ልጆች ሰላም ናችሁ! ከኮሮና ቫይረስ ራሳችሁን እየጠበቃችሁ እንደሆነ እገምታለሁ። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ሲባል ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። እናንተም ሙሉ ጊዜያችሁን የምታሳልፉት በቤታችሁ ነው። ስለዚህ እራሳችሁን በቀላሉ ከሰዎች ንክኪ ማራቅ ትችላላችሁ ማለት ነው። ነገር ግን መዘናጋት ካለ እቤታችሁ ብቻ ስለሆናችሁ አይዛችሁም ማለት አይደለም። እንዲሁም አብዛኛውን ጊዜያችሁን በቤት ስታሳልፉ እንዳይደብራችሁ የተለያዩ መፅሐፍትን ማንበብ ተገቢ ነው። በተለይ ደግሞ የሞባይል ጌሞችንና ፊልሞችን ለረጅም ሰዓት መመልከት ሌላ ተጓዳኝ ችግር ስለሚፈጥር ሁሉንም በልክ ማድረጋችሁን አትርሱ። ከሁሉም በላይ ደግሞ እጃችሁን በሳሙናና በውሃ በተደጋጋሚ በመታጠብ ንጽህናችሁን ጠብቁ።
ትምህርት ቤት ሲከፈት በባከነው ጊዜ የማካካሻ ትምህርት በስፋት ሊሰጥ ስለሚችል ያን ጊዜ መጨናነቅ ውስጥ እንዳትገቡ አስቀድማችሁ ማጥናትና ማንበብ እንዳለባችሁ አትዘናጉ። የተማራችሁትንም መከለስ ተገቢ ነው። የግል ንፅህናችሁን መጠበቅ የእለትዕለት ስራችሁ ማድረግ የግድ ነው። መረጃዎችን በየጊዜው በመከታተል ጥንቃቄዎች መውሰድ አስፈላጊ ነው። በቫይረሱ እንዳንያዝ መውሰድ ስላለብን ጥንቃቄና ተማሪዎች ጊዜያቸውን በቤት ውስጥ ምን እየሰሩ ማሳለፍ አለባቸው በሚሉ ጉዳዮች ላይ አንድ ተማሪ አናግ ሬላችኋለሁ።
ልጆች! ያነጋገርኩት ተማሪ ቅዱስ ያሬድ ይባላል። በቀበና አድቬንቲስት ትምህርት ቤት የአስረኛ ክፍል ተማሪ ነው። ራሱን ከኮሮና ቫይረስ ለመከላከል በርካታ ጥንቃቄዎችን እያደረገ ነው። በተለይ ደግሞ ከሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ መቀነሱን ይናገራል።” የግል ንፅህናዬን በደንብ እየጠበኩኝ ነው። የምጠቀምባቸውን የመመገቢያ እቃዎቼን በንፅህና ከመያዝም በላይ በመለየት እየተጠቀምኩኝ ነው። በአንድ ቤት ውስጥ የአንድ ሰው ጥንቃቄ ብቻ ዋጋ ስለሌለው ሁሉም ሰው መጠንቀቅ አለበት። እኔ በበኩሌ ከመጠንቀቅ ባለፈ በዙሪያዬ ያሉ ሰዎችን እንዲጠነቀቁ እያደረኩኝ ነው።” ብሎኛል።
ተማሪ ቅዱስ እቤት ሲውል ጊዜውን የሚያሳልፈው በርካታ ስራዎችን በመስራት መሆኑን ነግሮኛል። የመደበኛ ትምህርት መማሪያ መፅሐፎቹን ያነባል።፡ እንዲሁም የኮምፒዩተር ፕሮግራሚንግ ኮርሶችን ስለሚማር በአሁኑ ወቅት በቤት ውስጥ እየተለማመደ ይገኛል። ሌሎች መጽሀፍትንም በማንበብ ጊዜውን እያሳለፈ ይገኛል። ከማንኛውም አይነት ጨዋታ እራሱን ማግለሉን ገልፆልኛል። ትምህርት የተዘጋው ወረርሽኙ በቀላሉ እንዳይስፋፋና በርካታ ሰዎች ተጠቂ እንዳይሆኑ ስለሆነ በመሰብሰብ መጫወትም ሆነ ከሰዎች ጋር ያለንን አላስፈላጊ ንክኪ መቀነስ አስፈላጊ ነው። በበሽታው ተጠቂ ላለመሆን ከሰዎች ጋር ግንኙነት አያስፈልግም። መንግስት ያሰበውን አላማም ማሳካት አለብን ብሏል።
“ልጆች አንድ ቦታ ላይ በመሰባሰብ አንዳንድ ጨዋታዎችን ይጫወታሉ። ይህ ፈጽሞ ትክክልም ተገቢም አይደለም። ምክንያቱም እቤት እንድንቀመጥ የተደረገው ከነዚህ አይነት ንክኪዎች ለመቆጠብ ታስቦ ነው። ስለዚህ በመገናኛ ብዙኃን የሚነገረውን በማዳመጥ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ መጠበቅ ይኖርብናል። ከሰዎች ጋር የሚኖረንን ግንኙነት በጣም መገደብ አለብን። እንዲሁም ስራ እየዋሉ የሚመጡ ቤተሰቦቻችንን እንዲጠነቀቁ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ውጭ ውሎ ወደ ቤት የሚገባ ሰው በቫይረሱ ተጠቅቶ ሊሆን ስለሚችል ሳይዘናጉ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። ቤተሰቦቻቸው ከመቀላቀላቸው በፊት እጃቸውን በደንብ መታጠብ ይጠበቅባቸዋል። ካልሆነ ግን በርካታ ሰዎች ሊጎዱ ይችላሉ። ከፍተኛ የሆነ ችግር ካልተከሰተ በስተቀር ትምህርት እንደማይዘጋ አስበው መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።” ሲል መክሯል።
የኮሮና ቫይረስ ሁልጊዜ የሚተላለፈው በንክኪ፣ በሰላምታና በመሳሰሉት መሆኑን በመገንዘብ ለራሱም ሆነ ለሰዎች ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። ቫይረሱ አደገኛ ከመሆኑ የተነሳ መሬት ላይ እስከ ሰዓት ሊቆይ ይችላል እየተባለ ስለሆነ የሚጫወቱ ልጆች ካሉ ማቆም አለባቸው። ምክንያቱም በቀላሉ የቫይረሱ ተጠቂ ሊሆኑ ይችላሉ። ለቤተሰቦቻቸውም ያስተላልፋሉ።
ልጆች ብቻ ሳይሆን ስራ እየዋሉ ሚመጡ ሰዎች ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው የሚለው ተማሪ ቅዱስ ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር የሚያደርጉትን ግንኙነት መቀነስ፣ተራርቀው መስራትንና ሰላምታን መቀነስ አለባቸው። ወረቀት በሚቀባበሉበት ጊዜ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ሊሆን ይገባል። የሚቀበሉትን እቃ በአልኮል አፅድተው መጠቀም አለባቸው። ማፅዳት የማይችሉ ከሆነ ደግሞ ከተጠቀሙበት በኋላ እጃቸውን በአልኮል መታጠብ መርሳት የለባቸውም ሲል ሀሳቡን አካፍሎናል።
ልጆች! የተማሪ ቅዱስ ምክር ደስ እንዳላችሁ እገምታለው። እናንተም እንደ ቅዱስ እራሳችሁን ከበሽታ ለመከላከል ከቤት አለመውጣትንና ከሰዎች ጋር ያላችሁን ግንኙነት መገደብ አለባችሁ። እንዲሁም ጊዜያችሁን የተለያዩ መፅሐፍትን በማንበብ፣ ልዩ ችሎታችሁን በማዳበርና በቤት ውስጥ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ማሳለፍ አለባችሁ። ትምህርት ዝግ ስለሆነ ብቻ ለረጅም ሰዓት ፊልም ማየት እራሱን የቻለ ችግር ሊያመጣባችሁ ስለሚችል በግቢ ውስጥ በመንቀሳቀስ እንዲሁም በቴሌቭዝን የሚተላለፉ የሰውነት እንቅስቀሴ ፕሮግራሞችን በመክፈት አብሮ ስፖርት በመስራት ሰውነትንና አእምሮን ማነቃቃት ተገቢ ነው። የግል ንጽህናችሁን በመጠበቅ እና አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ከቫይረሱ እራሳችሁን ጠብቁ። መልካም ቀን!
መረጃ ለመላክ ወይም ለማግኘትለምትፈልጉ፣ ስልክ…0111264210 0111569873 ኢሜል….. addiszemen@press.et ፋክስ…….. 251-0111-56 98 62 ብላችሁ ብትልኩ ወይም ብትደውሉታገኙናላችሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 ቀን 2012 ዓ.ም