
ኢትዮጵያውን በእምነታቸው የማይደራደሩ ህዝቦች ናቸው፡፡ ይህንንም እምነቶቻቸውን ጠብቀው በማቆየት አስመስክረዋል፡፡ በክርስትናም ሆነ በእስልምና ሃይማኖት ጥላ ስር የተሰባሰቡ ዜጎች መረዳዳት፣ መከባበር፣ መሰማማትና ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችን ተቀብሎ መኖር ሃይማኖቶቹ የለገሷቸው እሴቶቻቸው ናቸው፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ የሃይማኖት አባቶች ትልቅ ስፍራ አላቸው፡፡ አንድ የሃይማኖት አባት በራሳቸው እምነት ተከታዮች ብቻ ሳይሆን በሌላ እምነት ተከታዮችም ዘንድ ክብርና ሞገስ ይሰጣቸዋል፡፡ የሃይማኖት አባቶች የሚሰጡት ምክርና ተግሳፅም በብዙ ሰዎች ዘንድ ቅቡልነት ያገኛል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ የእምነት አባቶች ከፈጣሪ ጋር ለመገናኘት ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው ተብሎ ይታሰባል፡፡
ባህላዊ እሴቶቻችንም ቢሆኑ አገራዊ አንድነታችንን ለማጠናከርና አብሮነታችንን ለማቆየት ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችም ሆኑ ግጭቶች የሚፈቱት በአብዛኛው በአገር ሽማግሌዎች ነበር፡፡ የነፍስ መጠፋፋት ያስከተሉ ግጭቶችን ጭምር በአገር ሽምግልና በመዳኘት ጥፋተኛን የመቅጣትና ተበዳይን የመካስ ተግባር በአገር ሽምግልና ሲከናወን የኖረ ትልቅ ማህበረሰባዊ ሀብት ነው፡፡
ታላላቆችን የማክበርና አርአያነታቸውን የመከተል፣ ርስ በርስ የመከባበር፣ አንዱ ሌላውን የመውደድና አብሮ የመብላትና የመኖር ባህልም ጠንካራ መሰረት ነበረው፡፡ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላው አካባቢ የሄደ እንግዳ ከማንም በላይ የሚከበርበትና ከቤተሰቡ አባል በላይ እንክብካቤ የሚያገኝበት ጠንካራ ባህል ይዘን ኖረናል፡፡ እነዚህ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻችን ደግሞ በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ ጭምር ይታወቃሉ፡፡ ቀደም ባሉት ዘመናትም ከውጭ የመጣ ወራሪ ኃይልን በአንድነት ለመመከትና የአገርን ሉአላዊነት ጠብቆ ለማቆየት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡
በአገራችን እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ታላላቆችን በተለይ በእድሜ የገፉ አባቶችና እናቶችን ማክበር የተለመደና በእያንዳንዱ ትውልድ ውስጥም የሰረፀ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ በአንድ አካባቢ የሚገኝ አንድ አባት የሁሉም የአካባቢው ወጣቶች አባት ተደርጎ ይታያል። ይከበራልም፡፡ በትምህርት ቤትም ቢሆን በመምህራንና በተማሪዎች መካከል የነበረው የመከባበር መንፈስ ጠንካራ ነበር፡፡ መምህራን የቀለም አባት ብቻ ሳይሆኑ የመንፈስ አባት ተደርገው ይታያሉ፡፡
ያም ሆኖ አሁን አሁን በተለይ ባህላዊ እሴቶቻችን ቀስ በቀስ እየተሸረሸሩ የመጡበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ በዚህ የተነሳም በአሁኑ ወቅት ሰላምን ለማምጣትም ሆነ ለመከባበር ጠንካራ መሰረት ጥለውልን በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ ጭምር ስንከበርባቸው የነበሩ ማንነቶቻችን እየተሸረሸሩ መጥተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሃይማኖት አባቶችንም ሆነ አዛውንቶችን የማክበርና የሚሉትን ሰምቶ የመተግበር ሁኔታ እየቀነሰ መጥቷል፡፡
በሌላም በኩል ኢትዮጵያ ጠንካራ የሃይማኖት ተቋማት ቢኖራትም እነዚህ የሃይማኖት ተቋማት በተለይ ዋነኛ ተግባራቸው የሆነውን ሰላም ከማስከበር አንጻር የሚፈለገውን ያክል ሚናቸውን መወጣት ሲሳናቸው ይታያል፡፡ ለዚህም በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች ለምን ተከሰቱ፣ እንዴትስ እነዚህ ሁሉ ጠንካራ የሃይማኖት ተቋማትና የአገር ሽማግሌዎች ይዘን ሰላማችንን መጠበቅ አቃተን የሚለው ጥያቄ ማሳያ ነው፡፡
እኛ ኢትዮጵያዊያን በአንድ ዘመን የስልጣኔ ማማ ላይ የነበርን ህዝቦች ነን፡፡ የአክሱም፣ የላሊበላ፣ የጎንደር፣ የሐረር፣ የጅማ አባጅፋር ወዘተ ጥንታዊ ስልጣኔዎች ዛሬም ድረስ የስልጣኔ አሻራዎቻችን ናቸው፡፡ የቀደመው ትውልድም እነዚህን ታሪካዊ አሻራዎቻችንን ለማቆየት አልከበደውም፡፡ አገሩንም ከወራሪ ኃይሎችና ከውስጥ ሽኩቻ ጠብቆ ዛሬ ላይ አድርሶናል፡፡ የቀደመው ትውልድ ይህንን ታሪክ ያቆየልን ደግሞ አንድም በእምነቱ ፀንቶና የሃይማኖት አባቶቹን ምክር ተቀብሎ በመኖሩ፣ በሌላም በኩል በየጊዜው የሚነሱ ችግሮችን ያለምንም ጣልቃ ገብነት በራሱ መንገድ የመፍታት ባህላዊ እሴቶቹን ጠብቆ በመጓዙ ነው፡፡
በመሆኑም የሃይማኖት አባቶች፣ አገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ ምሁራን፣ ወላጆች እንዲሁም በተለያየ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚገኙ አካላት ሁሉ የቀደመውን የአገራችንን ጠንካራ የአንድነትና የመቻቻል እንዲሁም የመከባበር ባህል በመመለስና በማጠናከር አገራችንን ወደ ሰላምና ወደ ብልጽግና ለማምጣት ትልቅ ኃላፊነት ወስዳችሁ መሥራት ይኖርባችኋል፡፡ ዛሬ ላይ አገራችንን ወደ አንድነትና ሰላም ሊያመጣት የሚችለው ይህ የቆየው ማንነት በመሆኑ እንደዚህ ዓይነት እሴቶችን ከያሉበት በማውጣት ማደስና ወደ ተግባር መቀየር ይገባል፡፡
ዛሬ ላይ እያጣን የመጣነው ቁምነገር መደማመጥ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ያለንን የተለያየ ማንነት፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ አንድ ላይ አጣምረን መኖር ለዕድገታችንም ጭምር ጠቃሚ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ትልቁ አቅም ደግሞ መደማመጥ ነው፡፡
የማይደማመጥ ማህበረሰብ ሊከባበር አይችልም፡፡ የቀደመውን የማያከብር ዜጋ ነገ ሊከበር አይችልም፡፡ አንዱ ሲናገር ሌላው ካላዳመጠና ሁሉም ተናጋሪ፣ እኔ ብቻ አዋቂ የሚል አስተሳሰብ ወንዝ አያሻግርም፡፡ በተለይ የሃይማኖት አባቶቻችን እና የአገር ሽማግሌዎቻችንን መስማት ብዙ ርቀት ለመጓዝ ያስችላል፡፡ ትላንትን መዘከርና ዛሬን መጠበቅ ለነገ ዋስትናችን ነው፡፡ ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ እንደማመጥ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 6/2011