
አዲስ አበባ፣ የቋንቋ ልማትና አጠቃቀም ፖሊሲ ዋናው ጠንካራ ጎን በሰዎች ዘንድ እርካታን የሚፈጥር መሆኑን ነው ሲሉ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ አስታወቁ:: ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሰው በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ በፖሊሲው አምስቱ ቋንቋዎች የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ የተወሰነው ሰዎች ሀሳባቸውን በትክክል በሚገልጹበት ቋንቋ እንዲናገሩ ፣አዳምጠውና አንብበው መረዳት በሚችሉበት ቋንቋ አገልግሎት እንዲያገኙ ነው።
ሚኒስትሯ እንዳሉት የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪዎች በአንድ ስብሰባ ላይ በሚሆኑበት ወቅት በአንዱ ቋንቋ ሀሳቡን በደንብ መግለጽና ማስረዳት የማይችል ሰው ቢኖር ይሄ ሰው በሚችለው ቋንቋ ሀሳቡን ያቀርባል።ይሄ ማለት ማንኛውም ሰው ማስተላለፍ የሚፈልገውን ወይም መረዳት ያለበትን ሀሳብ ካለምንም ችግር ስለሚያቀርብ በሰዎች ዘንድ እርካታን ያሳድራል። አዋጆች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና ሌሎችም ነገሮች ሲወጡ በአምስቱ ቋንቋዎች ማድረስ ማለት ሀሳብን በሚገባው ቋንቋ የመረዳት ዕድልን መፍጠር በመሆኑ ለህብረተሰቡ የበለጠ እርካታን ያመጣል ብለዋል::
ቋንቋ እንደሌላው ልማት መታየት አለበት ያሉት ሚኒስትሯ ፤ለግብርና፣ ለትምህርት፣ ለጤና ልማት ተብሎ እንደሚሰራው ሁሉ የማህበራዊ ልማትም አንዱና ከሰው ልጅ አእምሮ ጋር የሚገናኝ የልማት ዘርፍ መሆኑን አመልክተዋል። የሰው ልጅ በአፍ መፍቻ ቋንቋው ሲያስብ እና ሲማር በምንፈልገው ጊዜ፣ ጥራት እና አይነት የለማ አእምሮ ይኖረናል ያሉት ሚኒስትሯ: የሰውን ቋንቋ ማልማት ማለት የሰውን ጭንቅላት ማልማት በመሆኑም ቅድሚያ ሊሰጠው ከሚገቡ የልማት አይነቶች የመጀመሪያው የቋንቋ ልማት መሆን አለበት ብለዋል።
ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ የቋንቋ ልማትና አጠቃቀም ፖሊሲው ግጭቶችን የሚፈታ ነው። ህዝቦችን እርስ በእርስ የሚያፋቅርና የሚያገናኝ ነው።እስካሁን በቋንቋዎች መካከል ያለውን መጥፎ አመለካከት የሚቀርፍ እና እርስ በእርስ መከባበርና መፈቃቀርን የሚያመጣ ፣አንዱ የአንዱን ቋንቋ ለማወቅና ለመማር ፍላጎት የሚቀሰቅስ እንጂ ወደ ግጭት የሚመራ አይደለም።
ፖሊሲው የሀገራችንን ብቻ ሳይሆን የውጪ ቋንቋዎችንም ለመማር የሚያነሳሳ መሆኑን አስታውሰው ፤ በአጠቃላይ ሲታይ ፖሊሰው ግጭት የሚያስነሳ ሳይሆን አንደኛው የሌላውን ህዝብ ቋንቋ ለመማር የሚያነሳሳ ፣ እስካሁን የነበረውን አሉታዊ ጎን የሚቀርፍ እና አዎንታዊ አመለካከት የሚፈጥር ነው ብለዋል።
አምስቱ ቋንቋዎች የፌዴራሉ የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ እውቅና የተሰጠበት ምክንያት ብቁ ናቸው ከሚል ነው ያሉት ሚኒስትሯ ፤ ቋንቋዎች ከጽሁፍ ፣ከአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት አልፈው እስከ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት መስጠት የደረሱ እንዲሁም የክልል መንግስታት የስራ ቋንቋ መሆናቸው ከዛም አልፎ ኦሮሚኛ በኬንያ፤አፋርኛ በጅቡቲ ፤ትግርኛ በኤርትራ፤ ሱማሊኛ በሶማሊ የሚነገሩ በመሆናቸው ነው ብለዋል:: አማርኛም የሃገራችን የስራ ቋንቋ ከመሆኑ
ባሻገር በአሜሪካ እንደ ሁለተኛ ቋንቋነት እንዲሁም በእስራኤል እስከ ሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ድረስ እየተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል። እነዚህ ቋንቋዎች ታዲያ ከማደግም አልፈው ወደ መደበኛ አገልግሎት የገቡ፤የዩኒቨርሲቲ ፣ የመገናኛ ብዙኃን ፣የምርምር ቋንቋ በመሆን መደበኛ አጠቃቀም ደረጃ መድረሳቸውንና ድንበር ተሻጋሪ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ፖሊሲው ሲዘጋጅ የብዙ ቋንቋ ተናጋሪ ከሆኑት እንደ ህንድ፣ ደቡብ አፍሪካና ኢንዶኔዥያ ከመሳሰሉት ሀገራት ልምድ መወሰዱን ገልጸው ፤ ሆኖም ግን ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ እና የሀብት ደረጃ ታይቶ አምስት ቋንቋዎች የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ በፖሊሲው መቀመጡን አመልክተዋል :: ሌሎችም ቋንቋዎችም በየደረጃ ሲበቁና ሲለሙ የስራ ቋንቋ የመሆን እድላቸው በፖሊሰው ውስጥ ክፍት መደረጉን አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 13 ቀን 2012 ዓ.ም
አልማዝ አያሌው