
ካናዳ በኮሮና ቫይረስ ስጋት በዚህ ዓመት ይካሄዳል ተብሎ ከሚጠበቀው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ራሷን ማግለሏን ቢቢሲ ዘግቧል። ጃፓን ለማስተናገድ ለዓመታት ስትዘጋጅለት የነበረው የ2020ው ኦሊምፒክ ውድድር ከአራት ወራት በኋላ በሐምሌ ወር የሚካሄድ ቢሆንም በቫይረሱ ስርጭት ሳቢያ ላይካሄድ እንደሚችል ስጋት አድሯል፡፡ ኦሊምፒኩ ይካሄድም አይካሄድም በዓለም አቀፍ ደረጃ ወረርሽኝ በሆነው የኮሮና ቫይረስ ስጋት ምክንያት ካናዳ ከኦሎምፒክ መድረክ ራሷን ከወዲሁ ማግለሏ ተረጋግጧል፡፡
የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ለመጀመሪያ ጊዜ የኦሊምፒክ ውድድሩ ለሌላ ጊዜ ሊተላለፍ እንደሚችል ከተናገሩ በኋላ ካናዳ ይህንን ውሳኔዋን ልትወስን መቻሏን የዘገበው ቢቢሲ ፤ካናዳ የጨዋታው ዋነኛ ተሳታፊ ከሚባሉት መካከል መሆኗን ገልጾ ፤እራሷን በማግለሏ በውድድሩ መካሄድ ላይ ተጨማሪ ጥርጣሬ ፈጥሯል ብሏል።
የካናዳ የኦሊምፒክና ፓራኦሊምፒክ ኮሚቴ ውሳኔውን በተመለከተ እንደገለፀው፤ ከውድድሩ ለመውጣት ከውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ከአትሌቶች፣ ከስፖርት ቡድኖችና ከካናዳ መንግሥት ባለስልጣናት ጋር ተመካክሯል፡፡ ኮሚቴው ጨምሮም ለዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ ለዓለም አቀፉ የፓራኦሊምፒክ ኮሚቴና የዓለም የጤና ድርጅት የኦሊምፒክ ውድድሩ በአንድ ዓመት እንዲዘገይ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
«ውድድሩን ለሌላ ጊዜ በማሸጋገር ሂደት ውስጥ የሚያጋጥመውን ውስብስብ ሁኔታን ብንረዳውም፤ ምንም ነገር ከአትሌቶቻችንና ከዓለም ሕዝብ ጤናና ደህንነት የሚበልጥ አይሆንም» ሲል የካናዳ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫም አስታውቋል።
ካናዳ በኦሊምፒክ መድረኩ አልሳተፍም ማለቷን ተከትሎ የአውስትራሊያ የኦሊምፒክ ቡድን ውሳኔውን በመደገፍ መግለጫ ማውጣቱን ቢቢሲ አስነብቧል።
የአውስትራሊያ የኦሊምፒክ ቡድን እንዳለው አሁን ባለው ሁኔታ ውድድሩ በተያዘለት ጊዜ እንደማይካሄድ ግልጽ እየሆነ በመምጣቱ ተሳታፊ አትሌቶች ለቀጣዩ ዓመት እንዲዘጋጁ ተነግሯቸዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/ 2012
ዳንኤል ዘነበ