
አዲስ አበባ፡- የከተማዋን የትራንስፖር ችግር ለመፍታት በተያዘው በጀት ዓመት አንድ ሺ የሚሆኑ የግል ታክሲዎችን ለማስገባት መታቀዱን የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ባለሥልጣን አስታወቀ። በመንግሥት ሦስት ሺ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብሶችን ለማስገባት እየተሠራ መሆኑንም ገለፀ።
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ማዕረ መኮንን በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ ታክሲዎቹን ለማስገባት የታቀደው በግለሰቦች ሲሆን፣ ታክሲዎቹም አራት እና ሰባት ሰዎች የሚጭኑ ላዳዎች ናቸው። ይህም የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍና ለበርካታ ዓመታት ባገለገሉ ታክሲዎች ሲሰጥ የቆየውን የትራንስፓርት አገልግሎት ለማዘመን ያስችላል።
ከታክሲዎቹ 80 በመቶው አራት ሰዎች የሚጭኑ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የተቀሩት ደግሞ ሰባት ሰው የሚጭኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ታክሲዎቹን ለማስገባት የሚያስችለውን ብድር ለማግኘትም ለንግድ ባንክ ፕሮፖዛል መላኩን አመልክተዋል። በአንድ ተሽከርካሪ ታክስን ጨምሮ ወደ 800ሺህ ብር ብድር ግምት መያዙን አብራርተው፣ ከላዳ ኩባንያ ጋር ድርድር መጀመሩንም ተናግረዋል። ታክሲዎቹን ለመግዛት ገዥዎቹ እንደ ቤቶች ልማት የባንክ ሂሳብ ከፍተው እንዲቆጥቡ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
ምክትል ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት፤ አስተዳደሩ ከ10ሺ300 በላይ የሚሆኑ ተሽከርካሪዎችን ለማስመጣት አቅዶ የነበረ ሲሆን፣ ለእዚህም ወደ 184 ማኅበራት ተደራጅት ተመዝግበዋል። በየክፍለ ከተማው ማኅበራቱን የሚወክሉ ሁለት ሁለት ሰዎች እንዲመርጡ ተደርጎ ከሃያ ተወካዮች ጋር ውይይት እየተደረገ ነው።
ወደ 850 አዳዲስ አውቶቢሶች በአንበሳ አውቶብስ ድርጅት በኩል አስገብተናል ያሉት አቶ ማዕረ፣ መንግሥት 3ሺ አውቶቢሶችን ለመግዛት ቴክኒካዊ ውይይት እያካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል። የህዝብ ማመላለሽ አውቶብሶች ብቻ የሚሄዱበትን ኮሪደር በመንገድ ላይ ለመሥራት ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር እየተንቀሳቀስን ነው ሲሉም አቶ ማዕረ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ