
ዓድዋ፡- በዓድዋ ጦርነት ኢትዮጵያውያን ዓርበኞች የነበራቸው የመተባበር፤ የመደጋገፍና ለሀገራዊ ጉዳይ ቅድሚያ የመስጠት ተግባር በዛሬው ትውልድም ሊደገም እንደሚገባ ተገለጸ።
124ኛው የዓድዋ ድል በዓል ትናንት በዓድዋ ከተማ በተከበረበት ወቅት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንደገለጹት፤ የዓድዋ ዓርበኞች የህዝብና የሀገር ቀጣይነት በወቅቱ በውስጣቸው
ከነበረው ችግር ጋር የማይመጣጠን መሆኑን በመ ገንዘብ ልዩነታቸውን ወደጎን በመተው ሀገርን ለመታደግ በቅተዋል።
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ የቆመችባቸውን መሰረ ታዊ ምሰሶዎች የሚያናጋ ብሎም ህልውናዋንና ሉአላዊነቷን እንዲሁም መብቷን የሚፈታተን ሲመጣ የመደራደር ታሪክ እንደሌላት ለዓለም የታወጀበት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ ‹‹በዓድዋ ጦርነት ባለመን በርከካችን የዛሬ 75 ዓመት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መስራች እንዲሁም ከ57 ዓመት በፊት የዛሬው አፍሪካ ህብረት የወቅቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራች ሀገር ለመሆን በቅተናል።›› ሲሉ ተናግረዋል።
‹‹ዛሬም አንድነታችንን፤ አብሮ መኖርንና ሰላማችንን የሚፈታተኑ በርካታ ችግሮች እየተጋረጡብን ነው፤ አሁንም የዓድዋውን የአንድነት መንፈስ ልናድሰውና ልንመራበት ይገባል።›› ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ በመደማመጥና በመቻቻል ብሎም የውስጥ ችግርን ወደጎን በመተው በትንሹ ላይ ሳይሆን በትልቁ ጉዳይ ላይ ማተኮርና ለፍትህና ለህግ የበላይነት መቆም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቷ ገለጻ፤ ሀገርን ከግለሰብ፤ ከየትኛውም ወገን ወይም ስብስብ ፍላጎትና ጥቅም በላይ ማየት ይጠበቃል። ልዩነት ተፈጥሯዊ ነው፤የኢትዮጵያን ህልውናና በአንድነት የመቀጠል ሂደት የሚገታ ሲሆን የትኛውም አይነት ልዩነት ቦታና ዋጋ አይኖረውም።
የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው የዓድዋ ጦርነት ደካማ ይባሉ የነበሩት ህዝቦች ሳይለያዩ በአንድነት በመሰለፋቸው ከፍተኛ ስልጠናና ዝግጅት ያለውን ሰራዊት ለማሸነፍ የበቁበት መሆኑን አስታውቀዋል። ዓድዋ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ህዝብና በአፍሪካ በቀኝ ግዛት ይማቅቁ የነበሩትም ድል መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ለውጪ ሀይል ተጽእኖና ጣልቃ ገብነት እንደማንንበረከክ ያሳየነበትም ነው።›› ሲሉ ገልጸዋል።
‹‹አሁንም በሀገራችን እየተከሰተ ያለውን የውጪ ሀይሎች ጣልቃ ገብነትና በብሄራዊ ማንነታችን እንዲሁም በብሄራዊ ሉአላዊነታችንና ክብራችን ላይ የተደቀኑ ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት የዓድዋ ጦርነት መንስኤ የሆነውን የውጫሌ ውል በአስተማሪነት ልንጠቀምበት ይገባል›› ብለዋል።
በኢትዮጵያ ፖለቲካና በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ለሚታዩ ጣልቃ ገብነቶች ተገቢውን ጥንቃቄ በመውሰድ ወቅታዊ ፣በሳልና የማያዳግም ምላሽ መስጠት እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል። የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ የቀረበው የውል ሰነድም እንደ ውጫሌ ውል ሁሉ በውሉ የሰፈሩ ሀሳቦችና ቃላት በሉአላዊነታችን ላይ የመጡ ከዛም አልፈው ለሌላ የፖለቲካ አላማ ማስፈጸሚያ ገጸ በረከትና እጅ መንሻነት እንዳያገለግሉ በከፍተኛ ጥንቃቄና ኃላፊነት መፈጸም እንደሚገባቸውም አስታውቀዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የድሮ ቀኝ ገዢዎች የሚፈልጉትን ሀገር ወረው በመሳሪያ ጉልበት ይገዙ እንደነበር አስታውሰው፣የአሁኖቹ ደግሞ ሀገሮች የፖሊሲ ነጻነት እንዳይኖራቸው በማድረግ በቁጥጥራቸው ስር በማስገባት ዜጋው በመሰለው መልኩ ሀገሩን እንዳያስተዳድር የሚያደርጉ መሆናቸውን መገንዘብ እንደሚገባ አስታውቀዋል።‹‹እኛም እንደ ቅድመ አያቶቻችንና አያቶቻችን ሀገራችንን ከማንኛውም የውጪ ጣልቃ ገብነት ጠብቀን ለቀጣዩ ትውልድ ነጻነቷና ሉአላዊነቷ የተጠበቀ ሀገር የማስረከብ ኃላፊነትና ግዴታ አለብን›› ሲሉ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ