ከሚያብዱት ጋር ከማበድ ይልቅ ከአጥሩ ዘለቅ ብለው አይተው ትውልድን የሚያስጠነቅቁ ሰዎችም ሆኑ መገናኛ ብዙኃን ቢኖሩም የማይሰሙት ግን በየጊዜው እየበዙ ናቸው። ልምዳቸው ነው ይጩሁ የሚሉት ይበራከታሉ። ነገር ግን ለመጥፊያቸው መንገዶችን እያስተካከሉ መሆናቸውን አልተረዱም። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሁለት የመጽሀፍ ቅዱስ ታሪኮችን በማንሳት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በእይታዎቹ ያስቃኘውን ሃሳብ እንጠቁም።
የመጀመሪያው የኖኅ ታሪክ ሲሆን፤ በምድር ላይ ሊመጣ ያለውን የጥፋት ውኃ ለማስቆም ለ120 ዓመታት ያህል ትውልዱን መከረ፣ ዘከረ። ግን የሚሰማው ሰው አልነበረም። ይልቁንም መጥፋት ቀርቷል እያለ የበለጠ የጥፋቱን መስመር ማስፋቱን ተያያዘው። በዚህም ሕዝቡ በንፍር ውሃ ተጥለቀለቀ። ለመዳንም መንገድ አላገኘም።
ሁለተኛው ደግሞ የነብዩ ዮናስ ታሪክ ነው። በዘመኑ ልዕለ ኃያል ወደነበረችው የአሦር ዋና ከተማ ነነዌ ተልኮ ትውልዱን አስተማረ። የሀብት ብዛት የሥልጣን ትዕቢትና ጥጋብ የነፋቸው ነነዌያውያን ለያዥ ለገራዥ አስቸግረው ነበርና ራሳቸውን እንደ ምርጥ ዘር እንዳይመለከቱ፣ ሁሉ ለእኛ ሁሉም ወደ እኛ እንዳይሉ መከራቸው። ከዚያ በፊት በምድር ላይ ተሠርቶ የማያውቅ ግፍ በከተማቸው ውስጥ ይሠሩ ነበርና ይህንን ተግባራቸውን እንዲያቆሙ፤ ይህንን ካላደረጉ ግን እንደሚጠፉ ነገራቸው።
እነርሱም በሦስት ቀናት ምክር ብቻ ተመለሱ፤ በዙፋን ላይ ካለው ንጉሥ ጀምሮ እስከ አገልጋዩ ድረስ አሜን ብለው ተቀበሉት። በዚህም 100ሺህ ሰዎች ከጥፋት ዳኑ። እነዚህ ሁለት መዳኖች በቀጥታ ከስደት ጋር በእጅጉ ይቆራኛሉ። «ፈጣሪ እንዳለ» በሚል ምንም ሳይዘጋጅላቸው ጉዟቸውን ከአገር ውጪ የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን በርካታ ናቸው። ይሁንና መገናኛ ብዙኃን በስደት ምክንያት ይህ ሆነ የሚል ተሞክሮን በየገጻቸው ላይ ማስነበባቸውን አልተውም።
በተለይም እድሜያቸው 18 ሳይደርስ ሞልቶኛል በሚል የሃሰት መረጃ ፓስፖርት ይሰራልን የሚሉት ቁጥር ስፍር የሌላቸው የመሆኑ ምስጢር ያለመስማታቸው ምክንያት ነው። አሁን አሁን በኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ በጣም እንደተቸገረ በተደጋጋሚ ይናገራል። ምክንያቱም ሲታዩ 13ን የማይዘሉ ልጆች 21ና ከዚያ በላይ ተብሎ መታወቂያ ይሰራላቸዋል። አንድ ተጓዥ ወደ ኢሚግሬሽን ሲያቀና 8ኛ ክፍልን ማጠናቀቁ፣ እድሜው ከ21 በላይ መሆኑና በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ በኩል እውቅና ማግኘቱ ይረጋገጣል። ይሁንና መታወቂያው በተሳሳተ መንገድ መሰራቱን ለማረጋገጥ ብዙ ውጣ ውረድ አለውና ለመመለስ ይሞከራል። ሆኖም ያለመቀበል ደግሞ ያስጠይቃልና እድሜያቸው ሳይደርስም የሚላኩበት ሁኔታ ይኖራሉ። ይህ ደግሞ ከሄዱ በኋላ የሚደርስባቸው ችግር የትየለሌ እንዲሆን ያደርጋል። እናም ከቤተሰብ የጀመረ የአመለካከት ለውጥ መምጣት አለበት። ለዚህ ደግሞ የሚባለውንና የሚነገረውን ሰሚ ትውልድ ያስፈልጋል።
«ከውጭ በተለያየ ጉዳት ሳቢያ ወደ አገር ውስጥ ይህን ያህል ሰው ተመለሰ፣ እንዲህ ገጠማቸው» በሚል የተለያዩ ተሞክሮዎች በየጊዜው በመገናኛ ብዙኃኑ ይነገራል። በተለይ ከአደጋና ከሞት ጋር በተያያዘ የሚደመጡት የሚዘገንኑ ናቸው ። ይህንን አይቶ ወደ ተግባር ለመቀየር የውስጥ ፍላጎት ሊኖር ይገባል። በተለይም በአካል ሄደው የመጡ የሚሰጡትን ትምህርት ተቀብሎ በተግባር መተርጎም ከሄያጁ ይጠበቃል።
«እንደ እድሌ ነው የምኖረው፤ እዚህም እዚያም ሞት አለ» በሚል ደካማ አስተሳሰብ ምክንያት ሁልጊዜ ስደትን መናፈቅ አይበጅም። የወደቀውን እንጂ የተለወጠውን ብቻ ትኩረት ማድረግ አይገባም። ይልቁንም ምርጫን የሚወስነው ራሱ ባለቤቱ ነውና መዓቱን በሦስት ቀን ሱባኤ እንደመለሰው አለዚያም በንፍር ውሃ እንደተዋጠው መሆን የግለሰቡ እይታ ሊሆን ይገባል። ጥልቅ ምልከታ ዛሬ ይኑር።
ሁሉም መመረጥ ያለበት የብዙዎች ዕብደትን ተከትሎ መጓዝን ሳይሆን፤ ጥፋቱ እንዳይከተለው ምን ማድረግ እንዳለበት ማወቅ ነው። ራስን ማዳን ላይ ማተኮር አለበት። እንደ ኖኅና እንደ ዮናስ የሚያስጠነቅቁ ሰዎች ባሉበት ዘመን መጠቀም ያልቻለ በማይመከርበት ጊዜ ላይ ከመጣ የበለጠ ዋጋ ይከፍላልና ምክርን ለችግር መፍቻነት ማዋል ያስፈልጋል።
በትምህርቱ እንደ ዮናስ ሌሎችንም መታደግ አለዚያም እንደ ኖኅ እራስን ማዳን ያስችላልና መጠቀሙ ለነገ መባል የለበትም። የሁለቱንም መንገድ መከተል ያልቻለ ዋጋ ይከፍላልና መጠንቀቅ ይበጃል።
ኖኅ ራሱንና ቤተሰቡን ሲያድን አስተምሮ የሚሰማው ስላጣ ነው። ግን ድርሻው መናገርና ማስጠንቀቅ ነበርና አድርጓል። እንደዚያ ሁሉ መገናኛ ብዙኃንና በችግሩ ውስጥ ያለፉ ሰዎች ሁልጊዜ እየተናገሩ ነውና የመጠቀሙ ሁኔታ የራስ ድርሻ ነው። እንዲህ ባለው ጊዜ አቋምና እምነትን አጽንቶ፣ ትምህርቱ ምን እንደሚመስል ተገንዝቦ ወደትክክለኛው መንገድ የመግባት ምርጫ ተሰጥቷል። «በርታና ጩኽ፤ እውነቱንም ተናገር። ከቻልክ እንደ ዮናስ ሕዝብ ታተርፋለህ ካልቻልክ ግን ቢያንስ ራስህን ታወጣለህ» የተባለለትም መገናኛ ብዙኃን የዘወትር ስራው ያደረገው ለዚህ ነውና ልብ ያለው ልብ ይበል። የራሱን ምርጫ ያስተካክል።
አዲስ ዘመን ጥር 5/2011