ሰሞኑን በዓለም ዙሪያ መነጋገሪያ ብቻ ሳይሆን መተሳሰቢያ ርዕስ በመሆን እያሰባሰበን ያለው ርዕስ ኮሮና ወይም ኮቪድ -19 ሆኗል።ሁሉም የሰው ዘር በእርግጥም በአንድ ቃል የተነጋገረበት የተወዛገበበትና ዋነኛ ዒላማ የሆነ አርዕስት ሆኗል ።አርዕስት መሆኑና መነጋገሪያና የሀሳብ መለዋወጫ መሆኑ ምንም አያስከፋም።እንዲያውም ከመቼው ጊዜ በላይ በተለያየ ቋንቋ ስለአንድ ጉዳይ የሰው ልጆች ሁሉ ከኤች አይቪ/ ኤድስ ቀጥሎ የተወያዩበት ጉዳይ ሆኗል፤ ኮሮና።
መንስዔው፣ ምልክቶቹ፣ የሚያጠቃው የሰውነት ክፍል፣ የሚያደርሰው ጉዳት፣ አያያዙና የህክምና ዘዴው ሁሉ በስፋት እየተነገረ ነው።ሰው ሊሰማው በሚችለው መጠን ተራኪው በዝቶ ሰው ሁሉ ልምድ አካፋይና የልምድ አዋላጅ የመሰለበት ጊዜ ላይ ብንገባም በዝርዝር እየሰማነው ነው።
ከቤተ-እምነት እስከ ቤተሰብ ድረስ ሰው የሀኪምነት መንፈስ የተጠናወተው ጊዜ ቢኖር ይኼ ጊዜ ነው።አንድ ነገር አስደስቶኛል፤ እርሱም ሁሉን ሰው በአንድ ነገር ዙሪያ፣ የሚያሰባስብ “መልካም” ርዕስ ሆኗልናልና።ስጋቱ ማስፈራሪያው፣ የህክምና ዘዴውና ስልቱ ከገዳም እስከ አደባባይ ሆስፒታሎች ድረስ እየተነገረ መሆኑ አስገራሚ ነው።ሞት በደጅ አለሁ ሲል የሁሉም ሰው ቋንቋ ሌሎቹን ርዕሰ ነገሮች አስጥሎ ሁላችንንም ኮሮና ወደ ኮርና መምቻው ጥግ ሰበስቦናል።
ብዙዎቻችሁ እንደምታውቁት በእግር ኳስ ጨዋታ፣ የማእዘን ምት ወይም ኮርና ሲገኝ አንዳንዴ የባላጋራ በረኛ ሁሉ ጎሉን ትቶ በመምጣት እድል ለመፍጠር ሲጥር የሚታይበትና አስራ አንዱም የባላጋራ ቡድን ተጫዋቾች እድሉን ለመጠቀም የሚጥሩበት አጋጣሚ ይፈጠራል።ኮሮና ለሳይንቲስቶች መፍትሔ ነገር ፍለጋ አሯሯጭ ርዕስ ሆኖ ከጃፓን ቶኪዮ እስከ አሜሪካዋ ሳንፍራንሲስኮ ከኖርዌይ ኦስሎ እስከ ደቡብ አፍሪካዋ ኬፕታውን ድረስ የጸረ-ቫይረስ ምርምሮች እየተጧጧፉ ነው።በሌላ በኩል ደግሞ የኑሮ አበሳ ያበሳጨው ወገን ደግሞ የዚችን ምድር ዝባዝንኬ የምገላገልበት መንገድ ይሆን ብሎ ማሰላሰሉ ባይቀርም፤ ክፉው ነገር ግን የ10 ብር የአፍ ማስክ እስከ 250 ብር በሚደርስ ዋጋ ለመሸጥ የጨከነ አረማዊነት በአንድ በኩል፣ የሳኒታይዜሽን (የንጽህና እቃ) ከፋርማሲው ትይዩ አውጥቶ ሰዎች እጃቸውን በነጻ እየታጠቡ እንዲሄዱ የሚያደርግ ምግባረ መልካም ባለፋርማሲ ያየንበትም ወቅት ነው።ነጭና ጥቁር!
ሁለቱን ሰዎች ያፈራችው ይህችው ኢትዮጵያ የምትባለው ምድር ናት። አንደኛው በህዝብ እጦትና መከራ ለመክበር የሚጓጓ የቀን ቀበሮ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የተጎዳ ልብን ለመጠገን የሚታትር ሳምራዊ ልብ ያለው የሰው ደግ ነው።ለነገሩ እንዲህ ያለ ሰው ከአንድ ሐገር ምድር ብቻ ሳይሆን ከአንድ ማህጸን ይወጣል፤ የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንዲሉ።
ኮሮና ስንቱን ሰው እንድንታዘብና ራሳችንንም የምናይበትን መለኪያ ያስቀመጠልን ክስተት ሆኗል።እና በሰፈር የማውቃቸው “የኔ ብጤ” አሉ።ድንገት በእግሬ መንገድ አቋርጬ ሳልፍ “ልጄ አትለፈኝ፤ ስለኮሮና “ ሲሉ አንድ እርምጃ ጨምሬ መሄድ አልፈለግኩምና መለስ ብዬ “ምን ምን አሉ፣ እማማ? ” ስላቸው ፣“አሁን ወሬው ሁሉ እሱ ስለሆነ ነው እንጂ ምኑንም አላውቀውም ግን፤ ልጄ…” “ስለኮሮና” ነው ያልኩት” አሉን።የምሰጣቸውን ሰጥቻቸው ላልፍ ስል፣ ዘመን በሚያመጣቸው የወረርሽኝ ሀሳቦች አፋችን ስንቴ ተለዋውጦ ይሆን አልኩ።
ባለቅኔው መንግስቱ ለማ፣ ጸረ-ኮሎኒያሊስት” በሚለው አንድ የተውኔት ድርሰታቸው ላይ አንደኛው በልመና የሚተዳደር ገጸ-ባህሪ ሲለምን፣ “ስለባንዳ … ዓለሞቼ…ስለኮማንዳ” “በሳንታ ማሪያ ….በቅድስት ማርጋሬታ… በሲኞሪታ…” ማለቱን አስታውሳለሁ።ዋናው ነገር የዘመን አሻራዎቻችን ከእረኛ እስከ ለማኝ፤ ከሚኒስትር እስከ ዶክተር ሊሄድ ይችላል።እዚህ ላይ፣ ኤች አይቪ ታማሚ ነኝ ብለው ደብዳቤ ይዘው በየቢሮው “የሚዞሩትን የያኔዎቹን ሰዎች “ ታስታውሳላችሁ ብዬ አስባለሁ።እናም በአንዳንድ ስፍራ “ስለ ኤችአይቪ… ”ሳይባል እንዳልቀረ (ወይም እንደተባለ ቁጠሩት ) ገምታለሁ።በሁሉም አፍ በአንድ ወቅት ገንነው የሚታዩ ነገሮች በአስተሳሰባችንም ሆነ በአነጋገራችን ላይ ጥለውት የሚሄዱት አሻራ በቀላሉ የሚታሰብ አይደለም ።
ስለኤች አይቪ ካነሳሁ እግረ መንገዴን የማልረሳውን የልጅነት ጓደኛዬን ታሪክ ላወሳችሁ እወዳለሁ፤ መራርም ቢሆን።እናም ያ፣ አብሯ ደጌ ክፉኛ ይታመምና በሐገር ውስጥ ባሉት ስመጥር ሆስፒታሎች ይታከምና ሳይድን ይቀራል፤ ለከፍተኛ ህክምናም ወደባህር ማዶ ሊላክ ይወሰናል።አንድ ምሽት ታዲያ ብቻችንን ስንሆን “ ጓዴ፣ ያመመህ ነገር ኤች አይቪ ነው እንዴ? ለምን መዳን አልቻልክም?” አልኩት።የዚያን ጊዜ በእኔ ብጤው መደዴ የማይድን ህመም ተብሎ የሚታሰበው ኤች አይቪ ስለነበረ፤ ነው፤ ፈራ ተባ እያልኩ የጠየቅኩት፣ ሳቅ ብሎ “ምነው እሱ በሆነልኝ ፣” ሲል ደንግጬ ፣ “ከእሱ የከፋ ምናለና” አልኩት።አይ አንተ ፣ “ሂፓታይተስ” ይባላል ለመዳን ያለህ እድል 1/10 ነው፤ አለኝ።እናም ወንድሜ አልተረፈም ፤ ወደዘላለም ቤቱ ሄዷል፤ ግን በዘመነ- ኤች አይቪ እንኳን ኤች አይቪን የሚስያስንቅ በሽታ ነበረ፤ ልላችሁ ነው።
ዛሬስ? ዛሬም ሌሎች ገዳይ ህመሞች፣ ሌሎች ጨካኝና አሳሳቢ በሽታዎች በምድራችን ላይ አሉ።ድንገት ተከስተው ግን የሰውን ልጅ አንደበት፣ ሐሳብና ምናብ ሁሉ እንደ ደራሽ ወንዝ የሚሰርቁ ህመሞችም ይከሰታሉ።ኮሌራ በአንድ ዘመን እንዲህ አስፈሪ የነበረበትና ሰው የፈጀበት ዘመን በጣሊያን እንደነበረ፣ በአየርላንድ ደግሞ “የድንች ተስቦ” (The potato plague) የሚባል ህመም ገብቶ ብዙ ሺህ ህዝብ የገደለበትና ብዙ ሚሊዮኑን ያሸበረበት ጊዜ ነበረ:: ያኔ ነበረ ታዲያ ጆናታን ስዊፍት የተባለ እውቅ ደራሲ እልቂቱን በተመለከተ ድንቅ ወግ በመጻፍ የብሪታኒያን ፓርላማ አባላትን ሁሉ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ያደረገው።
የስዊፍት ጽሁፍ ርዕስ “ለጨረታ የቀረበ የህጻናት ሥጋ” የሚል አንድምታ ያለውና የአየርላንድ ህጻናት ህይወት እንደዘበት በሚያልፍበት ሐገር ፓርላማው በዝምታ ተቀምጧል፤ የሚል መልእክት ያዘለ ሐሳብ ነው ያንጸባረቀው።ጉዳዩ ከቤት እስከቤተመንግስት ምላሽ የሚያስፈልገው ነገር እንዳለው ለማሳሰብ ነበረ።
አሁን ከውሃን ቻይና ግዛት የተነሳው ወይም ተነሳ የተባለው ኮሮና ዓለምን በአንድ መዳፍ ውስጥ አንዳለች አንድ አነስተኛ መንደር በሁሉም አፍ ውስጥ የመነጋገሪያ አርእስት በመሆን የሰውን ዘር ሁሉ፣ እያስጨነቀ ያለ ጉዳይ ሆኗል።በዚህ ሳምንት መጀመሪያም የሀገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር በአርአያነት ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች፣ ጥንቃቄ ሊወሰድባቸው ስለሚገባቸው ቦታዎች፣ የትራንስፖርት መገልገያዎችና ሌሎች ተጨማሪ እርምጃዎች በአካል በቴሌቪዥን መስኮትና በሬዲዮ ቀርበው አስረድተዋል።
ጉዳዩ ሁሉንም መስሪያ ቤት፣ ሁሉንም ቤት፣ ሁሉን ቁሳቁስ (በንክኪ ነውና የሚተላለፈው) በንጽህና በመያዝ ሊመጣ የሚችለውን አደጋ ለማስቀረት አለያም ለመቀነስ እንደሚቻል አሳይተው አስጠንቅቀውናል።የመረጃ አንዱ ጥቅሙ ማሳወቅ፣ ማሳሰብና ማስጠንቀቅ ጭምር በመሆኑ አስጠንቃቂው ነገር፣ ሲሰጠን በመጠንቀቅ ማሳሰቢያ ሲሰጠን በማሰብ እርምጃ መውሰድ ካዳማጭ ጆሮና ከአስተዋይ ልቡና ይጠበቃል።
ኮሮናን እንደቃል በመውሰድ የመዝገበ-ቃላቸው አካል ለማድረግ ያልሰነፉ የመገናኛ ብዙሃን፣ የመማሪያ መጻህፍት ጋዜጦችና መጽሄቶች እነርሱም የዘመን አሻራቸውን በመጠበቅ ትውልዱ ያለፈበትን መንገድ ስለሚያሳዩ በደንብ ጽፈው ዘግበው ማስቀመጥ የተገባ ነው።በዚህም አጫጭር ልቦለዶች፣ ተውኔቶች፣ ወጎችና ይህንን መሰል መጣጥፎች እየቀረቡ ማንቃት ሊለመድ ይገባል።
በነገራችን ላይ ጠዋት የጽዳት ስራ ለመስራት ወደመኖሪያ ሰው ቤት ገብታ አራት ያህል ሌሎች የወንደላጤ ቤቶችን በጽዳትም በምግብ ስራም አገልግላ ገብታ ፍራሹዋ ላይ ጋደም የምትል ባተሌ ሰራተኛን ቤተክርስቲያን ደጅ ላይ አግኝቼ ስለኮሮና ጠየቅኳት።“ምንድነው ኮሮና” ስትል ነው፤ መልሳ የጠየቀችኝ።የሚገርመው ከሰው ጋር የሚገናኙ ከሰው ጋር ግን የማያወሩ እንደ እሷ ያሉ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ከስፍራ ስፍራ ኮሮናን ለማሸጋገር ያላዋቂ እጅና ሰበብ ይሆናሉ።ምክንያቱም ምንም መረጃ የላትማ ! ስለዚህ አቁሞ ማነጋገር እና ህመሙ በአሳሳቢ ደረጃ ያለ መሆኑን ለእርሷና መሰል ሰራተኞች መንገር ዜግነታዊ ግዴታችን መሆኑን ማጤን አለብን ።
ኮሮና ምንድነው ስትባል ምንድነው ብላ በመመለሷ፣ እና ለእሷ እንግዳ ሆኖ በመገኘቱ ፣ ይህቺ ሰው ምን ነካት? ማለት የለብንም።ማለት ያለብን ምንነቱን አጥርተን ለእርሷ ሊገባት በሚችል መንገድ በመንገር የመፍትሄው አካል እንድትሆን መርዳት እንጂ ባለማወቅ ጨለማ ውስጥ ለምን ቆመች ብለን ልንወቅሳት አይገባም።በየቤቱ ያላችሁ አሰሪዎች አስር ደቂቃ ወስዳችሁ እርሷን መሰል ከሆኑ ሰዎች ጋር የመነጋገርና የማስረዳት ሃላፊነት አለባችሁ።አለበለዚያ አደጋው ተመልሶ ፣ የሚጎዳው ያንን ቤት ነው።
አሁን በዓለም ዙሪያ፣ እኛም የዓለም አካል ነንና የተነሳው የኮሮና ቫይረስ ሙያ ሳያዳላ፣ የአካል ብቃት ሳይለይ፣ የአገልግሎት ዓይነት ሳይመርጥ እያጠቃ ነው።አሁን እንኳን ሰኞ ማታ በጣሊያን ሊግ ውስጥ የነበረ አንድ ኳስ ተጫዋች ለህልፈት ዳርጓል፤ ጣሊያን ከአውሮፓ ምድር ከፍተኛውን የኮሮና ሰለባ በማስተናገድ (ሟች) ወደረኛ አልተገኘላትም።ስፔን በትልቁ ሊግ “ላሊጋ” የሚገኙ ጫወታዎቿን ሙሉ በሙሉ ሰርዛለች፤ የሪያል ማድሪድ ተጫዋቾች በተገለለ ስፍራ ተቀምጠው እየተመረመሩ ነው፤ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊጓን ዘግታለች፤ የአርሰናሉ አሰልጣኝ ማይከል አርቴታ በቫይረሱ ተይዞ በማገገሚያ ሥፍራ መሆኑ ተነግሯል ።
እንግዲህ መላውን ለማግኘት ሳይንቲስቶቹ እየተጠዳደፉ ሲሆን (ጊዜ አልሰጥ ብሏልና ) አሜሪካ በአሳማዎች ላይ የተሞከረ፣ የመከላከያ ክትባት በቅርቡ አደርሳለሁ እያለች ነው። የጀርመን ሳይንቲስቶች ጫፍ ላይ ነን፤ ያለነው ሲሉ አሜሪካ ሙከራ ላይ ነን ነው፣ እያለች ነው፤ ጃፓን ውጤታማ መሆኗን እየነገረችን ነው። የእስራኤል ሳይንቲስቶች ዘጠና ቀን ብቻ ጠብቁን፣ ብለውናል። ሁሉም በዚህ አስከፊ ህመም ትውልድ ሳይበላሽና በርካታ ነፍስ ሳይጠፋ ሊደርሱ ካልቻሉ አደጋው የከፋ ነው፤ የሚሆነው።
እግረ መንገዴንም ህመሙ የፈጠረውን ስጋት ከውጭ ዜጎች ጋር በማያያዝ እየተፈጠሩ ያሉት እንግዳ የአጸፋ እርምጃዎች እጅግ አስደንጋጭና ከሰብአዊነት ያፈነገጠ እርምጃ መሆኑን ከመናገር ወደኋላ አልልም።በጣሊያን ወረራና ከዚያም ተሸንፋ በወጣች ጊዜ በፋሽስቶች በተፈጸመ ግፍ ሳቢያ እጅግ የተከፉ አንዳንድ ወገኖቻችን ነጭ ባዩ ቁጥር ካልገደልን እያሉ ያስቸግሩ እንደነበረ የታሪክ ድርሳናት አውስተውታል።አሁን ደግሞ በሽታው ምክንያት የውጭ ዜጎች የሆኑ ይመስል፤ ኮሮና ሰብዓዊ ጥፋት መፈፀሙን ያልተገነዘቡ ሰዎች አሳፋሪ እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን ሰምተናል።
ህመሙ ወይም ቫይረሱ ቀለም፣ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ትምህርትና እውቅናን ወይም አለመታወቅን ምክንያት አድርጎ የማይምር፣ ጸረ የሰው ልጅ ህመም መሆኑን አለማጤን አሳዛኝ እና ዘመኑን የማይመስል አስነዋሪ ድርጊት መሆኑን አበክሬ መግለጽ እፈልጋለሁ።ስለዚህ እንተዛዘን እንጂ አንጨካከን፤ እንረዳዳ እንጂ አንገፋፋ፤ እንከባበር እንጂ አንሸባበር።በድህነትና የጤና እጦቱ ላይ ጭካኔ ጨምረንበት የትም አንደርስም።አደብ እንግዛ፤ ማለት እወዳለሁ!
ስለዚህ ያለውን መልካም እየበሉ እንጂ እየተበሉና እየተባሉ ላለመክረም እየተደረገ ያለው ትብብር እንዲሰፋ የሰው ዘር በሙሉ በጥንቃቄና በጉጉት መድኃኒቱን ይጠብቅ። ኮሮናም ፣ በአስተሳሰብም፣ በአካልም ወደአንድ ጥግ “ወደ-ኮርና” የገፋንን መግፋት ለቀቅ በማድረግ ወደቀደመው ሜዳችን የምንመለስበትና እርሱን ስፍራ የምናስለቅቅበት ጊዜ እንዳይረዝም የሁላችንም ተገቢ ጥንቃቄና ጸሎት አስፈላጊ ነው፤ ብዬ አምናለሁ። መረጃዎችን ሁሉ ከተገቢው የጤና ተቋምና አካል ብቻ በመቀበል፣ በማንበብም ሆነ በማድመጥ ራሳችንን እንጠብቅ።እየተጠነቀቅን እንጠብቅ ፤ እየጠበቅንም እንጠነቀቅ!!
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 / 2012
አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
ኮሮናና ኮርና