
በሀገሪቱ ደቡብዊ ክፍል ከአዲስ አበባ በ85 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ከዋናው አስፓልት መንገድ ወደ ውስጥ አምስት መቶ ሜትር ገባ ብሎ ይህ ታሪክ ተቀምጧል። በ12ሺ ሄክታር መሬት ላይ የታጠረው ግቢ ምንነቱ ጠይቀው ካልተረዱ ለማወቅ የሚቸግር፤ ተመርተው ካልቀረቡት የሚነግር አንዳችም ማመላከቻ የሌለው ፀጥታ የዋጠው ነው። በውል ባልታነፀው አጥር ወደ ተከለለው ግቢ ሲገባ ተረስቶ የከረመ፤ ዘመናት ያለ ሰዎች የተሻገረ ይመስል ለአይን ማረፊያ የሚሆን ውል ያለው ነገር ማግኘት ያዳግታል፤ ግቢው ሰው ናፍቆታል።ፀጥ ረጭ ብሏል።
ሰፋ ተደርጎ የታጠረው ግቢ ስለምንነቱ የሚነግር ልሳን ተነፍጎታል። በወጉ ያልተደለደለው መንገድ ታልፎ ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ሌላ ከበፊቱ አንሶ የተከለለ ግቢ ይታያል። መግቢያ የተበጀለት አጥር በር ላይ “እንኳን ደህና መጡ” የሚል ፅሁፍ በእጅ ተፅፎበታል። ወደ ውስጥ ሲገባ ከመጀመሪያው ግቢ በተለየ መልኩ በተወሰነ ርቀት ዙሪያቸው ክብ ክብ ተደርገው በአጥር የተከለሉ ዘመናትን ተሻግረው የተፈጠሩበት ወቅትና ሁኔታን የሚመሰክሩ ትክል ድንጋዮች ይታያሉ።
ይህ ለኢትዮጵያ ድንቅ ለአለም ትልቅ ሀብት የሆነው በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበው የጥያየመካነ መቃብር ትክል ድንጋይ መገኛ ስፍራ ነው። ይህ ዘመናትን የተሻገረ የታሪክ አሻራ መገኛ የሰው ልጆች ቀደምት ስልጣኔና ባህል ማሳያና መግለጫ የሆነውና ስጋት ያጠላበት የጥያ ትክሎ ድንጋይ ማሳያ ስፍራ ነው።
ሀገሪቱ ካሏት በአለም ቅርስነት ከተመዘገቡ ውስን ውድና ድንቅ ቅርሶች መካከል አንዱ የሆነውና ቁጥራቸው 40 የሚደርሱት የጥያ ትክል ድንጋዮች በእንክብካቤና ጥበቃ ጉድለት ስጋት ላይ ወድቋል። በትክል ድንጋዮቹ ላይ የተቀረፁ ምልክቶች ደብዝዘው፤ በፀሀይና ዝናብ ቀድሞ የነበራቸው ይዘትና ቅርፅ አጥተው፤ አንዳንዶቹምተሰባብረው ወዳድቀው የተቀሩት ከተፈጥሮ ጋር በትግል አሻራቸውን ሳይለቁ ቆመው ይታያሉ።
አቶ ሽመልስ ተስፋዬ የመስህብ ጥናት ባለሙያና በጉራጌ ዞን የሶዶ ወረዳ ባህል ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ተወካይ ኃላፊ ናቸው። ‹‹ቅርሱ በአግባቡ ተጠብቆና ወደነበረበት መመለስ ካልተቻለ ከአለም አቀፍ ቅርስነት የመሰረዝ እድል ሊገጥመው ይችላል›› በማለት ስጋታቸውን ይናገራሉ። በ1972 ዓ.ም የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የአለም ቅርስ ተብሎ ከተመዘገበበት ጊዜ ጀምሮ ምንም አይነት ጥገናና እድሳት ያልተደረገለት መሆኑንም ይገልፃሉ ።
አሁን ላይ ትክል ድንጋዮቹ በዓለም አቀፍ ቅርስነት እንዲመዘገብ ያስቻላቸው የተለያዩ ምልክቶችና ቅርፆች በመጥፋት ላይ ይገኛሉ። ለዚህ የዳረገው ደግሞ ለረጅም ጊዜያት ጥበቃና እድሳት ሳይደረግለት መቆየቱ እንደሆነ ያስረዳሉ። እንደ ኃላፊው አባባል፤ አለምዓቀፍ ቅርሱ በአሁኑ ሰዓት አደጋ እየደረሰበት ይገኛል።
የጥያ ትክል ድንጋይ የጠቀሜታው ያህል ትኩረት ተነፍጎት ተገቢውን ጥበቃ እንዳልተደረገለት የሚገልፁት ኃላፊው፤ ፅህፈት ቤታቸው ስጋት ገብቶት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የጥገናና አካባቢውን የማስዋብ ስራዎችን መጀመሩን ያስረዳሉ። በዚህ የሶዶ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ቅርሱ ከሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመነጋገር ጥገና ለማድረግና አካባቢውን ለማስዋብ በቅርቡ ስራ መጀመሩን ይጠቁማሉ።
አቶ ሽመልስ እንደሚናገሩት፤ በቅርሱ መገኛ ስፍራ ላይ ምንም አይነት መሰረተ ልማት እንዳልተሟላና ጎብኝዎች ሊያስተናግድ የሚችል ምንም አይነት አገልግሎት ሰጪ ተቋም እንደሌለ ያስረዳሉ። ቅርሱን ለመጎብኘት ለሚመጡ ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታ እስካሁን ያልተፈጠረ መሆኑንም ይጠቅሳሉ። ጎብኚዎች በአካባቢው ምቹ የሆነ ሁኔታ ስለማይገጥማቸው በመስተንግዶው ቅሬታን እያቀረቡ መሆኑንም ይገልፃሉ።
በጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ በበኩላቸው፤ ለቅርሱ ከዚህ በፊት የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ ለጉዳት እንደዳረገውና የተፈለገው ያህል ጥቅም እንዳይሰጥእንዳደረገው ይገልፃሉ። ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት አለም አቀፍ ቅርሱ ያለበት ሁኔታ ጥናት ተደርጎ በመለየት የማደስና አካባቢውን የማስዋብ እንቅስቃሴ መጀመሩን ያስረዳሉ።
ቅርሱ ወደነበረበት ለመመለስ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመሆን እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ኃላፊዋ፤ በሌላ በኩል በአካባቢው ላይ የሚታየው የመሰረተ ልማት ችግር ለቱሪዝም እድገቱና ለጎብኝዎች ቁጥር መቀነስ ዋንኛ ችግር መሆኑን ገልፀዋል። በመሆኑም ችግሩ ተለይቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመስራት እቅድ መያዙን ያስረዳሉ።
ወይዘሮ መሰረት ቅርሱ እስካሁን ድረስ ተገቢው የሆነ ጥበቃና እድሳት ሳይደረግለት ለረጅም ጊዜ መቆየቱ የአካበቢው ማህበረሰብ ቅሬታ ፈጥሮ እንደነበር አመልክተው፤ አሁን በተጀመረው ጥገናና እድሳት ወደነበረበት እንደሚመለስና መፍትሄ እንደሚያገኝ ይጠቁማሉ።
የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ዳሬክተር ወይዘሮ ነዳች ጀማል፤ የጥያ ትክል ድንጋይ ጉዳት የደረሰበት መሆኑን ጠቁመው ባለስልጣኑ ጉዳዩን በመረዳት ለቅርሱ ጥገና ለማድረግ የሚያስችል በጀት መድቦ ወደ ስራ የገባ መሆኑን ያስረዳሉ።
ለቅርሱ ጉዳት ምክንያት የሆነው በቅርሱ መገኛ አካባቢ ያለው አፈር አሲዳማ መሆንና ለረጅም ጊዜ ጥገና ሳይደረግ መቆየቱ እንደሆነ የገለፁት ዳይሬክተሯ፤ በአሁኑ ሰዓት ቅርሱ ያለበትን ሁኔታና ችግር በመለየት አፈሩ የመቀየርና ቅርሱን የመጠገን ስራ የሚከናወን መሆኑ ይገልፃሉ።
ባለስልጣኑ ለሀገራዊ አለምዓቀፍ ቅርሶች ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራ መሆኑንና የጥያ ትክል ድንጋይ ያለበት አካባቢ የማስተካከል፣ የማስዋብ ቅርሱ የመጠገን ስራ በሶስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ያስረዳሉ።
በዚህም ትክል ድንጋዩ የተጋረጠበትን አደጋ ለማስቆምና ወደነበረበት ለመመለስ ጥረት የሚደረግ መሆኑ ይናገራሉ። ከሀገር አልፈው አለም ዓቀፍ ቅርስ የሆኑት ቅርሶች የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ሁሉም ማህበረሰብ ጥበቃና እንክብካቤ ሊያደርግላቸው እንደሚገባም ያሳስባሉ።
አዲስ ዘመን የካቲት 30/2012
ተገኝ ብሩ