የወልቃይቱ ወጣት የልጅነት ህይወቱን ያጋመሰው በትምህርት ገበታው ላይ ሆኖ ነው። ዕድሉ ቀንቶት የቀለም ‹‹ሀሁ››ን ለመቁጠር የታደለው ገና በጠዋቱ ነበር።የዛኔ እሱን መሰል እኩዮቹ ከእርሻ እየታገሉ ከከብቶች ጭራ ስር ሲውሉ ክፍሉ ሀጎስ ደብተር ይዞ ትምህርት ገበታ ላይ ተገኝቷል። ብዙዎቹ ቀለም መለየት ህልማቸው በሆነበት ጊዜም እሱ ከዕውቀት ተራ ተሰልፎ ፊደል ከቁጥር ለይቷል።
ክፍሉ የሁመራ ህይወቱ ከትምህርቱና ከቤተሰቦቹ ጋር ነበር። እንደ አገሬው ነዋሪ የግብርና ልፋትን ጠንቅቆ ያውቃል። እንደ አብዛኞቹም መልካም ገበሬ መባልን ይወዳል። በዕድሜው ከፍ ሲል ከእርሻ መዋልን ከበሬ ታግሎ መመለስን ለመደ። ይህ ዕድሜው ክፉ ደጉን የለየበት ነበርና በማንነቱ ለመወሰን ጭምር ምክንያት ሆኖታል።
አስረኛ ክፍል እንደገባ ለትምህርቱ የነበረው ፍላጎት ቀነሰ።ተምሮ ስለሚያደርገው ህልም ከማሰብ ይልቅ ውስጠቱ በሌላ ሀሳብ ተወጠረ። ከመማርና ትምህርት ቤት ከመዋል ይልቅ መሬቱን እያረሰ ጎተራ ሙሉ ምርት ማፈስ አማረው። ይህን ስሜቱን ዕውን ለማድረግ ጊዜ አልፈጀበትም። ትምህርቱን አቋርጦ ወደ እርሻው ዘለቀ።
ወረቀት መያዝ የለመዱ የክፍሉ እጆቹ እርፍ ነቅንቀው ደረቁን መሬት ለማረስ አልሰነፉም። ትምህርቱን ‹‹ደህና ሰንብት›› ያለው ወጣት ጠንካራ ገበሬ ሆነ። ምርት ማፈስና ጎተራ መሙላትንም ለመደ። ይህ አጋጣሚ ደግሞ የትዳር አጋሩን ለማግኘት ሰበብ ሆነለት። ገጠር ወርዶ ከቤተሰቦቹ የተጣመረው ክፍሉ የግራ ጎኑን አግኝቶ ጎጆውን አቆመ።
ክፍሉ ከትምህርት ከተረሳሳ ዓመታት ተቆጥረዋል።አሁን የዘወትር ህልሙ ሁለት ልጆቹን በወግ ማሳደግና የትዳር ጎጆውን በበረከት መሙላት ነው። ለዚህ ፍላጎቱ የማይቦዝነው ገበሬ ዘወትር ከእርሻው ውሎ በድካም ሲመለስ በሚስቱና በልጆቹ ፍቅር ይደሰታል።
ጠንካራው ገበሬ ሻካራው እጆቹ መልካም ፍሬን ያሳፍሱት ይዘዋል፣ የልቡን ፍላጎት ሞልቶ ቤተሰቦቹን አጥግቦ አድሯልና ደስተኛ እንደሆነ ውሎ ያድራል። ዘወትር በጉልበቱ ድካም፣ በላቡ ወዝ የሚሞላው ጎተራ ጎድሎበት አያውቅም። ይህ መሆኑ ስለነገው የልጆቹ ተስፋ ያለሀሳብ እንዲራመድ አግዞታል።
ሰሞኑን ግን የክፍሉ ልብ ርቆ ማሰብ ጀምሯል። ሲደክም ውሎ ከቤቱ ሲገባም የቀኑን ውጥን በቀላሉ መርሳት ይቸግረዋል።ይህን ሲያስብ ሚስቱንና በወጉ ያላደጉ ልጆቹን አይረሳም። ያም ሆኖ ግን በውስጡ የጸናው ውሳኔ እያመዘነ ያቀደውን ለመከወን ከቆረጠ ቆይቷል።
ክፍሉ ታላቅ ወንድሙን ጨምሮ ሌሎች ዘመዶቹ አዲስ አበባ እንደሚኖሩ ያውቃል።ሁሌም ቢሆን እነሱን ከራሱ ሲያወዳድር ልዩነታቸው ሰፍቶ እንደታየው ነው።የከተማ ሰው ልብሱ የጸዳ፤ ንግግሩ ያማረ መሆኑ ሲማርከው ቆይቷል። የሰሞኑ ሀሳብ ከዚህ እውነታ ጋር ተዳምሮም እግሮቹ ለመንገድ ተዘጋጅተዋል።
ወጣቱ ገበሬ ዛሬን ከበረታ ነገ ከእነሱ እንደማያንስ ውስጡን ካሰመነ ቆይቷል። ገበሬነቱን ረስቶ የከተማ ሰው ለመሆን ሲወስንም ፈጽሞ አላመነታም። ዛሬ ላይ ሆኖ ስለነገው መልካም መሆን እያሰበ የቋጠረውን ጓዝ አጠበቀ። ውስጡ ጥሩ የሚባል ስሜት አቀበለው። የሞቀ ጎጆውን የትዳር አጋሩንና የሚወዳቸውን ልጆቹን ትቶ ወደ አዲስ አበባ ኮበለለ።
አዲስ አበባ
ክፍሉና አዲስ አበባ ለመተዋወቅ ጊዜ አልፈጁም። እንግድነት እንዳይሰማው ያገዘው ታላቅ ወንድሙ ከተማውን አላምዶ ከወዳጀ ዘመድ አገናኘው። ወንድሙ ዘርአይ በተለያዩ ምክንያቶች በየአገሩ ዞሯል። በየደረሰበት ለስራ አይቦዝንም። ጥሩና ክፉ አጋጣሚዎችንም አልፏል።ታናሽ ወንድሙን ባገኘው ጊዜ ከእሱ የህይወት ልምድ እንዲማር እየመከረ መንገድ አመላ ከተው።
ክፍሉ ኑሮውን ሀያ ሁለት ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ አደረገ። ስራ ለማወቅም የሚሻለውን እያማረጠ ቆየ። የትናንቱ ገበሬ ዛሬ ከተሜ ሆኖ ዘመናዊነትን ሊጋራ ሲወድ መሰሎቹን መምሰል ግድ አለው። ታላቅ ወንድሙ ለእሱ ይበጃል ያለውን የጸጉር ስራ ሲጠቁመው ደስተኛ ነበር።
የጸጉር ማሳመሩ ስራ ለክፍሉ ወዳጅ ዘመድ አፍርቶለት ከአገሩ አላመደው። የሚያገኘው ገንዘብና ለቤተሰቦቹ ያለው ሀሳብ ግን ሊገናኝ አልቻለም።ጥቂት ተከፋዩ ወጣት እጅ ባጠረው ጊዜ ለልጆቹ አለመሆኑ ያሳስበው ጀመር። ይህን ጭንቀቱን የሚያውቀው ወንድሙ አዳሩን ከአክስታቸው ቤት አድርጎ ውሎውን በስራ እንዲያሳልፍ አመቻቸለት።
የእነክፍሉ አክስት ወይዘሮ ለታይ አዲስ አበባ ከመጣች ዓመታት ተቆጥረዋል።ከአገር ቤት ለሚመጡ ዘመዶች ደጋፊ በመሆኗም በርካቶቹ እያከበሩ ይወዷታል። አውራሪስ ሆቴል አካባቢ በከፈተችው የእንግዶች ማረፊያ የምትተዳደረው ለታይ ለስራው የቀጠረቻቸው ሰራተኞች አሏት። ወይዘሮዋ ክፍሉን ባገኘችው ጊዜ ምክሯን ለገሰችው። ለማደሪያው ይሆን ዘንድ ባዘጋጀችለት ክፍልም ባሻው ጊዜ እየገባ አረፍ እንዲል ፈቀደችለት።
ክፍሉ ቀን እየሰራ ምሽት ጎራ የሚልበት የአክስቱ ፔንሲዮን ለጎኑ ማረፊያ ሆነው። ከሚያገኘው ገንዘብ ለራሱና ለልጆቹ እየላከም አቅሙን አደራጀ። እንዲህ መሆኑ ዛሬን እፎይ ብሎ ለነገ የተሻለ እንዲያስብ አገዘው።ገቢው ከእጅ ወደአፍ ቢሆንም ከድካም መልስ ለጎኑ ማረፊያ ማግኘቱ ሰላም አስገኘለት።
አንድ ቀን ደግሞ አክስቱ የተሻለ ያለችውን ሀሳብ አንስታ አማከረችው። ቀን እየሰራ ከሚያገኘው ገቢ ሌላ አልጋ ቤቱን በዘበኝነት እየጠበቀ ተጨማሪ ደሞዝ ማግኘት እንደሚችል ነገረችው። ክፍሉ ይህን በሰማ ጊዜ ከልቡ ተደሰተ። የአክስቱን እጅም በምስጋና ጨበጠ።ለጎደለው ሙላት ዳግም መፍትሄ መሆኗ አስገርሞትም ስለውለታዋ መልካምነቷን መሰከረ።
ክፍሉ ከስራው እየዋለ ማታ ከፔንሲዮኑ በር አምሽቶ ለሊቱን ዘብ ማደር ጀመረ። በደማቅ ፈገግታ ለአዳር የሚመጡ ደንበኞችን እያስተናገደም ምስጋናን ከጉርሻ ጋር መቀበልን ለመደ። ከደሞዙ ሌላ የሚያገኘው ጥቅም ለእንጀራ ፈላጊው ሰው ቀላል አልሆነም።በየቀኑ በመታዘዝ ሰበብ የሚቀበለው ገንዘብ የተራቆተ ኪሱን ለመሙላት ምክንያት ሆነለት።
አሁን ክፍሉና አዲስ አበባ በደንብ ተዋውቀዋል።የከተማዋን መግቢያ መውጫ ከመለየት ባለፈ ኑሮውን በምን ብልሀት መምራት እንዳለበት ጭምር ገብቶቷል።የሰዎችን ባህርይ ከእሱ ማንነት ጋር ማዘመድን ህይወት ያስተማረችው ወጣት ሁሉን እንደአመጣጡ እያለፈ ከብዙዎች መግባባትን ለ ምዷል።
ክፍሉ አክስቱ ከሰጠችው የዘበኝነት ስራ ይበልጥ ደንበኞችን እየተንከባከበ የሚያገኘው ጥቅም በልጦበታል።ይህ የየዕለት ጉርሻ እየጣመው ሲሄድም ዘወትር ምሽት ከበሩ መግቢያ እያፈጠጠ ኪሱን የሚያረጥቡለትን እንግዶች መናፈ ቅ ጀምሯል።
አንዳንዴ የአልጋ ክፍሉን የምትቃኘው ለታይ የሚያስፈልገውን ሁሉ ታሟላለች። ከቦታው ላይ ስትቆይም የገባውን ሂሳብ ተቀብላ ስለግቢው ደህንነነት ለክፍሉ አደራ ትሰጣለች። አልፎ አልፎ ባመሸች ጊዜ የተያዙ አልጋዎችን ሂሳብ አታሳድርም። ይህን የሚያውቀው ክፍሉም ከደንበኞቹ የሚቀበለውን ብር በአግባቡ ቆጥሮ ያስረክባታል።
ለታይ ለዘመዶቿ አሳቢና በርካቶችን ባላት አቅም የምትረዳ ወይዘሮ ናት። የዛኑ ያህልም የማይመች ድርጊት ከገጠማት ትዕግስቱ የላትም። ይህ ስሜቷ ደግሞ አንዳንዴ በቁጣና በስድብ ጭምር ይገለጻል።በተለይ በለፋችበትና መተዳደሪያዋ በሆነው ገቢዋ ላይ ቀልድ ይሉትን አታውቅም። ሁሌም አመኔታን ትሻለች።
መጋቢት 26 ቀን 2011 ዓም
ክፍሉ የዕለት ተግባሩን አጠናቆ ምሽቱን በአልጋ ቤቱ ለማሳለፍ በሰዓቱ ተገኝቷል። ይህ ጊዜ የቀጣይ ስራው ጅማሬ በመሆኑ እንደሁልጊዜው ከበረንዳው ሆኖ የውጭ በሩን መንኳኳት ይጠብቃል። ውሎዋን በአልጋ ቤቱ ያደረገችው አክስቱ አሁንም በግቢው እንዳለች ነው።እሷ በስፍራው ከቆየች የዕለቱን ሂሳብ እንደምትቀበል ይታወቃል።
ምሽቱ መግፋት ይዟል። አክስት ለታይ በግቢው ካለ የማብሰያ ክፍል ቡና ለማፍላት ስኒዎችን እያቀራረበች ነው።ክፍሉ አሁንም ከሚጠብቃቸው ደንበኞች የሚናፍቀውን ጉርሻ ያብሰለስላል። በግቢው ያሉ አብዛኞቹ ክፍሎች ቀድመው በመጡ እንግዶች ተይዘዋል።የተቀሩት ደግሞ አዳሪ እንግዶችን ይጠብቃሉ።
ክፍሉ እየተንቆራጠጠ የእጅ ሰዓቱን ደጋግሞ ተመለከተ።ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ላይ ያመለክታል። ድንገት የውጩ ብረት በር በቀስታ ሲንኳኳ ጆሮዎቹ በንቃት አዳመጡ። ሮጥ ብሎ በሩን ከፈተ። ሁለት ጥንዶች ከደጅ ቆመዋል። የቤቱ ደንበኞች ናቸው።ፈገግ አለ። ወንዱ አልጋ ስለመኖሩ ጠየቀው። ክፍሉ በአዎንታ ወደውስጥ እንዲገቡ በሩን ከፈተላቸው። ይህኔ አክስቱ ለታይ የገቡትን ሰዎች ለማየት አንገቷን አሰገገች።
ክፍሉ ካልተያዙት አልጋዎች የተሻለውን መርጦ አሳያቸውና ሂሳብ ለመቀበል ቆም አለ። ደንበኛው ገንዘቡን አወጣና ቆጥሮ አቀበለው። ከመራቁ በፊት ጠራውና ውሀ እንዲገዛለት አንድ መቶ ብር ሰጠው። ክፍሉ በሀያ ብር ውሀውን ገዝቶ ቀሪውን ሰማንያ ብር መለሰ። ይህኔ ደንበኛው ከተመለሰው ገንዘብ ሀምሳ ብሩን በጉርሻ አስጨበጠው።ክፍሉ ፊቱ በፈገግታ እንደበራ ሌላ ትዕዛዝ ይኖር እንደሆን ጠየቀ።ደንበኛው አስራ አምስት ብር አንስቶ ኮንዶም እንዲያመጣለት አዘዘው።
ክፍሉ የተሰጠውን ብር ይዞ ሲወጣ በርቀት አክስቱ አየችው። ከተል ብላም ስንት እንደተቀበለ ጠየቀችው።ክፍሉ በእጁ ያለው አስራ አምስት ብር እያሳያት የታዘዘውን ለማምጣት ተጣደፈ። ወይዘሮዋ የኮንዶሙ ዋጋ ሀያ ብር መሆኑን እያውቀ አስራ አምስት ብር ብቻ ለምን እንደተቀበለ በቁጣ ጠየቀች። ሁኔታዋን ሲያይ ቀሪውን አምስት ብር እሱ እንደሚሞላ ተረጋግቶ መለሰላት።ምላሹን እንደሰማች ፊቷ ላይ ብስጭት ተነበበ።
አክስት ለታይ በንዴት እየተንጨረጨረች የእንግዶቹን ክፍል በሀይል ደበደበች። ለምን ስትልም አፈጠጠችባቸው። ደንበኛው በድርጊቷ ተናዶ ከነበረበት ተነሳና እሱም በንዴት አፈጠጠ። ጭቅጭቅና አለመግባባቱ ከመጠን ሲያልፍ ሰውዬው ክፍሉን ጠርቶ የወሰደውን ብር እንዲመልስ ጮኸበት። ክፍሉ ምርጫ አልነበረውም።በትኩስ ትንፋሹ እየጋየ ከደንበኛው የተቀበለውን አራት መቶ ብር አንድ ሁለት ብሎ መለሰ።ወዲያውም ሰውዬው ጓደኛውን ይዞ ከግቢው ሲወጣ ደም በለበሱ ዓይኖቹ ሸኘው።
እንግዶቹ ከበሩ እንደወጡ አክስቱ ከምትወቅጠው ቡና ላይ ተነስታ ክፍሉን በስድብ ወረደችበት።ከዚህ ቀድሞ የሰራውንና ዛሬም የደገመውን እያነሳችም ስለማንነቱ ከፍ ዝቅ አደረገችው። ክፍሉ የምትለውን ሁሉ እንዳልሰማ ለማሳለፍ ሞከረ። ለንግግሯ ምላሽ ሳይሰጥም በዝምታ ቆየ።አክስቱ ዝምታው አናደዳትና በቁጣዋ ቀጠለች።
አሁን ክፍሉ ወስጡ እየበሸቀ ነው። የአክስቱ ክፉ ንገግር ሰላም አልሰጠውም። በጀመረው ትዕግስት መቀጠል አልቻለም። ከተቀመጠበት ተነስቶ ወደ አክስቱ ተጠጋ። ሲቀርባት ይባስ ነደደው። የቡና ዘነዘናውን ቀምቶ አንድ ጊዜ አንገቷ ላይ መታት። ወደቀች።ስትንፈራፈር አያት። አልተነሳችም። አልደነገጠም። ጥርሱን እንደነከሰ ትቷት ወደ በሩ ወጣ።በግቢው ማንም የለም።
በቆመበት ወደኋላው ቃኘ። አክስቱ በጭንቀት እየተወራጨች ነው። ስቃይዋን እያየ ዝም አለ።ጥቂት ቆይቶ ለዘመዶቹ መደወል ፈለገ። አልተዋጠለትም።እንደገና መለስ ብሎ አክስቱን አያት ።በትንሹ እየተፈራገጠች ነው። ቀረብ ብሎ ትንፋሽዋን አዳመጠ።ጸጥ ብላለች። ክፍሉ ፈጥኖ ወደ ኩሽናው ገባና አካፋና ዶማ አነሳ። መሬቱን ቆፍሮም ጥልቅ ጉድጓድአዘጋጀ።እየተጣደፈ የአክስቱን ሬሳ ተሸከመና በለበሰችው ቀሚስ ጠቀለላት። በቆፈረው ጉድጔድ አጋድሞም የቆለለውን አፈር እየመለሰ በእግሩ ደመደመው። በላዩም ትላልቅ ድንጋዮችን ጭኖ ስፍራውን አጸዳ። ወዲያው ከራሱ መከረና ውስጡን አረጋጋ። ጥቂት ቆይቶ ደንበኞች የግቢውን በር አንኳኩ። ሁሉንም በፈገግታ አስተናግዶ የአዳሩን ገንዘብ እየቆጠረ ተቀበለ።
ከቀናት በኋላ
ቀናት ተቆጥረዋል። የቤቱ ባለቤት አልታየችም።ክፍሉ ግን ፔንሲዮኑን እያከራየ ገንዘብ መቁጠሩን ቀጥሏል።በፊቱ ላይ የተለየ ነገር የለም። ልክ እንደትናንትናው ደንበኞችን በፈገግታ ተቀብሎ ያስተናግዳል።ሌላ ሰራተኛ ቀጥሮም ገቢውን ይቆጣጠራል። የለታይ አለመታየት ያሳሰባቸው በርካቶች ግን ጥያቄ ማንሳት ጀምረዋል። ክፍሉ ለጠየቁት ሁሉ ከአገር ስለመውጣቷ መጠርጠሩን ተረጋግቶ ይመልሳል። አንዳንዴ ደግሞ ክፍሉ የአክስቱን ከጸበል መሄድ በእርግጠኝነት ይናገራል።ይህን ያመኑ ዘመዶችም ፎቶግራፏን በየቦታው ለጥፈው ‹‹በአፋልጉኝ›› ማስታወቂያ አሰሳቸውን ይቀጥላሉ።
ውሎ ሲያድር የብዙዎች ጥርጣሬ ጨመረ። ትገኝበታለች ባሉት ስፍራ ሁሉ ክፍሉን ይዘው ፍለጋቸውን አጠነከሩ።ጉዳዩ ያሳሰባቸው የቅርብ ዘመዶች ግን ፖሊስ ዘንድ ቀርበው አቤት አሉ።
የፖሊስ ምርመራ
ጥቆማ የደረሰው ፖሊስ ምርመራውን ቀጠለ ።የቤቱን ተቆጣጣሪ ክፍሉንና ሌሎች ዘመዶችን አቅርቦም በጥያቄ አጣደፈ። ክፍሉ ፖሊስ ለሚጠይቀው ሁሉ ተረጋግቶ ምላሹን ሰጠ።ዕንባ ካቀረሩ ዓይኖቹ እየታጋለም የአክስቱን መልካምነት ደጋግሞ መሰከረ።
ከቀናት በአንዱ ቀን ግን ክፍሉ ካራማራ ፖሊስ ጣቢያ ደርሶ የሆነውን ሁሉ ዘረዘረ።አክስቱን ስለመግደሉ ተናግሮም በድርጊቱ መጸጸቱን ተናገረ።ፖሊስ ከተባለው ግቢ የምርመራ ቡድኑን ይዞ ደረሰ።ከኩሽናው ገብቶም ቁፋሮውን ቀጠለ።ግድያ የተፈጸመባት ወይዘሮ ከሁለት ወራት በላይ ተቀብራ መቆየቷንም አረጋገጠ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 / 2012
መልካምስራ አፈወርቅ