ያለፉትን ሰንበቶች (ቅዳሜ እና እሁድ) ቤቴ አረፍ ብዬ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን እያዟዟርኩኝ እመለከት ነበር። አልጀዚራ፣ ቢቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ ቪኦኤ…በሚገርም ሁኔታ ዜና እና ትንታኔያቸው የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ብቻ የጎላበት ነበር። የእኛዎቹ እነኢቲቪም እንደዚያው። ምናልባትም የዓለም ሚዲያዎች እንደአሁኑ በአንድ አጀንዳ ዙሪያ ተሰብስበው የከረሙበት ጊዜ ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም።
የኮሮና ቫይረስ ከሰረገባቸው አገራት መካከል በተለይ እንደጣሊያን ጢባ ጢቤ የተጫወተበት አገር ስለመኖሩ አልሰማሁም። መዘናጋት በለው፣ ቸልተኝነት በለው…ጣሊያንን የቫይረሱ መነሻ ከሆነችው ቻይና በተለየ መዓቱን አውርዶባታል። የጣሊያን መንግሥት የሚያደርገው ጠፍቶት ሟች መቁጠርና መቅበር ሥራው ወደመሆን መሸጋገሩ አሳዛኝ ነው። ባለፈው ቅዳሜ ዕለት ብቻ ከ793 በላይ ዜጎች በሞት መነጠቋ ልብን የሚያደማ ነው። ምን ይህ ብቻ፤ በጣሊያን ቤርጋሞ የተሰኘው የመቀበሪያ ቦታ መሙላቱ በራሱ አስደንጋጭ ነበር።
በዚህም ምክንያት ሕዝቡ ሳይወድ በግድ የቁም እስረኛ እንዲሆን ተፈርዶበታል። በጣሊያን ኮሮና ቫይረስ የተቀሰቀሰባትና በቫይረሱ ክፉኛ የተጎዳችው የሎምባርዲ ግዛት ነዋሪዎቿ ለሳምንታዊ ግብይቶችና የግል ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወንም ጭምር በምንም ምክንያት ከቤታቸው እንዳይወጡ በመንግሥት ታግደዋል።
የጣሊያኗ ግዛት ይህንን ጥብቅ መመሪያ ያስተላለፈችው ባለፈው ቅዳሜ ዕለት ብቻ ጣሊያን ወደ ስምንት መቶ የሚጠጉ ሰዎችን በኮሮና ቫይረስ ማጣቷን ተከትሎ ነው ተብሏል።
በአጠቃላይ በጣሊያን ከተመዘገበው 4 ሺህ 825 ሰዎች ሞት ውስጥ 3 ሺህ ዘጠና አምስት የሚሆነው በሎምባርዲ ግዛት የተመዘገበ ነው ተብሏል።
በጎረቤት ኬንያ ምንም እንኳን ቫይረሱ ከባድ አደጋ ባያደርስም ጥንቃቄዋን ከፍ ካደረገች ሰንበት ብላለች። የኬንያ አየር መንገድ በረራ ካቆመ ቆየ። አሁን ደግሞ የኬንያ መንግሥት ሕዝቡ አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎችን በመላው አገሪቱ እንዲያቆም እና ቤት እንዲቆይ አዟል። ይህን በማይከተሉ ላይ በየደረጃው ሕጋዊ እርምጃ ይወስዳል ብሏል። በዚህ ውሳኔ መሠረት አውቶቡሶች አገልግሎት አቁመዋል። ማታቱ የሚባሉት ሚኒባሶች መጫን የሚፈቀድላቸው ጥቂት ሰዎችን ብቻ ይሆናል።
ቤተ እምነቶች በመላው አገሪቱ ታግደዋል። ሰዎች ሲሞቱ የቅርብ ቤተሰብ ብቻ አሥራ አምስት ሰው መቅበር ይፈቀድለታል።
የኬንያ ብሔራዊ የኮሮና ቫይረስ ቡድን የጤና ሚኒስትሩን፣ የፖሊስ ኮሚሽነሩን፣ የካውንቲ እና የግዛት ኃላፊዎችን እና ሌሎች ባለሥልጣናትን ያቀፈ ሲሆን ከልመና ወደ ማስገደድ መሄዳቸውን ገልጸዋል። ምግብ ቤቶች ገዝቶ ለሚሄድ ብቻ ይፈቀዳሉ። ከዚያ ውጪ ማንኛውም ስብስብ የተከለከለ ሲሆን አስፈላጊ ላልሆነ ጉዳይ ወደ ውጭ የሚወጡ ይጠየቃሉ። ከጣሊያኖች መዘናጋት እና የመንግሥትን ትዕዛዝ አለመስማት እንማር የሚሉት የኬንያ ባለሥልጣናት ያ መዘናጋት የሰለጠነችውን ጣሊያን በሽታውን ለመቆጣጠር ከአቅሟ በላይ አድርጓል፤ ከዚያ መማር እና መንግሥት አስገዳጅ እርምጃ መውሰድ አለበት ብለዋል።
ከመንግሥት ባለሥልጣናት በተጨማሪ የፓርላማ አባላት ጭምር በየአካባቢያቸው ካሉ ጋር ተባብረው አመራር እንዲሰጡ ትዕዛዝ ተላልፎ ማንኛውም መሰባሰብ በጥብቅ ተከልክሏል።
እኛስ? እኛም የጣሊያንን ሽቅብ ጎዳና ስለመያዛችን አስረጂ ምልክቶች አሉ። ሌላው ቀርቶ ተሰብስቦ መብላት መጠጣት፣ መሥራት፣ መጓዝ…ለቫይረሱ አጋላጭ መሆኑ እየተነገረ ባለበት በዚህ ወቅት የሚሰማው ሰው በተግባር አነስ ብሎ መታየቱ ያስገርማል።
እንግዲህ ማህበራዊ ርቀት ፍጠሩ ሲባል እምቢተኛ ሆነናል። በየቦታው በአጀብ ተቀምጦ መሰብሰብ ልማድ ቀጥሏል። አዲሱ ነገር ጀዳፍ ላይ እጅን መታጠብ ብቻ ነው። ቫይረሱ ደግሞ እጅን በሳሙና ሙልጭ አድርጎ በመታጠብ ብቻ የሚፈወስ ቢሆን ምንኛ ጥሩ በሆነ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ሁሉም የሀገሪቱ ድንበሮች ለሰዎች ዝውውር ዝግ መደረጋቸውን ከትናንት በስቲያ ሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም በተናገሩበት ወቅት ማህበረሰቡ ከንክኪ ተራርቆ እንዲንቀሳቀስ የተላለፈው መልዕክት ባለፉት ቀናት በአግባቡ እየተፈጸመ አይደለም ማለታቸውን ሰምተናል። በእርግጥም ጠ/ሚኒስትሩ ትክክል ናቸው። ሕዝቤ የቆየ፣ አብሮት የኖረ፣ አብሮት የተወለደና ያረጀ ልማዱን እንደኮት አውልቆ በቀላሉ ሊጥለው ስለመቻሉ ዛሬም፣ ነገም እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ግን ይህም ሆኖ በየተገኘው አጋጣሚ ከማሳሰብና ከማስተማር አለመቦዘን ብልህነት ይሆናል።
እናም አስገዳጅ ነገር እየመጣብን ነው። ለምን ቢሉ አማራጭ የለማ። እናም መንግሥት የኢትዮጵያ መውጫ መግቢያ ድንበሮቿን ከትናንት በስቲያ ሰኞ ዕለት ጀምሮ እንዲዘጉ ከመወሰን ጎን ለጎን የደኅንነት ዘርፉ ማኅበራዊ ርቀት (Social Distancing) እንዲያስተባብር ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ይህ ምን ማለት ነው? በቃ እንደደርግ ዘመን ተሰባስቦ፣ ተዛዝሎ የሚሄድን ሰው፣ ስብሰባ ጠርቶ ሰዎችን የሚያንጋጋ የፖለቲካ ፓርቲን «ተበተን» የሚል ኃይል መጣ ማለት ነው። ይህን በራሳችን ማድረግ አለመቻላችን ምንኛ ያሳዝናል።
ለመሆኑ ማኅበራዊ ርቀት (Social Distancing) መጠበቅ ሲባል ምን ማለት ነው?
ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅ ማለት ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚኖርን አላስፈላጊ ቅርርብና ንክኪን ማስወገድ ማለት ነው። ይህም ማለት በርካታ ሰዎች ሊገኙባቸው በሚችሉ የሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች ላይ የምናሳልፈውን ጊዜ መቀነስ ወይም ማስቀረት ነው።
ሁሉም ሰው በተለይ አዛውንቶችን፣ ነፍሰጡር ሴቶችና ለጉንፋን ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች በዙሪያቸው ካሉ ሰዎች ጋር የሚኖራቸውን መቀራረብ በማስወገድ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ ይመከራል።
እንዴት አድርገን ርቀታችንን እንጠብቃለን? የሚቻል ከሆነ ሥራችንን ከቤታችን ሆነን ማከናወን፣ አስፈላጊ ያልሆኑ ጉዞዎችን ማስቀረት፣ ቡና ቤቶች፣ የምሽት መዝናኛዎችና ብዙ ሰዎች ከሚሰበሰቡባቸው ቦታዎች እራስን ማራቅ፣ በተቻለ መጠን ከጓደኞችና ከቤተሰብ ጋር የሚደረግ መሰባሰብን ማስቀረት ያስፈልጋል። ከማኅበራዊ ግንኙነት በምንርቅበት ጊዜ ምን ማድረግ እንችላለን።
ከሌሎች ሰዎች በሁለት ሜትር መራቅ ከቻልን ከቤት ወጥተን በእግር መንሸራሸርና ዱብዱብ ማለት፣ የበሽታው ምልክት ከሌለባችሁ ለአረጋውያን የቤተሰብ አባላትና ለጎረቤቶቻችሁ ድጋፍ ማድረግ፣ ወደ መደብሮች በመሄድ አስፈላጊ ሸቀጦችን መግዛት፣ በቤት ውስጥ ፊልም ማየት፣ መጽሐፍት ማንበብ፣ በቤት ውስጥ ልጆችን ማስጠናት እና የመሳሰሉትን ማድረግና ጊዜያችንን በአግባቡ መጠቀም እንችላለን።
ልንተዋቸው ከሚገቡን ልማዶች አንዳንዶቹ
ይሉኝታን መጋፈጥ፣
በኢትዮጵያውያን ዘንድ ይሉኝታ ሰፊ ቦታ የሚሰጠው ነው። «ሠላም ባልለው ይቀየመኛል፣ ኮራህ ወይንም ኮራሽ ይለኛል…» በሚል ለሠላምታ እጅን መዘርጋት፣ መተቃቀፍ፣ መሳሳም… ለአደጋ ይዳርጋል። ማህበራዊ ሕይወት ላይ በስፋት መሳተፍ ማለትም ሐዘን፣ ሠርግ፣ ጠበል ጸዲቅ፣ ተዝካር፣ ልደት…መቀነስ፤ ከተቻለ ጨርሶ አለመሳተፍ የቫይረሱን ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ ያግዛል። እናም ይሉኝታን ማስወገድ እና ትክክለኛውን ሁኔታ ለሰዎች በማስረዳት ችግሩን መጋፈጥ ይገባል።
ጉርሻ፣
ሰብሰብ ብሎ ገበታ መቅረብ እና ጉርሻ ኢትዮጵያዊ መልክ አላቸው። ለዘመናት መለያችን ሆነውም ቆይተዋል። ገበታን አብሮ መቅረብ ለኮሮና ስርጭት የማርያም መንገድ መስጠት ነው። «ፍቅርና ጉርሻ ሲያስጨንቅ ነው» የሚለው የአበው ተረት በዘመነ ኮሮና አያስኬድም። ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት ግንኙነት ለቫይረሱ ስርጭት ምቹ መደላድል ነውና። እናም በሞቴ እየተባባሉ ጉርሻ ከመቀባበል በመላቀቅ «በሞቴ አታጉርሰኝ» ወደማለት ማሸጋገር የየራሳችን ኃላፊነት ነው።
የትራንስፖርት ችግርን በራሳችን አቅም መፍታት፣
አንዳንዶች እጅግ አጭር የሚባል ርቀት ለአብነት ያህል በአዲስአበባ ከተማ የ1 ብር 50 ሳንቲም መንገድ ወረፋ ጠብቀን፣ ተጉላልተን በታክሲና በአውቶቡስ መጓዝ የምንወድ ሰዎች እጅግ ብዙ ነን። ይህ ከኮሮና ጋር ብቻ ሳይሆን ከዘላቂ ጤና ጥበቃ ጋር ተያይዞ ትልቅ የስንፍና ምልክት ነው። አጭር ርቀት በእግር መጓዝ የሰውነት ክብደትን መቀነስን ጨምሮ ጤናን ለመጠበቅ እጅግ ጠቃሚ ነው። በተጨማሪም የኮሮና ስርጭትን ለመግታት የሚረዳ እርምጃ ነው። የእግር ጉዞ መለማመድ የትራንስፖርት እጥረት ችግርን ለመቅረፍም አንድ መንገድ ነው። እናም በእግር የመጓዝ ልማድ ሊሰለጥንብን ይገባል።
ሌላው የትራንስፖርት ችግርን ለመቅረፍ ረፈድ አድርገን ወደሥራ መውጣት የምንችል ሰዎች ይህን ዘዴ መጠቀሙ ትልቅ ጠቀሜታ አለው። ጠዋት በተለይ ከ1 ሰዓት ከ30 እስከ 2 ከ30 ድረስ ከመውጣት ይልቅ ከረፋዱ 3 ሰዓት በኋላ መውጣት ወይንም ማልዶ መውጣት የትራንስፖርት መጨናነቅ ስለሚቀንስ ለኮሮና ቫይረስ ሊኖረን የሚችለውን ተጋላጭነታችን ለመቀነስ በእጅጉ ይረዳል።
በተጨማሪም የመንግሥት ተቋማት የተቀጣሪዎ ቻቸውን ሁኔታ በማጣራት እንደየሁኔታው አንዳንዶች በቤታቸው ሆነው የሚሰሩበትን መንገድ እንዲመቻች በመንግሥት በኩል መፈቀዱ የትራንስፖርት ጫናውን ለመቀነስ ጉልህ ድርሻ አለው።
በተመሳሳይ ሁኔታ ሰዎችን አጨናንቀው የሚጭኑ የሕዝብ መጓጓዣ አገልግሎት ሰጪዎች በትራፊክ ፖሊስ እና በበጎ ፈቃደኞች አማካኝነት ቁጥጥር የሚደረግበት ሁኔታ እንደሚተገበር በመንግሥት ውሳኔ ማግኘቱም እንዲሁ ከሕዝብ ጤና ጥበቃ አንጻር የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ ነው።
አጠቃላይ መረጃ
የኮሮና ቫይረስ በቻይናዋ ውሃን ግዛት ለመጀመሪያ ጊዜ ከተከሰተ እነሆ አራት ወራትን ቆጠረ። በእነዚህ አጭር ጊዜያት ቫይረሱ ከቻይና ተነስቶ ወደ 193 ያህል አገራት ሊስፋፋ ችሏል (የዓለም አገራት ጠቅላላ ቁጥር 195 መሆኑን ልብ ይሏል)። እስከ ሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ብቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ 350 ሺ 457 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፤ 100 ሺ 354 ያህል ሰዎች አገግመው 15 ሺ316 ያህሉ ግብዐተ መሬታቸው ተፈጽሟል። ከፍተኛ ሞት ካስመዘገቡ አገራት መካከል ጣሊያን 5 ሺ 476 ሰዎችን በሞት በመነጠቅ ቀዳሚ ስትሆን ቻይና 3 ሺ 270 ሰዎችን እንዲሁም ስፔን 2 ሺ 180 ሰዎችን በሞት በመነጠቅ ተከታታይ ደረጃን ይዘዋል።
በቫይረሱ በመያዝ መጠን ቻይና (81ሺ093)፣ ጣሊያን (59ሺ 138)፣ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ (35ሺ 70) ዜጎቻቸው በቅደም ተከተል በቫይረሱ መያዛቸውን የወርልድ ሜትር ሪፖርት ያሳያል።
በኢትዮጵያ እስካለፈው ሰኞ ዕለት ቀትር ድረስ 11 ሰዎች ብቻ የቫይረሱ ምልክት እንደታየባቸው እና የሞተ ሰው አለመኖሩን መነገሩ የሚታወስ ነው። ደስ የሚለው ዜና ደግሞ ቫይረሱ ከተገኘባቸው መካከል ሁለቱ አገግመው ወደአገራቸው የመሸኘታቸው ነገር ነው። ዜናው እንዲህ ይላል።
«የጤና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ከተያዙ 11 ሰዎች መካከል ሁለቱ ጃፓናውያን ወደ ሀገራቸው መሸኘታቸውን አስታወቀ። ሌሎች በቫይረሱ የተያዙ እና ከሰዎቹ ጋር ግንኙነት ነበራቸው የተባሉ ሰዎችም ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል።
ከዚህ ቀደም በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች መካከል አራቱ የህመም ስሜት ማሳየት ማቆማቸውን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ መግለጻቸው ይታወሳል።»
በተጨማሪም ከሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ከውጭ የሚገቡ እንግዶች ለ14 ቀናት ተገልለው እንዲቆዩ የሚያስገድደው የመንግሥት መመሪያ በሥራ ላይ ውሏል።
የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቀነስ ከውጭ አገር የሚገቡ እንግዶች ለ14 ቀናት በራሳቸው ወጪ በሆቴል ቆይታ በማድረግ ጤንነታቸውን የማረጋገጥ ሥራ ይከናወናል።
በተለያየ መንገድ፣ ለተለያየ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ውጪ የነበሩ ወገኖች (የውጭ አገር እንግዶችን እንደሚጨምር ታውቋል) ወደ ኅብረተሰቡ ከመቀላቀላቸው በፊት ሁለት ሳምንታት ለየት ብለው የሚቆዩባቸውን ስፍራዎች መሰናዳታቸውን የአዲስአበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በማህበራዊ ድረገፃቸው ይፋ አድርገዋል። ዲፕሎማቶች በኤምባሲያቸው እንዲቆዩ ይደረጋል።
ከመንግሥት በተገለጸው መሠረት ለማረፊያ እንዲሆኑ የአየር መንገዱ ስካይላይት ሆቴል እና ግዮን ሆቴል መዘጋጀታቸውን መነገሩን ተከትሎ «ገንዘብ የሌላቸው እንግዶች ምን ሊሆኑ ነው» የሚል ጥያቄን አስነስቷል። ሆኖም ም/ከንቲባ ታከለ በቆይታ ጊዜው ወጪያቸውን ለመሸፈን ለማይችሉ ዜጎች ሙሉ ወጪያቸውን መንግሥት እንደሚሸፍን አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩል ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ሰኞ ዕለት ከደህንነት ዘርፍ ኃላፊዎች ጋር ከመከሩ በኋላ ይፋ እንዳደረጉት መንግሥት ለቫይረሱ መከላከያ 5 ቢሊዮን ብር መመደቡን ተናግረዋል። በተጨማሪም ከመጋቢት 14 ቀን አንስቶ፣ የደህንነት ዘርፉ በቁጥር የበዛ ሰው የሚሳተፍባቸውን ስብሰባዎችን የሚያስቆምና ማህበራዊ ርቀት መጠበቅን የሚያስተገብር ይሆናል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ የመንግሥት ተቋማት ማህበራዊ ርቀትን ተፈጻሚ ማድረግና ስብሰባ ሲያካሂዱ ቫይረሱን የመከላከል ቅድመ ጥንቃቄዎችን ተፈጻሚ ማድረግ እንዳለባቸው ተነግሯቸዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 16 /2012
ፍሬው አበበ