‹‹ዝዋይ አዋሳ ዝዋይ…›› በአንድ በኩል የሚሰማ የተሽከርካሪ ረዳቶች ድምፅ ነው። በሌላኛው ጠርዝ የቀኑን ብርሃን በጫት መቃምና በሺሻ የሚያሳልፉ የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ሌቱን ሲዋትቱ የሚያድሩ የወሲብ ተዳዳሪ ሴቶች የምሬት ሕይወታቸውን የሚያሳብቅ ጫጫታ አዕምሯቸው በሱስ የናወዘ ወጣቶች ድምፅ ጋር ተደማምሮ ለሰሚው ጭንቀትን ይፈጥራል። የጫት ንግዱም ቢሆን ሞቅ ደመቅ ያለ ነው።
ታዲያ በእነዚህና በፊት ለፊት ሕገወጥ ነጋዴዎች በደንብ ማስከበር ‹‹ተያዝኩ አልተያዝኩ›› ስጋት የሚሯሯጡበት፣ በመንገዱ ወደ ተለያየ የከተማዋ አቅጣጫ የሚጓዙ የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ድምፅና የረዳቶች ጥሪ ታጅቦ የሚገኘውን አዲስ ከተማ መሰናዶ ትምህርት ቤት ለተመለከተ የተማሪዎቹ የወደፊት ራዕይ ምን ይሆን? የሚል ጥያቄን በእዝነ ሕሊናው መጫሩ አይቀሬ ነው።
‹‹ልጆቻችን አዋኪ ድርጊቶች የተሞላበት አስቸጋሪ ሁኔታን ተቋቁመው ትምህርት ቤት መዋላቸው አስደናቂ ነው›› በማለት ከመዋል ባሻገር ዕውቀት ለመቅሰም አዳጋች መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ኑሪ መሐመድ ይናገራሉ። ችግሩን መንግሥት ለብቻው ሊፈታው የሚችለው አለመሆኑን በመግለጽ፤ ህብረተሰቡ የነገ አገር ተረካቢ ትውልድ እንዲሁ በከንቱ ሲቀጠፍ መመልከት ተገቢ ባለመሆኑ ህብረተሰቡ የራሱን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
አያይዘውም ተግባሩ የአንድ ተቋም ብቻም ሳይሆን የንግድ ቢሮ፣ የምግብና መድሐኒት ቁጥጥር፣ ደንብ ማስከበርና ትምህርት ቢሮ በመሆኑ እነዚህ ተቋማት በጋራ ተቀናጅተው መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ ዘሪሁን ታምሩ በትምህርት ዙሪያ የሚመለከታቸው አካላት ዘወትር ችግሮችን ከማንሳት በዘለለ የእርምት ዕርምጃም ሆነ ለችግሮች የተቀመጡ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በተግባር ሲያውሉ እንደማይታይ ትዝብቸውን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ችግሮችን ከማመላከት የዘለለ ሪፖርት ሊኖር ይገባል፡፡
ለዚህም እያንዳንዱ አካል ለጉዳዩ የሚገባውን ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ከሰሞኑ በትምህርት ጥራትና ተገቢነት ዙሪያ በተለይም በተማሪዎች ሥነምግባር፣ በአዋኪ ጉዳዮችና በከተማዋ የሚገኙ ትምህርት ተቋማት ደረጃ ጋር በተያያዘ የከተማው የአጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ ከህዝብ አደረጃጀት ተወካዮች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ በውይይቱ የተማሪዎችን ውጤትና ሥነምግባር፣ መምህራን ለሙያቸው የሚሰጡት ክብር አናሳነት፣ ተገቢ ያልሆነ የማህበራዊ ሚድያዎች አጠቃቀም፣ የትምህርት ደንቦችና መመሪያዎች በአግባቡ አለመተግበር፣ የወላጅ ተሳትፎ በሚፈለገው ደረጃ አለመሆን፣ በትምህርት ቤቶች ላይ መጤ ባህሎችን መከላከል አለመቻል፣ የሥርዓተ ትምህርት ጥሰት መኖርና መሰል ለትምህርት ጥራትና የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል ምክንያት ናቸው የተባሉ ችግሮች ተነስተዋል፡፡
በተመሳሳይ ትምህርት ቤቶች በራቁት ዳንስ ቤቶች፣ ፔንስዮን፣ ማሳጅ ቤቶች፣ ጠጅ ቤትና ጃንቦ ቤቶች የተከበቡ በመሆናቸው አደንዛዥ ዕፅ ተጠቅመውና መጠጥ ጠጥተው ወደ ክፍል የሚገቡ፣ ለትምህርት ቤቶች ደንብ ተገዢ ያልሆኑ፣ ለዕውቀት አባቶቻቸው ተገቢውን ክብር የማይሰጡ፣ አጥር የሚዘሉና ኩረጃን እንደ ባህል የሚያዩ ተማሪዎች እየተፈጠሩ መሆናቸው ተነስቷል፡፡ በኤጀንሲው የአጠቃላይ ትምህርት ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ ዘመነ አብዩ ስለጉዳዩ ባነጋገርናቸው ወቅት እንደገለጹልን፤ በክፍለ ከተሞች በየዓመቱ ከሚሰበሰበው መረጃ በተጨማሪ ኤጀንሲው በደንብ 68/2008 መሠረት ዋነኛ ሥራው መፈተሽ፣ ማረጋገጥና መቆጣጠር ነው፡፡
አዋኪ ጉዳዮችን ከትምህርት ቤቶች የማራቅ፣ የማስተካከል የመዝጋት ከሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ኤጀንሲው ሥራዎቹን ለማከናወን ከትምህርት ቢሮ ጋር ለማከናወን ስምምነት የፈጠረ ሲሆን፤ ቀጣይ አዋኪ ችግር ያለባቸው የትምህርት ተቋማት በትምህርት ጥራት መረጋገጥ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ በመሆናቸው በሚደረጉ ጥናቶችና ቁጥጥሮች 395 ትምህርት ቤቶች በዚህ መሰል ችግር እንደተከበቡ መረጋገጡን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ያቀኑበትን ዓላማ ለማሳካት ከመጣር ይልቅ በሱስና በተለያዩ ያልተገቡ ድርጊቶች ውስጥ መጠመዳቸው አይቀርም፡፡ ይህም የመማር ማስተማሩን ሂደት ከመጉዳቱ ባሻገር የተማሪዎችን ውጤት እንደሚቀንስም አያጠራጥርም፡፡ ዳይሬክተሩ፤ ችግሮቹን ኤጀንሲው እንደደረሰባቸው የገለጹ ሲሆን፤ በቀጣይም ለመፍታት እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም በተለይም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ጥር ስር ሱቅ ያከራዩ ቤቶች እንዲዘጉ ትምህርት ቢሮ ውሳኔ አሳልፏ፡፡
ከሱቆቹ ባሻገር አሳሳቢ የሆኑት ትውልዱን በመጤ ባህል ሸብበው ከመንገዱ የሚያሰናክሉ ተቋማት ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ምን አገዳችሁ ለዳይሬክተሩ ያነሳንላቸው ጥያቄ ነበር፡፡ ዳይሬክተሩ በምላሻቸው፤ ኤጀንሲው ዕርምጃ ለመውሰድ ያገደውና በቀጣይ መሠራት ያለበት ከሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት ጋር ያለ ቅንጅታዊ አሠራር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ማሳጅ ቤቶቹም ሆነ መሰል ሌሎቹ ተቋማት ፍቃድ ሰጪውና ብቃት የሚያረጋግጡ አካላት ሌሎች በመሆናቸው ኤጀንሲው ያልከፈተው ተቋም ላይ የመዝጋት ስልጣን የለውም፡፡
ይልቁንም ኤጀንሲው ችግሩን ለሚመለከታቸው በሕግ ኃላፊነት ለተሰጣቸው ተቋማት ሲገልጽ ቢቆይም ዕርምጃ ወሳጆች ሌሎች በመሆናቸው ችግሩ በአጣፋኝ እንዳይፈታ ማነቆ ሆኖበት ቆይቷል፡፡ ከዚህ አንፃር 18 ከሚሆኑ የመንግሥት ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የትስስር ሰነድ ተፈርሟል፡፡ ይህን ተጠናክሮ ለማስኬድ ይሠራል፡፡ ህብረተሰቡም በዚህ ላይ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪያቸውን ዳይሬክተሩ አስተላልፈዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 6/2011
በፍዮሪ ተወልደ