ምርጫ የአንድ ሀገርን መጻኢ ዕድል ከሚወስኑት ጉዳዮች አንዱና ግንባር ቀደሙ ነው።ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ያካሄዱ ሀገሮች በልማትም ሆነ በመልካም አስተዳደር ብሩህ ተስፋ እንደሚጠብቃቸው ይታመናል። በአንጻሩ ተአማኒነት የጎደለውና ከዴሞክራሲያዊ ሂደት ያፈነገጠ ምርጫ ያካሄዱ ሀገራት ሰላም የራቃቸውና በልማትም ወደ ኋላ የቀሩ እንደሚሆኑ የበርካታ የአፍሪካና ታዳጊ ሀገራት ተሞክሮ ያሳያል።
ለአንድ ምርጫ ስኬታማነት መንግስትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር የሲቪክ ማህበራት ሚና መተኪያ የማይገኝለት ነው።የሲቪክ ማህበራት ያልተሳተፉበት ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ቢሆንም እንኳን ሙሉነት አይኖረውም።ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ባደረገቻቸው አምስት ሀገር አቀፍ ምርጫዎች ለሲቪክ ማህበራቱ የተሰጠው ትኩረት አናሳ ከመሆኑም ባሻገር ከሂደቱ እንዲወጡ የተለያዩ ጫናዎች ሲደረጉባቸው ተስተውሏል።
ይህም በምርጫው ተአማኒነት ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖች እንዲፈጠሩ አድርጓል።ስለሆነም በዘንድሮው ምርጫ ይህንን የሚያርም ስራ መስራት ይገባል። በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ በተሻለ ዴሞክራሲያዊነትን ተላብሷል በሚባለው በ1997ቱ ሀገር አቀፍ ምርጫ እንኳን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ምርጫውን እንዲታዘቡ ሲጋበዙ ሀገር በቀል የሆኑት የሲቪክ ማህበራት በበርካታ ክርክርና በፍርድ ቤት ውሳኔ ምርጫውን እንዲታዘቡ ተደርጓል።
ይህ ሁኔታ ደግሞ ከጅምሩ ስለምርጫው ተአማኒነት ጥያቄ እንዲነሳበት አድርጓል።ከምርጫ 97 በኋላም መንግስት የሲቪክ ማህበራትን እንደ ጠላት በመቁጠርም ማህበራቱን እጅ ከወርች ቀፍድዶ የሚይዝ አዋጅ አወጣ። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ አዋጅ ቁጥር 621/2001 በሚል የወጣው አዋጅም የሲቪክ ማህበራት ህልውና አደጋ ውስጥ እንዲገባ አድርጓል።
በብዙዎቹም ላይ የሞራል ውድቀት አሳድሯል። ብዙ ነገርም ገድቧል። በአገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል። መንግስት ፊት በመንሳቱና እንቅስቃሴያቸውን በአዋጅ በመገደቡ ብዙዎቹ ዓለም አቀፍ ደጋፊዎች ለሲቪክ ማህበራቱ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያቆሙ አስገድዷቸዋል። በተለይም በሰብአዊ መብት ዙሪያ፣በሰላምና በማህበረሰብ ልማት ግንባታ፣ከዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ ከምርጫና ከመሳሰሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ይሰሩ የነበሩ ድርጅቶች በሙሉ ስራቸውን እንዲያቆሙ ተገደዋል።
ከ1997 በኋላ የተካሄዱ ሁለት ምርጫዎችም ያለ ጠንካራ ሲቪክ ማህበራት ተሳትፎ የተካሄዱና አሸናፊውም መንግስት፤ታዛቢውም መንግስት የሆኑባቸው ምርጫዎች ሆነው አልፈዋል። ከለውጡ ወዲህ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ አዋጅ ቁጥር 621/2001 እንዲሻሻል ተደርጓል። አዲሱ አዋጅም በሲቪክ ማህበራት ላይ ተጥሎ የነበረውን ገደብ ያነሳና ለማህበራቱም ሰፊ ነጻነት የሚሰጥ ነው።በተለይም ዘንድሮ ለሚካሄደው ስድሰተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሲቪክ ማህበራት ሀገራዊና ሙያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ በር የሚከፍት ነው።
የሲቪክ ማህበራቱ ለመራጩ ማህበረሰብ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ከመስጠት ባሻገር ከቅድመ ምርጫ እስከ ውጤት ድረስ ያሉትን ሂደቶች በመታዘብና ህጸጾች በወቅቱ እንዲታረሙ በማድረግ ረገድ የሚጫወቱት ሚና በማንም ሊተካ የሚችል አይደለም። ስለሆነም መንግስትም ሆነ በምርጫው ውስጥ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሲቪክ ማህበራት የማይተካ ሚና እንዳላቸው በማመን አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ ሊያደርጉላቸው ይገባል።
የሲቪክ ማህበራትም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሰረታዊ የሆነውን የዘንድሮ ምርጫ ሰላማዊ፤ ዴሞከራሲያዊና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የማይተካ ሚናቸውን መወጣት አለባቸው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 ቀን 2012 ዓ.ም