ዓለማችን በዘመናት ሂደት በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ በሆኑ አደጋዎች በዓመታት ፍርርቆሽ ውስጥ ስትናጥ ኖራለች፤ ለችግሮችና አደጋዎቿም የየዘመኑን ልህቀት ያማከለ መፍትሄ ስትሰጥ ቆይታለች፤ በችግሮቹ ጠባሳም ለዘመናት በትውልድ ቅብብሎሽ ሲነገር ሲዘከር መኖሩ ቀጥሏል። የቅርብ ጊዜዎቹን በርድ ፍሉ እና ኢቦላን የመሳሰሉትም የዚህ አንድ ማሳያ ሲሆኑ፤ የዚሁ የዘመናት የዓለማችን ክስተቶች አንድ ገጽታ የሆነው የአሁኑ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝም ዛሬ ላይ በመቶ ሺዎች በበሽታው የተያዙበት፤ በአስር ሺዎችም ሕይወታቸውን ያጡበትና የሰው ልጆች ማህበራዊ መሰረት የተፈተነበት እውነት ሆኗል።
ይህ ዓለምና ህዝቦቿን ያስጨነቀ፤ ከሞት ጋር ግብግብ አጋጥሞ ጠቢባን ለመፍትሄ እንዲተጉ፣ ፖለቲካኞችም እንቅልፍ አጥተው ስለ ህዝባቸው እንዲጨነቁ ያደረገው የኮሮና ቫይረስ ወደ አገራችን ኢትዮጵያ ከገባ ዋል አደር ብሎ፤ የሞት ዜና ባንሰማም ከአስር የዘለሉ ሰዎች ህመሙ ተገኝቶባቸዋል። በሽታውም ወረርሽኝ እንደመሆኑ ዘር ቀለም ሳይለይ እምነት ሳይመርጥ ሁሉንም የሰው ልጅ የሚያጠቃ መሆኑን የተረዱ ከአገር መሪዎች እስከ መንደር ወጣቶች ድረስ በእኔነት ስሜት ችግሩን ለመግታት እየሰሩ ይገኛል። ሆኖም ‹‹የእናት ሆድ ዥንጉርጉር›› እንዲሉ ጥቂት ራስ ወዳድና ችግሩን ለራስ ጥቅም ማግኛ አድርገው ሊጠቀሙ የሚሯሯጡ የገንዘብም የፖለቲካም ነጋዴዎች አልታጡምና ሃይ ሊባሉና ሊወገዙ ይገባል።
በአንፃሩ በህዝብ ላይ አንዣብቦ በመጣ ፈተና ወቅት እኔ የምኖረው ህዝቤ ሲኖር ነው፤ ህዝቤን በችግሩ ዝም ብዬው ገንዘቤን ባሳድድ የሰበሰብኩትን ገንዘብ የትና ከምን ጋር ሆኜ ልበላው፣ ለልጆቼስ ምን ታሪክ ላስተምር ነው፤ ያሉ እልፍ ወገኖች ስለህዝባቸው ሲታትሩ፤ ዝቅ ብለውም ህዝባቸውን በበጎነት ሲያገለግሉ ተስተውሏል። እኛም በዛሬው ሀገርኛ እትማችን ከገንዘብ በፊት ህዝብ ይቀድማል፤ ህዝብ ሲኖር ነው ያለውም የሚበላው ኑሮውም በደስታ የሚሞላው ብለው ከመደበኛ ስራቸው በተጓዳኝ የኮሮናን ቫይረስ በመከላከል ሂደት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ እያሳረፉ ያሉ የአንድ ባለታክሲ ተግባርና ተሞክሮ ይዘን ቀርበናል።
አቶ ተስፋዬ መላኩ ይባላሉ፣ በ‹‹ዘ-ሉሲ›› ታክሲ የፋይበር ሜትር ታክሲ አባል ናቸው። ሁለት ሮቶዎችን በመኪናቸው ላይ ጭነው በየደረሱበት የእጅ ማስታጠብ አገልግሎት ሲሰጡ ተመለከትናቸው። ተግባሩ ቀልባችንን ቢገዛው ይሄን ለማድረግ ምን አነሳሳቸው? ዓላማውስ ምንድን ነው? በሚሉት ዙሪያ አነጋገርናቸው። ምላሹንም ከራሳቸው አንደበት እንደተነገረው በቀጥታ እንዲህ አቅርበነዋል። የዚህ ተግባሬ ዓላማው ሁለት ነው። አንዱ እንደ አገርም እንደ ዓለምም ትልቅ ፈተናና ችግር የሆነውን የኮሮና ቫይረስ በመከላከል ሂደት ውስጥ የድርሻዬን ማበርከት ሲሆን፤ ይሄም የጠቅላይ ሚንስትሩን አገራዊ ጥሪ ተግባራዊ የማድረግ ፈጣን እርምጃ ነው።
ሁለተኛው ዓላማ ደግሞ ማህበራዊ ኃላፊነቴን የመወጣት እርምጃ ነው። ማህበራዊ ኃላፊነት ሲባል፣ አንደኛ፣ አሁን ያለውን ነገር ከመቀልበስ አኳያ እኛም ያገባናል ብለን ከመንግስት ጎን መቆምን የሚመለከት ሲሆን፤ እኔም እንደ ግለሰብ ይሄን በምን መልኩ ላደርግና ሃላፊነትን ልጋራ ይገባል ብዬ ቁጭ ብዬ ሳስብ አንድ ሀሳብ መጣልኝ። ይሄም ለትራንስፖርት አገልግሎት በምጠቀምባት ሜትር ታክሲ ኮርቶ መጋላ ላይ ሁለት ሮቶዎችን በመበየድ አንድም ለተገልጋዮች፤ ሁለትም የጎዳና ተዳዳሪዎችን፣ ሶስትም በስራ ባህሪያቸው ምክንያት ቶሎ ወደቤታቸው ደርሰው ውሃ የማግኘት ሰፊ እድል የሌላቸውን ፖሊሶችና የትራፊክ ፖሊሶች እንዲሁም ሌሎች ሰዎች መንገደኞችን እጅ ማስታጠብን ያለመ ነበር። ለዚህም ሁለት ሰላሳ ሰላሳ ሊትር በድምሩ ስልሳ ሊትር የሚችሉ ሁለት ሮቶዎችን ኮርቶ መጋላ ላይ በመጫን አገልግሎቱን መስጠት ጀመርኩ።
ለምሳሌ፣ አየር ማረፊያ(ኤርፖርት) በምንሄድበት ጊዜ የተለያዩ የውጭ ዜጎች አሉ፤ ከአረብ አገር የሚመጡ ሴት እህቶቻችንም አሉ፤ እነዚህ ደግሞ አድረው የሚወጡ እንደመሆናቸው መታጠብን ይፈልጋሉ። ለእነዚህ የውጭም ሆኑ የኢትዮጵያ ዜጎች ይሄን መሰል የማስታጠብ አገልግሎት መስጠት ደግሞ አንድም በሽታውን ከመከላከል አኳያ ማህበራዊ ሃላፊነትን ከመወጣት ባለፈ፤ ለዚህን አይነት መልካም ዓላማ እነዚህን ወገኖች ማገልገል በራሱ የሚያስከብርም የሚያኮራም ተግባር ነው።
ምክንያቱም እንደ ግለሰብ በታክሲ አገልግሎት ከ16 ዓመት በላይ አገልግያለሁ። በዚህ ሁሉ ዓመታት ጉዞ ውስጥ ህብረተሰቡ ውለታ ስላለብኝ የዚህን ህብረተሰብ ውለታ መመለስ እፈልጋለሁ። ምንም እንኳን እኔም የህብረተሰቡ አንድ አካል እንደመሆኔ ችግሩ የጋራ ቢሆንም፤ ራሴንም እየጠበኩ ሌሎችን መጠበቅ ስላለብኝ የራሴን ድርሻ መወጣት እንዳለብኝ ወሰንኩ። ምክንያቱም ቀደም ሲል ላዳ ስንሰራ ሲበላሽብን እየገፋ ጭምር በአሮጌ መኪና ከእኛ ጋር እየተቸገረ እስከዛሬ አድርሶናል። በህዝብ እና በመንግስት ድጋፍ በተመቻቸ እድል ተጠቅመንም አዲስ መኪና ስንይዝ ከእዳ ነጻ ሆነን ስንሰራም የዚህ ህዝብ ድጋፍና ውለታ የሚዘነጋ አይደለም። ሁሌም ቢሆን ከቤታችን ስንወጣ ፈጣሪን ለምነንና ህብረተሰባችንን ተማምነን ነው። በዚህ መልኩ በመልካሙ ግዜ ሲያግዘኝ የነበረው ህዝብ ውለታ ስላለብኝም ይሄን ህብረተሰብ በዚህ አስከፊ ግዜ በጥቂቱም ቢሆን ከጎንህ አለሁ ማለት እፈልጋለሁ።
ይህ ክስተት ከዚህ በተቃራኒው ግን የሚሰሩ አሳዛኝ ምግባር ያላቸው ግለሰቦች አሳይቶናል። ሆኖም በየትኛውም ማህበረ ስርዓት ቢሆን ህዝብም ሆነ መንግስት ጠላት የለውም፤ ጠላት የሚሆኑት እንዲህ ወቅት እየጠበቁ በህዝብ ችግር ላይ ተመስርተው ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ ስግብግብ ነጋዴዎች ናቸው። እነዚህ ደግሞ ከብዙ መልካም ነጋዴዎች መካከል እንደ ስንዴ ውስጥ እንክርዳድ የሚበቅሉ ስግብግቦች ሲሆኑ፤ የህዝብን ችግር እንደ ችግራቸው ከማየት ይልቅ ባቋራጭ ለመክበርና ሀብት ለማጋበስ የሚሯሯጡ ናቸው።
እኔ የሚገርመኝ ግን በዚህ መልኩ በህዝብ ችግር ላይ ቆምረው የሚያገኙትን ገንዘብ የት ቁጭ ብለው ሊበሉ እንዳሰቡ ነው። ይሄ ያልተገባ አሻጥር ሲሆን፤ ሰው ሰራሽ የሸቀጦች እጥረትን በመፍጠርና ዋጋን በመጨመር የሚከናወነው ተግባር ደግሞ አንድም የግል ጥቅምን የማሳደድ፤ ካልሆነም ህዝቡ በመንግስት ላይ እንዲማረር የማድረግ ዓላማ ነው። ይህ ደግሞ ለነጋዴውም ሆነ ለማንም የማይጠቅም፤ የሚያሳዝንና የሚያሳፍርም ነው። እኔም በዚህ ተግባር በጣሙን አዝኛለሁ፤ ህብረተሰቡም ሊያወግዘው ይገባል።
እኔም ወደዚህ ስራ ስገባ ይሄንኑ በመገንዘብ አራት መሰረታዊ መልዕክቶችን በማስተላለፍም ነው። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ‹‹እባክዎትን እጅዎትን ላስታጥብ›› የሚል ሲሆን፤ ይሄም የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ከመቀነስ አኳያ እጅ መታጠብ ጉልህ ድርሻ እንዳለው የማስገንዘብም፤ የማገዝም ተግባር ነው። ሁለተኛው የጠቅላይ ሚንስትሩን መርህ መሰረት ያደረገ ‹‹አንዳችን ሌላችንን እንጠብቅ›› የሚል ሲሆን፤ ‹‹ፎር ኦል ኔሽንስ/ ለሰው ልጅ በሙሉ›› የሚል መልዕክት ያለው ሶስተኛው መርሄም፤ እኔ የምጭነውና አገልግሎት የምሰጠው ሰው ከመላው ዓለም የሚመጣ ጥቁር ነጭ፣ አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ አፍሪካ፣ ኤስያና ሌላውም አህጉርና አገር ህዝብ መሆኑን የሚያመለክት ነው።
ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ የበርካታ አገራት ዲፕሎማቶችና ዜጎች መዳረሻ፤ አዲስ አበባም ትልቅ የዲፕሎማቶችና ዓለማቀፍ ተቋማት መገኛ ከተማ፤ እንደ አገርም ሰፊ የቱሪስም ሀብትና ፍሰት ያለባትና ተጠቃሚነቷ እያደገ ያለች አገር እንደመሆኗ እኔ የምሰጠው አገልግሎትም ይሄንኑ ያማከለ፤ ኢትዮጵያዊነት ወግና እሴትንም የተላበሰ መሆኑን የገለጽኩበት ነው። አራተኛው የጽሑፍ መልዕክቴ ‹‹አይ ፕራውድ ቱ ሰርቭ ዩ/ እርሶን በማገልገሌ ደስታ ይሰማኛል›› የሚል ሲሆን፤ ዘር፣ ብሔር፣ ቀለምና ሃይማኖት ሳልለይ ሁሉንም የሰው ልጅ በእኩልነት በገዛ ፈቃዴ ማገልገል በመቻሌ ደስታና ኩራት የሚሰማኝ መሆኑን ያመለከትኩበት ነው። ይህ ለሰዎች ችግር የመድረስና አጋር ሆኖም የማገልገል በጎ ተግባር ደግሞ ኢትዮጵያዊ ባህልና ወግ ሲሆን፤ ከዚህ በተቃራኒው የሰዎችን ችግር ተገን አድርጎ ሰዎችን ማግለልና የራስን ጥቅም ለማሳካት የሚደረግ ሩጫ ግን ሊወገዝና ሊታረም የሚገባው እኩይ ድርጊት ነው። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያንን የእርስ በእርስ መተጋገዝን ብቻ ሳይሆን፤ የውጭ ዜጎችን ቀርቦ ማገዝን ይጨምራል።
ለምሳሌ፣ አንድ የውጭ ዜጋ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ከአውሮፕላን ትኬት ጀምሮ የታክሲ፣ በግብይትና የሆቴል አገልግሎቶችን በመጠቀም ሂደት ውስጥ ብዙ መልካም ነገርን ይዞ ይመጣል። ይህ ሁሉ አንድ ወገንን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ዜጋ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚጠቅም ነው። እናም በዚህ መልኩ የሚገለጽ አስተዋጽዖ የሚያበረክት የውጭ ዜጋን በችግሩ ጊዜ ከማገዝና ከማበረታታት ያለፈ ለአንድ ወገን ባልተላከ በሽታ ምክንያት በቅርቡ እንደተሰማው አይነት ማግለልና ሌላም ችግር መፍጠር ተገቢ አይደለም። ምክንያቱም ችግሩ ራስን ከመጠበቅ እንጂ ሌሎችን ከማግለል ጋር የሚገናኝ አይደለም።
እኔም ይሄን መሰል አገልግሎት ለሁሉም የሰው ዘር ያለአድሎ መስጠት በመቻሌ ደስታ የሚሰማኝ ሲሆን፤ እንደ አገርም ቢያንስ ሶስትና አራት ተቋማትን ወክያለሁ ማለት እችላለሁ። ከእነዚህ መካከል አንዱ መንገድ ትራንስፖርት ሲሆን፤ ይህ ተግባሬም በዘርፉ የተሰማሩ ሁሉ ከራስ ባለፈ ለሰዎች ደህንነት ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አስተምሬበታለሁ የሚል እምነት አለኝ። እናም በአዲስ አበባም ሆነ ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አካላት ይህ ችግር እንደሚያልፍ በመገንዘብ እስከዛሬ ሲተባበራቸው የነበረውን ህዝብ በችግሩ ጊዜ አለኝታ ሆነው ሊያግዙት፤ ከታሪፍ፣ ከትርፍ መጫንና መሰል ነገሮች ጋር በተያያዘ ሊፈጠር ከሚችል ያልተገባ ተግባር መቆጠብ ይኖርባቸዋል። ይህን ማድረግ ሲችሉ የበሽታውን ስርጭት ሂደት በመግታት ውስጥ የድርሻቸውን እያበረከቱ መሆኑን አውቀው ሊደሰቱና ሊኮሩ፤ ይህን የማያደርጉና ህዝቡ እንዲተፋፈግ በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት እንዲባባስ ካደረጉ ደግሞ ህዝብን በጥቅም የቀየሩ መሆናቸውን አውቀው ሊያፍሩና ከድርጊታቸውም ሊቆጠቡ ያስፈልጋል።
ሁለተኛው ወክዬዋለሁ ብዬ የማምነው የቱሪዝም ተቋምን ሲሆን፤ እኔ የማደርጋት ይህቺ ትንሽ መልካም ተግባር የኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ገጽታ በመቀየርና ሰዎች ስለ ኢትዮጵያውያን አዎንታዊ ምልከታ እንዲኖራቸው ጥቂት አስተዋጽዖ ይኖራታል፣ ለኢትዮጵያ ቱሪዝም እድገትም አበርክቶ ታደርጋለች የሚል እምነት አለኝ። ሶስተኛው ወክዬዋለሁ ወይም ስራውን አግዤዋለሁ የምለው ተቋም ደግሞ የጤናው መስሪያ ቤት ሲሆን፤ ወረርሽኙን ከመከላከል አኳያ ሰዎች ንጽህናቸውን እንዲጠብቁ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ውቂያኖስን ለመሙላት አንድ ጠብታ ውሃ እንደ ማበርከት ቢሆንም እጅ በማስታጠብ ተግባር በመሰማራቴ አግዣለሁ የሚል እምነት አለኝ። በተለይ እኔ ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀስኩ የምሰራ እንደመሆኑም ማንኛውም ፈቃደኛ የሆነና ሊታጠብ የፈቀደ ሁሉ በእኔ የታክሲ ላይ ሮቶ ውሃን መጠቅም ይችላል።
ይሄን በማዘጋጀት ሂደት ከሮቶ ግዢና ብየዳ ጀምሮ ያለው ወጪ ከኪሴ ሲሆን፤ በየቀኑ ጥቅም ላይ የሚውለው የውሃም ሆነ የሳሙና ወጪም በተመሳሳይ ከኪሴ የሚወጣ ነው። ይህ ግን ለዓመታት ከህዝብ ጋር ሰርቼ ያገኘሁት እንደመሆኑ ትናንትም ሆነ ዛሬና ነገ ከጎኔ ሆኖ ለሚኖር ህዝብ መልካም ስራ ስል ያዋልኩት እንደመሆኑ እርካታን እንጂ ቁጭትን አያሳድርብኝም። ሆኖም በሂደቱ የሚያጋጥሙኝ በርካታ ችግሮች አሉ። ለአብነት፣ ነጮች እንዲታጠቡ ስጋብዛቸው ያገለልኳቸው ያህል እየተሰማቸው ፈቃደኛ ያለመሆን የሚስተዋልባቸው ሲሆን፤ ይሄን የማስረዳት ትልቅ ስራ ይጠይቃል። ኢትዮጵያውያንም ቢሆን ተግባሩን የሚደግፍና የሚያበረታታ በርካታ ሰው የመኖሩን ያክል፤ የማከናውነውን ስራ ከፖለቲካ፣ ከጥቅም ፍለጋ፣ ከልወደድ ባይነትና ሌሎች ጉዳዮች ጋር በማያያዝ ሊያሸማቅቁኝ የሚሞክሩ ሰዎችም አሉ።
ይህ ሙገሳም ሆነ ወቀሳ ደግሞ የሚጠበቅና ሌላው ቀርቶ ጠቅላይ ሚንስትሩ ዝቅ ብለው ቆሻሻ ባጸዱና አበባ በተከሉ ሲደርስባቸው የነበረ ጉዳይ እንደመሆኑ ከዓላማዬ ወደኋላ የሚያደርገኝ አይሆንም። ከዚህ ሁሉ ግን የሳኒታይዘር ጉዳይ ፈተና የሆነብኝ ሲሆን፤ ምንም እንኳን በገንዘቤ የምገዛው ቢሆንም ከነማ መድሃኒት ቤቶች ጭምር በተደጋጋሚ ተሰልፌ ማግኘት አልቻልኩም። ይህ ደግሞ ሰዎችን እጅ ካስታጠብኩ በኋላም ሆነ በእጅ የሚነካኩ የመኪና ውስጥ ብረትና መሰል ነገሮችን በአልኮል ለማጽዳት የማደርገው ጥረት ላይ ፈተና ሆኖብኛል። በመሆኑም የሚመለከተው አካል ይሄን ተገንዝቦ በእርዳታ ሳይሆን በግዢ የማገኝበትን እድል ቢፈጥርልኝ የበለጠ ለስራዬ አጋዥ ይሆነኛል።
ምክንያቱም በአገር የመጫን ችግር የመከላከል ስራ ለአንድ ወገን ወይም መንግስት ብቻ የሚተው ባለመሆኑና ሁሉም ባለው አቅም ልጅ አበርክቶ ሊኖረው እንደሚገባ ስለማምን ነው እኔም ያለምንም ድጋፍ ስራውን የጀመርኩት። በርካታ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችም ይሄን መሰል ሃላፊነት ወስደው በየመንገዱና ሰፈሩ በእጅ ማስታጠብ ተግባር ላይ ተሰማርተው ህዝቡን ዝቅ ብለው ሲያገለግሉ ይስተዋላል። እኔም 60 ሊትር ጭኜ ስራውን ስሰራ፤ ሮቶዎቹን በጫንኩበት ቦታ እቃ ጭኜ የማገኘውን ገንዘብ ትቼ ነው። ምክንያቱም ገንዘብ ከህዝብ ጤንነት አይበልጥምና። መልካም ነገር ለመስራት ትልቁ ነገር ስለ ህዝብ ራስን ማስገዛት፤ ለህዝብ ቅድሚያ መስጠት፤ የምኖረውም የምጠቀምውም ህዝብ በሰላም ወጥቶ በጤና ሲገባ ነው ብሎ ማመን፤ አገርን ስለመውደድና ነገ ለልጄ ምን ማስረክብ ብሎ መጨነቅ ነው።
ይህ ችግር ሌላው ቀርቶ አህጉርን ከአህጉር ያልለየ በመላው ዓለም ላይ ባሉ የሰው ልጆች ላይ የመጣ ወረርሽኝ ነው። ይሄን መከላከል ደግሞ የእከሌና የእከሌ ተብሎ የሚተው፤ የሚሰራውንም በማሸማቀቅ የሚፈታ አይደለም። ሁሉም በአንድነት ሊሰራ የሚጠበቅበት ነው። በየቦታው የታዩ መልካም ጅምሮችም የዚሁ ማሳያ ናቸው። ሆኖም እንዲህ አይነት ስራዎች በአንድ ሰሞን ሞቅታና ዘመቻ ተከናውነው የሚቆሙ መሆን የለባቸውም። ይልቁንም ችግሩ እስኪወገድ ድረስ በትጋት ያለማቆራረጥ ሊተገበር ያስፈልጋል። ከዚህ አኳያ በአንዳንድ አከባቢዎች ያለው እንቅስቃሴ ሲጀመር እንደነበርው በግለት ያለ አይመስልም። ለዚህ ደግሞ በየቦታው የነበሩ የእጅ ማስታጠብ ተግባራት አሁን ላይ በተቋማትና በተወሰኑ አከባቢዎች ተወስነው መስተዋላቸው ነው።
በመሆኑም እነዚህ የመልካምነት ተግባራት የህዝቡ ችግር የእኛም ችግር መሆኑን ተገንዝበን ቀጣይ ልናደርጋቸው ያስፈልጋል እንጂ ለአንድ ሰሞን የሚዲያ ፍጆታ ያክል ሞቅ ብሎ ሊከስም የሚገባው አይደለም። እኔም እንደ አንድ ግለሰብ ይሄን የምገነዘብ ሲሆን፤ ከዚህ ችግር ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ነጻ ሆናለች እስከሚባል ድረስ የምሰጠውን የእጅ ማስታጠብ አገልግሎት አጠናክሬ እቀጥላለሁ። ሌሎችንም አበረታታለሁ። ከዚህ ባለፈም የትኛውም ግለሰብም ሆነ ተቋም ለዜጎች ማደል የሚፈልጉት የጽዳትም ሆነ የአፍ መሸፈኛ ቁሳቁሶችን በእኔ መኪና ውስጥ በማኖር እንዳድልላቸው ማድረግ ይችላሉ። ምክንያቱም ደስታዬም እርካታዬም ህዝብን ዘንግቶ ገንዘብ ማግኘት ሳይሆን ህዝብ ጤናው እንዲጠበቅና ያለኝን ከህዝብ ጋር ሆኜ በደስታ ተካፍዬ መጠቀም ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2012
ወንድወሰን ሽመልስ