
አዲስ አበባ፡- በሰባት ወራት ጊዜ ውስጥ በብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ፤ በኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ 23 ሚሊዮን 289 ሺህ አምስት ነጥብ 38 ዶላር ዋጋ ያላቸው የተለያዩ ምርቶች ወደ ውጭ መላኩን የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
የኢንስቲትዩቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ፊጤ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ከሐምሌ 2011 እስከ ጥር 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ፤ በኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ 35 ሚሊዮን 229 ሺህ 270 ነጥብ 96 ዶላር ዋጋ ያለው ምርት ለመላክ እቅድ ተይዞ ነበር፡፡ በሰባት ወራት ጊዜ ውስጥ በብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግና በኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ 23 ሚሊዮን 289 ሺህ አምስት ነጥብ 38 ዶላር ዋጋ ያላቸው የተለያዩ ምርቶች ወደ ውጪ መላክ ተችሏል፡፡
በሰባት ወራት ውስጥ በብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ስምንት ሚሊዮን 991 ሺህ 453 ነጥብ 86 ዶላር ዋጋ ያለው ምርት ለመላክ ታቅዶ፤ ሁለት ሚሊዮን 411 ሺህ 467 ነጥብ 89 ዶላር የሚያወጣ ምርት የተላከ ሲሆን፤ በኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ ደግሞ 26 ሚሊዮን 237 ሺህ 817 ነጥብ 10 ዶላር ዋጋ የሚያወጣ ምርት ለመላክ ታቅዶ 20 ሚሊዮን 877 ሺህ 537 ነጥብ 50 ዶላር ዋጋ ምርት መላኩን አመልክተዋል፡፡
እንደ አቶ ፊጤ ገለፃ፤ በወጪ ንግዱ ተሳትፎ ያደረጉ ድርጅቶች በቁጥር 16 ሲሆኑ፤ የገበያ መዳረሻ አገሮች ደግሞ ከአፍሪካ እስከ አሜሪካና አውሮፓ፤ እንዲሁም ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ እስያ ያሉትን ያጠቃልላል፡፡ ይህ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶች ያሉበት ቢሆንም፤ በገበያ ተደራሽነት፣ ወደ ውጭ በሚላከው የምርት ዓይነትና መጠን፤ እንዲሁም በተሳታፊ የንዑስ ዘርፉ ኢንዱስትሪዎች ብዛት ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል የታየበት ውጤት ተመዝግቧል፡፡
በ2012 በጀት ዓመት የወጪ ንግዱን ለማሳለጥ የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ፤ የኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ ኢንዱስትሪዎችን አቅምና ፍላጎት መሠረት ያደረገ 60 ሚሊዮን 836 ሺህ 400 ዶላር ዋጋ ያለው ምርት ወደ ውጭ ለመላክ እቅድ መያዙ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 30/2012
መርድ ክፍሉ