– በኦነግ ሸኔ ላይ ዕርምጃ እየተወሰደ ነው
አዲስ አበባ፡- በምዕራብ ጎንደር ዞን በተከሰተው ግጭት ዙሪያ እየወጡ ያሉ የተምታቱ መረጃዎች ለውጡን የሚጎዱ መሆናቸውን የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ አስታወቁ፡፡ በኦነግ ሸኔ ላይ ዕርምጃ እየተወሰደ መሆኑንና በዛላምበሳና ሽሬ በተፈጠረው ችግር መከላከያ እቅዱን እንደማያጥፍ አመለከቱ፡፡
በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጡት ምክትል ኤታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ፤ እንደተናገሩት፤ በምዕራብ ጎንደር ሰሞኑን የሰው ህይወት መጥፋትን አስመልክቶ የተምታቱ መግለጫዎች እየወጡ ነው፡፡ በማህበራዊ ሚዲያም የተለያዩ መረጃዎች በመሰራጨት ላይ ናቸው፡፡ ጉዳዩ በተገቢው መንገድ የማጣራት ሥራ ከተካሄደ በኋላ መግለጫ መሰጠት የነበረበት ቢሆንም ሁሉም አካል የየራሱን ሪፖርት ይዞ መግለጫ እየሰጠ ነው፡፡
እየተሰጡ ያሉ መግለጫዎችና በማህበራዊ ሚዲያ ላይ እየወጡ ያሉ መረጃዎች፤ አሁን ያለውን ለውጥ የሚጎዱ ናቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር ህዝብ ለህዝብ እንዲጋጭ የሚያደርጉ ከመሆናቸውም ባሻገር፤ የመንግሥት ተቋማትን ህዝቡ እንዲጠላቸው የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ ኢትዮጵያን እወዳለሁ በሚል በማንኛውም አካል መከናወን ያለበት አይደለም ብለዋል፡፡
እንደ ጄኔራሉ ማብራሪያ፤ በምዕራብ ጎንደር ዞን ሸሄዲ በሚባል አካባቢ በሠራዊቱና በታጠቁ ኃይሎች መካከል ተኩስ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ሠራዊቱ የእጀባ ግዴታ ተሰጥቶት ግዴታውን በመወጣት ላይ ባለበት ወቅት እጀባ የተደረገለት ኩባንያ በደል ሲፈጽምብን ነበር ስለዚህ ሳይፈተሽ አያልፍም የሚል ሃሳብ በመነሳቱ ተፈትሾ እንዲያልፍ ተደርጓል፡፡ ኮንቮዩ ተፈትሾ ካለፈ በኋላ ውሃ ለመቅዳት የሚሄዱ የመከላከያ ቦቴዎች ጋር አብረው 10 ወታደሮች ደፈጣ ተደርጎባቸዋል፡፡ በተደረገው ደፈጣ ሁለት ወታደሮች ቆስለዋል፡፡ ወታደሮቹ ራሳቸውን መከላከል ስላለባቸው ሲተኩሱ በነበሩ ታጣቂ ኃይሎች ተኩሶ ዕርምጃ ወስዷል፡፡
«መከላከያ ራሱን ስለተከላከለ መከላከያው ሰው ገድሏል» የሚል ወሬ በመናፈሱ ቀደም ብሎ ተፈትሾ ያለፈው ኮንቮይ እንደገና እንዲቆም መደረጉን የሚያነሱት ጄኔራል ብርሃኑ፤ እንደገና እንዲቆም ከተደረገ በኋላ ህዝቡና መከላከያው ተቀላቅሎ ኮንቮዩ ዙሪያ በቆሙበት ወቅት የታጠቀው ኃይል ጋራና ተራራ ላይ ሆኖ ህዝብና ሠራዊት ሳይለይ ተኩስ እንደከፈተ አብራርተዋል፡፡ በዚህ ሰላማዊ ዜጎች መጎዳታቸውን የገለጹት ጄኔራሉ፤ ይህም መሆን ያልነበረበት ነው ብለዋል፡፡
ጄኔራሉ እንዳብራሩት ምንም ያልታጠቀው ሰው መገደል ቀርቶ መቁሰል አልነበረበትም፡፡ የታጠቁት ኃይሎች የፈጸሙት ጥቃት የሚወገዝ ነው፡፡ መከላከያውም በተፈጠረው ጥቃት አዝኗል፡፡ መከላከያው አድፍጦ የሚተኩሰውን ትቶ በአጠገቡ ወዳለው ህዝብ የሚተኩስበት ምክንያት አይኖርም፡፡ መከላከያ ተሳስቶ ከግዳጁ ውጪ ፈጽሞ ከሆነ ይጠየቃል፡፡ መከላከያም ይቅርታ ይጠይቃል፤ ይክሳልም፡፡ ክልሉ በርካታ ታጣቂዎችና ተኳሾች ያሉበት እንደመሆኑ መከላከያን መፈረጅ ግን አስፈላጊ አይደለም፡፡
እንደ ጄኔራሉ ማብራሪያ፤ ‹‹መከላከያ ሰው ገደለ›› እየተባለ እየወጣ ያለው መረጃ ስህተት ነው፡፡ በተለይም ከለውጡ በኋላ መከላከያ ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ ህገ መንግሥቱን መሰረት አድርጎ እየሠራ ነው፤ከለውጡ በኋላ መከላከያው ህዝብ ላይ ተኩሶ ገድሎ አያውቅም፡፡ መከላከያ ምንም ትጥቅ የሌለው ህዝብ መንገድ ላይ ወጥቶ አትሂድ ስላለው ህዝብ ላይ አይተኩስም፡፡ ይህንን ዶክተሪኑም አይፈቅድም፡፡ በህግ እንደሚያስጠይቀው ያውቃል፡፡ መርህ በኪሱ ይዞ ነው የሚሄደው፡፡ በቅርቡ በዛላምበሳና ሽሬ ላይ ሕፃናት እና ወጣቶች ከትምህርት ቤት ወጥተው፤ መንገድ ላይ ሆነው ስጋት አለብን አትሂዱ ብለው መንገድ ሲዘጉ ዕርምጃ አለመውሰዱ መከላከያው ህዝብ ላይ እየተኮሰ ላለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡መከላከያ፣የክልሉ መንግሥትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተጨምረውበት ይህ ጉዳይ እንዲጣራ ይፈልጋል፡፡
በመግለጫው በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ስላለው ነባራዊ ሁኔታ ጄኔራሉ እንዳብራሩት፤ ከህዝቡ ጋር በመሆን በኦነግ ሸኔ ላይ በተወሰደው ዕርምጃ አካባቢው ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሰ ነው፡፡ ህዝቡም ወደ ሥራው እየተመለሰ ነው፡፡ ዕርምጃው ዘግይቶ በመጀመሩ ዋጋ አስከፍሏል፡፡ ህዝቡ ውስጥ የተሰገሰገ ቡድን በመሆኑ ጊዜ ሊፈጅ ችሏል፡፡
በቅርቡ በትግራይ ክልል ዛላምበሳና ሽሬ አካባቢ ከሕፃናቱና ወጣቶቹ ጀርባ ሆነው ስጋት ስላለብን መከላከያው ትግራይን ለቆ መውጣት የለበትም በሚል የመከላከያው እንቅስቃሴ እንዲስተጓጎል መደረጉን የተናገሩት ጄኔራል ብርሃኑ፤ከጀርባ ሆነው የሚቀሰቅሱ አካላት እንዳሉ ስለታወቀ ዕርምጃ ሳይወሰድ ከህዝቡ ጋር ውይይት መደረጉን አንስተዋል፡፡ የእነዚህ አካላት ዋናው ዓላማም ህዝብና መከላከያውን በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ ማግኘት ነበር ብለዋል፡፡ ከህዝቡ ጋር በተደረገው ውይይት ወጣቶችና ሕፃናት መንገድ እንዲዘጉ ሲያስደርጉ የነበሩ አንዳንድ አካላትን ማጋለጣቸውን ተናግረዋል፡፡
ከኤርትራ ጋር ወደ ጦርነት ሊከት የሚችል ምንም ዓይነት ምክንያት የለም ያሉት ጄኔራሉ፣ መከላከያው በእቅድ የሚንቀሳቀስ መሆኑን በመግለጽ በዛላምበሳና ሽሬ በተፈጠረው መስተጓጎል ምክንያት እቅዱን እንደማይከልስ አብራርተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 4/2011
መላኩ ኤሮሴ