
አዲስ አበባ፡- ራሳቸውን ጠብቀው ህብረተሰቡ ራሱን መከላከል እንዲችል የሚያግዝ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በቀበሌ ደረጃ ላሉ አመራሮች እየተሰጠ መሆኑን ብልጽግና ፓርቲ ገለጸ፡፡ በማህበራዊ ሚዲያዎችና አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ፓርቲው አባላቱን በብዛት እየሰበሰበ ስልጠና እየሰጠ ነው የሚለው ውንጀላ የተዛባና የራስን ፍላጎት ለማራመድ የሚደረግ ተግባር መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አወሉ አብዲ ትናንት እንደተናገሩት፤ በዓለም የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ አደገኛና ጥንቃቄን የሚሻ ብቻ ሳይሆን የአመራሩንም ቁርጠኝነት ይፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ብልጽግና ፓርቲና መንግስት በጋራ እየሰሩ ሲሆን፤ በቀጣይም ከህዝብ ጎን በመሆን ችግሩን ለመቀልበስ ይሰራል፡፡ በተለይም በየቀበሌውና ጎጡ ሊደርስ የሚችለው አመራር የዚህ ተግባር አጋዥ ሆኖ ራሱንም ህብረተሰቡንም ከቫይረሱ በመከላከል ሂደት የድርሻውን እንዲወጣ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እየተከናወነ ነው፡፡
እንደ አቶ አወሉ ገለጻ፤ ብልጽግና ፓርቲ በለውጡና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በየደረጃው ላሉ አመራሮች ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በዚህም ለውጡን ተከትሎ ባለው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችና የሰላም ጉዳዮች ዙሪያ በሶስት ዙር የአመራር ስልጠና እየሰጠ ሲሆን፤ ሁለቱ ዙር በስኬት ሲጠናቀቅ፤ ሶስተኛውና የቀበሌ አመራሮች ስልጠና ግን ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ጋር በመገጣጠሙ የተለየ መንገድ መከተልና እድሉን ለተሻለ ስራና ተልዕኮ መጠቀም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ለስልጠና የመጣውን አመራር ከመበተን ይልቅ ብሔራዊ የወረርሽኝ መከላከል ኮሚቴ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የጥግግት፣ የቁጥጥርና ጥንቃቄ መርሆችን በመከተል አመራሩ ቫይረሱን መከላከል በሚቻልበት ሂደት ላይ ግንዛቤ እንዲኖረው እየተደረገ ሲሆን፤ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራው አመራሩ ራሱን እንዲጠብቅ በሚደርስባቸው ቀበሌዎችና ጎጦች ሁሉ ህብረተሰቡን በማስተማር አስፈላጊውን የመከላከል ስራ እንዲያከናውን እድል የሚሰጠው መሆኑን አቶ አወሉ ተናግረዋል፡፡
አቶ አወሉ እንደሚሉት፤ ይሄን መሰል የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ መከናወኑ አመራሩ የህዝቡን ደህንነት ከመጠበቅ አኳያ የበኩሉን እንዲወጣ የሚያደርገው ሲሆን፤ ህብረተሰቡ ለሚያነሳቸው የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና የመልካም አስተዳደር ብሎም የሰላም ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ መስጠት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይም አቅጣጫ የሚቀመጥበት መድረክ ነው፡፡ መድረኩም ብሔራዊ ኮሚቴው ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በጤና ባለሙያዎች ጭምር ታግዞ በከፍተኛ ክትትል እየተከናወነ ይገኛል፡፡
በአንዳንድ አካላት ፓርቲው ብዛት ያላቸውን አባላት እየሰበሰበ እያሰለጠነ ነው በማለት የሚያናፍሱት የተዛባ መረጃ በመሆኑ ህብረተሰቡ ሊገነዘበው ይገባዋል፤ መረጃን አዛብቶ ማቅረብ የራስን ድብቅ አጀንዳ ለማራመድ መሆኑንም ማወቅ ያስፈልጋል ያሉት አቶ አወሉ፤ የተፈጠረውን ችግር ተጠቅሞ የተለያዩ የፖለቲካ አጀንዳዎችን በመፍጠር፤ የሸቀጦች እጥረትና ዋጋ እንዲንር የሚሰሩ አካላት መኖራቸውን መዘንጋት እንደሌለበት፣ ህብረተሰቡ ለተዛቡ መረጃዎች ቦታ ሳይሰጥ በሽታውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ ንቁ ተሳታፊና ከመንግስትና አመራር ጎን ቆሞ ቤተሰቡን፣ ህዝቡንና አገሩን ሊታደግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 16 /2012
ወንድወሰን ሽመልስ