በኢትዮጵያ ግብርና ላይ ልዩነት የሚያመጡ ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን ለአርሶ አደሮች ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት በቅርቡ ተፈርሟል። ስምምነቱ ኢትዮ ሊዝ በተሰኘ የውጭ ኩባንያ፣ በግብርና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ መካከል የተፈረመ ሲሆን፣ መርሀ ግብሩ ለሶስት አመታት የሚዘልቅ ይሆናል።
በስምምነቱ መሰረት መንግስት የውጭ ድርጅቶች በፋይናንስ ሊዝ መሳተፍ እንዲችሉ በፈቀደው መሰረት ኢትዮ ሊዝ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ የኢትዮጵያን ግብርና ለማሻሻል በ150 ሚሊዮን ዶላር ለአርሶ አደሩ የእርሻ ትራክተሮችን፣ጀነሬተሮችን ፣ኮምባይነሮችን ፣ወዘተ በኪራይ /በፋይናንስ ሊዚንግ/ያቀርባል።
አርሶ አደሩ መሳሪያዎቹን ለማግኘት ቤቱን ወይም መሬቱን ማስያዝ አይጠበቅበትም።ከእሱ የሚጠበቀው መሳሪያውን በደንብ በመያዝ ምርቱን ማሳደግና እዳውን ቀስ በቀስ መክፈል ብቻ ይሆናል።አርሶ አደሮች ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎቹን እንዲያገኙ የሚደረገው ከህብረት ስራ ማህበራት ፣ከግል ድርጅቶችና ከተደራጁ ወጣቶች ጋር በሚደረግ ግንኙነት ይሆናል።
በተመሳሳይ መረጃ የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ አስር ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎች አገልግሎት መስጫ /ሜካናይዜሽን/ማእከላት በተለያዩ ክልሎች እንደሚገነቡ አስታውቋል።እነዚህ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነቡት ማእከላት ከመሬት ዝግጅት አንስቶ እስከ ምርት መሰብሰብ ድረስ የአርሶ አደሩ ዘመናዊ የግብርና ማሽነሪዎች አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችሉ የጥገና፣ የቢሮ ፣የስልጠና የመሳሰሉት አገልግሎት የሚሰጡባቸው ናቸው።
ስምምነቱ እና የማእከላቱ መከፈት መንግስት የዳቦ ስንዴ ፍላጎትን ለማሟላት የያዘውን ቁርጠኝነት በቆላማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ስንዴ ማልማት ውስጥ በመግባት ግብርናውን ለማዘመን የጀመረው ተግባር ይበልጥ መሬት መያዝ መጀመሩን ያመለክታል።
ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችን ለአርሶ አደሮች በሊዝ ኪራይ ለማቅረብ እንዲሁም የእርሻ መሳሪያዎቹን ለመጠገንና የመሳሰለውን ተግባር ለማከናወን እንዲያስችል የእርሻ መሳሪያዎች አገልግሎት መስጫ ማእከላትን ለማቋቋም የተጀመረው እንቅስቃሴ መንግስት ግብርናውን ለማዘመን ያረጋገጠው ቁርጠኝነት ሌላ ማሳያ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ።
ኢትዮጵያ በተለይ ለአነስተኛ አርሶ አደሮች የፋይናንስ አቅርቦት የማይደረግባትሀገር መሆኗ ይገለጻል።ግብርናውን ለማዘመን አንዱ ማነቆ ሆኖ የቆየውም የፋይናንስ አቅርቦት አለመኖር መሆኑ ይታወቃል።ግብርናውን የማዘመኑ ስራ በፋይናንስ አቅርቦት ችግር የተነሳ ብዙም ርቅት ላይሄድ ይችላል የሚል ስጋት ያደረበት ሁኔታም ነበር።
በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩን የዘመናዊ የግበርና መሳሪያ ባለቤት የሚያደርግ ተግባር መፈጸሙ የግብርናውን ምርትና ምርታማነት ወሳኝ በሆነ መልኩ የመቀየሪያው ጊዜ ብዙም ሩቅ እንደማይሆን ይጠቁማል።
የግብርና ዘርፍ በዘመናዊ የግብርና መሳሪያ ተደግፎ ሰራ ማለት ምርትና ምርታማነት ያድጋል ማለት ብቻ አይደለም ፤ሀገሪቱ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ለጀመረችው ተግባርም ግብአት በበቂ መልኩ ለማቅረብ እድል ይፈጥራል።ለአርሶ አደሩ ምርት ጥሩ ገበያ የሚፈጠር በመሆኑም ሕይወቱ ይቀየራል ማለት ነው ። ሸማቹም እንዲሁ በምርት አቅርቦት ማነስ ሳቢያ ይደርስ የነረበው የእህል ዋጋ መናር እንዲረግብ ሊያደርግ ይችላል።
በመሆኑም ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎቹ ለአርሶ አደሩ መቅረባቸውን አንደ ትልቅ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል።ግብርናውን የማዘመኑ ጥረት ገና በጀምር ላይ መሆኑም ሊታወቅ ይገባል።የግብርና መሳሪያዎቹን ለማቅረብ የተደረሰበት ሂደት ሌሎች ተመሳሳይ አቅራቢዎች እንዲመጡም በር ይከፍታል።
ይህ የመንግስት ቁርጠኝነት አሁን ይበልጥ መሬት አንዲነካ በተለይ ከአርሶ አደሩ፣ከህብረት ስራ ማህበራቱ እና ከዩኒየኖቻቸው ብዙ ስራ ይጠበቃል።አርሶ አደሩ የመሳሪያ ኪራዩን ለመክፈል ቁጠባን በሚገባ ባህሉ ማድረግ ይኖርበታል።አርሶ አደሩ በአነስተኛ ቁጠባና ብድር የህብረት ስራ ማህበራቱ አማካይነት የሚቆጥብበት ሁኔታ እንዳለ ይታወቃል።ይህ ከእስከ አሁኑ በበለጠ መጠናከር ይኖርበታል።ከአፉ ከፍሎ በመቆጠብ የመሳሪያውን ኪራይ ዋጋ በወቅቱና በአግባቡ ለመክፈል መዘጋጀት ይጠበቅበታል።
ማህበራቱ አርሶ አደሩ ቆጣቢ እንዲሆን እየሰሩ መሆናቸው ይታወቃል።የቁጠባ ፋይዳ ይበልጥ የሚታወቀው በዚህ የሊዝ ኪራይ ክፍያ ወቅት መሆኑን በመገንዘብ የአርሶ አደሩ የቁጠባ ባህል እንዲያደግ በትኩረት መስራት አለባቸው።
እንደሚታወቀው ፤ከኢትዮጵያ ህዝብ 85 በመቶው አርሶ አደር ነው።የዚህን አርሶ አደር ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያ ፍላጎት ለመመለስ ሌሎች የግሉ ዘርፎች እና የፋይናንስ ተቋማት ጭምር ይህን ጥረት መቀላቀል ይኖርባቸዋል። በተለይ ባንኮች ለአርሶ አደሮች ብድር የሚያቀርቡበትን መንገድ መፈለግ ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 30/2012