
አዲስ አበባ፡- የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ግድብ ማስተንፈሻ በጊዜ ተጠናቆ በዘንድሮው ዓመት ውሃ መሙላት ካልተጀመረ የፋብሪካው የማምረቻ ጊዜ ከሦስት ዓመት በላይ ሊራዘም እንደሚችል ተገለጸ። የፋብሪካው ግንባታ 84ነጥብ5 በመቶ ደርሷል።
የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ልማት ፕሮጀክት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ውበት ገብረመድህን፤ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ግድብ ዲዛይን ሲደረግ ተካቶ የነበረው የግድቡ ውሃ ማስተንፈሻ «ሜደል አውትሌት ሌቭል» በዝቅተኛ ቦታ ላይ ስላለ ውሃው ሲለቀቅ ግድቡን በድጋሚ ለመሙላት ሁለት ዓመት ይፈጃል።
በዚህም የተነሳ ‹‹ማስተንፈሻውን መስራት አስፈላጊ አይደለም›› በሚል በአመራር ውሳኔ እንዲቀር ተደርጎ የግድቡ ሥራ ተጠናቋል። ይሁን እንጂ የግድቡ ሥራ ከስኳር ኮርፖሬሽን ወደ ውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ከተዛወረ በኋላ የግድብ ግንባታ በባለሙያዎች ሲገመገም የግድቡ ማስተንፈሻ መኖር እንዳለበት ሃሳብ መቅረቡን ጠቅሰው፤ ሃሳብ ቢቀርብም እስካሁን እንዲሰራ ወይም እንዲቀር አልተወሰነም ብለዋል። እንደ ምክትል ዋና ሥራአስኪያጁ ገለፃ፤ ማስተንፈሻው ይሰራ ወይም አይሰራ የሚለው ተወስኖ ወደ ሥራ ካልተገባና በዘንድሮው ክረምት ውሃ መያዝ ካልተቻለ የፋብሪካው የማምረቻ ጊዜውን ከሦስት ዓመታት በላይ ይራዘማል።
የፋብሪካው ግንባታ ዘንድሮ ተጠናቆ ወደ ሥራ መግባት ቢቻልም ግድቡ ውሃ ይዞ በመስኖ ምርት ለማምረት ተጨማሪ ሦስት ዓመታት ይፈጃል። ‹‹የፋብሪካው የምርት ጊዜ እንዳይራዘም መስራት ያስፈልጋል›› ያሉት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ ግድቡ ጉዳት እንዳያደርስበት የማስተንፈሻ ግንባታው በፊት ሊሰራ ከታሰበበት ቦታ ርቆ በአዲስ መልኩ የሚሰራ በመሆኑ ሥራውም ሆነ ወጪው ከባድ እንደሚሆን አንስተዋል። በዚህ ምክንያት በቶሎ ውሳኔ ሰጥቶ ወደ ሥራ መግባት ያስፈልጋል ብለዋል።
ስራው ተሰርቶ ውሃ መያዝ በሚገባው ጊዜ ካልተሞላ የፋብሪካውን ማምረቻ ጊዜ ያጓትተዋል። ፋብሪካውም ተጠናቆ ያለምርት በመቆየት ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል አሳስበዋል። የስኳር ፋብሪካው ግንባታ በሁለት ምዕራፍ ተከፍሉ እየተገነባ መሆኑን የገለጹት ኢንጅነር ውበት፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ 86 በመቶ ሁለተኛው ምዕራፍ 80 በመቶ በጥቅል በአማካይ 84ነጥብ5 በመቶ መድረሱን አመልክተዋል። ለመስኖ የሚያስፈልገው ‹‹ዛሬማ›› ወንዝ ላይ ያለው ግድብ ከማጠቃለያ ሥራ ውጪ መጠናቀቁን ያነሱት የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ የማምረቻ ጊዜ ከሦስት ዓመት በላይ ሊራዘም እንደሚችል ተገለጸ አጎናፍር ገዛኽኝ ኢንጅነሩ፤ በውሃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሚሰራው 76 ኪሎ ሜትር የውሃ ማስተላለፊያ ቦይ ግንባታ በዝግጅት ላይ መሆኑን አንስተዋል።
በፍጥነት ግንባታውን ለማጠናቀቅ የሚመለከታቸው ተቋማት ድጋፍና ግፊት ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል። የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታው ተጠናቆ ሙከራ መደረጉንና ከፋብሪካው ጋር የማገናኘት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። ፋብሪካው በ2013 ዓ.ም የሙከራ ምርት ለማስጀመርና በ2014 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ስኳር ማምረት ለመጀመር ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በጋራ ችግሮችን እየፈቱ ከሄዱ በእቅዱ መሠረት ምርት ማምረት ይጀመራል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
በውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የመስኖ ልማት ኮሚሽነር ዶክተር ሚካኤል መሃሪ፤ የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ በዛሬማ ወንዝ ላይ የሚገነባው ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲል የተጀመሩ በርካታ የመስኖ የግድብ ሥራዎች የኮንትራት፣ የዲዛይንና የጥናት ችግር እንዳለባቸው ተናግረዋል። ወጪያቸው፣ የሚጠናቀቅበት ጊዜና ሥራቸውም ከሦስት ዕጥፍ በላይ መራዘሙን አስታውቀዋል።
ኮሚሽኑ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የፕሮጀክቶቹን የዲዛይን ሥራ በማጠናቀቅና ፕሮጀክቶቹ ተገንበተው ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ ለማድረግ ወደ ሥራ ገብቷል ያሉት ዶክተር ሚካኤል፤ በዛሬማ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው ፕሮጀክትም የመካከለኛው ማፋሰሻ ያልተሰራለት ሲሆን፤ የፕሮጀክቱ አማካሪ የነበረው የጣሊያን ኩባንያ ከግብር ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ዲዛይኑን ሳያስረክብ ከአገር በመጥፋቱ አዲስ ዲዛይን ተሰርቷል።
ከዚህም በተጨማሪ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራ የሚቀር ሲሆን ሁለቱን ሥራዎች ለማከናወን ጨረታ ወጥቶ በአየር ላይ መሆኑንም አመልክተዋል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ሁለቱ ፋብሪካዎች በቀን 24ሺ ቶን የሚፈጩ ሲሆን ለዚህ የሚሆን በ50ሺ ሄክታር መሬት ላይ የሸንኮራ አገዳ ያስፈልጋል። ይህም በሦስት ምዕራፍ ተከፍሎ እንደሚለማ በእቅድ የተያዘ ሲሆን፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ 10ሺ ሄክታር ለማልማት እየተሰራ ነው። በ7ሺ ሄክታር መሬት ላይም በእስራኤል ኩባንያ የልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው።
15ሺ እና 25ሺ ሄክታር በሁለተኛውና በሦስተኛው ምዕራፍ በቅድም ተከተል እንደሚለማም ታውቋል። ለወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ግንባታ በ82 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ውል የተገባ ሲሆን፤ 69ሚሊዮን ዶላር ክፍያው ተፈፅሟል። ለግድቡ ግንባታም በ12 ቢሊዮን ብር ስምምነት ተደርጓል። የመስኖ ሥራውን ከሚያከናውነው የእስራኤል ኩባንያ ጋር 3ነጥብ7 ቢሊዮን ብር ስምምነት መደረጉም ታውቋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 13 ቀን 2012 ዓ.ም
አጎናፍር ገዛኽኝ