አዲስ አበባ፡- ትናንትና መጋቢት 15 ቀን 2012 በተጀመረውና በቀጣይ ለአንድ ሳምንት በሚቆየው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቦንድ ሽያጭ ሳምንት እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ህዝቡ በንቃት እንዲሳተፍ ተጠየቀ፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን ዘጠነኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በትናንትናው የቦንድ ሽያጭ ሳምንት በይፋ ሲጀመር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ እንደተናገሩት በአሁኑ ሰዓት የግድቡ ግንባታ 71 በመቶ ተጠናቋል ፡፡
በእስካሁን ሂደት ህዝቡ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ባደረገው ድጋፍ 13 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሯ ግድቡ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው በሃገር ውስጥና በመላው ዓለም በሚኖሩ ኢትዮጵያውን ድጋፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የግድቡን ዘጠነኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በተጀመረው የቦንድ ሽያጭ ሳምንትም “እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ህዝቡ በንቃት በመሳተፍ ግንባታውን ለማጠናቀቅ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ” ብለዋል፡፡
በቦንድ ሽያጭ ሳምንት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለ እየሱስ በቀለ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም እንደተደረገው ሁሉ በአሁኑ የቦንድ ሽያጭ ሳምንትም የቦንድ ሽያጭና ህትመት የሚከናወነው በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል በመሆኑ ባንኩ አስቀድሞ ዝግጅቱን አጠናቆ እየተጠባበቀ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የታደሙት የዋሪት ሙሉ ጥላ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዳይሬክተር ወይዘሮ ትህትና ለገሰ አንድ ሚሊዮን ብር ለግድቡ ግንባታ ስጦታ ያበረከቱ ሲሆን በዕለቱ በጠቅላላው አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሁለት ሺ ብር ተሰብስቧል፡፡
“ጤናችን ይጠበቃል፤ ግድባችን ይጠናቀቃል” በሚል መሪ ሃሳብ ከትናንትና ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በሚዘልቀው የቦንድ ሽያጭ የቦንድ ስጦታ ለሚያበረክቱ 1000291929609 ፣ የቦንድ ግዥ ለሚፈጽሙ 1000291927738 የባንክ ሂሳብ ቁጥር መክፈቱን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 16 /2012
ይበለ ካሳ