የዘንድሮ አገር አቀፍ ምርጫ ይካሄድ፣ አይካሄድ በሚል ያላባራ ክርክሮች ነበሩ። ምርጫው ዘንድሮ መካሄድ የለበትም ከሚሉ ወገኖች ጎልቶ የሚሰማው ድምጽ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ሥነምህዳር የለም፣ ሠላምና መረጋጋት የለም፣ ይህ በሌለበት ምርጫ ማከናወን የማይታስብ ነው የሚል ነበር። ይህን ሃሳብ የሚደግፉ እንደነ አቶ ልደቱ አያሌው ዓይነት ፖለቲከኞች ምርጫው መካሄድ የለበትምን ከደገፉ በኋላ በአስቸኳይ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ወደማሳሰብ ተሸጋግረዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ምርጫው መካሄድ አለበት ባይ ወገኖች የምርጫ ጉዳይ ሕገመንግሥታዊ መሆኑን በማንሳት አይካሄድ ባዮችን ከገሰጹ በኋላ ጉዳዩ ለክርክር የሚቀርብ አይደለም ሲል ይሞግታሉ። የዚህ ሃሳብ አራማጆች ገፋ ብለውም ምርጫው በጊዜው የማይካሄድ ከሆነ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ሕጋዊ መሠረቱን ያጣል በማለት ያስጠነቅቃሉ።
ይህ ክርክር አሁንም ድረስ መቋጫ ባላገኘበት ሁኔታ ተፈጥሮ በራሷ መንገድ ነገሮችን መለዋወጥ መጀመሯ አንዳች ግርምትን የሚያጭር ነው።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ 19) በአስደንጋጭ ፍጥነት እየተዛመተ መምጣትና ብዙ ሰዎችን ወደሞት እየነዳ መሆኑ እንኳንስ እኛን ድሆቹን ቀርቶ በገንዘባቸውና በደረሱበት ቴክኖሎጂ አብዝተው የሚኩራሩትን አሜሪካኖች እና አውሮፓውያንን አንገት ወደማስደፋት ደረጃ ገፍቷቸዋል። የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሀኖም በያዝነው መጋቢት ወር የመጀመሪያ ሳምንት በሰጡት መግለጫ የኮሮና ቫይረስ «ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ» መሆኑን አውጀዋል። አንድ በሽታ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሚባለው በዓለም ዙሪያ በተመሳሳይ ጊዜ በተለያዩ አገራት ውስጥ ሲሰራጭ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተሩ እንዳሉት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከቻይና ውጪ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በ13 እጥፍ ጨምሯል። ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ጨምረውም በሽታውን በተመለከተ እርምጃ ለመውሰድ የታየው ቸልተኝነት «በጣም እንዳሳሰባቸው» ተናግረዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ሰሞኑን ስለጉዳዩ የሰጡት ተጨማሪ የፕረስ መግለጫ ትልቅ መጋገሪያ ሆኖ መሰንበቱ የሚታወስ ነው። «በኮሮና ቫይረስ የተያዘው የመጀመሪያ ሰው ሪፖርት ከተደረገ በኋላ፤ የመጀመሪያዎቹ 100ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ለመያዝ 67 ቀናት ወስደዋል። ቀጣዮቹ 100ሺህ ሰዎች የተያዙት በ11 ቀናት ውስጥ ሲሆን፤ ሦስተኛ 100ሺህ ሰዎች የተያዙት ደግሞ በ4 ቀናት ውስጥ ነው» ማለታቸው ቫይረሱ የቱን ያህል ስር እየሰደደና ፈጣን በሆነ መንገድ እየተሰራጨ መምጣቱን በራሱ ጮክ ብሎ የሚናገር ነው።
በወርልዶ ሜትር ሪፖርት መሠረት በኮሮና ቫይረስ ሞት ከቻይና የመሪነቱን ቦታ የተረከበችው ጣሊያን ናት። በጣሊያን እስከትናንት ወዲያ ሐሙስ ዕለት ድረስ ብቻ 7 ሺ 503 ሰዎች የሞቱ ሲሆን በሁለተኛዋ ስፔን ደግሞ 4 ሺ89 ሰዎች ሞተዋል። በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠችውና በአሁን ሰዓት የቫይረሱን ስርጭት በመግታት በአርአያነት ስሟ እየተነሳ ያለችው ቻይና 3 ሺ 287 ሰዎች በሞት አጥቻለች።
ብዙዎች እንደሟርት ቢቆጥሩትም ቢሊየነሩ ቢልጌትስ የኮሮና ቫይረስ ከ10 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያንን ሊገድል እንደሚችል ከወዲሁ አስጠንቅቀዋል። የማይክሮሶፍት መስራች እና የቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን መሥራች አሜሪካው ቢሊየነር ቢል ጌትስ የአፍሪካ የጤና አገልግሎት ደካማ በመሆኑ ኮሮና ከ10 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያንን ሊገድል ይችላል ብለዋል።
በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ የአሜሪካ የሳይንስ ማህበር ሰሞኑን በዋሺግተን ባዘጋጀው መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት ቢልጌትስ ወረርሽኙ በአፍሪካ አህጉር የከፋ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችልም ጠቁመዋል።
ኮሮና የሰውን ልጅ እየተፈታተነ እንደሚገኝ የገለፁት ባለሀብቱ በተለይም የአፍሪካ አገራት የጤና አገልግሎታቸው እና ኢኮኖሚያቸው ያላደገ በመሆኑ 10 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎችን ለሞት ሊዳርግ ይችላል። ቫይረሱ ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት በፍጥነት ሊሰራጭ ስለሚችል አገራቱ በትኩረት ሊከላከሉ እንደሚገባም ያሳሰቡት ቢልጌትስ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል 100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጋቸውን ዘገባው አስታውቋል።
የኮሮና ቫይረስ ሀብታም፣ ድሃ፣ መሪ ወይንም ተመሪ ብሎ አይመርጥም። የብዙዎች በር አንኳኩቷል። እዚሁ በግብጽ ሁለት የከፍተኛ ጀኔራሎችን ወደሞት ሸኝቷል። በኮሮና ቫይረስ ሁለት ጀኔራሏን ጨምሮ 20 ዜጎቿን አፈር አልብሳ ርዕሰ ብሔሯን አልሲሲን ኳራንቲን አድርጋ እና በርካታ የጦር አባላቷን ጨምሮ 400 መቶ የሚቆጠሩ ዜጎቿን አልጋ አስይዛለች።
ከወደእንግሊዝ የተሰማው ወሬ ደግሞ ቫይረሱ የንጉሳውያንን ቤተሰብ እንደጎበኘ የሚያትት ነው። የዌልሱ ልዑል ቻርለስ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል። ባለቤታቸው ሶፋኒተ ኮርንዎል ካሚላ በተደረገላቸው ምርመራ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው የታወቀ ቢሆንም ሁለቱም ስኮትላንድ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተገልለው እንዲቆዩ ተደርገዋል።
ልዑል ቻርለስ ፊልፕ አርተር ጆርጅ የብራታኒያዋ ንግሥት ኤልሳቤጥ ልጅና የቀድሞዋ የዌልስ ልዕልት ዳያና ስፔንሰር ባል ነበሩ ።
የታዋቂው የካሜሩን ሙዚቀኛ ማኑ ዲባንጎ ሕይወት ቀጥፏል። ካሜሩናዊ የአፍሮ ጃዝ ሙዚቃ ኮከብ ማኑ ዲባንጎ በኮሮናቫይረስ ህመም ምክንያት ማረፉን ቤተሰቦቹ ባስታወቁበት ወቅት እንዲህ ማለታቸው ተዘግቧል። «የማኑ ዲባንጎ (ፓፒ ግሩቭ) ህልፈትን ይፋ ስናደርግ በታላቅ ኀዘን ውስጥ ሆነን ነው» ያሉት ቤተሰቦቹ።
ለጥቂት ከቫይረሱ ሥጋት መትረፋቸው በጀ እንጂ የጀርመኗ መራኄ መንግሥት አንጌላ መርከል፣ በኮሮና ቫይረስ ሥጋት ራሳቸውን ነጥሎ እስከማቆየት የደረሰ እርምጃ ወስደው ነበር። መርከል ራሳቸውን የነጠሉት ሐኪማቸው በኮሮና ቫይረስ መያዙ ከተሰማ በኋላ ነው ተብሏል። ይኸው ዶክተር አርብ ዕለት፣ ለአንጌላ መርከል ለሳንባ ምች መከላከያ ክትባት ወግቷቸው እንደነበረ ተሰምቷል።
ኮሮና እና ምርጫ
ከችግሩ ጋር ተያይዞ እንደፈረንሳይ፣ እንግሊዝ ያሉ አገራት ሎካል ብለው የሚጠሩትን ምርጫዎች ለማራዘም ተገድደዋል። በርካታ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች፣ ስብሰባዎች፣ ስፖርታዊ ውድድሮች ተሰርዘዋል። በአጭሩ ዓለም የቫይረሱን ስርጭት ሊያባብሱ ከሚችሉ ነገሮች በመራቅ እያንዳንዱ አገር ዜጎቹን በአስገዳጅ ሁኔታ ጭምር ከቤት ባለመውጣት የቫይረሱን ስርጭት እንዲገታ ርብርብ እያደረገ ይገኛል።
እኛም ይህንኑ ጎዳና ጀምረነዋል። የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አስገዳጅ ሁኔታ ካልገጠመ በስተቀር ከቤታቸው ሆነው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ተወስኗል። የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ተዘግተዋል። ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን ወደቤታቸው እንዲሸኙ ተደርጓል። የአየር በረራ ከ30 አገራት በላይ እንዲቋረጥ ከመደረጉ በተጨማሪ ድንበሮች እንዲዘጉ ሆነዋል። ርቀትን መጠበቅ ለቫይረሱ ስርጭት መገታት ዓይነተኛ አስተዋጽኦ ቢኖረውም ይህ በአግባቡ እየተተገበረ አለመሆኑን በመገንዘብ የደህንነት ኃይሉ ይህን እንዲያስፈጽም ታዟል።
ጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ ሐሙስ ዕለት ተከታዩን መልዕክት አስተላልፈዋል። «ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኮቪድ19 ምን ሊያስከትል እንደሚችል በርግጥ መናገር አልቻለም። ሁኔታውን ተቋቁሞ ችግሩን በድል አድራጊነት እንድንወጣ የሚያስችለን ሁለት ነገሮች አሉ። ቅድመ ዝግጅትና መመሪያዎችን ያለማመንታት ተፈጻሚ ማድረግ።
የመጨረሻው አስከፊ ሁኔታ ቢደርስ እንኳን ተዘጋጅተን መቆየታችን ጉዳቱን ይቀንሰዋል። ለዚህም የገንዘብና ሌሎች አቅርቦቶችን የማሰባሰብ ሂደትን ለማስተባበር ብሔራዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴን አዋቅረናል። በፌዴራል ደረጃ፣ ለይቶ የመከታተያ፣ ለይቶ የማቆያ እና የማከሚያ ማዕከላት ተዘጋጅተዋል። ቀጣዩ ሥራ የሚያስፈልጋቸው ግብአት እንዲሟላላቸው ማድረግ ነው። የክልል መንግሥታትም ተመሳሳይ ዝግጅት ማድረግ ይቀጥላሉ።
ይህ ጊዜ ከድንጋጤ፣ ከፍርሃት እና ከጭንቀት ወጥተን ያሉንን ግብአቶች ሁሉ አሰባስበን ወደ ብሔራዊ ድጋፍ ማሰባሰቢያው በመጨመር አስተዋጽኦ እናድርግ።
ገንዘብ ለማዋጣት እንዲቻለን የባንክ ሂሳብ ቁጥሮች እና የአጭር ጽሑፍ መላኪያ ሥርዓቶች ተዘጋጅተዋል። ታታሪ አርሶ አደሮቻችን እና የምግብ አምራቾች የምግብ አቅርቦቶችን መለገስ እንዲችሉ የምግብ ባንክም በመዘጋጀት ላይ ነው። እጅግ ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎቻችን የሚያስፈልጉ ሸቀጦችን የማዘጋጀት ሥራው እንዳለ ሆኖ፣ ለይቶ የመከታተያ፣ ለይቶ የማቆያ እና የማከሚያ ማዕከላት የሚያስፈልጓቸውን መሣሪያዎች ማሟላትም ይጠበቅብናል።
መከራ በገጠመን ጊዜ በአብሮነት እንደምንጋፈጠው በተግባር እናሳይ። «ኢትዮጵያ ብለን ለምንጠራት የጋራ ቤታችን እያንዳንዳችን አስተዋጽኦና ኃላፊነት አለብን።»
እንደትግራይ ባሉ ክልሎች ለሚቀጥሉት 15 ቀናት የሚቆይ የዕለትና የሳምንት ገበያዎች እንዲዘጉ፣ እንደሰርግ፣ ተዝካር ያሉ ማህበራዊ ትስስሮሽ ለጊዜው እንዲቆሙ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ ታግደዋል።
በዚህ አስከፊ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምን ሊያደርግ ይችላል? መልሱ ምንም ይሆናል። ሌላው ቀርቶ ቦርዱ የቫይረስ ሥጋት ጥርጣሬ በገባው ዕለት የዋና ጽ/ቤቱን ዘግቶ እስከመሄድ የደረሰበት ሁኔታ በቅርቡ የመገናኛ ብዙኃን ወሬ ነበር። ይህም ሆኖ የቫይረሱ ሁኔታ በምርጫው ላይ ምን አንደምታ ይኖረው ይሆን በሚል የሚመለከታቸው ፓርቲዎች ጋር ከሰሞኑ ምክክር ማድረጉም የሚታወስ ነው።
ከቦርዱ በተገኘ መረጃ መሠረት በስብሰባው ላይ የገዢው ፓርቲን ጨምሮ 45 የፖለቲካ ፓርቲዎች በሁለት የተለያየ ዙር በዚህ ጉዳይ ላይ በተደረገው ውይይት የተሳተፉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ያለው አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ለጥቂት ሳምንታት እንኳን ከቀጠለ በቀጣይ በዋናነት መፈጸም በሚገባቸው የመራጮች ትምህርት፣ የአስፈጻሚዎች ስልጠና፣ የቁሳቁስ ስርጭት ከፍተኛ የሰው ዝውውርን የሚያሳትፉ በመሆናቸው የመራጮች ምዝገባ ዝግጅት ላይ የሚያደርሰውን ተጽእኖ ለፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አቅርቧል። ከዚህ በተጨማሪ ወረርሽኙ በዚሁ መልኩ ከቀጠለ ምርጫው ዝርዝር አፈጻጸም እና የጊዜ ሰሌዳ ላይ ሊያደርስ የሚችለው ተጽእኖዎችን እና ሊፈጠሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ግምገማ ከፓርቲዎች እና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በተከታታይ እንደሚያደርግ አሳውቋል።
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ካስከተለው ችግር ጋር ተያይዞ ቦርዱ በአሁን ሰዓት የዕለት ተዕለት ሥራዎችን በብቃት እያከናወነ ነው ማለት እንደማይቻል ለቦርዱ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ለዚህ ዘጋቢ ነግረውታል። ሌላው ቀርቶ ሰዎችን ሰብስቦ ማነጋገር የሚቻልበት ሁኔታ አለመኖር በቦርዱ ሥራ ላይ ከባድ ጫናን አሳርፏል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የምርጫ ማስፈጸሚያ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሩቅ ሳንሄድ በመጋቢት እና በሚያዝያ ወራት ብቻ የሚካሄዱትን ትልልቅ ክንውኖች እንመልከት። መጋቢት 28 ቀን 2012 ዓ.ም የምርጫ ጣቢያዎች ዝርዝር ይፋ የሚደረግበት ነው። ከመጋቢት 28 እስከ ግንቦት 12 ስለመራጮች ምዝገባ ትምህርትና መረጃ መስጫ ጊዜ ነው። ከሚያዝያ 14 እስከ ግንቦት 13 ቀን 2012 ዓ.ም የመራጮች ምዝገባ ጊዜ ነው። እነዚህ ክንውኖች ብቻ የብዙ አካላት ተሳትፎ የሚፈልጉ ናቸው። የኮሮና ቫይረስ ባህርይ አኳያ እነዚህን በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ ማከናወን እንደማይቻል ለማንም ግልጽ ነው። ለመራጮች ትምህርት ለመስጠት ሰዎችን መሰብሰብ የግድ ነው። በአሁን ሰዓት መንግሥት ቫይረሱን ለመግታት ካስቀመጠው መመሪያ አኳያ ይህን ሥራ ማከናወን አለመቻሉ የቦርዱን የጊዜ ሰሌዳ አፈጻጸም ያዛባዋል። ከምንም በላይ ደግሞ ሕዝቡ በአሁኑ ወቅት ቫይረሱ ያስከተለውን ጫና ስር ሆኖ እየማቀቀ ባለበት ወቅት ስለምርጫ ማውራት በራሱ ከሕዝብ ቀዳሚ ፍላጎት በተጻራሪ እንደመቆምም ሊቆጠር ይችላል።
እንደመሰናበቻ
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዘንድሮ የምርጫ ክንውን ላይ አሉታዊ ጫና የማሳረፉ ነገር ፀሐይ የሞቀው እውነታ ሆኗል። አሁን ቀጥሎ ምን ይደረግ? የሚለውን ግን ገዥው ፓርቲ እና ተቀናቃኝ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ ምሁራን፣ የወጣት ተወካዮችና ሌሎች ጉዳዩ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው አካላት ሊያስቡበት የሚገባ ጉዳይ ነው። መንግሥት የኮሮና ወረርሽኝን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ከእነዚህ ወገኖች ጋር ተከታታይ ውይይቶችን ማድረግም የሚገባው ጊዜ ቢኖር ዛሬ ነው። በአንድ በኩል ዜጎች ከአስከፊው ወረርሽኝ የመጠበቁ ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ በሌላ በኩል የምርጫው ሥራ ሁሉም ወገን ባሳተፈ መልኩ አንድ የሚያግባባ መፍትሄ እንዲያገኝ ሁሉም ወገኖች በቅንነት ሊንቀሳቀሱ ይገባል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 / 2012
ፍሬው አበበ