የሆስፒታሉ መግቢያ በር ላይ የእጅ ጓንት እና የፊት መሸፈኛ (ማስክ) ያደረጉ ጥበቃዎች መደበኛ ፍተሻቸውን ያደርጋሉ፡፡ ከእነዚህ ጥበቃዎች በኋላ አሁንም ሌሎች ጥበቃዎች አሉ፡፡ እነዚህ ደግሞ በግቢው ውስጥ ወደተዘጋጀው መታጠቢያ ቦታ የሚጠቁሙ ናቸው፡ ፡መታጠቢያዎቹ ከበቂ ሳሙና እና ሳኒታይዘር ጋር ተዘጋጅተዋል፡፡
ማንም ባለጉዳይ እጁን ሳይታጠብ ማለፍ አይችልም፡፡ ለዚህም ያመች ዘንድ ከዚህ በፊት አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ በሮች ተዘግተው በአንድ አቅጣጫ ብቻ ነው መግባት የሚቻለው፡፡ ማንም ሰው ሳይታጠብ እንዳያልፍ የሚቆጣጠሩ ሰዎች አሉ፡፡ አሁንም ሌላ ቁጥጥር አለ፡፡ እዚህ ጋ ደግሞ እጃቸውን ታጥበው ያለፉ ሰዎች የሙቀት መጠናቸውን የሚለኩበት ነው፡፡ ለዚህ የተዘጋጁ ባለሙያዎች በተዘጋጀው መግቢያ በር ላይ ቆመዋል፡፡ ግንባር ላይ በሚደረገው የመሳሪያ ምርመራ ‹‹ስክሪን›› ተደርገው ይገባሉ፡፡
ከገቡ በኋላ በየቅርብ ርቀቱ ሳኒታይዘር ይታያል፡፡ ግንዛቤ የሚሰጡ ባለሙያዎችም አሉ፡፡ ሃሌሉያ ጠቅላላ ሆስፒታል ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የነፃ ምርመራ አገልግሎት ጀምሯል፡፡ ከግል ሆስፒታሎች በነፃ አገልግሎት በመስጠት ምናልባትም የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም፡፡ የሃሌሉያ አጠቃላይ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ቃልአብ ደረጃ እንደገለጹት፤ የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ የሃሌሉያ አጠቃላይ ሆስፒታል ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት 11 አባላት ያሉት ኮሚቴ አዋቅሯል፡፡ ለዚህም 400 ባለሙያዎችን አሰልጥኗል፡፡
ለሙቀት ልየታ የሚያገለግሉ መሳሪያዎችን ገዝቷል፡፡ ሆስፒታሉ ይህን ማድረጉ ‹‹ማህበራዊ ግዴታ ነው›› ይላሉ ዶክተር ቃልአብ፡፡ በኢትዮጵያ መከሰቱ ከታወጀበት ዕለት ጀምሮ የሙቀት ልየታ ምርመራ የማድረግ ሥራ ጀምሯል፡፡ ይህ መደረጉ የቫይረሱን ሥርጭት ይቀንሰዋል፡ ፡ ለ400 ባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠት ወደ ሆስፒታሉ ለሚመጡ ደንበኞች የሙቀት ልየታ ምርመራና የገለጻ ትምህርት እየተሰጠ ነው፡፡ ወደ ግቢው የሚያስገቡ በሮች ተዘግተው አንደኛው ብቻ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ በግቢው ውስጥ ድንኳን ተዘጋጅቶ ምርመራ እየተደረገ ነው፡፡ ለዚህም ስድስት ስፔሻሊስት ነርሶች ሥልጠና ወስደው አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ እንደ ዶክተር ቃልአብ ገለጻ፤ የሃሌሉያ ሆስፒታል ለማንኛውም ሰው ነፃ የምርመራ አግልግሎት ለመስጠት ወስኗል፡፡
የሚሰጠው የምርመራ አገልግሎት የሙቀትና የትኩሳት ልየታ ነው፡፡ ትኩሳት ያለበት ሁሉ የኮሮና ቫይረስ ያለበት ላይሆን ስለሚችል ሌሎች ምርመራዎችን እንዲያደርግ በለይቶ ማቆያ ክፍል ውስጥ ይቆያል፡ ፡ ለዚህም ቦታ ያዘጋጀ ሲሆን በቀጣይም አራት ኪሎ ያለውን የሆስፒታሉን ቅርንጫፍ ሙሉ በሙሉ ለዚህ አገልግሎት እንዲውል ተወስኗል፡፡ ሆስፒታሉ በራሱ የለይቶ ማቆያ ክፍል ውስጥ ሲያቆይ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ከራሱ ከሆስፒታሉ በመሸፈን ነው፡፡
ሌሎች አስፈላጊ ምርመራዎች ሲኖሩም ከመንግስት ጋር ይሰራል፡፡ የሃሌሉያ ሆስፒታል ባለቤትና የሳንባ ስፔሻሊስት ፕሮፌሰር ጌታቸው አደራዬ በሰጡት ማብራሪያ፤ የኮሮና ቫይረስ የመተንፈሻ አካላትን የሚጎዳ በሽታ ነው፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት ከተከሰቱ የቫይረስ ወረርሽኞች ሁሉ የከፋ ሆኗል፡፡ ከዚህ በፊት ከነበሩት የሚለየው የወረርሽኝ ፍጥነቱ ነው፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ጌታቸው ገለጻ፤ የኮሮና ቫይረስ አስከፊነት በፍጥነት መስፋፋቱ ብቻ ሳይሆን የትኛውን የህብረተሰብ ክፍል እንደሚያጠቃና በምን ምክንያት እንደሆነ በግልጽ ተለይቶ አለመታወቁ ነው፡፡
እንደ ኤች አይ ቪ ኤድስ ያሉት በወሲባዊ ግንኙነትና በደም ንኪኪ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ግን በእጅ ንኪኪ፣ በትንፋሽ፣ ከማስነጠስ በሚወጡ ነጠብጣቦች ይተላለፋል፡፡ የት ጋ ማስቆም እንደሚቻል ለጊዜው አስቸጋሪ ነው፡፡ የኮሮና ቫይረስ ገዳይነት በመቶኛ ሲሰላ ትንሽ ቢመስልም ከሌሎች ወረርሽኞች ሲነፃፀር ቀላል እንዳልሆነ ነው ፕሮፌሰር ጌታቸው የሚናገሩት፡፡ በኮሮና ቫይረስ የሞተው ከአራት ወይም አምስት በመቶ አይበልጥም፤ ዳሩ ግን ከመቶ ሰው አራት በመቶ እና ከአሥር ሺህ ሰው አራት በመቶ ትልቅ ልዩነት አለው፡፡
‹‹የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት ኢትዮጵያ ውስጥ እየተደረገ ያለው ርብርብ አስደሳች ነው›› ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ አገሪቱ ውስጥ ከገባ 10 ቀን እንኳን ሳይሞላው በብዙ ቦታዎች ላይ ግንዛቤ እየተሰጠ እንደሆነ ታይቷል፡፡ ይህ ርብርብር መቀጠልና መጠናከር አለበት፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በልማድ መድሃኒት ይሆናሉ በተባሉ ነገሮች ላይም ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡ መድሃኒት ናቸው ተብሎ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የተደረገባቸው ነገሮች መድሃኒትነታቸው የተረጋገጠ አይደለም፡፡ ኤች አይ ቪ ኤድስ የመጣ ጊዜ አረቄ መወደድ ብቻ ሳይሆን በከተማዋ ውስጥ ጠፍቶ ነበር፡፡ አሁንም ያ ነው እየሆነ ያለው፡፡ የተረጋገጠ መድሃኒት የለም፤በሳይንስ የተረጋገጡት የመከላከያ መንገዶች ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 ቀን 2012 ዓ.ም
ዋለልኝ አየለ