የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባለፉት ዓመታት የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶችን ወደ አገር ውስጥ በመሳብ፣ ሀገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን በመግለጽ እና ለኢንቨስትመንትም ምቹ ሁኔታዎችና ማበረታቻዎች መኖራቸውን በመጥቀስ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸው የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ፈቃድ ወስደዋል። በተለያየ የስራ ዘርፍ ላይ መሰማራታቸውም ሲደመጥ ቆይቷል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት ብቻ ከ900 በላይ ለሚሆኑ የቱርክ፣የቻይና፣የአሜሪካና የጀርመን ትልልቅ ኩባያዎች በግብርና፣በማምረቻ ኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት ዘርፎች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ፈቃድ መስጠቱን የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል፡፡የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱት መካከል 500 ያህሉ በቅድመ ትግበራ ሂደት ላይ ሲሆኑ፤በትግበራ ላይ የሚገኙት 136 ናቸው፡፡አገልግሎት ወደመስጠት የተሸጋገሩትደግሞ 275 ብቻ ናቸው፡፡ይህ ቁጥር የሚያሳየው አብዛኞቹ ወደ ምርትና አገልግሎት መስጠት አለመግባታቸው ነው፡፡ስለሆነም ፈቃድ መስጠት ብቻ ሳይሆን ክትትልና ድጋፍ ሰጥቶ ተግባራዊ ስራ እንዲሰራ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
የውጭ ባለሀብቶች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ያሉትም በግል ወይም በሽርክና በኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሰማሩ በማድረግ የመስሪያ ቦታ ተሰጥቷል። ይሁን አንጂ ብዙዎቹ በታሰበው ልክ በኢንቨስትመንቱ ውጤት እንዳላመጡ ታይቷል። የባለሀብቶቹ ቁጥር ምከሪፖርት ባለፈስራቸውና ውጤቱ የታሰበውን ያክል ተጨባጭ ውጤት የተገኘበት አይደለም። ለቀጣይ ይህንን አርሞ መሄድ ተገቢ ይሆናል፡፡
በአዲስ አበባ እና በክልሎች ጭምር ወደ ስራ ያልገቡና ለረጅም ዓመታት መሬት አጥረው በተቀመጡ ባለሀብቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል። ለምሳሌ ያህል በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የ102 ባለሀብቶች ፈቃድ ተሰርዟል። የወሰዱት መሬትም ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ተደርጓል። በአዲስ አበባ አራዳ ጊዮርጊስ ፊት ለፊት ከ40 ፎቅ በላይ ለመገንባት በሚል የተወሰደው መሬት ከአስር ዓመታት በላይ ታጥሮ በመቀመጡ ዘንድሮ የከተማ አስተዳደሩ አጥሩ ፈርሶ መሬቱ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ አድርጓል። ይሄ ቦታ በወቅቱ ህንፃው ቢገነባ ኖሮ ምን ያህል ገቢ ለከተማው ያስገባ ነበር? ለምን ያህል ዜጎች የስራ ዕድል ይፈጥር ነበር? ከሁሉም በላይ ደግሞ ምንያህል የከተማው ውበትና ድምቀት ይሆን ነበር? ብለን ብናሰላው በወቅቱ ኢንቨስትመንቱ ባለመከናወኑ በአጠቃላይም እንደ ሀገር ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑን ተንታኝና ባለሙያ ሳያስፈልግ መመለስ ይቻላል። በተመሳሳይ መልኩም በተለያዩ ባለሀብቶች ሳይለሙ የቀሩት መሬቶች ሲታዩ በሀገር ላይ ያስከተለውን ኪሳራ መገመት አያዳግትም።
ባለሀብቶችን በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ጋብዞ ነገር ግን ከውጭ የሚመጡትንም የሚያስፈልጋቸው ድጋፍ እና ክትትል ከማድረግ፣የብድር አቅርቦት ከማመቻቸት፣ከመሰረተ ልማት ማሟላት በአጠቃላይ ምከቢሮክራሲው ጋር ተያይዞም ባለሀብቱን የሚያማርሩ ነገሮች አሉ። በተለይም የመጣውን ባለሀብት በየቢሮው በማመላለስና በማንገላታት ተስፋቆርጦ እንዲወጣ የሚያደርጉ አሰራሮችም ነበሩ፤አሁንም ሙሉ ለሙሉ አልተቀረፉም። እነዚህን አሰራሮች በትክክል ፈትሾ አሁንም ፈቃድ የወሰዱትን ባለሀብቶች ወደ መስመር ማስገባት ያስፈልጋል።
አሁን አገራችን በአዲስ የለውጥ ሂደትና በሁሉም መስክ የአሰራር ማሻሻያ በማድረግ ላይ ናት። ይህንንም ለውጥ በመተግበር ላይ ካሉ ተቋማት አንዱኢንቨስትመንት ኮሚሽን ነው። ኮሚሽኑ በተለያየ መልኩ ባለሀብቶች በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይ እንዲሳተፉ የተለያየ ጥረት ማድረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም ጉድለቶችን ፈትሾ ለኢንቨስትመንቱ ምቹ የሆኑ አሰራሮችን መፍጠር ቀዳሚው ስራው ማድረግ ይኖርበታል። አሁንም እንደ ከዚህ ቀደሙ ወደ ኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሀብቶችም ዝገባ በማድረግና ይሄንኑ ሪፖርት በማቅረብ ላይ መጠመድ ብቻም ሳይሆን በትክክል በሚታይ እና ለውጥ በሚያመጣ መልኩ ባለሀብቶቹ በመጡበትና ሊሰማሩ በሚፈልጉበት ዘርፍ ተሰማርተው ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላትጋርተናቦና ተደማምጦ በመስራት የሚተገበር ይሆናል።
በተለይ በዚህ ወቅት ሀገሪቱ የውጪ ምንዛሪ ፍላጎቷን ለማሟላት አንዱ መንገድ የውጪ ኢንቨስትመንትን መሳብ ነው። ባለሀብቶች እንዲመጡ ማድረግ ብቻም ሳይሆን ከመጡም በኋላ ለስራቸው ምቹ ሁኔታ በመፍጠር እንዲሰሩ፣ለስራአጥ ዜጎችም የስራ ዕድል እንዲፈጥሩና ግብር እንዲያስገቡ ማድረጉ ላይ በልዩ ትኩረት መስራት ያስፈልጋል። የሀገር ውስጥ ባለሀብቱንም በተለያዩ ማበረታቻዎች መደገፍና ማገዝ ስራዎችንም መከታተል ደግሞ ከእያንዳንዱ ጉዳዩ ከሚመለከተው አካል የሚጠበቅ ተግባር ነው። ይሄ ካልሆነ የሚታሰበው ዕድገትና የሚታለመው ልማት ሁሉ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ይሆናል።
ስለዚህ የውጭውንም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ወደ ስራው እንዲገቡና ውጤታማ ስራ እንዲያከናውኑ ስንፈልግ ከሪፖርት ባለፈ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ጭምር መሆን ይኖርበታል። በባለሀብቱ ላይ የሚታዩ ድክመቶችን በቅድሚያ በመመካከር በዚህ አልታረም ሲልም በፍጥነት የእርምት እርምጃ በመውሰድ ማስተካከል ለነገ ይደር ሊባል አይገባም። ይሄ ሌላውንም የሚያስተምር ይሆናል። በየስብሰባ አዳራሹ የሚቀርበውም ሪፖርት ከሪፖርት ባሻገር በተግባር መሬት የወረደውን ነገር የሚያሳይ መሆን አለበት። ያለዚያ ቁጥር ብቻ እያወሩ ውሃ የሚቋጥር ውጤት ይጠፋና ትዝብት ላይ ከመጣሉም በላይ በሀገር ላይ የሚያስከትለው ዳፋ የከፋ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ጥር 4/2011