የዓለም የጤና ድርጅት የዓለም የጤና ስጋት ብሎ ባወጀው በኮረና ቫይረስ (ኮቪድ-19) የመጀመሪያ ተጠቂ የሆነው ሰው መጋቢት አራት ቀን 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ መገኝቱ ይፋ ተደርጓል። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የጤና ባለሙያዎች ማህበረሰቡ እንዴት እራሱን ከወረርሽኙ መከላከል እንዳለበት በሰፊው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን በተለያዩ መንገዶች በማሰራጨት ላይ ናቸው።
ከጤና ባለሙያዎች ባሻገር የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ማህበረሰቡ ማህበራዊ ንክኪን በመቀነስና እጅን በእያንዳንዱ ንክኪ በንጹህ ውሃና ሳሙና በመታጠብ እንዴት እራሱን ከቫይረሱ መከላከል እንደሚገባ በመገናኛ ብዙሃን የግንዛቤ ማስጨበጫ ቢሰጡም፤ በአዲስ አበባ ጀሞ አንድ በተለምዶ ኢስት ዌስት አካዳሚ አካባቢ የሚኖሩ የመዲናዋ ነዋሪዎች ግን እንኳን በእያንዳንዱ ንክኪ እጅን በመታጠብ እራሳቸውን ከቫይረሱ ሊከላከሉ ቀርቶ የሚጠጡት ውሃ አጥተው እየተቸገሩ መሆናቸውን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተናግረዋል።
የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት አቶ ልዑልሰገድ ሰይፉ እንደሚሉት፤ ከሁለት ወር በፊት ውሃ በፈረቃ ከሶስት ቀን አንድ ቀን ሲያገኙ እንደነበር አውስተው፤ ከሁለት ወር ወዲህ ግን በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ውሃ እያገኙ ነው።
ነገር ግን የመጀመሪያው የኮረና ቫይረስ ተጠቂ በኢትዮጵያ መገኝቱ ይፋ ከሆነበት ቀን ማግስት ጀምሮ የአካባቢው ማህበረሰብ ውሃ በሳምንት አንድ ቀን እንኳን ለማግኘት እንደተቸገረ አቶ ልዑልሰገድ ጠቁመው፤ አማራጭ በማጣታቸው ለመጠጥነት የሚውል የታሸገ ውሃ ገዝቶ ከመጠቀም ባለፈ እራሳቸውን ከቫይረሱ ለመከላከል አንድ ጀሪካን ውሃ ከ 30 እስከ 40 ብር እየገዙ በመጠቀም ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኑሮ ውድነቱ ጣራ ነክቶ ሰው ዳቦ ገዝቶ ለመብላት ጊዜ ውሃን በዚህ መልኩ ለመግዛት ያቃተው ብዙ ነዋሪ እንዳለም አመልክተዋል።
በሚኖሩበት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሰዎች እንዴት እራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ቢሰጡም ውሃ በአካባቢው በመጥፋቱ ማህበረሰቡ እንዴት አድርገን ነው ራሳችንን የምንጠብቀው የሚል ስጋት ላይ መው ደቁንም ጨምረው ገልጸዋል።
ስለዚህ በጋራ መኖሪያ ቤት ሰውና መጸዳጃ ቤት በአንድ ላይ የሚኖር በመሆኑ በቂ የውሃ አቅርቦት ኖሮ ማህበረሰቡ የግል ንጽህናውን መጠበቅ ካልቻለ፤ ለቫይረሱ ተጋላጭ የሚሆንበት እድሉ ሰፊ መሆኑን ተናግረዋል።
“አሁን ላይ ውሃ ማለት የአንድ ሰው በህይወት የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው፤ መንግስት ለህብረተሰቡ በሚገባ የውሃ አቅርቦት ለማዳረስ በገባው ቃል መሰረት ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን እንኳን ውሃ የሚያገኝበትን መንገድ ያመቻችልን ” ብለዋል።
በአካባቢው ለሰባት አመታት እንደኖሩ የሚናገሩት ወይዘሮ መልካምስራ አፈወርቅ በበኩላቸው፤ ጀሞ አንድ ቀደም ሲልም ከፍተኛ የውሃ ችግር ያለበትና በተለይም እርሳቸው የመንግስት ሰራተኛ ስለሆኑ በሳምንት አንድ ቀን በፈረቃ የሚመጣውን ውሃም ቢሆን ውሃው ቀን ሲመጣ ቤት ስለማይኖሩ የማያገኙበት ሁኔታ ከመኖሩ ባለፈ ቤት እያሉ ውሃው በሚመጣበት ወቅትም ወዲያውኑ በቂ ውሃ ሳይዙ ተመልሶ የሚሄድበት ሁኔታ መኖሩን ይናገራሉ።
ነገር ግን ቀደም ሲል እንደአሁኑ አሳሳቢ የጤና ችግር ባለመኖሩ ለመጠጥ የሚሆን ትንሽ ውሃ ካገኙ አብቃቅተው ከሳምንት ሳምንት እንደሚደርሱ ገልጸው፤ አሁን ላይ የዓለም የጤና ስጋት የሆነው የኮረና ቫይረስን ለመከላከል እጅን በተገኘው አጋጣሚ መታጠብና ልብስና ገላን በየቀኑ ማጽዳት እንደሚገባ የጤና ባለሙያዎች ቢመክሩም በሳምንት አንድ ቀን እንኳን ውሃ ለማግኘት ስለተቸገሩ አይደለም ጽዳትን ለመጠበቅ ውሃ ጠጥቶ ለማደር መቸገራቸውን ተናግረዋል።
ስለዚህ ከቫይረሱ እራስን ለመከላከል የመጀመሪያ ጥንቃቄ ተደርጎ የተወሰደው እጅን በንጹህ ውሃና ሳሙና መታጠብ እንዲሁም በየዕለቱ የግል ንጽህናን መጠበቅ አማራጭ የሌለው ቢሆንም፤ በቂ የውሃ አቅርቦት በአካባቢው ባለመኖሩ ህብረተሰቡ የተሰጠውን ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ እየተቸገረ መሆኑን ጠቁመዋል።
አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ውሃ የለም ማለት ማህበረሰቡን ወደ ሞት ጎዳና መጋበዝ ስለሆነ፤ መንግስት አስፈላጊውን የውሃ አቅርቦት ለማህበረሰቡ አደርሳለሁ ብሎ በገባው ቃል መሰረት በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ወረርሽኙ ተከስቶ ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ በፊት ቃሉን እንዲፈጽም ላሳስብ እወዳለሁ ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ዘለቀ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ፤ በመዲናዋ ውሃ እጥረት በመኖሩ በፈረቃ ውሃ እንዲዳረስ እየተደረገ ነው። በጀሞ አንድም በተመሳሳይ እንደሌሎች አካባቢዎች በተቀመጠው ፈረቃ ማህበረሰቡ የውሃ አቅርቦት እያገኝ እንደሆን ነው መረጃው ያለኝ ብለዋል።
ነገር ግን የጀሞ አንድ ማህበረሰብ በተቀመጠው ፈረቃ የውሃ አቅርቦት ያላገኝበትን ምክንያት ከቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ መረጃ አጣርተው ምላሽ የምንሰጥ መሆኑን የገለጹት ስራ አስኪያጁ፤ ባለስልጣኑ ችግሩንም እስከታች ድረስ ወርዶ በመስራት እንዲስተካከል ያደረጋል ብለዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 16 /2012
ሶሎሞን በየነ