ወጣት ደሳለኝ ይመስላል እና ጓደኞቹ አራት ኪሎ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት ባለች አንዲት ነጭ ድንኳን አካባቢ አዘውትረው ይገኛሉ። በድንኳኗ ፊት ለፊትና ከአስፓልት ማዶ ባሉ የእግረኞች መተላለፊያ መንገዶች የሚዘዋወሩ መንገደኞችን የማግባባት ስራ ደግሞ የዘወትር ተግባራቸው አድርገዋል። እነዚህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በዚህ ቦታ የመገኘታቸውን ምክንያት ሲያስረዱ፣ ነጯ ድንኳን የበጎነት ሁሉ አውራ የሆነው፤ ያውም በደም ዋጋ የሰው ህይወትን ከሞት የመታደግ የሰው ልጅ ታላቅ መልካምነት የሚገለጽበት የደም ልገሳ የሚከናወንባት በመሆኗ ነው።
ወጣት ደሳለኝ እንደሚያስረዳው፤ በዚህ ቦታ የሚከናወነው የደም ልገሳ እንቅስቃሴው አሁን ላይ መልካም ቢሆንም የኮሮና ወረርሽኝ እንደተከሰተ በእጅጉ ተቀዛቅዞ ነበር። እነርሱም እንደ በጎ ፈቃደኛ ወጣት በዚህ ቦታ ተገኝተው ሰዎች ደም በመለገስ ወገንን ከመታደግ አኳያ ያለውን ፋይዳ በማስረዳት፣ ደም መለገስ ለወላድ እናቶች፣ በአደጋ ለተጎዱ ወገኖች፣ በችግር ላይ ያሉ የእኛው ቤተሰብና ወገኖችን ከሞት መታደግ መሆኑን በማስረዳት፣ ደም እንዲለግሱ የማግባባትና የማሳመን ተግባር በማከናወን እንዲለግሱ ያደርጋሉ። ከዚህ አኳያ አራት ኪሎ አካባቢ ያለው የደም ልገሳ ሂደት ጥሩ የሚባል ነው።
“እኔ ለመጀመርያ ጊዜ ደም የለገስኩት ከክልል ወደ አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ ነው። ይህን ያደረኩት ደግሞ እኔ ሐኪም ሆኜ ሰው ማዳን ባልችልም እኔ የምሰጠው ደም ህይወትን መታደግ እንደሚችል በተገነዘብኩበት ወቅት ነው፤” የሚለው ወጣት ደሳለኝ፤ ለዚህ ደግሞ ከራሴ አልፌ ሌሎች ጓደኞቼም እንዲለግሱ የማስገንዘብ ተግባር እያከናወንኩም፤ እንዲለግሱ እያደረኩም እገኛለሁ ሲል ያስረዳል። ይህ ደግሞ ከምንም በላይ እርካታን የሚሰጥ ሲሆን፤ ህብረተሰቡም ይሄን ተገንዝቦ ደም ሊለግስ እንደሚገባ በመጠቆምም፤ ደም መለገስ በፍላጎት እንጂ በግፊት የሚከናወን አለመሆኑንም ይገልጻል። አሁን ያለው ሁኔታም በህብረተሰቡ ላይ ስጋት ያሳደረ ቢሆንም ከኮሮና የባሰ ወገንን ችግር ላይ የጣለና አደጋው የከፋ የመጠባበቂያ ደም ችግር መኖሩን በመገንዘብ፤ ህብረተሰቡ ኮሮናን እየተከላከለ በደም ችግር የሚሞት ወገኑን ለመታደግ ደም የመለገስ ተግባሩን አጠናክሮ ሊቀጥል መልዕክት አስተላልፏል።
የወጣት ደሳለኝን እና ጓደኞቹን ውትወታ የታከለበት የማግባባት ስራም ሆነ በራስ ተነሳሽነት በዚህ ስፍራ ደም ሲለግሱ ካገኘናቸው ሰዎች መካከል የአራት ኪሎ ነዋሪው አቶ ዮሐንስ አጥናፉ እንደሚሉት፤ ቀደም ሲል ብዙ ደም የሚለግስ ሰው ነበረ። እርሳቸውም ቀይ መስቀል በመሄድ ደም ይለግሱ ነበር። አሁን ላይ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ ግን ደም ለጋሾች በመቀነሳቸው የደም እጥረት መኖሩን ስለሰሙ በአካባቢው ሲያልፉ ደም እንዲለግሱ በመጠየቃቸው ጥያቄውን በደስታ ተቀብለው ነው የለገሱት።
እንደ አቶ ዩሐንስ አባባል፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ በዚህ ደረጃ ሰው ደም ለመስጠት የፈራው አንዱ ምክንያት ንክኪውን ፍራቻ ነው። ምክንያቱም እንደሚባለውም ቫይረሱን ከመከላከል አኳያ ጠረጴዛ፣ ወንበር፣ ብረት፣ ወዘተ ቁሳቁሶችን ጭምር ከንክኪ ማራቅ እንደሚገባ ነው የሚነገረው። እኔም በዚህ ስፍራ የምመላለስ ብሆንም የቫይረሱ መከሰትን ተከትሎ የማልሰጥበት ዋና ምክንያቴ ይሄንኑ ንክኪ በመፍራት ነው። ይህ ንክኪን የመራቅ ፍላጎቱ ደግሞ አሁን ሰው ፍርሃት ላይ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ደም ከሚለገስባቸው ስፍራዎች ያራቀው ሲሆን፤ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ አይደለም ደም ወደመለገስ ሲታመም እንኳን ወደ ክሊኒክ መሄድ እየተወ ይገኛል። ነገር ግን ደም ሲለግሱ የተመለከቱትና የታዘቡት ነገር እና ቀደም ብለው በግምት የፈሩት ጉዳይ የተለያዩ ሆነው አግኝተውታል። ምክንያቱም ደም ተቀባዮች ስራቸውን በጥንቃቄና በንጽህና የሚያከናውኑ በመሆናቸው የነበረባቸውን ስጋት ቀንሶላቸዋል። በመሆኑም ይሄው ጥንቃቄ ያለመዘናጋት ሊቀጥል ይገባዋል።
እኔ በአካባቢው የምመላለስ እንደመሆኔ የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ ብዙም ደም የሚሰጥ አልመለከትም ነበር የሚሉት አቶ ዮሐንስ፤ አሁን ላይ እንደርሳቸው ሁሉ ሌላውም ሰው እየተገነዘበ በመምጣቱ የለጋሾች ቁጥር እየጨመረና ደም
ለመስጠትም ወረፋ እስከመያዝ መደረሱን ይገልጻሉ። ይህ ደግሞ ህዝቡ የተፈጠረበት ስጋትና ፍርሃት እንጂ ደም ለመስጠት ወደኋላ የማይል መሆኑን አመላካች መሆኑን በመጥቀስም፤ ደም መለገስ ደግሞ በርካታ በደም ችግር ህይወታቸው የሚያልፍ ወገኖችን መታደግ ብቻ ሳይሆን ለራስ መስጠት መሆኑን ይናገራሉ።
አቶ ዮሐንስ ስለ ደም ልገሳና ጠቀሜታው በራሳቸው አንደበት ሲያስረዱ እንዲህ በማለት ነበር። “እኔ እኔ ብቻ ሳይሆን እናቴ ትታመማለች፤ ሚስቴም ትታመማለች፤ ብዙ ጊዜም በወሊድ ምክንያት ደም የሚያጥራቸው እናቶች አሉ። በዚሁ ልክ ደግሞ በኢትዮጵያ ብዙ የመኪና አደጋ አለ። እኔም ብሆን ዛሬ ምን ሆኜ ልገባና ደም ሊያስፈልገኝ እንደሚችል አላውቅም። እናም ደም መለገስ ማለት ለእነዚህ ሁሉ ወገኖች መድረስ፤ ህይወታቸውን መታደግ ብቻ ሳይሆን ለራስ መስጠት መሆኑን መገንዘብ ይገባል”።
ለምሳሌ፣ አንድ ሰው አንድን ሰው በደም ምክንያት ህይወቱ ልታልፍ ሆኖ ደም ባንክ ባለ ደም ምክንያት ህይወቱ መትረፉን ሲሰማ ደስ ይለዋል። ይሁን እንጂ አንድ ደም ለለገሰ ሰው እና ደም ላልለገሰ ሰው ይህ ዜና እኩል የደስታ ስሜት አይፈጥርለትም። ምክንያቱም ደም የለገሰው ሰው ያሰው በእርሱ ደም ህይወቱ የተረፈች መስሎ ስለሚሰማው በሰውየውም መዳን ብቻ ሳይሆን በራሱ ተግባርም ደስታም ኩራትም ይሰማዋል። በአንጻሩ ደም ያልለገሰው ሰው በሰውየውም መዳን ቢደሰትም ለእርሱ መዳን የእርሱ አሻራ እንደሌለበት ስለሚሰማውና ምናልባትም ደም ባይኖር ያ ሰው ህይወቱ ሊያልፍ እንደሚችል ሲገነዘብ የቁጭትና የጸጸት ስሜት ይፈጥርበታል።
በተመሳሳይ አንድ ሰው ለራሱም ሆነ ለቤተሰቦቹ ደም የሚያስፈልገውና ለጊዜው ደም የሚለግስ ጠፍቶ ከሆስፒታል ደም ሲጠይቅ ቀድሞ ደም የሰጠና ደም ሰጥቶ የማያውቅ ሰው እኩል የመጠየቅ ሞራሉም ስሜቱም የላቸውም። ምክንያቱም ደም የለገሰው በባንክ አካውንቱ ያለውን ብር ጠይቆ እንደመውሰድ ሲቀለውና ነጻነት ሲሰማው፤ ደም ለግሶ የማያውቅ ሰው ግን ይህ ነጻነትና ሞራሉ አይኖረውም። እናም ደም መለገስ የወገንን ህይወት ከመታደግ ባለፈ ለራስ ማስቀመጥ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል። በመሆኑም አሁን ባለው ሁኔታ የኮሮና ወረርሽኝን ስጋት ደም ባለመለገስ የበርካታ ወገኖችን ህይወት አደጋ ላይ መጣል መሆኑን በመገንዘብ፤ አንድ ሰው ደም ሲለግስ አንድ ህይወት ማዳኑን በማዋቅ ከቫይረሱም ራሱን እየጠበቀ፣ ለወገኑም ደሙን እየሰጠ ከቫይረሱም በደም ችግር ምክንያት ከሚከሰተው ሞትም ራሱንም ወገኑንም መታደግ ይችላል። በያቅራቢያው በሚገኙ የደም መቀበያ ቦታዎች በመሄድም ይሄንኑ ኃላፊነቱን ሊወጣም ይገባዋል።
አራት ኪሎ አካባቢ ማስታወቂያ ለማንበብ በመጣበት ወቅት በዚሁ ድንኳን ውስጥ ደም ሲለግስ ያገኘነው የሳሪስ አካባቢ ነዋሪው ወጣት ጌታቸው ማሞ በበኩሉ እንደሚለው፤ የስራ ማስታወቂያ ለማንበብ አራት ኪሎ ሲመላለስ በዚህ ቦታ ደም እንደሚለገስ ተመልክቷል። ሆኖም ከቫይረሱ መስፋፋት ጋር ተያይዞ
የለጋሹች ቁጥር መቀነሱንም አስተውሏል። እርሱም የዚሁ ፍራቻ ተጠቂ ስለነበር ደም ከመለገስ ተቆጥቦ ሰንብቷል። ሆኖም አሁን ላይ ስለ ቫይረሱ ግንዛቤ ሲያገኝ በልቡ ይዞ የነበረውን ደም የመለገስ ፍላጎት ለማሳካት የሚያስችል ድፍረት አገኘ። እህቱም የህክምና ባለሙያ ስለሆነች እርሷንም ሲያማክር ተገቢው ጥንቃቄ ተደርጎ ስለሚከናወን ቫይረሱ ደም ከመለገስ እንደማያግደው ታስረዳዋልች። እናም ደም ለመለገስ ቻለ። እናም ለእርሱ ደም መለገስ ማለት በደም ችግር አደጋ ላይ የወደቁና የተጎዱ ወገኖችን መታደግ ነው። እርሱም ደም ሲለግስ ያንን ያደረገ ያክል ይሰማዋል። ምክንያቱም እርሱ ደም እያለው በደም ችግር ወገኖቹ ሲሞቱ ከሚያይ ያውም ሲሰጥ ችግር የማይፈጥርበት ደም ለግሶ ወገኖቹን ከሞት ማዳን በመቻሉ ከምንም በላይ ደስታን ፈጥሮበታል።
ወጣት ጌታቸው እንደሚለው፤ ምንም እንኳን ሰዎች በልባቸው ደም ለመለገስ ቢያስቡም ያንን እውን የሚያደርጉበት ስፍራ በአቅራቢያቸው ካላገኙ በተለያየ ምክንያት ሳይመቻቸው ቀርቶ ሀሳባቸውን ሳይተገብሩ የሚቀሩበት እድል ሰፊ ነው። ይሄን መሰል የደም መቀበያ ቦታዎች ሲኖሩ ደግሞ ያሰበውም በቀላሉ እንዲሰጥ፤ ባለማወቅ ውስጥ የነበረም ተነሳስቶ እንዲለግስ ያደርገዋል። በመሆኑም ህብረተሰቡ አንደኛ፣ ኮሮና ቫይረስና ደም መስጠት የተለያዩ መሆናቸውን መገንዘብ፤ ሁለተኛም እርሱ የሚለግሰው ደም ቢያንስ አንድ ወገን ከሞት የሚታደግ መሆኑን ማወቅ ይገባዋል። በዚህም በአንድ በኩል ቫይረሱን ከሚያስተላልፉ ተግባራት ራስን በመቆጠብና ራስን መታደግ፤ በሌላ በኩል ደም በመለገስ ሌሎች ወገኖችን መታደግ ይቻላል።
በብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ውስጥ ተንቀሳቃሽ ደም ሰብሳቢ ቲም አባላት አንዷ የሆነችው ሲስተር ራሄል በለጠ እንደምትለው፤ የደም ልገሳ ባህሉ እያደገ ቢሆንም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሰው ከቤት አትውጡ ሲባል መቀዛቀዝ ትቶ ነበር። ይሄን ተከትሎም “መውጣት ካሰባችሁ ለደም ልገሳ ብቻ ውጡ” የሚለውንና መሰል መልዕክቶችን በብሔራዊ ደም ባንክ የትስስር ገጾችም ሆነ በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች በተላለፈ የቅስቀሳና የግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክት ሰው እየመጣ መስጠት በመጀመሩ የተሻለ ደም እየተሰበሰበ ይገኛል።
ሲስተር ራሄል ስለ ደም ልገሳ ሂደት ስለሚወሰደው ጥንቃቄና ፋይደው ስታስረዳ እንዲህ በማለት ነው። ሰው ደም መለገስ ንክኪ ሊኖረው ይችላል ብሎ ሊሰጋ ይችላል። ነገር ግን በተቻለ መጠን ችግሩን ከመከላከል አኳያ በዓለም ጤና ድርጅትም ሆነ በጤና ሚኒስቴር የተቀመጡ አቅጣጫዎችን በመተግበር ነው ደም እየተቀበልን ያለነው። በዚህም የደም ለጋሾችን አልጋ ርቀት ወስኖ የማስቀመጥ፤ አልጋዎችን በበረኪናም በአልኮልም የማጽዳት፤ ከመግባታቸው በፊት እጅ እንዲታጠቡም ሳኒታይዘር እንዲጠቀሙም የማድረግ፤ ደም ለግሰው ሲወጡም ሳኒታይዘር ተጠቅመው እንዲወጡ የማድረግ ስራ እየሰራን ነው። በዚህ መልኩ ደም ለጋሾች ላይ ስጋት በማይፈጥር መልኩ
ተጠንቅቀን የደም መቀበል ስራውን የምናከናውን መሆኑን ማህበረሰቡ አውቆ ደም የመለገስ ተግባሩን እንደወትሮው ሁሉ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
ሲስተር ራሄል እንደምታስረዳው፤ ድሮ ድሮ ደም የሚፈሰው የአገር ዳር ድንበርን በማስከበርና አገርን ባለማስደፈር ትንቅንቅ ውስጥ ነው። ከዚህ አኳያ ደም መስጠትን ከባድ አድርገው የሚመለከቱ ማህበረሰቦች ይኖራሉ። ይሁን እንጂ አገርን በማስከበር ሂደት የሚሰጥ ደም አንድም ህይወትን ሊያሳጣ፣ ካልሆነም አካልን ሊያጎድል ይችላል። በዚህ ሂደት ነው አገር ከጠላት ድና ተከብራ የምትኖረው። የሰውን ህይወት ለመታደግ የሚደረገው የደም ልገሳ ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው። ምክንያቱም ደም መስጠት በአካልም ሆነ በህይወት ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ የለም። ከዚህ ባለፈም በአንድ ሰው አካል ውስጥ ከአምስት እስከ ስድስት ሊትር ደም አለ ተብሎ ያታመናል። በደም ልገሳ ሂደት ደግሞ ከዚህ ውስጥ 300 ሚሊ ሊትር ወይም 450 ሚሊ ሊትር ነው የሚወሰደው። የዚህ መቀነስ ደግሞ በጤና ላይ የሚያመጣው አንዳችም ጉዳት የለም።
አንድ ሰው ደግሞ ዛሬ ከለገሰ ከሶስት ወር በኋላ ነው የሚለግሰው። ሰዎች ደግሞ ደም ሲለግሱ ቢያንስ አራት አይነት ምርመራዎችን በማድረግና ውጤቶቻቸውንም በማወቅ ተጨማሪ ጥቅም ያገኛሉ። ከዚህ አኳያ ሲታይ ሰዎች ደም ሲለግሱ አንድም ራሳቸውን ይጠቅማሉ፤ ሁለተኛም ሌሎችን ከሞት ይታደጋሉ። በመሆኑ አሁን ባለው ሁኔታ ሳይደናገጡ እጅን ከመታጠብና ርቀትን ከመጠበቅ ጀምሮ የሚሰጡ ምክሮችን በመተግበር ከኮሮና ራሳቸውን እየጠበቁ ደም በመለገስ ኮሮናን የመከላከልም፤ ወገናቸውን የመታደግም ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።
“ለእኔ ደም መለገስ ማለት ካለው ላይ ቆርሶ በመስጠት ርህራሄና ወገናዊነትን ማሳየት ነው” የምትለው በዚህች ድንኳን ከወገን ለወገን የሚለገሰውን ደም ለወገኖቿ በመሰብሰብ ሂደት ላይ ተጠምዳ ያገኘናት በብሔራዊ ደም ባንክ ውስጥ የኬዝ ቲም አንድ አስተባባሪ ሲስተር ሸዋዬ ሞላ ናት። እርሷ እንደምትለው፤ በአዲስ አበባ ያለው የደም ልገሳ ሂደት ጥሩና የህዝቡንም መልካምነት የሚያሳይ ነው። ምክንያቱም የአዲስ አበባ ህዝብ ዘይት ወይም ስኳር ለመውሰድ ቀበሌ ሲሰለፍ ለራሱ ጥቅም ነው ሊባል ይችላል፤ ብዙ ሰዓት ተሰልፎ ደም ሲለግስ ማየት ግን ከምንም በላይ ከራሱም በላይ ለሌሎች የሚኖር ህዝብና ለወገን መቆሙን ያመላክታል።
ይህ ተግባር ግን የኮሮና ወረርሽንን ተከትሎ ተቀዛቅዞ ነበር። ሆኖም በተሰራው የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ደም በመለገስ ዓርአያነታቸውን በተግባር በመግለጻቸው ስጋቱ ተቃልሎ ቀድሞ ወደነበረበት ደም የመለገስ ሁነት ተመልሶ በሚያስደስት ሁኔታ ላይ ይገኛል። በዚህ መልኩ በድንኳን የሚከናወኑ የደም ልገሳ ተግባራት የሚፈጠሩ ንክኪዎች የኮሮና ስርጭት መከላከልን መሰረት ባደረገ መልኩ በሙሉ ጥንቃቄ የሚተገበሩ ሲሆን፤ አንድ ደም ለጋሽ ወደ ድንኳን ሲገባ ጀምሮ ደም ለግሶ እስኪወጣ ድረስ ያሉ ንክኪዎች ከቫይረሱ ስርጭት ምክንያት እንዳይሆኑ ተገቢው ጥንቃቄ እየተደረገ ይገኛል።
ለዚህም ወደ ድንኳን ከመግባታቸው በፊት እጃቸውን እንዲያጸዱ ይደረጋል፤ የደም ግፊታቻው ሲለካም የመለኪያ ቁሱ የሚያርፍበት የክንድ ክፍል አልኮል እንዲቀባ ይደረጋል፤ እያንዳንዱ ደም ለጋሽ ደም ከመለገሱም ሆነ ደም ለግሶ ሲነሳ የማረፊያ አልጋዎች በአግባቡ ይጻዳሉ፤ ለአንድ ሰው አንድ የእጅ ጓንት መጠቀም ስለሚያስፈልግም ግላብ በመጠቀም ጭምር ነው ጥንቃቄ እየተደረገ ያለው። ሆኖም ኮሮናን ከመከላከል አኳያ ህብረተሰቡ ቀድሞ የነበረው ፍርሃት ሲለቀው አሁን መዘናጋት የጀመረ በሚመስል መልኩ እጅ የመታጠብ ልምዱ እየቀነሰ ነው።
በመሆኑም ጥንቃቄው በመዘናጋት ሳይተካ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ችግሩን ቸል ብሎ እንደ ሌሎቹ መሆን ስለማይገባም፤ ህብረተሰቡ አንድም ከቫይረሱ ራሱን ሊጠብቅ፤ ደም በመለገስም ወገኑን ሊታደግ ይገባል። ምክንያቱም ደም ለሰጪው ቀላል፤ ተግባሩ ግን የሰው ልጅን መታደግ እንደመሆኑ ከባድ ነው። ስለዚህ ህብረተሰቡ ደም መለገስን ባህል አድርጎ በሶስት ወር አንድ ቀን በእቅዱ አስገብቶ በመለገስ፤ ሲችልም ቤተሰብና ጓደኛን ጨምሮ ሊተገብረው እንደሚገባ ነው ሲስተር ሸዋዬ የምትናገረው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2012
ወንድወሰን ሽመልስ