“መቻቻልን ናቅን፤ ለፀብ አሟሟቅን፣
ለአመፅ ስንነሳ፤ ለሰላም ወደቅን፣
ሀገር ስትቃጠል፤ ከዳር ሆነን ሞቅን። ”
በብልህ ብዕር የተከሸኑት እነዚህ ሦስት ስንኞች የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ በሚገባ የመግለጽ ብቃት አላቸው። (የታላቁን የጥበብ ሰው የጸጋዬ ገ/መድኅንን “ፍቅር ጠላን” ግጥም ያስታውሷል። ) ሀገር ስትታመም ባለሀገር አብሮ ያቃስታል፤ መሪዎችን የጭንቀት ውጋት ይቀስፋቸዋል። ታዳጊ ፍለጋም ዓይናቸውን ከወዲያ ወዲህ ማንከራተቱ የተለመደ ይሆናል። ዓለም በደዌ መማቀቅ ስትጀምር ግን የሰማይ ወስከነባይ ምድር ላይ ስለሚደፋ ህምሙ የጠና ይሆናል። ማን ለማን “አለሁ! ደረስኩልህ!” ይላል።
ፍጥረተ አዳም ቅስሙ እንክትክት ብሎ ስለሚሰባበር ሰማይ ምድሩ ይዞርበታል። ሰብዓዊያን ፍጡራን ብቻ ሳይሆኑ አራዊትና የቤት እንስሳት፣ እፅዋትና የባህር ነፍሳት ሳይቀሩ ተስፋቸው ተሰነጣጥሮ በህገ ልቦናም ይሁን በደመ ነፍስ፣ ብቻ በአንድነት እግዚኦ እያሉ ወደ ፈጣሪ የሚቃትቱ ይመስለኛል። ለምን ይመስለኛል? እያየነውም አይደል! እርግጥ ነው እንጂ!
ፕላኔታችን ከየትኛውም ዘመን ይልቅ ዛሬ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተጠቅታ አልጋ ላይ የዋለችው ብቻዋን ሳይሆን ከፍጡራኗ ሁሉ ጋር በክፉ ደዌ ተለክፋ ነው። “የታላላቅ ሀገራት ታላላቅ መሪዎች” ትምክህታቸው ወድቆ በተስፋ መቁረጥ ዓይናቸው ማዝ አርግዟል። የሥልጣናቸው ትሩፋት እጅግም የረዳቸው አይመስልም። ይልቁንም ወደ ፀባዖት ማንጋጠጡን መርጠዋል። እኛን መሰል በማደግ ላይ ያሉ በርካታ ሕዝቦችም የመድኃኒት ግኝቱ ተስፋ ገና ቀጠሮው ስላልታወቀ ከመጣው ክፉ ወረርሽኝ ለማምለጥ አምላካቸውን አጥብቀው እየተማፀኑ ይገኛሉ።
በዚህ ጨፍጋጋ ወቅት ከዚህ ወረርሽኝ ጋር ግብ ግብ ፈጥረው ድሉን ለመቀዳጀት እየተፋለሙ ላሉት ተመራማሪዎችና የየሀገራቱ የሕክምና ባለሙያዎች ከፍ ያለ አክብሮትና ምሥጋና ሊቸራቸው ይገባል። መልካም ቀን ያላቀራረባቸው አንዳንድ መንግሥታትም ሳይቀሩ ዓለም አቀፉን ደዌ ግንባር ፈጥረው በቁጥጥር ስር ለማዋል እየተወያዩና እየተመካከሩ፤ እየተረዳዱና እርስ በእርስ እየተመካከሩ ለመቀራረብ ሲሞክሩ እያስተዋልን ነው። በአንጻሩ በሕዝብ እልቂት ትርፍ ለማጋበስ፣ ጊዜያዊ ሀብት ለማፈስ ህሊናቸውን የሸጡ አንዳንድ ዓለም አቀፍም ይሁን የሠፈር ነጋዴዎችና አገልግሎት ሰጭዎች (በእኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሀገራትም ጭምር) የህሊናቸውን ዓይን ዓይነርግብ ሸፍነው እየተስገበገቡ ከደዌው እኩል ሕዝብ ሲያስለቅሱ እየተመለከትን ነው። ድርጊታቸው ከክፉ እርግማን ቢከፋ እንጂ አያንስም።
የዓለማችንን ውሎ አምሽቶ በግርድፉ እንቃኝ ብንል ጥቅል ምልከታው የሚከተለውን ይመስላል። በኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በአሁኑ ወቅት አውሮፓ ምጡ በዝቷል። ሰሜን አሜሪካም ግራ መጋባቱ ጨምሯል። አፍሪካ የፍርሃት ቅዝቃዜ ውስጡን እያንቀጠቀጠ አንዘፍዝፎታል። የአረብ ሀገራት የእንቆቅልሹ ፍቺ ጠፍቷቸው ናውዘዋል። ኤዢያ በመፍትሔ እጦት ተናውጧል። ላቲን አሜሪካ ናላው ዞሯል። ስካንድኔቪያ ሀገራት ክፉው ወረርሽኝ ደጃፋቸውን በርግዶ እንዳይገባ ደጅ ደጃቸውን እያዩ በፍርሃት ተደናግጠዋል። በአጭሩ ሁሉንም አህጉራት እንደ ጫጩት በብብቷ ሰብስባ የያዘችው ዓለማችን በወቅታዊው የቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በኢኮኖሚ መዳሸቋና መፍትሔ እጦቷ እንደተጠበቀ ሆኖ በሕዝቦቿ የታደጉኝ እዮታ አቅሟ ተልፈስፍሷል። ጥቁር የሀዘን ከል ለብሳም በቁዘማ ላይ እንዳለች መርዶው በነጋ በጠባ እየደረሰን ነው።
እንዲህም ሆኖ ግን ወረርሽኙን ለመግታትና መፍትሔውን ለማመላካት የየሀገራቱ ተመራማሪዎች በየላቦራቶሪያቸው ማይክሮስኮፕ ላይ አቀርቅረውና አፍጥጠው በምርምር እየተጉ ስለመሆናቸው መካድ አይቻልም። የብዙኃን መገናኛ ጥረትም ዋጋው ከፍ ያለ ነው። የሃይማኖት ቤተሰቦች ወደ ፈጣሪያቸው በመማጠን እየቃተቱ እንዳሉም ማስታወሱ አግባብ ይሆናል። ብዙ ሀገራት ለባዕዳን ዜጎች ድንበሬን አትሻገሩ በማለት በራቸውን መጠርቀማቸው እንዳለ ሆኖ በርቀትና የአቅምን ያህል መተጋገዛቸውም አልቀረም። ሁሉም የየራሱን ቤት እሳት ለማጥፋት መረባረብ ላይ ስለሆኑ ሊኮነኑና ሊተቹ አይገባም።
ወቅቱ የሰው ልጅ እውቀትና ጥበብ የተፈተነበት፣ የኢኮኖሚውና የፖለቲካው ጡንቻ የሟሸሸበት፣ ለጋስ የነበሩ ሀገራት ለእርዳታ እጃቸውን የዘረጉበት፣ የሥልጣኔያቸውን ምጥቀት ከፍ አድርገው የሚያንጎራጎሩ መሪዎች አንገት ደፍተው የተከዙበትና በለሆሳስ ድምጽ ሕዝባቸውን እያጽናኑ የሚውሉበት የዘመን ክፉ ሆኖ ተመዝግቧል።
ወረርሽኙ ከተራ ዜጎች እስከ ዝነኞች፣ ከተመሪዎች እስከ መሪዎች፣ ከግለሰብ ጓዳ እስከ ቤተመንግሥት ዙፋን፣ ከታካሚ እስከ አካሚ፣ ከመራጭ እስከ ተመራጭ፣ አቤት የስብጥሩ አበዛዝ! ሁሉም የሰው ዘር፤ ቀለም፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሥልጣኔ፣ ድህነት፣ ብልፅግና ልዩነት ሳይፈጠር የአዳም ዘር በሙሉ በጥቃት ሰለባው ተዳብሷል።
ይህንን ወረርሽኝ ለመርታት የበርካታ ሀገራት ምሁራን፣ የኪነ ጥበባት ባለሙያዎች፣ የፖለቲካ ልሂቃንና የማኅበረሰብ አንቂዎች የሚያለያያቸውን የግልና የቡድን አጀንዳዎቻቸውን ለጊዜው አቆይተው እውቀታቸውንና አቅማቸውን ሁሉ በአንድነት በማስተባበር የራሳቸውን ሕዝብና ሰፊውን የዓለም ማኅበረሰብ ክፍል ለመድረስ አቅም የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ እየጣሩ ነው። በፍርሃት የዛለውን ሰብዓዊ ፍጡር ሁሉ በማረጋጋቱና በማጽናናቱ ረገድም በምሣሌነት የሚጠቀስ አስተዋጽኦ ለማበርከት እየተጉ መሆናቸውን እያስተዋልን ነው።
“ለዓይጥ ሞት ብርጉድ አይገኝለት!”
የእኛን ሀገር በተመለከተ ግን ከኮረና ቫይረስ መዛመት እኩል በተለይ ፖለቲከኛ ነን ባዮች አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች (አብዛኞቹ ለማለት ድፍረት አጥቼ ነው) የሕዝብ አፍ ማሟሻ ሆነው ለትዝብት መዳረጋቸው ለእነርሱም አይጠፋቸውም እኛም እየተገረምን የገሃድ ሃሜቱን አጧጡፈነዋል።
የቫይረሱን ወረርሽኝ በተመለከተ በሌሎች ሀገራት እንደምናስተውለውና እንደምናደምጠው የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ መንግስት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ግለሰቦች፣ በጎ ፈቃደኞችና ቡድኖች፣ የፖለቲካ ልሂቃንና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ከራሳቸው ሀገራት አልፈው በተቻለ አቅማቸው ሁሉ ለዓለም ማሕበረሰብ ርብርብ በማድረግ የታዳጊነት አደራቸውን እየተወጡ ይገኛሉ። አንዳንድ የተኮራረፉ ቡድኖችና ግለሰቦች እንኳን ሳይቀሩ ቅይማታቸውን በይደር አስተላልፈው ፍልሚያውን በጋራ ለመምራት አብረዋል።
እንደ በርካታ ሌሎች ሀገራት በእኛም ሀገር የቫይረሱ ስርጭት የከፋ ደረጃ ላይ ላለመድረሱ መንግሥትን ጨምሮ በርካታ ባለድርሻ አካላት ቀን ከሌት እየተጉ ስለሚገኙ ሊመሰገኑ ይገባል። ይህ ማለት ግን ወረርሽኙ በቁጥጥር ሥር ውሏል ማለት አይደለም፤ ዜጎችም ሊዘናጉ አይገባም። በጤና ተቋማትና በሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጡ የጥንቃቄ ጉዳዮችም በአግባቡ መተግበር እንዳለባቸው አስረግጦ ማሳሰቡ አግባብ ይሆናል።
“ለአይጥ ሞት ብርጉድ ለምን እንደማይገኝለት” ወደ ተመሰጠረው የምጸት ገለጻ ጉዳይ የምንደረድረው የአንድ ወዳጄን መራር ትዝብት እንደወረደ ለአንባቢያኑ በማድረስ ይሆናል። የቀልደኛነቱን ጥበብ በማድነቅ ከአሁን በፊት በአንደኛው ጽሑፌ የጠቀስኩት ይህ ወዳጄ ከቫይረሱ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ፖለቲከኞቻችንን አስመልክቶ በቀልድ የወዛ ሂሳዊ ትዝብቱን ሲያካፍለን ፈገግ ያልንለት የፈጠራ ችሎታውንም ጭምር በማድነቅ ነበር። ልገልጽ የማልችለው አስፈጋጊ የሰውነት እንቅስቃሴውንና ሲያወራ አድማጩን የመማረክ ጥበቡን ብቻ እንጂ ዋናውና የተጠቃሽ አንኳ ሃሳቡ የሚከተለው ነው።
“ምናለበት በኮሮና ቫይረስ እንደተለከፉት ወገኖቻችን ሁሉ ከገጠመን የወረርሽኝ አደጋ ተረዳድቶ ከመታደግ ይልቅ ለስልጣን ብቻ የሚቋምጡ እነዚህን የሀገራችን አፍቃሬ ራስ ወዳድ ፖለቲከኞችና ብዙኃኑን የሚበክለውን የሃሳባቸውን ቫይረስ ወደ ኳራንቲን የሚያስገባ ህግ በተደነገገልን። ”
መራሩን ትዝብት እንደ አዘቦት ቀን ተራ አስተያየት በቸልታ የምናልፈው ሳይሆን በቂ መረጃዎችን እያጣቀስን በስፋት ልንወያይበት የሚገባ ሃሳብ ይመስለኛል። በግሌ ወረርሽኙ ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ ዛሬም ድረስ አንድም የተፎካካሪ ፓርቲን እወክላለሁ የሚል ግለሰብ የምርጫ አጀንዳውን “ለጊዜው አዘግይቻለሁ” ብሎ ሕዝብን ወደ ማረጋጋትና መምከር መመለሱን አላስተዋልኩም።
ይልቅስ ሀገር ግራ በተጋባችበት በዚህ ወቅት ስለ ምርጫ አሸናፊነትና ገና ለገና የምርጫ ኮሮጆ ሊገለበጥ ይችላል ብሎ ግምታዊ ትንቢቱን ተቀበሉኝ እያሉ ማቅራራት በግሌ ስህተት ብቻ ብለን የምናልፈው ትዝብት ሳይሆን በሕዝብ ህመም ላይ የሚፈጸም ኢሰብዓዊ ጥቃት ጭምር እንደሆነ አስባለሁ።
ቀልድ አዋቂው ወዳጄ እንዳለው ለዚህን መሰሉ አፍቅሮተ የራስ ደዌ ሃሳቡን ብቻ ሳይሆን የሃሳብ አመንጭውንም ጭምር ለረጅም ዘመን በኳራንቲን ውስጥ አስገብቶ ተፈውሶ የሚወጣበት ዘዴ ቢቀየስ “አንጀታችን ቅቤ ይጠጣ ነበር። ” (የኮሌስትሮል ስጋቱ ለጊዜው ይቆየን)።
ሀገራችን ብቻ ሳትሆን ዓለማችን ራሷ የቫይረሱን ወረርሽኝ መግታት ተስኗት ነገሮች እየተዘጋጉ መሆኑን በዓይናቸው እያስተዋሉ፣ በጆሯቸው እየሰሙ “ይሄ የመንግሥት ሴራ ነው። በእንቅስቃሴዎቻቸው ሁሉ እኛን ለማዳከም አቅደው እየሰሩ ነው። የእኔ የፖለቲካ ድርጅት በዚያና በዚህ ክልል ውስጥ መቶ በመቶ እንደሚያሸንፍ አልጠራጠርም። እከሌ የተባለው የፖለቲካ ቡድን አንድም የሕዝብ ድምጽ ከዚያ አካባቢ ይዞ እንደማይወጣ እርግጠኛ ነኝ። ” ብሎ በክፉ ቀን ያለ ዐውዱ መፎከር ወቅትን የማያገናዝብ የእውቀት ድህነት ብቻ ሳይሆን ጨርቅ የሚያስጥል እብደት መገለጫ ጭምር ነው።
እንዲያው ለነገሩ አይበለውና እነዚህን መሰል በአፍቅሮተ ግለ ነፍስ የናወዙና የሰከሩ አንዳንድ የፖለቲካ ካባ የደረቡ ግለሰቦች የሥልጣኑን ወንበር ቢቆጣጠሩ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም። እነዚህ የፖለቲካ አትራፊዎች በፉክክር ወቅት ሊመዘኑ የሚገባቸው በፖለቲካ ፕሮግራማቸው ይዘት ብቻ ሳይሆን በግላዊ ስብእናቸው፣ በቤተሰብ አቋማቸውና ለማሕበረሰብ ባላቸው አክብሮትና ተቆርቋሪነት ጭምር መሆን ይገባዋል ባይ ነኝ።
ማን ማን እንደሆነ፣ ማን ለሕዝብ ፍቅርና አክብሮት እንዳለው፣ ማን ለራሱ ክብር ሌት ቀን እንደሚተጋ፣ እየተመለከትንና እየታዘብን ስለሆነ ውጤቱን ሳይውል ሳያድር የምናየው ይሆናል። ምናልባትም ወረርሽኙ ተገትቶ፣ ሀገርም በደዌ ከተያዘችበት አልጋ ላይ ተነስታ መከረኛው የምርጫ ፕሮግራም በተያዘለት ቀጠሮ መሠረት ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ እነርሱን እንደ ግለሰብና ማኒፌስቷቸውንም እንደ ቡድን መርህ የምንሞግትበትን ጥሩ አቅጣጫዎች የጠቆሙን ይመስለኛል።
የገጣሚ አበረ አያሌው ጥቂት ስንኞች (ፍርድና እርድ፤ 2008 ዓ.ም) ትዝ ያሉኝ ብዕሬ በአፍቅሮተ ራስ “ፖለቲከኞች” ድርጊት እየተከዘ በነበረበትና የኮሮና ቫይረስ የመከራ ግዝፈት እያሳሰበ ባስጨነቀኝ የአርምሞ ቅጽበት ነበር።
አዲስ ዘመን መጋቢት 16 /2012
የአፍቅሮተ ራስ ኳራንቲን አያስፈልገንም ይሆን?