መረዳዳት ለኢትዮጵያውያን የቆየ ባህል ነው። ቤተሰብን፣ ጎረቤትንና በአካባቢ የሚገኙትን አቅመ ደካሞች፣ ህጻናትና ሴቶችን መንከባከብና መደገፍ በየማህበረሰቡ ያለና እንደ ሞራላዊ ግዳጅ የሚወሰድ ተግባር ነው። እነዚህ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህሎች ደግሞ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ዜጎች ነገ አንዳች ነገር ብንሆን ሀገሬ ትደርስልኛለች፤ ወገኔ ከጎኔ አለ ብለው እንዲያስቡ ያደርጋል፡፡ ይህም ማህበራዊ ዋስትና እንዲኖራቸው ያስችላል። በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሀገር በቀልና ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የኢትዮጵያውያንን ቀደምት ባህል እነሱ በዘመናዊ መንገድ ተቋማዊ አድርገው እየተገበሩት ይገኛሉ። በተለያዩ ጊዜያትም በመንግስትና የሀይማኖት ተቋማት በኩል አቅም በፈቀደ መጠን አቅመ ደካሞችን፤ ህጻናትና ሴቶችን ለመደገፍ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል በመሀል አዲስ አበባ የሚገኘውና ከ90 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው «የዳግማዊ ምኒሊክ መታሰቢያ የእጓለማውታና የአረጋውያን መጦሪያ ቤት» አንዱ ተጠቃሽ ነው።
እማሆይ እቴነሽ ተሾመ ለ16 ዓመታት ያህል ያሳለፉት በዚሁ መጦሪያ ቤት ነው። ከ16 ዓመታት በፊት ኑሯአቸው ሀረር ከተማ ነበር፡፡ ዩኒቨርስቲ የሚማሩ ልጆችም አሏቸው፤ በአጋጠማቸው የጤና መቃወስ ምክንያት ነገሮች ሁሉ መስመር ሳቱብኝ። እናም «የዳግማዊ ምኒሊክ መታሰቢያ የእጓለማውታና የአረጋውያን መጦሪያ ቤት»ተቸግሬ መውደቂያ ሳጣ ያገኘሁት የችግር ቤቴ ነው ይላሉ። ከዓመታት በፊት የተሻለ እንክብካቤ ይደረግላቸው እንደነበር የሚያስታውሱት እማሆይ እቴነሽ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በየቀኑ ደረቅ እንጀራ ብቻ እንደሚሰጣቸው በመግለጽ ህዝበ ክርስቲያኑ ዝክር ሲያዘክርና ሙት ዓመት ሲኖር ይዘውላቸው ስለሚያመጡ ዘላቂነት ባይኖረውም ከመጦሪያ ቤቱ በተጨማሪ ያንን ተስፋ አድርገው እንደሚኖሩና እስካሁንም ጦም አድረው እንደማያውቁ ይናገራሉ።
በተመሳሳይ እማሆይ በላይነሽ ሀይሉ በመጦሪያው ከ20 ዓመት በላይ ኖረዋል፡፡ ተወልደው ያደጉት በትግራይ ክልል ተንቤን የሚባል አካባቢ ነው፡፡ ከቀን ወደ ቀን የሚደረገው ዕርዳታ የተቀዛቀዘ ቢሆንም እዚህ ብዙ ሰላም አለ ባይ ናቸው። “እርስ በእርስ እንረዳዳለን፤ ጾማችንን አናድርም። አቅም ያለው አቅም የሌለውን በስራም፤ በቁሳቁስም ይደግፋል፡፡ እንደ አንድ ቤተሰብ ስለምንተያይ ያለው ችግር ያን ያህል አያስከፋንም። ያም ሆኖ ሁሌም በየቀኑ የሚያስፈልገንን ነገር እንዴት ልናገኝ እንደምንችል ማሰባችን አልቀረም” ይላሉ።
ሌላዋ የመጦሪያ ቤቱ ነዋሪ ወይዘሮ አመልማል ዘለቀ ተወልደው ያደጉት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረሊባኖስ አካባቢ ነው፡፡ ከዓመታት በፊት አይናቸውን ለመታከም ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ስላልፈለጉ እዚሁ መጦሪያ ቤት ገብተው ኑሮቸውን እንደ አዲስ “ሀ” ብለው ይጀምራሉ። በዚህ መጦሪያ ቤት ያሳለፉትንም 10 ዓመታት እንዲህ ያስታውሳሉ፡፡ ቀደም ሲል የተለያዩ ድጋፎች ይድረጉልን ነበር፡፡ አሁን ግን በየቀኑ ሁለት እንጀራ ከግማሽና በወር አንድ ሳሙና ይሰጠናል፡፡ ከውጭ የሚመጡ ለጋሾች ስለማይጠፉ ያን ያህል ተርበንም፤ ታርዘንም አናውቅም። አንዳንዴ ደግሞ አንዷን እንጀራ በመሸጥ የጎደለንን ነገር እንሞላባታለን ሲሉ የኑሮቸውን ሁኔታ ይገልጻሉ።
እማሆይ ወለተዮሀንስ አስፋው ደግሞ 22 ዓመታትን ያሳለፉት በዝቋላ ገዳም ነበር። በወገብ ህመም ምክንያት እዛ ሆነው ስራ መስራት ባለመቻላቸው እዚህ መጥተው እንዲጦሩ በመደረጉ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ያለፉትን ዘጠኝ ዓመታት ያሳለፉት በዚሁ አንጋፋ የመጦሪያ ቤት ነው። ስመጣ እንጀራም፣ ወጥም ይቀርብልን ነበር፡፡ አሁን የመጦሪያ ማዕከሉ አቅም ስላነሳቸው ወጥ ማቅረብ ቀርቷል። ይህም ሆኖ ለሚጎድለን ነገር አንዳንድ ጊዜ እጁን የሚዘረጋልን በጎ አድራጊ አይጠፋም። በአንድ ወቅት በቢሮው በኩል አንዳንድ ጋቢ ተሰጥቶናል፡፡ በሌላ ጊዜም ከቤተመንግስትም ለተወሰነው የግቢው ሰዎች ብርድ ልብስ ሰጥተውናል። ወደፊት ደግሞ አቅም ሲገኝ ሌላው ባይሳካ እንኳ ቁርስ፣ ምሳና እራት እንጀራና ወጥ ይቀርብልናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ሲሉ ተናግረዋል።
የዳግማዊ ምኒሊክ መታሰቢያ ታእካ ነገስት ባዓታ ለማርያም ገዳምና የደብረ መንክራት ስእል ቤት ኪዳነ ምህረት አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪ ሊቀ ሊቃውንት አባ ሲራክ አድማሱ እንደገለጹት፤ የዳግማዊ ምኒሊክ መታሰቢያ የእጓለማውታና የአረጋውያን መጦሪያ ቤት መሰረቱን የጣለው በዳግማዊ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት ነበር። ንጉሰ ነገስቱ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላይ ከመሰረቱ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ እሳቸው የመጡ እንግዶችን እንዲሁም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች አቤት ለማለት የሚመጡትንና ሌሎች ድሆችን ዛሬ በታላቁ ቤተ መንግስት በሚገኘው ግብር ቤት (የግብር አዳራሽ) ያበሉ ነበር። ለብዓላት ቀናት ደግሞ በዚሁ ቤት ካህናቱ፣ ነገስታቱና መኳንነቱ ይታደሙበታል ፡፡በዚህም የግብር ቤቱ አገልግሎት የሚሰጠው በየዕለቱ ነበር። ንጉሰ ነገስቱ በ1906 ዓ.ም ካረፉም በኋላ ልጃቸው ንግስተ ነገስታት ዘውዲቱም ይህንን ያባታቸውን መልካም ስራ ተከትለው በኋላ ጥይት ቤት በተባለው አካባቢ ላይ የጡረተኞች፣ የደካሞችና የእጓለማውታዎችን መኖሪያ ያስገነባሉ።
ንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ምኒሊክ አባታቸውን ዳግማዊ ምኒሊክ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ለማዘከር አስበው ከ1910 እስከ 1920 ዓ.ም ባእታ ለማርያም ገዳም ቤተክርስቲያንን አሰርተዋል። በተጨማሪ በዚሁ ቦታ ትምህርት ቤት ለማቋቋምም አስበው ስለነበር ለአልጋ ወራሻቸው ለቀዳማዊ ሀይለስላሴ ይህንን ነግረውና አሳስበው ያርፋሉ። ንጉሱም ቃላቸውን በመጠበቅ ትምህርት ቤቱን አስገንብተው ስለጨረሱና መምህር የሚሆኑትንም ሊቃውንትን ስላስመጡ በ1925 ዓ.ም «የዳግማዊ ምኒሊክ መታሰቢያ መምህራንና ቀሳውስት ማሰልጠኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት» በመባል በይፋ ማስተማር ይጀምራል። በዚህ ጊዜ የአረጋውያንና አቅመ ደካሞች መጦሪያውና የእጓለማውታ ማሳደጊያውም ከነበረበት ጥይት ቤት ከሚባለው ቦታ ይነሳና ግቢ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ስር ከትምህርት ቤቱ ጋር በአንድ ቦታ እንዲሰራ ተደርጎ በኢትዮጵያ ቀዳሚው የእርዳታ ድርጅት ሆኖ ስራውን ይጀምራል። በህንፃ ግንባታው ወቅት ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ለህዝባችንም ለካህናትም የስራን ክቡርነት ልናስተምረውና አርአያ ልንሆን ይገባል ብለው በተለያዩ ቀናት ድንጋይ እያጓጓዙ ለሰራተኞች ያቀርባሉ፤ ግንባታውንም ይከታተሉና ይጎበኙ ነበር።
ከአቧሬ ጀምሮ እስከ ቤተ መንግስቱ የነበረውንም ቦታ በባእታ ገዳም ስር ለሚተዳደረው ለዚሁ እጓለ ማውታና መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ይሰጣሉ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮም በንግስቲቱ ቃል መሰረት «የዳግማዊ ምኒሊክ መታሰቢያ የእጓለማውታና የአረጋውያን መጦሪያ ቤት» ተብሎ ስራውን ይጀምራል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም የሀገሪቱን ዳር ድንበር ሲያስጠብቁ ለኖሩ አባቶች፤ በቤተ መንግስትም ሆነ በጦር ሜዳ ውሎ ነገስታቱንና ባለሟሎችን በመአድ ቤት ስራ ሲያገለግሉ ለነበሩ እናቶች እንዲሁም በተለያየ መስክ ሀገራቸውን ሲያገለግሉ የነበሩና ጧሪ የሌላቸው አዛውንቶች ጡረታ ሚኒስትር ሳይቋቋም ሲጦር ቆይቷል። ከዚያም አልፎ እናት አባታቸውን ላጡና አለሁ ባይ ለሌላቸው ህጻናት መጠጊያ በመሆን እጓለማውታዎችን (የሙት ልጆችን) እንደ እናትና አባት ተንከባክቦ ማሳደጉን ይቀጥላል። ከዓመታት በኋላ ደግሞ ነገሮች እየተቀየሩ ሲመጡ እጓለ ማውታዎቹ ከቀበሌ አሳዳጊ እንደሌላቸው ሲረጋገጥ በተመሳሳይ፤ አረጋውያኑም ጧሪ እንደሌላቸው ካሉበት ቤተክርስቲያንም ሆነ ከቀበሌ አልያም ካሉበት አካባቢ አስመስከረው ሲመጡ ያለው በጀት ታይቶ እንዲገቡ መደረግ ይጀምራል።
የተረጂውም፤ የተማሪውም ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ የአቅመ ደካሞች መጦሪያውና የእጓለማውታ ማሳደጊያው ቤት ከትምህርት ቤቱ ጋር በመሆን በገዳሟ ስር መተዳደር ይጀምራል። ለመተዳደሪያውም «ምኒሊክም እኛ ርስት ከተካፈልን ህዝቡ ምን ያገኛል ርስታችን ኢትዮጵያ ናት፤ የግል ርስት ሊኖረን አይገባም» ይሉ ስለ ነበር ገዳሟ የቤተመንግስቱ አንድ አካል ነበረች። የማደሪያ ብቻ ሳይሆን የህክምና፣ ልብስ፣ ምግብና የትምህርት ቁሳቁስ በመንግስት በኩል ከመሳፍንቱና ከመኳንንቱ የሚቀርብ ሲሆን በዘመኑ ባልተለመደ መልኩ ለተማሪዎቹ የደንብ ልብስ ሳይቀር ይዘጋጅላቸዋል። በመጦሪያው ቤት የሚያድጉትም ልጆች ዘመናዊ ትምህርትም እንዲከታተሉ በመደረጉ ከዚያ ወጥተው በመንፈሳዊውም አለማዊውም ትምህርት ተምረው አንቱ የተባሉ ሰዎችን ለማፍራት ችሏል። ትምህርት ቤቱም ላለፉት 87 ዓመታት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ከሚሰጠው ትምህርት ባለፈ ለአካባቢው ነዋሪ ልጆች ቅድመ መደበኛ ትምህርት ፊደል ማንበብና መጻፍ በማስተማር ቁጥር ስፍር የሌላቸውን ልጆች ለቁም ነገር አብቅቷል። ይህ ትምህርት ቤት የቤተክርስቲያኒቷን ስርአት ያሉትን ሁሉ ትምህርቶች የሚሰጥ ሲሆን እስካሁንም 28 ሊቃነ ጳጳሳትን፣ በርካታ ዲያቆናትና ካህናትን አፍርቷል።
በርካታ መሳፍንትና መኳንንትም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከነበራቸው ርስት፣ ቤትና ንብረቶችን ለቤተክርስቲያኗ አውርሰዋት ነበር። በዚህም ገዳሟ በገጠር ብዙ ጋሻ መሬቶች ስለነበሯት ከእነዚህ መሬቶች የሚመረተው እህል በየዓመቱ ለተረጂዎቹና ለተማሪዎቹም ይቀርባል። ቤተክርስቲያኗ የከተማ ቦታና ህንጻ ነበራት፡፡ በተለይ መርካቶ አካባቢ የሚገኘውና የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ቦታ የነበረው ዛሬ ልዩ ስሙ አሜሪካ ግቢ የሚባለው፤ ሜክሲኮ የአዋሽ ባንክ ህንጻ የተሰራበት፤ እንዲሁም ጀርመን ትምህርት ያረፈበት ቦታ በስጦታ የተበረከቱ ስለነበሩ ከእነዚህ የሚገኘው ገቢ ተረጂዎችና ተማሪዎች ይደጎማሉ። በጥሬ ገንዘብም ቀዳማዊ ሀይለስላሴ በዝግ የባንክ ሂሳብ ቁጥር በገዳሟ ስም 350 ሺህ ብር አስቀምጠዋል። ነገር ግን በ1966 ዓ.ም ደርግ ሁሉንም ንብረቶች፣ መሬቶችና ገንዘቡን ሳይቀር እንዲወረስ በማድረጉ በወቅቱ ከገንዘብ ሚኒስቴር ለአረጋውያንና ህጻናት ማቆያው ድጎማ የሚሰጠው ብቻ ቀረ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት በማጋጠሙ አጠቃላይ ሲሰሩ የነበሩት የተጠናከሩ ስራዎች እየተቀዛቀዙና የተረጂውም ቁጥር ሆነ የእርዳታውም አይነት እየቀነሰ መጥቶ ዛሬ ያለበት ሁኔታ ላይ ለመድረስ በቅቷል።
የዳግማዊ ምኒሊክ መታሰቢያ መምህራንና ቀሳውስት ማሰልጠኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ኃላፊ ሊቀ ጉባኤ በኩረ ታይቶ በበኩላቸው በአሁኑ ጊዜ በገዳሟ ስር የሚገኘው ንብረት ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝ የተመለሱት ፒያሳ የሚገኙት ጽርሀ ምኒሊክ (መሀሙድ ሙዚቃ ቤት ያለበት)ና ዘውዲቱ ህንጻ ብቻ ናቸው። እነዚህም ሲመለሱ በቀጥታ ለገዳሟ ሳይሆን ለጠቅላይ ቤተክህነቱ ነው። ቤተክህነቱ ለካህናቱ፣ ለተማሪዎችና ለጡረተኞች ድጎማ ያደርጋል። አሁን ካለው የኑሮውድነት አንጻር ግን እየተደረገ ያለው ድጎማ በቂ አይደለም። ይህ በእንዲህ እንዳለ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ 100 ዓመታትን ሊያስቆጥሩ የተቃረቡት ህንጻዎች በእድሜ ብዛት በመፈራረስ ላይ በመሆናቸው ከሀገር ውስጥም ከውጭም የሚገኘው ድጋፍ ለህንጻ ማደሻውም እየዋለ ነው። በአካባቢው የተፈጠረውም ለውጥ ገዳሟ ላይ የራሱን ተጽእኖ አሳርፎባታል። ከአዲስ አበባ በመልሶ ማልማት የፈረሱ አካባቢዎች ሸራተን አዲስ ሆቴል የተሰራበት፤ ፊት በርና አራት ኪሎ በርካታ ለጋሽ ምእመናን ነበሩ። እናም በየሰንበቱ ከገዳሟ የማይጠፋውና ድጋፉን የሚያደርገው ህብረተሰብ ዛሬ በአካባቢው የዓመት ንግስ ከሌለ አይገኝም። በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የበጀት እጥረት በመኖሩ የተረጂዎቹ ቁጥር ወደ 33 ዝቅ ብሏል። ለእነዚህ ተረጂዎች ገዳሟ እያቀረበች ያለችው እንጀራ ብቻ ነው። ተጧሪዎቹም ሆኑ እጓለ ማውታዎቹ ወጥና ልብስን ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎታቸውን የሚሸፍኑት ራሳቸውና እርዳታ እድራጊዎችን በመጠበቅ ብቻ ነው።
የገዳሙ ትምህርት ቤት ለዘመናዊ ትምህርት በር ከፋች ነበር፡፡ ያኔ እንኳን መደበኛ ትምህርት ይቅርና ፊደል እስቆጣሪ ብርቅ በነበረበት ጊዜ ከአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም ለመማር የሚመጡት በርካቶች ናቸው። ዶክተር፤ ዳኞች፣ ጋዜጠኞችና የመንግስት ሰራተኞችን ያፈራ ትምህርት ቤትም ነው። ዛሬም ድረስ ከጀርመንና ከእንግዚዝ ድረስ መጥተው ለእረፍት በክረምት ሲመጡ ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ አሉ። በአሁኑ ጊዜ 70 ተማሪዎች ትምህርት ቤቱ ውስጥ እየኖሩና ከ500 በላይ በተመላላሽነት በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙ ናቸው። በትምህርት ቤቱ እያስተማሩ የሚገኙ 15 መምህራን አሉ፡፡ ቀደም ሲል ግን ሁለት ሺህ የሚደርሱ ተማሪዎችና 350 መምህራኖች እንደነበሩ ያስታውሳሉ።
ዛሬም ግን የሰነቅነው ተስፋ አለ የሚሉት የገዳሙ አስተዳዳሪ ሊቀ ሊቃውንት አባ ሲራክ አድማሱ ወደፊት የመማሪያ ቤቶቹንና የቤተ ክርስቲያኑን ህንጻ ለማደስ ግቢውንም ለማስተካከል ዕቅድ ተይዟል። በገዳሟ ውስጥ የሚገኙ ቅርሶችን መካካልም በቤተክርስቲያኒቱ ምድር ቤት የሚገኙት የዳግማዊ ምኒሊክ፤ የባለቤታቸው የእቴጌ ጣይቱ፤ የንጉሱ ልጅ የንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ፣ አጼ ምኒሊክን ቀብተው ያነገሱት ግብጻዊው ጳጳስ አቡነ ማቴዎስ፣ የቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ ልጅና የመጀመሪያዋ ነርስ ልእልት ጸሀይ መቃብር ይገኙበታል፡፡ እንዲሁም ለንጉሰ ነገስቱ ከጀርመን፣ ከራሻ፣ ከፈረንሳይ፣ ከግሪክ፣ ከእስራኤልና ሌሎች ሀገራት የተበረከቱላቸው ስጦታዎች አሉ። ከተለያዩ አካባቢ ሀገረ ገዢዎችና ባለሟሎቻቸው በስጦታ የተበረከቱላቸው የክብር ወንበሮች፤ አድዋ ላይ ጣሊያንን ድል ባደረጉ ጊዜ ተቀምጠው ይመሩበትና ይፈርዱበት የነበረው ወንበርና መስቀሎች ስዕሎችና ንዋየ ቅዱሳት ጭምር ለጉብኝዎች ክፍት ለማድረግ የሙዚየም ግንባታ የሚከናወን ይሆናል። ይህም ገቢን ለማሳደግ የሚያስችል ነው፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአሁኑ ጊዜ ቤተመንግስቱ ግቢ ውስጥ የሚገኝ፤ ቀደም ሲል ደግሞ በገዳሟ ስር የሚተዳደር የሊቀ ሊቃውንት ማረፊያ የሚባል ቤት በደርግ እንዲወረስ ተደርጓል። ይህንን ለማስመለስ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ክርክር ሲደርግ ቀይቷል። በዚህ ቦታ ምትክ መንግስት በቅርቡ አሮጌው ቄራ አካባቢ 450 ካሬ ቦታ ላይ ካርታ አውጥቶ ሰጥቶናል፡፡ እዚህ ቦታ ላይ ህንጻ በመገንባት ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለመፍጠር የሚሰራ ይሆናል። ይሄ የእጓለ ማውታዎችንም ሆነ አቅመደካማ አረጋውያኑን በተገቢው መንገድ ለመንከባከብና ቁጥራቸውንም ለማሳደግ ትልቅ የገቢ አቅም ለመፍጠር እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 27/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ