ጊዜው ከንፏል፤ ትዝታው ግን የትናንት ያህል ትኩስ ነው። አሥራ አምስት ዓመታትን ወደ ኋላ እንደረደራለሁ። ሀገሩ አሜሪካ፤ ሚኒሶታ ክፍለ ግዛት፤ ሴንት ፖል ከተማ። ቀኑ ኤፕሪል 3 ማለዳ ላይ። ጸሐፊው በወቅቱ የቤቴል ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበር። የሰርክ ልማዱ የሆነውን የማለዳ ጸሎት ካደረሰ በኋላ ከቁርሱ ጋር አንድ ፍንጃል ቡና ፉት እያለ የዓለምን ውሎ አዳር የሚተነትነውን የቴሌቪዥን ዜና እየተከታተለ ነበር። ዛሬም በማለዳ ቡና ፉት ሳይልና ዓለም አቀፍ ዜናዎችን ሳይቃኝ ከቤቱ አለመውጣቱ የፀና ልማዱ እንደሆነ ቀጥሏል። የዚያን ዕለት የሆነውም ይሄው ነበር።
ጥሩ የዜና ትንታኔ ከሚያቀርቡ የቴሌቪዥን ቻናሎች አንዱ የሆነው በዚያ ዕለት ኤፕሪል 3 ደጋግሞ ያሳይ የነበረው በመላው ዓለም ተወዳጅ የሆነን አንድ ፎቶግራፍ ነበር። የፎቶግራፉ ስም ፀጋ (Grace) በመባል ይታወቃል። የበርካታ ሀገራት ሰዓሊያን (የእኛንም ሀገር ጨምሮ) ያንን ፎቶግራፍ ወደ ስዕል ለውጠው እየተባዛ እንደሚሸጥ አውቃለሁ። መርካቶ መሃል ወደሚገኘውና አዳራሽ በመባል በሚጠራው የገበያ ማዕከል ቅርጻ ቅርጽ መሸጫ ሱቆች ጎራ የሚል ገበያተኛ “የፀጋን የስዕል ቅጂ” ዛሬም በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት ይችላል። በፖስተር መልክም ታትሞ መሰራጨቱንም አውቃለሁ።
ለምን ያ ፎቶግራፍ ኤፕሪል በዚያን ዕለት ተደጋግሞ በተለያዩ የአሜሪካ የቴሌቪዥን ቻናሎች ሳይቀር ተላልፎ እንደነበር ከመግለጼ አስቀድሞ ስለ ፎቶግራፉ ይዘት ጥቂት ማብራሪያ ልስጥ። ፎቶግራፉ ላይ የሚታዩት ሞገሳቸው የከበደ አንድ አዛውንት ናቸው። የአዛውንቱ ፀጉርና ጢም የተነደፈ የጥጥ ሃመልማሎ ይመስላል። አለባበሳቸው አንደነገሩ ነው። ሁለት እጃቸውን አጣምረው ግንባራቸው ላይ በማሳረፍ ከፊታቸው የቀረበውን ቁርስ ለመባረክ በተመስጦ ጸሎት ውስጥ ሆነው ይታያሉ። ከፊት ለፊታቸው ባለው የምግብ ጠረጴዛ ላይ አንድ የዳቦ ሙልሙልና ቡና የሞላበት ሲኒ ቀርቧል። እዚያው ጠረጴዛ ላይ ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚታይ ሲሆን መነጽራቸው በመጽሐፉ ላይ ተቀምጧል። አቀማመጣቸው፣ የጸሎት ተመስጧቸው፣ ቁርሳቸውና ቅዱስ መጽሐፋቸው “ከሺህ ቃላት አንድ ስዕል የበለጠ ይናገራል” ለሚለው ይትባሃል በጥሩ ማሳያነት ሊጠቀስ ይችላል።
ይህንን ድንቅ ፎቶግራፍ እ.ኤ.አ በ1918 ዓ.ም ያነሳው ሰው ኤሪክ ኤንስትሮም ይባላል። ሰውዬው እንደ ሀገራችን የአደባባይና የጎዳና ላይ ፎቶግራፍ አንሺዎች እየተንቀሳቀሰ ሰዎችን ፎቶግራፍ በማንሳት በሚያገኘው ገቢ ለዕለት ጉርሱ የሚተጋ ባለሙያ ነበር። አንድ ዕለት (ከመቶ ዓመት በፊት መሆኑን ልብ ይሏል) ከመንትዮቹ የሚኒሶታ ከተሞች (ሚኒያፖሊስና ሴንት ፖል) ወጣ ብላ በምትገኘው ገጠራማና ጭቃ በማይጠፋባት የዱሉዝ አነስተኛ የመንደር ገበያ ውስጥ ፎቶግራፈሩ ኤሪክ ካሜራውን አንግቦ እየተንቀሳቀሰ ፎቶግራፍ ተነሺዎችን ሲፈልግ ከእኚህ አዛውንት ጋር ይገጣጠማል። አዛውንቱን ልክ እንዳያቸው አንዳች የአድናቆት ስሜት አንዝሮት ቀረብ በማለት ፎቶግራፍ ቢያነሳቸው ፈቃደኛ መሆናቸውን ጠይቆ ስምምነታቸውን ያገኛል።
አዛውንቱ ስማቸው ዊልደን እንደሚባል ከገለጹለት በኋላ ፎቶግራፋቸውን ከመውሰዱ በፊት ሻይ ቡና እያሉ ለመጨዋወት እንዲያመቻቸው እንደነገሩ ወደሆነች የአካባቢው ካፊቴሪያ ይዟቸው ጎራ ይላል። በዚህ ወቅት ነበር የቀረበላቸውን ቁርስ በልዩ የጸሎት ተመስጦ ውስጥ ሆነው አመስግነው ለመመገብ ጎንበስ ሲሉ ያ ፎቶግራፈር ምስላቸውን በካሜራው ያስቀረው።
ይህ የአንድ ክፍለ ዘመን የዕድሜ ባለጠጋ ፎቶግራፍ ነበር በዚያ ማለዳ በመላው አሜሪካ በሚገኙ የቴሌቪዥን ቻናሎች ሲተላለፍ የዋለው አለምክንያት አልነበረም። ፎቶግራፉ ለሚኒሶታ ክፍለ ግዛት ከተራ ፎቶግራፍነት ላቅ ብሎ የክፍለ ግዛቱ ኦፊሴላዊ ተምሳሌትና ምልክት ሆኖ መወሰኑን ለማብሰርና እውቅና ለመስጠት ነበር ፎቶግራፉ ሲታወስና ሲወደስ የዋለው። የፕሮግራሙ የክብር እንግዳ የነበሩትና እውቅናውን ያበሰሩት የወቅቱ የሚኒሶታ ክፍለ ሀገር ገዥ (Governor) የነበሩት ጄሲ ቬንቹራ ናቸው። ጄሲ ቬንቹራ ወደ ፖለቲካ ሥልጣን ከመምጣታቸው አስቀድሞ የታወቁ የሬስሊንግ ተፋላሚ አንደነበሩ ብዙ ሰዎች የሚያስታወሱ ይመስለኛል።
ከሞገሳማው “የፀጋ ፎቶግራፍ” ጀርባ የነበረው የሰውዬው የኋላ ታሪክ ግን እንደ ምስሉ የሚመሰገንና የሚወደድ አልነበረም። እንዲያውም ተቃራኒ ነበር ማለቱ ይቀላል። በሚሊዮን በሚቆጠሩ የዓለም ዜጎች የተወደደውና የሚኒሶታ ክፍለ ሀገር ተምሳሌት ለመሆን ዕድል ያገኘው የዚያ ፎቶግራፍ ባለቤት አዛውንት በወቅቱ ሕይወታቸው ሲጠና በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ በተግባራቸው የተወገዙ፣ አንቱታንም የተነፈጉ፣ ትዳራቸውን በመፍታት የሚታወቁ፣ በተደጋጋሚ ጥፋቶች ፍርድ ቤት ያሰለቹ መሆናቸው በግለ ታሪካቸው ጥናት ተረጋግጧል። “ታቦተ ክፉ፤ አፀደ መልካም” ይሏል እንዲህ ዓይነት ተቃርኖ የሚስተዋልበትን ክስተት ለመግለጽ ታስቦ ይመስለኛል። የውስጥና ውጭ ማንነት ሲቃረን። በነገራችን ላይ ይህ ስዕል ትልቅ ተጽእኖ ስላሳደረብኝ ፎቶግራፉ በተነሳበት በውቧ የዱሉዝ ከተማ ተገኝቼ የአንድ ቀን ጉብኝት ለማድረግ እድል ገጥሞኛል።
የፀጋ ስዕል ያስታወሰኝ ሰሞንኛ ጉዳይ፤
የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ከቀናት በፊት በሚሊኒዬም አዳራሽ ለፓርቲያቸው የሀብት ማሰባሰቢያና የምሥጋና ፕሮግራም በተዘጋጀ የራት ግብዣ ላይ ባደረጉት ንግግር ከተግባር የተፋቱ የሀገራችንን ምሁራን ሸንቆጥ አድርገው ማለፋቸው ይታወሳል። ይሄው ንግግር በበርካቶች ዘንድ ዋናና የሳምንቱ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል። አንዳንዶች እንዴት የፓርቲው ፕሬዚዳንትና የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲህ የመሰለ ዘለፋ ያስተላልፉብናል ብለው ሲቆጡ፤ በርካቶች ደግሞ ለንግግራቸው ድጋፍ በመስጠት “እውነት ነው! ሁሉም ለማለት ቢያዳግትም ብዙዎቹ የሀገራችን ባለማስትሬትና ባለዶክትሬት ዲግሪ ምሁራን ዲግሪያቸው የተሸከመውን የሙያ ዓይነትና ብዛት ከመዘርዘር የዘለለ ለሀገራችን ምን ፈየዱ። የፕሮፌሰርነት ማዕረጋቸውስ ድህነታችንን አሽቀንጥረን እንድናስወገድ መች አገዘን።”
በማለት ሲሞግቱ ተስተውለዋል። የአንዳንዶቹ ሃሳብ በምሁራዊ ገለጻ የወዛ ብቻ ሳይሆን በዘለፋም የተዋዛ ነበር፤ በተቃውሞም በድጋፍ አሰጣጡም። ስለሆነም እንደ ጸሐፊው እምነት የፓርቲው ፕሬዚዳንትና የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ያስተላለፉት መልዕክት አንዳንዶች በተቃራኒ እንደተረዱት ሀገሪቱ የማይተመን ዋጋ ከፍላ ያፈራቻቸውን ምሁራን በጅምላ ለመውቀስና ለመኮነን አስበው አይመስለኝም።
ለማንኛውም “ለብልህ አይነግሩም፤ ለአንበሳ አይመትሩም” ብለን ጠቅላዩ ባነሱት ዋና ሃሳብ ላይ እኔም መስማማቴን ለመግለጽ የጥናት ውጤት ሳይሆን ስሜቴን ላጋራ ወድጃለሁ።
በተፈጥሮ ሳይንስም ይሁን በማሕበረሰብ ሳይንስ አንቱታን ያተረፉ የሀገራችን ምሁራን በየሰለጠኑበት የዕውቀት ዘርፍ ለሀገር የሚበጅ ምንም ውጤት አላስመዘገቡም ብሎ መበየኑ በራሱ ትልቅ ስህተት ይሆናል። ጠቅላዩም ይህንን ማለታቸው አይመስለኝም “ታስቧል” ተብሎም ሊታመን አይገባም። እነዚያ ውጤታቸው አልተጨበጠም ተብለው የሚታሙት ምሁራንም እኮ፤ ቢያንስ በማስተማርና በምርምር ሙያ ውስጥ የተሰማሩቱ፤ ከፋም ለማ አሰልጥነው የሚያስመርቋቸው ወጣቶች ለሀገራቸው ተስፋ መሆናቸው ግን በራሱ ለምስጋና የሚያንስ አይደለም።
ጸሐፊው በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚጠቃቅሳቸው በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም ለጋዜጣው አምድ ሊመጥኑ የሚችሉትን ጥቂት ማሳያዎች ብቻ ለማመላከት ይሞክራል። ብዙ ቴክኖሎጂስት ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች አሉኝ የምትል ሀገር ዛሬም አርሶ አደሮቿ እየመገቡን ያሉት የሺህ ዘመናት ዕድሜ ያለውን ሞፈር እየሳቡ መሆኑ ማስከፋት ብቻ ሳይሆን ለምሬትም ይዳርጋል። ሁለት በሬ ጠምዶ የሚያርሰው ገበሬ ለራሱም ሆነ ለዜጎች ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ጉርሻ የሚያቃምሰን ዘመን ባሸበት የእርሻ ባህሉ ልምምድ ምርኮኛ እንደሆነ ነው። በዚህ ረገድ ቴክኖሎጂስት የሚባሉት ምሁራኖቻችን ራሳቸውን ቢፈትሹ አይከፋም።
በጂኦሎጂ ዘርፍ ሰልጥነው የሚያሰለጥኑ ምሁራን የተትረፈረፉባት ሀገር ዛሬም ማእድኗን በማህፀኗ እንደታቀፈች እያንጎላጀጀች አለች። የውሃ ሃብቷንም አልምተውላት ከጥም ሊገላገሉን አልቻሉም። በቡናዋ ላይ እሴት፣ በቆዳና ሌጦ ላይ ውበት ጨምረው ከዓለም ጋር እንድትወዳደር “አላሰለጠኗትም”። የውሃ ግድብ ለመሥራት፣ የባቡር መስመር ለመገንባት ዛሬም ለገንዘቡም፣ ለእውቀቱም የምናፈጠው በባእዳን ዳረጎት ላይ ነው። ያውም ዓይናችንን በጨው አጥበን። የኢኮኖሚው ሥርዓት መስመሩን ይዞ እንዲያድግ፣ የሕክምና ጥበቡ ጎልብቶ “እልል ሊያሰኘን” አልቻለም። ምሁራኖቻችን ጠቋሚ እንጂ የሀገሪቱን እድሜና ልምድ ያህል “የመፍትሔ አዋላጅ” ሊሆኑን ስለመቻላቸው ገና በጋራ መግባባት ላይ አልተደረሰም። የእውቀት ዘርፉን እንዘርዝር ብንል ብዙ ማለት ይቻላል።
እርግጥ ነው የተጀማመሩ ውጤቶች፣ ሙከራና ጥረቶች፣ ዲስኩሮችና በሼልፍ ላይ አቧራ የሚጠጡ የማስትሬትና የፒ.ኤች.ዲ የጥናትና የምርምር ጥናቶች እንደተትረፈረፉ መካድ አያዋጣም። ተገቢ የምርምር ፈንድ፣ በርቱ ባይ የመንግሥት ቢሮክራሲና ሹመኞች፣ አበረታች ፖሊሲዎች እንደሌሉንም ፀሐይ የሞቀው ምስክር ነው። የምክንያቶቻችን አበዛዝና የችግራችን ተራሮች ቁመት የገዘፈ መሆኑ ባይካድም የችግሮቻችንን ተራሮች ሙሉ ለሙሉ ደልዳላ ሜዳ ማድረጉ ቢሳነንም እንኳ ምሁራኖቻችን የመሹለኪያ ዋሻ እየፈጠሩልን ወደ ስልጣኔ ብርሃን እንድንወጣ በሙሉ ኃይላቸው ተረባርበው አልረዱንም። እውቀቱ ጠፍቷቸው ሳይሆን የትኩረታቸው ቀስት “ሀ ራስህን አድን!” ለሚለው መሰል ወታደራዊ መርህ ቅድሚያ በመስጠታቸው ይመስላል። መዳፈር ካልሆነብኝ በስተቀር ብዙዎቹን የሀገሬን ምሁራን የማስተያየው “ከፀጋ ስዕል” ጋር እያቆራኘሁ ነው፤ ወይንም ለርዕሴ እንደሰጠሁት ብሂል “ታቦተ ክፉ፤ አፀደ መልካም።” ሥምና ተግባር ለየቅል እንዲሉ።
ትዝታ ሁለት- ሦስት ዐሠርት ዓመታት ወደኋላ፤
እኔና ዘመነኞቼ የቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የትምህርት ገበታ ከዘረጉልን በርካታ የወቅቱ ምሁራን የገበየናቸው እጅግ በርካታ እውቀቶች እንዳሉ ሳልጠቅስ አላልፍም። በመልካም እውቀት ለቀረፁን መምህራኖቻችን ክብረት ይስጥልን። ረጂም ዕድሜ ያዋርስልን። በአንጻሩም “የሚያድግ ልጅ አይጥላህ” እንዲሉ በዚያ ዘመን ትውልድ ላይ ክፉ መርዝ ነዝተው ምሁርነትን ልክ እንደዛሬው የጠቅላዩ ንግግር እንድንኮንን የዳረጉን በርካቶች “የተማሩ ልሂቃን” እንዳጋጠሙን ሳላስታውስ አላልፍም። አንዱን ብቻ ለአብነት ላስታውስ። እንዘርዝር ብንል ብዙ ሰው ያነካካል። እኒህን “ምሁር” የመረጥኩት ዛሬም በዘመነ እርጅናቸው እኔና ዘመነ አቻዎቼ “ምን ነካቸው!” እየተባባልን መገረማችን ስላልቀረ ነው።
የትናንትናውና የዛሬው ስዕላቸው በተቃርኖ ቀለማት የደመቀው እኚህ ምሁር የፍልስፍና ትምህርት ሊቅ ናቸው፤ ዛሬም። በእኛም ግዜ እንደዚያው። ገና የዩኒቨርሲቲውን ግቢ ሳንላመድ በፊት በመጀመሪያው ዓመት፣ በመጀመሪያው ክፍለ ጊዜ ማን የእርሳቸውን ዲፓርትሜንት እንደሚቀላቀል እንኳ በቅጡ ሳያውቁ ራሳቸውን ያስተዋወቁን እንዲህ በማለት ነበር። “በፍልስፍና ትምህርት እንዳስመርቃችሁ የምትጓጉ ተማሪዎች አንድ ነገር ልብ ብላችሁ እወቁ።
ዲግሪ ከመቀበላችሁ አስቀድሞ አማኑኤል ሆስፒታል ታክማችሁ መውጣታችሁን አረጋግጡ። (አስመርቃችኋለሁ ሳይሆን አሳብዳችኋለሁ ማለታቸው ነበር።) የማርክ አሰጣጤን ልምድን በተመለከተም A – የሚገባው ለማርክስ ነው። B – ለእኔ ለፕሮፌሰሩ፣ C – እጅግ ጎበዝ ለሆኑ ጂኒዬስ ተማሪዎች፣ D – ለጎበዝ ተማሪዎች፣ F – ለብዙኃን ተማሪዎች። ምሁሩ ፎክረው ብቻ አልቀሩም እንዳሉትም በየአመቱ ካስመረቋቸው ሁለትና ሦስት የፍልስፍና ተማሪዎች መካከል አንዳንዶች የተመረቁት በአማኑኤል ሆስፒታል ህክምና እየተረዱ ነበር። ለምስክርነቱ እውነትነት ዛሬም ቢሆን አለሁ ባይ ምስክር የሚጠፋ አይመስለኝም።
የቀድሞ መምህራችንን በሰፈርንበት አንድ መስፈሪያ ምሁራንን ሁሉ አንመዝንበትም። አዝመራው በዘረዘረ ማሣ ውስጥ እንክርዳድ እንደማይጠፋ ሁሉ ምሳሌውም እንደዚያ እንዲታይ እፈልጋለሁ። ሃሳቤን ልሸምልል። ድንቅዬው የሀገራችን ደራሲና ፀሐፌ ተውኔት አብዬ መንግሥቱ ለማ “ባሻ አሸብር ባሜሪካ” በሚለው የግጥም መድብላቸው ውስጥ “መርፌ ትሠራለህ” ብለው የዘመናቸውን ተማርን ባይ እንደሞገቱት ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይም ሆኑ እኛ ተራ ዜጎች ደጋግመው ጥቁር ጋዋን የደረቡ ምሁራኖቻችንን በሙሉ አንድ ሙቀጫ ውስጥ ከተን አንደልዛቸውም። አንዳንዶቹን “መርፌ ትሠራለህ” ብለን በአደባባይ ብንሞግታቸው ግን ክፋት ያለው አይመስለኝም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም በሚሊኒዬም አዳራሽ ንግግራቸው ሊያስተላልፉ የፈለጉት ይህንንው የአብዬ መንግሥቱ ለማን ዓይነት መልእክት ይመስለኛል። ወይንም በዚህ ጽሑፍ እንደተሰጠው ርዕስ “አፀዱ ብቻ ሳይሆን ዋናው ታቦትም መልካም ይሁን!” እንደማለት። “ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው!” እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ “ውጤት የማያስገኝ ምሁርነትም እንዲሁ የሞተ ነው!” ብንልስ አያስኬድ ይሆን። ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2012
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com