በኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 ላይ እንደተመለከተው፤ የፕሬስ እና የሌሎች መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የስነ ጥበብ ፈጠራ ነጻነት ተረጋግጧል:: የፕሬስ ነጻነት በተለይ የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ መሆኑን እንዲሁም የህዝብን ጥቅም የሚመለከት መረጃ የማግኘት እድልን ያጠቃልላል፤ ለዴምክራሲያዊ ስርአት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች ሀሳቦችና አመለካከቶች በነጻ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ፕሬስ በተቋምነቱ የአሰራር ነጻነትና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የህግ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡ ህገ መንግስቱ በእነዚህ መብቶች ላይ ገደብ ሊጣልባቸው የሚችሉ ሁኔታዎች እንዳሉም አያይዞ አስፍሯል፡፡
የሀገሪቱ ሚዲያ ከህገመንግስቱ ወዲህ ባለው ሁኔታ ያሳለፋቸውን ታሪኮች ስንመለከት ግን ሚዲያው በህግ በተደነገገው መሰረት እንዲሰራ አልተደረገም:: ህጉ የይስሙላ ሆኖ ሚዲያው ማሳደድ ሲደርስበት ነው የተስተዋለው፡፡ ህጉ በተለይ በግል ሚዲያ ላይ እንዲሰራ አልተደረገም፡፡ ሚዲያ ማቋቋምም ሆነ ተቋቁሞ መስራት ፈተና ነበር፡፡ በአንዳንድ የፖለቲካ ለውጦች ሳቢያ ሚዲያዎች ቀና ቀና ያሉበት ሁኔታ ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፣ በመንግስት ጣልቃ ገብነት መረጃ ሲከለከሉ፣ እንዳያትሙ፣ያተሙትን ለህዝብ እንዳያደርሱ ሲደረጉ ኖረዋል፡፡
ሚዲያው እንዲኖር እና እንዲያድግ አልተሰራም፡፡ ሌላው ቀርቶ ሚዲያዎች የራሳቸውን ካውንስል በማቋቋም ሚዲያው አጥፍቷል፤ አላጠፋም የሚለውን የሚመለከቱበት እና ራሳቸውን የሚያስተካክሉበት መንገድ አልነበረም:: ካውንስሉን ለማቋቋም እንቅስቃሴዎች ከተጀመሩ ዓመታትን ቢቆጥሩም፣ እውን የሆነው በቅርቡ ነው፡፡ ተመዝግቦ ፈቃድ ለማግኘት ደግሞ ዓመታት ውስደውበታል፡፡ ከብዙ ጥረት በኋላ አሁን ካውንስሉ እውን ሆኗል፡፡ የሚቀረው ወደ ስራ መግባት ብቻ ነው፡፡
ከካውንስሉ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ 52 የሚዲያ ተቋማትን በአባልነት ይዟል፡፡ ሌሎችም ሊቀላቀሉት እየፈለጉም ናቸው፡፡ በሚዲያ በኩል የአቅም ውስንነት አለ፡፡ ካውንስሉ ይህን ችግር ለመፍታት ስልጠናዎችን ይሰጣል:: መንግስት፣ በርካታ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲሁም ሀገሮች ድጋፍ እንደሚያደርጉለት አረጋግጠውለታል፡፡
«ምጡን እርሽው ልጁን አንሺው» እንዲሉ ካውንስሉ ለመቋቋም ያሳለፈውን ውጣ ውረድ ማሰቡን ትቶ በአስቸኳይ ወደ ስራ መግባት ይኖርበታል፡፡ በለውጡ ወቅት እንደ መምጣቱ ለውጡን ወደፊት ሊያራምዱ የሚችሉ ስራዎች እንደሚጠብቁት መረዳት ይኖርበታል፡፡
ሚዲያው ለውጡ የፈጠረለትን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በነጻነት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ነጻነቱ ያስገኘው እድል እንዳለ ሆኖ ነጻነቱን በአግባቡ ካለመጠቀም ጋር በተያያዘ በሚዲያው ዘንድ አንዳንድ ክፍተቶች እየታዩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ይህን ለማረም የካውንስሉ ሚና ከፍተኛ እንደመሆኑ ፈጥኖ ወደ ስራ መግባት ይኖርበታል፡፡
ሚዲያው በስነምግባር ተመርቶ እንዲሰራ በማገዝ ለመንግስት አጋዥ እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡ መንግስት ሚዲያው አውቆም ይሁን ሳያውቅ በሚለቃቸው የተሳሳቱ መረጃዎች የተነሳ ባለፉት ጊዜያት እንደተስተዋለው በእያንዳንዱ ጉዳይ እየገባ ችግሩን ለመፈታት ጥረት ማድረግ ላይጠበቅበት ይችላል፡፡ ሚዲያውም ለሙያ ስነ ምግባር እየተገዛ የሚሰራበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ በሀገሪቱ ጠንካራ ሚዲያ እየተፈጠረም ይመጣል፡፡ የህዝቡ የዘመናት የመረጃ ጥማትም ይረካል፡፡
ሀገሪቱ በርካታ እውነተኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሳተፉበትን ምርጫ 2012 በመጪው ነሐሴ ወር መጨረሻ ለማካሄድ እየተዘጋጀች ናት፡፡ ምርጫው ነጻ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ በእዚህ ውስጥ መገናኛ ብዙሃኑ የህዝብ ድምጽ በመሆን እንዲያገለግሉ ይጠበቃል፡፡ የምርጫ ዘገባውም ከፍተኛ ጥንቃቄን ይጠይቃል፡፡ ካውንስሉ መንግስት እና መገናኛ ብዙሃኑ ለምርጫው ከሚያደርጉት ዝግጅት በተጓዳኝ የራሱን ዝግጅት አድርጎ በመስራት ለምርጫው ስኬት የበኩሉን ሚና መጫወት ይኖርበታል፡፡
ለውጡ እና ምርጫው ለካውንስሉ መልካም አጋጣሚዎች መሆናቸውን መረዳት ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ ህገመንግስቱ ለሚዲያው የሰጠው ትኩረት በተግባር ስራ ላይ እንዲውል ካውንስሉ የራሱን አሻራ በማሳረፍ ለራሱም መሰረት መጣል ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም ካውንስሉ ይህን ወቅት እንደ መልካም አጋጣሚ ይጠቀምበት!
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2012