
አዲስ አበባ፡- የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተለየ ስርዓተ ትምህርት አዘጋጅተው ልዩ ተልእኮ በመውሰድ የተለዩ ምሩቃንን የሚያፈሩ ለማድረግ ትኩረት መስጠቱን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ሚኒስትር ደኤታው ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ለምርምር፣ ለአፕላይድ ሳይንስ እና ለአጠቃላይ የሚባሉት ዩኒቨርሲቲዎች ተለይተዋል፡፡ የትምህርት ዘርፍ ልማት በመከተል በተሰራው የማሥፋፊያ ሥራ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 50 ደርሰዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አይነት የተደራጁ ሲሆን፤ ልዩ ተልእኮ ኖሯቸው ልዩ አይነት ምሩቃንን የሚያመርቱ ግን አይደሉም፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው ትኩረታቸው ለአንድ ልሕቀት ብቻ የሆነ መምህራንን፣ ሃኪሞችን፣ በግብርናው እና በሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደሚያስፈልጉ ጠቅሰው፤ ያደጉ አገራት በተልዕኮ ከፋፍለው ተጠቃሚ በመሆናቸው ከእነሱ ትምህርት በመውሰድ ለምርምር የሚሆኑ፣ ለአፕላይድ ሳይንስ የሚመጥኑ፣ አጠቃላይ የሚባሉ ትምህርት ተቋማት መለየታቸውን አብራርተዋል፡፡
ሚኒስትር ደኤታው መንግሥት ከአምስት ዓመታት በፊት ሁለት አጠቃላይ ዩኒቨርሲቲዎችን ማለትም የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂና የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉንም ትምህርቶች እንደማያስተምሩና የሳይንስና ቴክኖሎጂ መፍለቂያዎች ተደርገው ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውሰዋል፡፡
‹‹የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአንድ ምጣድ የተጋገሩ እንጀራዎች ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያ እንደዚህ አይነቶች ብቻ አያስፈልጉም›› ያሉት ፕሮፌሰር አፈወርቅ፤ በፍኖተ ካርታው ጥናት የተለየው ዩኒቨርሲቲዎች አንድ አይነት መሆናቸው እንደነበረ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትር ደኤታው ልዩ ስርዓተ ትምህርት አዘጋጅተው ከኢንደስትሪው ጋር ተቀራርበው የሚሰሩ፣ በትምህርት ስርዓት ውስጥም የኢንዱስትሪ ባለሙያዎች ተሳትፈው እየተጋገዙ ምሩቃንን የሚያፈሩበት አሰራር መፈጠሩን ጠቁመው፤ እንደነዚህ አይነት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለኢትዮጵያ በብዛት እንደሚያስፈልጉ አመልክተዋል፡፡
ሚኒስትር ደኤታው አስተሳሰቡ ቀድሞ የነበረ መሆኑን፣ ፍኖተ ካርታው ይህንኑ አዳብሮ በተልዕኮና በልሕቀት መለየቱን፤ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎችም እንደሚያስፈልጉ፣ በዓለም አንደኛ የሚባለው ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ መሆኑን፤ ጀርመን አገርም ተወዳዳሪ የሌለው የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደሚገኝና ተሞክሯቸውን መውሰዱ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2012
ዘላለም ግዛው