
በመሃል አዲስ አበባ የሚገኘው የዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ ገና በጠዋቱ በበርካታ ህዝብ ተከቧል። ፖሊሶች ህዝቡ ወደ መሃል እንዳይጠጋ አጥር ሰርተው ይጠባበቃሉ። የኢፌዴሪ መከላከያና የፌዴራል ፖሊስ ማርሽ ባንዶች እየተፈራረቁ የሚያሰሟቸው ሀገራዊ ጥኡም ዜማዎች የታዳሚያንን ስሜት ይኮረኩራሉ።
ወደ አዲሱ ገበያ በሚወስደው የአደባባዩ አቅጣጫ ጦርና ጋሻ ያነገቡ የጥንታዊት ኢትዮጵያ እናትና አባት ዓርበኞች ሽለላና ፉከራ ያሰማሉ። በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ባሸበረቀው አደባባይ መሃል የሚገኘው የዳግማዊ ምኒልክ ሃውልት የበዓሉ ታዳሚያንን በኩራት የሚመለከት ይመስላል።
ናቸው። እኚህ ዓርበኛ ጣሊያን በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ዳግም ለመውረር በመጣበት ጊዜ የሃገራቸውን ነፃነት ለማስጠበቅ በዓርበኝነት ተዋግተዋል። ወደ ውጊያው የገቡትም የቀድሞ ኢትዮጵያውያን ዓርበኞች በዓድዋ ጦርነት የፈፀሙትን አርያነት ያለው ጀብዱ ተግባር በመከተል እንደሆነም ይናገራሉ።
የአሁኑ ትውልድም የቀድሞዎቹን ጀግኖች በመከተል የሀገሩን ሉአላዊነት መጠበቅ እንደሚገባው አስገንዝበው፤ በተለይ የእርስ በርስ ጥላቻና ፀብን ትቶ ለስራ፣ ለብልፅግናና ለትምህርት መታገል እንዳለበት ያስገነዝባሉ።
ዓርበኞች በዓድዋ ተባብረው ጣልያንን ድል እንዳደረጉ ሁሉ ትውልዱ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ለህዝብ ጥቅም እንዲውል እውቀቱንና ገንዘቡን ማበርከት እንደሚገባውም አሳስበዋል። ህዘቡ በበዓሉ አከባበር ላይ ያሳየውን ኢትዮጵያዊ ወኔ በልማቱም እንዲደግመው ጥሪ አቅርበዋል።
ሌላኛው የበዓሉ ታዳሚና የዓርበኛ ቤተሰብ የሆኑት አቶ ካሳሁን ግርማ የአሁኑ ትውልድ ወደቀደመው ታሪኩና ወኔው እየተመለሰ መሆኑን ይናገራሉ። ይህንን ታሪኩን ጠብቆ እንዲሄድ በተለይ ምሁራንና የታሪክ ሰዎች ታሪክ በማሳወቅ ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው ይላሉ።
መላው ኢትዮጵያን በጋራ በመተባባራቸው የዓድዋ ድል ሊመዘገብ መቻሉን አቶ ካሳሁን ጠቅሰው፤ የአሁኑ ትውልድ ከቀድሞው ኢትዮጵያውያን ዓርበኞች ትምህርት በመውሰድ ልዩነቱን ወደ ጎን በመተው በአንድነትና በፍቅር ሃገሩን ማሳደግ እንደሚገባውም ያስገነዝባሉ። ኢትዮጵያውያን መሪዎችም አሁንም ሆነ ወደፊት ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለትውልዱ ማስተማር እንዳለባቸውም ይመክራሉ።
የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች ዓርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በዓድዋ ጦርነት ምንጊዜም የማይበገረውና ማንኛውንም ጥቃት ተምበርክኮ የመቀበል ልምድ የሌለው የኢትዮጵያ ህዝብ ባደረገው መሬት አንቀጥቅጥ መራራ ትግል ወራሪውን የጣልያን ጦር ሽንፈት ማከናነቡን ያስታውሳሉ።
እነዚህ ጀግኖች በጊዜው ሃገርንና ህዝብን ለድል ያበቁበት ዋናው ሚስጥር ውስጣዊ ልዩነታቸውን አቻችለው በህብረትና በአንድነት ተሳስረው አንድ ለሆነችው ሀገራቸው በፍቅር በመቆማቸው ብቻ መሆኑንም የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያውያን ከልዩነት ይልቅ አንድነትን፣ ከጥላቻ ይልቅ መፈቃቀርን በማጎልበት ለሀገራቸው ዘብ ሊቆሙ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የበዓሉ የክብር አንግዳ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አወቀ ሃይለማሪያም እንደገለፁት፤ የዓድዋ ድል ከ124 ዓመት በፊት አባት ጀግኖች ዓርበኞች በአጭር ጊዜ ውስጥ ስኬታማ ወታደራዊ ድል የተጎናፀፉበት ነው።ድሉ የኢትዮጵያውያን ጀግንነት የታየበት ብቻ ሳይሆን ወደፊት ሊነገሩ የሚችሉ በርካታ ጥበባትን የያዘና፣ የተቀናጀ አንድነትን ያሳየ ድል ነው።
ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ልዩነታቸውን ወደኋላ በመተው ቋንቋ፣ ሃይማኖትና ባህላቸው ሳይለያቸው ከሁሉም በላይ የሃገራቸው አንድነትና የህዝባቸው ሉዓላዊነት በልጦባቸው ወደ ጦር ግምባር መትመማቸውን ዋና ስራ አስኪያጁ ያስታውሳሉ። የአሁኑ ትውልድም ከዚህ ድል ብዙ መማር እንደሚገባውም ይናገራሉ።
ትውልዱ በአንድ በኩል ከጀግኖች ዓርበኞች የተረከበውን ሀገሩን ሳይለያይና ሳይሸራርፍ ውስጣዊ ልዩነቱን በሰከነና በምክንያታዊ መንገድ በማስታረቅ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚኖርበት አስገንዝበው፣ በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት ከድህነት ለመውጣት በሚያደርጋቸው ሁለንተናዊ ጥረቶች ውስጥ በግምባር ቀደምነት በመሰለፍ ሀገሪቷን ጠላት በድጋሚ ሊመኛት እንዳይችል በኢኮኖሚያዊ አቅሟ ጠንካራ እንድትሆንና ወደ ብልፅግና እንድትሸጋገር የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2012
አስናቀ ፀጋዬ