ስለፖለቲካው፣ ኢኮኖሚው፣ ግለሰባዊ ሕይወትም ሆነ ማንኛውም ነገር ለማውራት ቅድሚያ የአገርና የሕዝብ ሰላምና ደህንነታቸው ሊጠበቅ ይገባል። አገርና ሕዝብ ሰላምና ደህንነታቸው ሳይረጋገጥ እንኳንና የዓመቱን የነገን ማለም ከቶውኑ አይታሰብም።
በተለያዩ ጊዜያት ተከስተው የዓለማችንና ሕዝቦቿን ደህንነት የተፈታተኑ በርካታ ችግሮችን ምድራችን አስተናግዳለች። ሰው ሰራሽ በሆኑት ሁለት የዓለም ጦርነቶች የሰው ልጅ ህልውና ሊያከትም ከጫፍ ደርሶ እንደነበርም የታሪክ ድርሳናት ያወጉናል።
ከዚህም በተጨማሪ አንዴ በቫይረስ ሌላ ጊዜ ደግሞ በባክቴሪያ አማካኝነት የተከሰቱ በሽታዎችና ወረርሽኞችም በምድራችንና በሕዝቦቿ ህልውና ላይ ከፍተኛ ስጋት ሲደቅኑ እንደኖሩና አሁንም እንዳሉ ለማንም ግልጽ ነው። የኋላ ኋላ ጊዜያዊም ዘላቂ መፍትሄ ቢገኝላቸውም ኤች አይቪ ኤድስ፣ ሳርስና ዚካ የመሳሰሉት በሽታዎች ዓለማችንን አስጨንቀውና የበርካታ ነዋሪዎቿን ሕይወት ቀጥፈው እንዳለፉ የቅርብ ጊዜ ትውስታዎቻችን ናቸው።
አሁን ደግሞ በተራው ዓለማችንና ሕዝቦቿን ለከፍተኛ አደጋ በመዳረግ የበለጸጉ የሚባሉ አገራትን ሳይቀር ከሰማይ ካልሆነ በስተቀር ምድራዊ ተስፋችን ተሟጧል እስከማስባል የደረሰው አደገኛ የኮሮና ቫይረስ ምድራችንን ያስጨንቃት ይዟል። ከቻይና እስከ አሜሪካ፣ ከጣሊያን እስከ ብራዚል፣ ከግብጽ እስከ ደቡብ አፍሪካ በዚሁ ኮሮና በተባለ ቫይረስ ወረርሽኝ የተነሳ ዓለማችን ስታምጥ ውላ ስታምጥ ማደር ዕጣ ፈንታዋ ሆኗል።
ከበሽታው አደገኛ የመተላለፍ ባህሪ የተነሳና እስካሁን ድረስም ይህ ነው የሚባል መፈወሻ መድኃኒትም ሆነ መከላከያ ክትባት ከመጥፋቱ ጋር ተያይዞ ብቸኛው መፍትሄ ከእንቅስቃሴ መታቀብ ሆኖ በርካቶች ሳይወዱ በግድ ቤታቸውን ቆልፈው በቤታቸው ለመቀመጥ ተገደዋል።
የሕክምና መስጫ ተቋማት ከሚገባው በላይ በሰዎች ተጨናንቀዋል፣ ሌት ተቀን ሲያመርቱ የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ባድማ ሆነው በጸጥታ ተውጠዋል።
የአየርና የየብስ ትራንስፖርትም በከፍተኛ ሁኔታ ተስተጓጉሏል። በምርቱ ዓለምን ሊያበልጽግ የሚችል ትልቅ ኃይል ከበሽታው ስጋት የተነሳ እጅና እግሩን አጣጥፎ ቤቱ ለመቀመጥ ተገዷል።
የዚህ በሽታ ጦስ ለአገራችንም ተርፎ እስካሁን ድረስ 12 ሰዎች በቫይረሱ እንደተጠቁ ተረጋግጧል። ይህንንም ተከትሎ መንግሥት ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ፣ በርካታ የመንግሥት ሠራተኞች በቤታቸው ሆነው ሥራቸውን እንዲያከናውኑና የኢትዮጵያ አየር ወደ 30 አገራት የሚያደርገውን በረራ እንዲያቋርጥ አድርጓል።
ከወረርሽኙ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የአበባ፣ የጨርቃ ጨርቅና የቆዳን የመሳሰሉ ምርቶች የውጭ ገበያ በከፍተኛ ሁኔታ ተቀዛቅዟል።
እስካሁን ባለው መረጃ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ190 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኪሳራ ደርሶበታል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ቀድሞውኑ በድህነት ውስጥ በነበረው ኢኮኖሚያችን ላይ ይህን መሰሉ አስከፊ ችግር መደረቡ ኢኮኖሚያዊ ችግሩን ወደከፋ ደረጃ ያደርሰዋል።
ወረርሽኙ ከባድ እንደመሆኑ ከዚህ በኋላም የሚያስከትለው ጉዳት የከፋ እንደሚሆን ይታሰባል። የውጭ ምንዛሬ ግኝቱን በከፍተኛ መጠን እንደሚቀንሰው፣ በውጭ ኢንቨስትመንት ግኝቱ ላይ ደንቃራ እንደሚሆንና ለሥራ አጥነት ችግሩ መባባስ ከፍተኛ ምክንያት እንዲሆን እንደሚያደርገው ይታመናል።
ከዚህ በተጨማሪ በሌለ አቅም ለሕክምና የሚወጣውን ወጪም ያንረዋል። የዕለት ሥራዎች ሰርተው አስፈላጊ ወጪዎቻቸውን በመሸፈን ጉሮሯቸውን ደፍነው በሚያድሩ ዜጎች ላይ የሚያደርሰውም አሉታዊ ተጽእኖ በቀላሉ የሚገመት አይሆንም።
ይሁንና ጨለማውን በመጋፈጥ ጽልመቱን መግፈፍ እንጂ በጨለማው ላይ በማፍጠጥ የሚመጣ ለውጥ ስለሌለ ይህን ችግር በተባበረ ክንድ መክቶ የሕዝብንና የአገር ህልውና ለማስቀጠል ከመስራት ውጪ ሌላ ምንም ዓይነት መፍትሄ አይኖርም።
ስለሆነም መንግሥት አላስፈላጊ ወጪዎችን በመቀነስና የውጪ ድጋፎችን በማሰባሰብ ኢኮኖሚውን ለመፈወስ ጠንክሮ መስራት ይኖርበታል። ዜጎችም ጤናቸውን በመጠበቅና አላስፈላጊ ወጪዎችን ለጊዜው ገታ በማድረግ ራሳቸውን የመፍትሄ አካል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ዓለም አቀፍ ለጋሾችና የኢኮኖሚ አቅማቸው ጠንካራ የሆኑ ወዳጆቻችንም በዚህ አደገኛ ጊዜ እውነተኛ ወዳጅነታቸውን በዕዳ ስረዛና በእርዳታ በመተግበር የምር ወዳጅ መሆናቸውን ሊያስመስክሩ ይገባል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2012