
በኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ስፖርት ታሪክ ውስጥ አንቱታን ማትረፍ ችለዋል። የእጅ ኳስ ስፖርትና እርሳቸው የሚነጣጠሉ አለመሆኑን ብዙዎች ይመሰክሩላቸው። ለእጅ ኳስ ስፖርት ጥልቅ ፍቅር ያላቸው ኢንስትራክተር አሰፋ ገለቱ። በእጅ ኳስ ስፖርት በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ተጫውተው ከማለፍ ባሻገር በርካታ ወጣት አሰልጣኞችን ማፍራት መቻላቸው ለዚህ ክብር እንዲበቁ አድርጓል። የኢንስትራክተር አሰፋ የስፖርት ህይወት ጅማሮ ከ40 ዓመታት በፊት እንደነበር እንዲህ ይናገራሉ።
«ስፖርታዊ እንቅስቃሴን የጀመርኩት በሰፈር ውስጥ ሲሆን ከልጅነት ጀምሮ ንቁ ተሳትፎ አደርግ ነበር። በስፖርቱ የነበረው ተሳትፎ ግን እግር ኳስን ያስቀደመ ነው።›› ኢንስትራክተር አሰፋ ከእግር ኳሱ እኩል ቅርጫት ኳስ እና እጅ ኳስን ይጫወቱም ነበር። በተለያዩ ስፖርቶች ተወጥሮ የነበረው የስፖርት ፍቅር በአንድ አጋጣሚ ነበር ወደ እጅ ኳሱ ብቻ ሊያመዝን እንደቻለ የሚናገሩት፡፡ ‹‹በወቅቱ ከአዲስ አባባ ፖሊስ የእጅ ኳስ ቡድን ጋር በመሆን እጅ ኳስ እጫወት ነበር። ከቡድኑ ጋር አደርገው በነበረው እንቅስቃሴ ከቡድኑ ተጫዋቾች ብሎም አሰልጣኞች በእጅ ኳሱ እንድገፋበት አድርጎኛል። በዚህ ግፊት የአዲስ አበባ ፖሊስ የእጅ ኳስ ቡድንን በመቀላቀል ወደ እጅ ኳስ ስፖርት ሙሉ ለሙሉ መግባት ቻልኩ›› ይላሉ።
ኢንስትራክተር አሰፋና እጅ ኳስ በዚህ መልኩ ትውውቅ ካደረጉ በኋላ በበርካታ የከተማ አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ውድድሮች ላይ የመጫወት እድሎችን አገኙ። በእጅ ኳሱ የተጫዋችነት ሂደት ውስጥ ከክለብ ባለፈ እስከ ብሔራዊ ቡድን ውክልና ዘልቋል፡፡ ለኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ብሄራዊ ቡድን በመመረጥ ለአምስት ዓመታት እስከ መጫወትም ደርሰዋል፡፡ ኢንስትራክተር አሰፋ በተጫዋችነት ብቻ 20 ዓመታት ማሳለፍ የቻሉ ሲሆን በእነዚህ ዓመታት ውስጥ «በተጫዋችነት ዘመኔ የማይቆጩኝን 20 ዓመታትን አሳልፌያለሁ። በስፖርቱ ሀገሬን በመወከል በብሄራዊ ቡድን ደረጃ የተጫወትኩበት እነኚህ ዓመታት ለእኔ ልዩ ኩራቴና ትዝታዎቼ ነበሩ» ሲሉ ያለፈውን የተጫዋችነት ዘመን ያስታውሳሉ፡፡
ለሀገር ክብርና ፍቅር እንዳላቸው ደጋግመው የሚናገሩት ኢንስትራከተር አሰፋ የተጫዋችነት ዘመናቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ አሰልጣኝነት ነበር የተሸጋገሩት። ኢንስትራከተር አሰፋ በእጅ ኳሱ አሰልጣኝ በመሆን በአዲስ መንፈስ እንዴት ብቅ እንዳሉ ሲያስታውሱ፤ «የእጅ ኳስ አሰልጣኝነትን የአዲስ አበባ ፖሊስ እጅ ኳስ ቡድን በመያዝ ነበረ የተጀመረው። ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በርካታ ጊዜያትን ካሳለፍኩኝ በኋላ ቀጣዩ መዳረሻዬ የነበረው ኦሜድላ ነበር» ይላሉ። የኦሜድላን እጅ ኳስ ቡድን ወደ ማሰልጠኑ መሸጋገራቸው ለስፖርቱ የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ እንዲጨምር እንዳደረገላቸው ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ታሪክ በተለይ በ70ዎቹ ውስጥ በጥንካሬያቸው ከሚጠቀሱት ክለቦች መካከል ኦሜድላ ዋነኛው ነው። ከክለቡ ጋር በነበራቸው ቆይታ ስፖርቱን ወደ ፊት ማራመድ የሚያስችሉ ስራዎችን ለመስራት እንዳስቻላቸው ኢንስትራክተር አሰፋ ይናገራሉ፡፡ በአሰልጣኝነት ቆይታቸው ጊዜ እየተመዘገቡ ባሉ ውጤቶች ደስተኛ የነበሩት ኢንስትራክተር አሰፋ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የእጅ ኳስ ስፖርት መዳከምና ውጤት አልባ እየሆነ መምጣት በቁጭት እንዲሞሉ ያደረጋቸው ነበር። በወቅቱ ስፖርቱ ረጅም ዓመት እንደቆየ ባለሙያ መፍትሄ መፈለግ እንደሚገባ ለሚመለከተው አካል ሃሳብ እስከ ማቀበል መድረሳቸውን ያስታውሳሉ፡፡ በሃሳብ ብቻ መወሰን ግን አልፈለጉም ነበር ። ከኦሜድላ ክለብ ጋር የነበራቸውን ጉዞ በመግታት መፍትሄው ላይ ወደ ማነጣጠር አዘነበሉ፡፡ ስፖርቱን መሰረት አሳጥቶ ውጤት አልባ ያደረገው የተተኪ ችግር እንደሆነ በማጥናት ታዳጊዎች ላይ መስራት ይጀምራሉ፡፡
በ1990 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ውጤት ያጣውን የእጅ ኳስ ስፖርት ለመታደግ ታዳጊዎችን መሰረት ያደረገውን ተግባር በቁጭት ጀመሩ። ከአዲስ አበባ እጅ ኳስ ፌዴሬሽንና ከሙያ አጋሮቻቸው ጋር በመቀናጀት ታዳጊዎችን በፕሮጀክት ደረጃ በማቀፍ ስልጠናዎችን በስፋት መስጠት ተያያዙት፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም ውጤታማ ስራዎች ማከናወን ቻሉ፡፡
የኢንስትራክተር አሰፋ ታዳጊዎችን መሰረት ያደረገ ስልጠና በትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት አድርጎ ወደ መስራት ሽግግር ያደረገ ነበር። በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የሚገኙ የአንድኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን በመመልመል የእጅ ኳስ ስፖርት ወደ ማሰልጠን ነበር የተሸጋገሩት። ኢንስትራክተር አሰፋ ትምህርት ቤቶች ላይ መሰረት በማድረግ በርካታ ታዳጊዎችን አሰልጥነው ማስመረቅ እንደቻሉ ይናገራሉ። «የአምናውን ብቻ ብናስታውስ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ የሆኑ 300 ታዳጊዎችን በፕሮጀክት ደረጃ በማሰልጠን ተመርቀዋል።
በዘንድሮ ዓመትም በተመሳሳይ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ከ20 በላይ መንታዎች ሰልጠነው ተመርቀዋል» ሲሉ ይናገራሉ።
በእጅ ኳስ ስፖርት ውስጥ ትልቅ አሻራ ማሳረፍ የቻሉት ኢንስትራክተር አሰፋ፤ የስፖርት ህይወት ጉዞን አስደናቂ የሚያደርገው ለስፖርቱ እድገት ታዳጊዎችን መሰረት አድርጎ መስራት እንደሚበጅ በማመን በሰሩት ውጤታማ ተግባር የተቸራቸው ምስጋና ሳያባራ፤ በሀገራችን ባልተለመደ መልኩ መስማት የተሳናቸውን ዜጎች እጅ ኳስ ለማሰልጠን የሚያስችል ንድፈ ሀሳብ በመያዝ መስማት የተሳናቸውን ታዳጊዎች ማሰልጠን መጀመራቸው ነው፡፡ ኢንስትራክተር አሰፋ ለዚህ እንደመነሻ የነበራቸውን አጋጣሚ ሲያስረዱ፤« በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ስልጠና በሚሰጡበት ወቅት የታዘብኳቸው ነገሮች ወደዚህ እንድገባ ያደረጉኝ። ለተማሪዎች እጅ ኳስ ስልጠና በምሰጥበት ወቅት እዛ አካባቢ መስማት የተሳናቸው እኔ የምሰጠውን ስልጠና ቁጭ ብለው ይመለከቱ ነበር። በእነዚህ ታዳጊዎች ተግባር ውስጤ ተነሳሳ።
ስልጠናውን ወደ መስጠት ከመሸጋገሬ በፊት ግን ከተማሪዎቹ ጋር ለመግባባት እንድችል የምልክት ቋንቋ መቻል አስፈላጊ ነበር። በመሆኑም ቋንቋውን ለሶስት ወራት ያህል ተማርኩ። በዚህ መሰረት በአዲስ አበባ መስማት የተሳናቸውን ተማሪዎች ከሚያስተምሩ ሶስት ትምህርት ቤቶች ጋር በመነጋገር እንዲሰለጥኑ ማድረግ ችያለሁ» ይላሉ፡፡
ኢንስትራክተር አሰፋ በእጅ ኳስ ስፖርት ውስጥ ያከናወኗቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት ቢሆኑም እሳቸው ዛሬም በአዲስ ወኔ ለመስራት ያሰቧቸው ስራዎች መኖራቸውን ይናገራሉ። «ስፖርት ለእኔ ህይወቴ ነው፤ ልጅነቴን ፣ ወጣትነቴን ከእጅ ኳስ ስፖርት ሳልነጠል አሳልፌያለሁ። ዛሬም ነጭ ፀጉር አብቅዬም ከስፖርቱ መለየት አልሻም። ስፖርቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ አማራጭ ያልኳቸውን ተግባራት ለማከናወን አልተኛም» የሚል ጽኑ እምነት አላቸው። ስፖርቱን ለማሳደግ እንደ እርሳቸው ሁሉ በርካታ ባለሙያዎች ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸውና ለዚህ ደግሞ ስፖርቱን ከሚመሩት አካላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ የሚገባ መሆኑን ማስገንዘብ እንደሚፈልጉ ያብራራሉ፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/ 2012
ዳንኤል ዘነበ