ዓለማችን የደረሰችበትን የቴክኖሎጂ ደረጃ የሚፈታተን ጋሬጣ ከፊቷ ተደቅኗል፤ ኮሮና ቫይረስ። ይህ ወረርሽኝ በስልጣኔያቸው አንቱታን ያተረፉትንና ከፈጣሪ በታች ማንኛውንም ነገር መስራት ይችላሉ እስከማለት የተዘመረላቸውን አውሮፓውያን ጭምር ከመፈተን አልፎ እጅ እስከማሰጠት ደርሷል። ጣልያን፣ ስፔንና ጀርመንን የመሳሰሉ አገራት የዜጎቻቸውን እልቂት ለማስተናገድ ተገደዋል።
ወረርሽኙ በመጀመርያ የተከሰተው በቻይና መሆኑ ይታወቃል። በወቅቱም አንዳንድ አገራት ቻይናን እስከማግለል የደረሱበት ሁኔታ እንደነበር ይታወሳል። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢኮኖሚ እድገቷና በዜጎቿ ታታሪነት ዓለምን እያስደመሙ ያለችው ቻይና ለዚህ በሽታ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት መከላከሉ ላይ ተረባረበች። ዜጎቿም የመንግስታቸውን ትዕዛዝ በመቀበል በቁርጠኝነት ተንቀሳቀሱ። እናም በዓለም ላይ ሃያል የመሆን ግስጋሴዋን ዳግም በጤናውም መስክ አስመዘገበች። ቻይና በዚህ ጥረቷ የበሽታውን ስርጭት በመቆጣጠር ግንባር ቀደም መሆን ችላለች።
በአንፃሩ የአውሮፓውያኑ፤ በተለይ የጣልያን ተሞክሮ ደግሞ ከዚህ የተለየ ነው። በሽታው ወደ አውሮፓ የገባው ከቻይና በኋላ ቢሆንም በመጀመርያዎቹ ቀናትና ሳምንታት ስለበሽታው የነበረው ግንዛቤ አነስተኛ ፤ አገሪቱ ለመከላከል ያደረገችው ጥረትም አናሳ ሲሆን ህዝቦቿ በሽታውን ለመከላከል የነበራቸው እንቅስቃሴ አዝጋሚ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። በዚህ መዘናጋት የተነሳም በአሁኑ ወቅት በዓለማችን በበሽታው ምክንያት ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ገብታለች። በአሁኑ ወቅትም አገሪቱ በዓለማችን ትልቁን የሰዎች ሞት እያስተናገደች ትገኛለች።
በጣልያን በአንድ ቀን ብቻ 800 የሚጠጋ ሰዎች ያለቁባት አገር ስትሆን ወረርሽኙ ከተከሰተ ወዲህ ብቻም ከሰባ ሺህ በላይ ዜጎቿን አጥታለች። በርካታ ሰዎችም በየዕለቱ ለበሽታው በመጋለጥ ላይ ናቸው። በቻይናና በጣልያን መካከል ያለው ልዩነት የተፈጠረው ደግሞ ወረርሽኙን ለመከላከል ተገቢውን ትኩረት በመስጠትና ባለመስጠት መካከል ባለው ልዩነት የተከሰተ ነው።
በአገራችንም በሽታው ከተከሰተ ከሁለት ሳምንታ በላይ ተቆጥረዋል። ነገር ግን እስካሁን ብዙ ጉዳት አላደረሰም። በተለይ አንድም ሰው በበሽታው ምክንያት ህይወቱ አለማለፉ ትልቅ ስኬት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ይህ የሚያዘናጋን ሊሆን አይገባም። ምክንያቱም እንደነጣልያንና ስፔን መዘናጋት በኋላ ላይ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል።
አሁን በአገራችን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እጅን በሳሙናና በውሃ በአግባቡ ከመታጠብና ንፅህናን ከመጠበቅ አንፃር እንዲሁም ሳኒታይዘርና ሌሎች የእጅ ማፅጃ ኬሚካሎችን ከመጠቀም አንጻር እየተደረጉ ያሉ ስራዎች በጥሩ ጎኑ የሚነሱ ናቸው። እነዚህ ተግባራትም ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል። ይህ ደግሞ በተቋማትም፣ በየመንገዱም ሆነ በተለያዩ ስፍራዎች የሚታይ ነው።
ያም ሆኖ ግን አሁንም ቢሆን የመከላከሉን ስራ በአግባቡ ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ መዘናጋት ይስተዋላል። በተለይ በትራንስፖርት ውስጥ አሁንም ተጠጋግቶ የመንቀሳቀስ እና የመሰለፍ እንዲሁም የመጨባበጥና የመተቃቀፍ እንዲሁም ቫይረሱን ለማስተላለፍ የሚያስችሉ ግንኙነቶች አሁንም ሙሉ ለሙሉ አልተገደቡም። በሃይማኖት ተቋማትም ተጠጋቶ የመፀለይና ለቫይረሱ ሊያጋልጡ የሚችሉ ድርጊቶች ይስተዋላሉ። ይህ ደግሞ ቫይረሱን ለማስፋፋት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል።
የጤና ባለሙያዎች እንደሚመክሩት በሽታውን ለመከላከል አንደኛው መንገድ ማህበራዊ ጥግግትን ማስቀረት ሲሆን ከዚህ ጎን ለጎንም የተለያዩ ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉ ኬሚካሎችን መጠቀምና እጅን በተደጋጋሚ ለሃያ ሰከንድ በሳሙናና ውሃ መታጠብ ነው። በመሆኑም እነዚህን የጤና መርሆዎች በአግባቡ በመጠበቅ የቫይረሱን ስርጭት መከላከል ይገባል። ይህ ደግሞ ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር ነው።
በሌላ በኩል አፍና አፍንጫን በመሸፈን እና የእጅ ጓንትንም መጠቀም ሌላው በሽታውን የመከላከያ መንገድ እንደሆነ ይታወቃል። ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎችን ከማበረታታት ይልቅ የመተቸትና አልፎ አልፎም ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የመመልክት ሁኔታ ይስተዋላል። ይህ ደግሞ በሽታውን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፍ በመሆኑ በአጭሩ ሊገታ ይገባል።
በመሆኑም ይህንን ወረርሽኝ ለመከላከል በአንድ በኩል ከመንግስትና ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችና መመሪዎችን በመተግበር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለራሳችንና ለቤተሰባችን ጥንቃቄ በማድረግ ይህን ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ መከላከል ያስፈልጋል። ከዚህ አደጋ ለማምለጥ ብቸኛው መንገድ በመሆኑ ሁላችንም እንጠንቀቅ። ለራሳችን ስንጠነቀቅ ለሌሎችም እንተርፋለን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2012