሕይወታቸው ብዙ ገጠመኞች አሏቸው። ከሁሉም ግን በልጅነታቸው የሆነውን ዛሬ ድረስ ሲያስታውሱት ያስገርማቸዋል። ምክንያቱም ቀድመን በአዕምሯችን ውስጥ የምንስለው ነገር ማንነታችንንና አቅጣጫችንን ያስታል ብለው ስለሚያስቡ ነው።
እናም ለሰዎች ትምህርት ከሰጠ ብለው የልጅነት ገጠመኛቸውን ቃል በቃል እንዲህ አውግተውናል ‹‹በቅዳሴ የማገለግልበት ቦታ ከቤታችን ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ ያስኬዳል። እናም አነሳሴ ከወትሮው ያለሰዓት በሌሊት ነበር። ለዚህ ያበቃኝ ደግሞ በተበሳው የቆርቆሮ ጣሪያችን ውስጥ የጨረቃ ብርሃን በመግባቱ ወገግታው የነጋ መስሎኝ ፈጥኜ ተነሳሁ። ጉዞዬን ስቀጥል ግን የጨረቃ ብርሃን ቢኖርም ገና ከሌሊቱ ወደ ሰባት ሰዓት ስለሆነ ምንም የወፍ ድምጽ እንኳን አይሰማምና በጣም ያስፈራ ነበር። እናም በፍራቻ መጓዜን ቀጠልኩ። ማዶ ላይ ስብስብ ብለው ጅቦች ይታያሉ። ዛሬ ተበላሁ አልኩ።
ሌላ ማቋረጫ ባለመኖሩ በትሬን አስተካክዬ ወደኋላ መመለሴን ትቼ ጉዞዬን ቀጠልኩ›› የሚሉት እንግዳችን፤ ይበልጥ እየተጠጉ ሲሄዱ ጅቦች መሀል በመግባታቸው መደናገጣቸውን ይናገራሉ። በጣም ሲጠጉ ደግሞ መሀላቸው ሊገቡ ሊበሉም ነውና ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንኳን ግራ ተጋብተው እንደነበር አይረሱትም። ሆኖም ብበላም ልበላ ብለው ቆርጠው በመሄድ ልክ አጠገቡ ሲደርሱ ግን ያዩት ነገር ጅቦችን ሳይሆን የዛፍ ጉቶዎችን ነው። ቢሆንም ግን አላመኑም ነበርና እግሬ አውጪኝ ብለው ከ30 ደቂቃ በላይ የሚወስደውን ተራራ በአንድ ትንፋሽ እንደወጡት አጫውተውናል። እናም በራሳችን ላይ እንዲህ የማይኖር ነገር መሳል ካረጋገጥንም በኋላ ቢሆን ፍራቻን ይፈጥርብናልና ሁኔታዎችን በደንብ ማጤንና መንቀሳቀስ እንዲሁም ዓላማን ለማሳካት ወደ ኋላ ማለት እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ።
አባታዊ ምክር
ሞት በሰው ያለመታዘዝ የመጣ ነው የሚሉት እንግዳችን፤ እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥረው ዘላለማዊ ህይወት እንዲኖረው አድርጎ ነው። ሆኖም ሰው ግን አትብላ የተባለውን ህግ ባለማክበሩና ባለመታዘዙ የተነሳ በመንፈስም ሆነ በስጋ ተስፋውን አጨለመ። ሞት እንዲመጣም ፈቀደ። ሞት ካለ ደግሞ ህመም ይኖራልና ይህም ህመም የመጣው ክፋታችን በማየሉ ምክንያት ነው።
ባለመታዘዝና ህግን ባለማክበር የተነሳ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተነገረው ብዙዎች ተቀጥተዋል። በእሳት የጋዩ የሰዶምና ገሞራን ከተሞች እንዲሁም የተነገራቸውን የሰሙት የኖህ ቤተሰቦች ብቻ ሲቀሩ ዓለም በንፍር ውኃ እንደጠፋ ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። የፈርኦን ሰራዊትን ብንወስድም እንዲሁ የእግዚአብሔርን ቃል ባለማክበራቸው የበኩር ልጆቻቸውን በሞት ከማጣት ባሻገር እነሱም በባህር ውስጥ ሰጥመው ቀርተዋል። ዛሬም ቢሆን የጥፋታችን ልክ እየበዛ በመምጣቱ በተለያየ መንገድ አምላክ እያስተማረን ነው። ስለዚህም መመለስ ያስፈልጋል።
የነነዌ ሰዎች በዮናስ ምክር አማካኝነት ከጥፋታቸው ተመልሰው ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ማቅ ለብሰው ድንጋይ ተንተርሰው በመጾማቸውና በመጸለያቸው ሀገራቸው ላይ ከመጣባቸው መከራ ድነዋል። ስለዚህ እኛም ዛሬ የሚያስፈልገን ከጾምና ጸሎቱ ጋር የታዘዝነውን እሺ ብለን መተግበር ነው ይላሉ። በእሽታ መንፈስ ተቃኝተን የአባቶች ምክርን፤ የጤና ባለሙያዎችና በመንግስት የሚወጡ ህጎችን ማክበርም ይገባናል።በደም የተጨማለቀውን እጃችንንም በንሥሐ ልናነጻው ያስፈልጋል።በብሔር የተከፋፈልንበትንና የተጠላላንበትን መንገድ ዘግተን በአንድነት አምላክን ይቅር በለን ማለት አለብን።
የኮሮና ቫይረስ መምጣቱ ትዕዛዝን ለማክበር እንደሆነ የሚያነሱት አቡነ ናትናኤል፤ መፍትሄው እሺ ማለትና ህግን ማክበር በመሆኑ ይህንን ማድረግ እንደሚገባ ያስረዳሉ። ህመም ሲመጣ አንድም ሊያስተምር፤ አንድም ለቅጣትና ለሞት ሊሆን ይችላል። ስለዚህም ህመሙ ለሞት እንዳይሆንብን በተለይ ኢትዮጵያውያን አማኞች በመሆናችን ሀጢአታችንን አምነን ከልባችን በመመለስ ይቅር ልንባባል ይገባል ይላሉ።
በሰው አገር ላይ የሆነው እልቂት እኛጋ በስፋት ያለመሆኑ ምስጢር ከሌሎቹ እንድንማር እድል ሊሰጠን ስለፈለገ ነው። ስለሆነም ከራስ ስህተት ሳይሆን ከሰዎች መማርን እንልመድ። ሃይማኖተኛ ሰው ስርዓትን ያከብራል፤ የታዘዘውንም ይሰማል፤ ጥንቁቅም ነውና ይህንን እድል የሰጠንን አምላክ እያመሰገንን መታዘዝን እንልመድ ይላሉ።
ሀገረ እግዚአብሔርነቷ እንደተጠበቀ ነውና መመለስን ገንዘብ አድርገን በእሽታ በሽታውን ድል እናድርግ የሚሉት እንግዳችን፤ ይህ ጊዜ ዓለም በሙሉ በአንድነት በአንድ ጉዳይ ላይ ያወራበት ነው። ይህ ሁሉ የሆነው ህዝቡ አይሙት፤ ራሱን ይጠብቅ ለማለት ተፈልጎ ነውና ማንም እንዳይሞት ህግን ለማክበር እሺ ማለት ያስፈልጋል። ለህዝቡ ደህንነት የሚጮኸውን ጩኸት አድምጦ ወደ ተግባር መቀየር ይገባል ብለዋል።
እንደ ቤተክርስቲያን ምዕመኑ የለመደውን ተግባር በአንድነት እንዳይተገብር የሆነው ህዝቡንም ሆነ ሊቃውንቱን በአንድነት ላለማጣት ነው። ነገ ቤተክርስቲያንንም የሚያገለግል እንዳይጠፋ ታስቦ ነው። በአጭር ጊዜ የሚጠፋውን በጊዜው ለመቅጨትም ነው። እናም ይህንን አስቦ የታዘዙትን ለመተግበር ‹‹እሺ ማለት ከሞት ይታደጋል›› የመጨረሻ መልዕክታቸው ነው።
ጽጌረዳ ጫንያለው